በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ የአቅማችንን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል

ይሖዋ የአቅማችንን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል

ወደ አምላክ ቅረብ

ይሖዋ የአቅማችንን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል

ዘሌዋውያን 5:2-11

“የቱንም ያህል ብደክም ያደረግኩት ነገር በቂ እንደሆነ ፈጽሞ ተሰምቶኝ አያውቅም።” አንዲት ሴት አምላክን ለማስደሰት ያደረገችውን ጥረት በተመለከተ ስሜቷን የገለጸችው በዚህ መንገድ ነበር። ይሖዋ አምላክ፣ አገልጋዮቹ እሱን ለማስደሰት የአቅማቸውን ያህል ካደረጉ በዚህ ይደሰታል? አቅማቸውንና ያሉበትን ሁኔታስ ግምት ውስጥ ያስገባል? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት፣ አንዳንድ መሥዋዕቶችን በተመለከተ በዘሌዋውያን 5:2-11 ላይ የሠፈረው የሙሴ ሕግ ምን እንደሚል መመርመራችን ይረዳናል።

በሙሴ ሕግ መሠረት እስራኤላውያን የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የተለያዩ መሥዋዕቶች እንዲያቀርቡ አምላክ ይጠብቅባቸው ነበር። በዘሌዋውያን 5:2-11 ላይ በተገለጹት ሁኔታዎች ግለሰቡ ኃጢአት የሠራው ሳያውቅ ወይም ሳያስበው ነው። (ቁጥር 2-4) ግለሰቡ ኃጢአት መሥራቱን ሲገነዘብ ኃጢአቱን እንዲናዘዝና ለበደል መሥዋዕት “አንዲት የበግ ወይም የፍየል እንስት” እንዲያቀርብ ይጠበቅበት ነበር። (ቁጥር 5, 6) ይሁንና ድሃ ከመሆኑ የተነሳ በግ ወይም ፍየል ማቅረብ ባይችልስ? ግለሰቡ ዕዳ ውስጥ ገብቶም ቢሆን እንዲህ ያለ እንስሳ እንዲያቀርብ ሕጉ ያዛል? የኃጢአት ይቅርታ የሚያገኝበት ጊዜ ሊራዘም ቢችልም አንድ በግ ወይም ፍየል ለመግዛት የሚያስችለውን ገንዘብ እስኪያገኝ ድረስ እንዲሠራ ይጠበቅበት ነበር?

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተሰጠው ሕግ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ከርኅራኄ የመነጨ አሳቢነት እንደሚያሳይ ያጎላል፤ እንዲህ ይላል፦ “ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች . . . ለእግዚአብሔር ያቅርብ።” (ቁጥር 7) “ዐቅሙ ካልፈቀደ” የሚለው ሐረግ “እጅ ካጠረው” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አንድ እስራኤላዊ በጣም ድሃ በመሆኑ በግ ለማቅረብ ካልቻለ አቅሙ የፈቀደለትን ይኸውም ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶችን ቢያቀርብ አምላክ መሥዋዕቱን በደስታ ይቀበለዋል።

ይሁንና ግለሰቡ ሁለት ዋኖሶችን እንኳ ለማቅረብ አቅሙ የማይፈቅድለት ቢሆንስ? በዚህ ጊዜ ሕጉ “የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ [አንድ ኪሎ ግራም ገደማ] የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ” ይላል። (ቁጥር 11) ይሖዋ፣ በጣም ድሃ ለሆኑ ሰዎች ልዩ አስተያየት በማድረግ ደም ሳይፈስ የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። * አንድ እስራኤላዊ የቱንም ያህል ድሃ ቢሆን፣ ይህ ሁኔታው የኃጢአት ይቅርታ እንዳያገኝ እንቅፋት አይሆንበትም፤ ወይም ከአምላክ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሚያስችለውን አጋጣሚ አይነፍገውም።

ሕጉ የበደል መሥዋዕትን በተመለከተ የሚሰጠው መመሪያ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋ የአገልጋዮቹን የአቅም ውስንነት ግምት ውስጥ የሚያስገባ ደግና ርኅሩኅ አምላክ እንደሆነ ያስተምረናል። (መዝሙር 103:14) የዕድሜ መግፋት፣ የጤና ማጣት፣ የቤተሰብ ወይም ሌሎች ኃላፊነቶች ጫና የሚፈጥሩብን ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ እንዲሁም ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ይፈልጋል። አቅማችን የሚፈቅደውን ያህል የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ አምላክ ይደሰትብናል፤ ይህን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ለመሥዋዕት የሚቀርብ አንድ እንስሳ፣ ኃጢአት የማስተሰረይ ኃይሉ ያለው አምላክ እንደ ቅዱስ አድርጎ በሚመለከተው በደሙ ላይ ነው። (ዘሌዋውያን 17:11) ታዲያ ይህ ሲባል ድሆች የሚያቀርቡት የዱቄት መሥዋዕት ዋጋ የለውም ማለት ነው? በፍጹም። ይሖዋ፣ አንድ እስራኤላዊ እንዲህ ያለውን መሥዋዕት እንዲያቀርብ ያነሳሳውን የትሕትናና የፈቃደኝነት መንፈስ እንደሚያደንቅ ብሎም ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ጥርጥር የለውም። ከዚህም ሌላ ድሆችን ጨምሮ የመላው ብሔር ኃጢአት በዓመታዊው የስርየት ቀን ለአምላክ በሚቀርቡት የእንስሳት ደም ይሸፈን ነበር።—ዘሌዋውያን 16:29, 30