በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ እኔ በእርግጥ የሚያስብ አለ?

ስለ እኔ በእርግጥ የሚያስብ አለ?

ስለ እኔ በእርግጥ የሚያስብ አለ?

አንዳንድ ጊዜ ረዳት የለሽ እንደሆንክና ምንም ማድረግ እንደማትችል እንዲሁም ያጋጠመህን ችግር በሚገባ የሚረዳልህ እንደሌለ ሆኖ ይሰማሃል? ችግርህን የሚያውቁልህ ሰዎች ቢኖሩም ደግሞ ስለ አንተ ምንም ደንታ እንደሌላቸው አድርገህ ታስባለህ?

በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች መቋጫ የሌላቸው ሊመስሉን ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜም የደረሰብን ችግር ስሜታችንን በጣም ስለጎዳውና ፍጹም ፍትሐዊ ስላልሆነ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ እንደሆነብን ሊሰማን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ የሚሰማን የስሜት ቀውስ፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ አቅም የሚያሳጣ አደጋ ሲያጋጥመን እንዲሁም ሥር የሰደደ በሽታ ሲይዘን ወይም እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ችግሮች በሕይወታችን ሲደርሱ ነው። በዚህ ጊዜ ምንም ማድረግ እንደማንችል ስለሚሰማንና ተስፋ ስለምንቆርጥ ‘መጽናኛ ከየት ማግኘት እችላለሁ?’ ብለን እንጠይቃለን። ይሁንና ስለ አንተ በእርግጥ የሚያስብ አለ?

“የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ያስብልሃል

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ሲል ይጠራዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3) ስሙ ይሖዋ የሆነው አምላክ መጽናኛ እንደሚያስፈልገን ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘መጽናኛ’ የሚለውን ቃል በተለያየ መንገድ ከመቶ ጊዜ በላይ የተጠቀመበት ሲሆን አምላክ የሚደርሱብንን ችግሮች እንደሚያውቅ ብቻ ሳይሆን እኛን ለማጽናናት ፍላጎት እንዳለውም ያረጋግጥልናል። ይህንን እውነታ ማወቃችን ሌሎች ችግራችን እንደማይታያቸው፣ ያለንበትን ሁኔታ እንደማይረዱ ወይም ስለ እኛ ምንም ደንታ እንደሌላቸው በሚሰማን ጊዜም እንኳ ይሖዋ አምላክ እንደሚያስብልን እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ይሖዋ ለሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብላቸው የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎችን ይዘዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ዐይኖች በሁሉም ስፍራ ናቸው፤ ክፉዎችንም ደጎችንም ነቅተው ይመለከታሉ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:3) በተመሳሳይም ኢዮብ 34:21 “ዐይኖቹ የሰውን አካሄድ ይመለከታሉ፤ ርምጃውንም ሁሉ ይከታተላሉ” ይላል። ይሖዋ ጥሩም ይሁን መጥፎ የምናደርገውን ነገር ይመለከታል፤ እንዲሁም አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት እንዲያስችለው ያለንበትን ሁኔታ ይከታተላል። ባለ ራእዩ ተብሎ የተጠራው ነቢዩ አናኒ እንደሚከተለው በማለት ለይሁዳ ንጉሥ ለአሳ የተናገረው ሐሳብ ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል፦ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።”—2 ዜና መዋዕል 16:7, 9

ይሖዋ እኛን የሚመለከትበት ሌላም ምክንያት አለው። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:44) ይሖዋ አንድ ሰው እሱን ለማወቅ ይፈልግ እንደሆነ ለማየት ልቡን ይመረምራል። በግለሰቡ ልብ ውስጥ እንዲህ ያለ ዝንባሌ ከተመለከተም አስገራሚ በሆነ መንገድ ሊረዳው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የምትኖር አንዲት ሴት በካንሰር በሽታ ምክንያት ቀዶ ሕክምና እንዲደረግላት ሆስፒታል ተኝታ ነበር። እዚያው ሆና እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘት እንድትችል ይረዳት ዘንድ አምላክን ለመነች። ወዲያውኑም ባለቤቷ የዚያኑ ዕለት ጠዋት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል ከነበረች የይሖዋ ምሥክር የተቀበለውን አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? * የተባለውን ብሮሹር ይዞላት መጣ። ይህች ሴት ብሮሹሩን ካነበበች በኋላ አምላክ ለጸሎቷ መልስ እንደሰጣት ተረዳች። በኋላም ብሮሹሩን ለባለቤቷ ካበረከተችለት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማች ሲሆን ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ለአምላክ ወስና ተጠመቀች።

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመዝሙር መጽሐፍ፣ ንጉሥ ዳዊትን የመሰሉ በጥንት ዘመን የነበሩ ዕብራውያን የዘመሯቸውን በርካታ ማራኪ መዝሙሮች የያዙ ሲሆን እነዚህ መዝሙሮች ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚያሳይ ይገልጻሉ። በመዝሙር 56:8 ላይ ንጉሥ ዳዊት “እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?” በማለት አምላክን እንደተማጸነ እናነባለን። ከዚህ ንጽጽር ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ መዝሙራዊው እየደረሰበት ያለውን መከራ ብቻ ሳይሆን መከራው በስሜቱ ላይ ያስከተለውን ሥቃይ ጭምር እንደሚያውቅ ዳዊት ተረድቶ ነበር። ይሖዋ የዳዊትን ሥቃይ ያውቅ የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንባውን እንዲያፈስ ያደረገውን ውስጣዊ ስሜት ተመልክቶ ነበር። እውነት ነው፣ ፈጣሪያችን ፈቃዱን ለማድረግ የሚጥሩትንና “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን” ሰዎች ሁሉ ይመለከታል።

የአምላክን ፍቅራዊ አሳቢነት የሚገልጸው ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ደግሞ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው 23ኛው መዝሙር ነው። ይህ መዝሙር የሚጀምረው “[ይሖዋ] እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም” በማለት ሲሆን አምላክን ከአንድ አፍቃሪ እረኛ ጋር ያነጻጽረዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖር አንድ እረኛ እያንዳንዱን በግ በእንክብካቤ የሚይዝ ሲሆን ሌላው ቀርቶ ስም ያወጣላቸዋል። በየቀኑ እያንዳንዱን በግ ጠርቶ በፍቅር ያሻሸዋል፤ እንዲሁም ጉዳት ደርሶበት እንደሆነ ለማየት ይሞክራል። አንድ በግ እንደተጎዳ ከተመለከተም ቁስሉ ቶሎ እንዲድን ዘይት ወይም ሌላ ነገር ይቀባዋል። በጉ እንደታመመ ካስተዋለ ደግሞ በግድም ቢሆን መድኃኒት ያጠጣውና ተኝቶ በዛው እንዳይሞት በማሰብ ደግፎ ያቆመዋል። ይሖዋ የእሱን እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ምን ያህል እንደሚያስብ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

ጸሎትና ትንሣኤ—አምላክ እንደሚያስብልህ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

ከላይ ያየናቸውም ሆኑ ማራኪ የሆኑት ሌሎች መዝሙሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት በማንበብ ደስታ እንድናገኝ ተብሎ ብቻ አይደለም። መዝሙሮቹ በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ የአምላክን እርዳታ እንደሚፈልጉ እንዲሁም ከእሱ ለሚያገኙት መመሪያና በረከት አመስጋኝ እንደሆኑ ለመግለጽ ለይሖዋ ልባቸውን ያፈሰሱት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው። የጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ እንደሚያስብላቸው ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው ከእነዚህ መዝሙሮች በግልጽ መረዳት ይቻላል። እነዚህን ከልብ የመነጩ መዝሙሮች ማንበብና በሐሳቦቹ ላይ ማሰላሰል እኛም ስለ አምላክ ተመሳሳይ የሆነ ስሜት እንዲያድርብን ሊረዳን ይችላል። በእርግጥም የጸሎት መብት አምላክ እንደሚያስብልን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው!

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በችግራችን በጣም ከመዋጣችን የተነሳ ስለ ጉዳዩ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን እንኳ ይጠፋናል። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጭንቀታችንን ሳይረዳ ይቀራል ማለት ነው? ሮም 8:26 እንዲህ ሲል መልሱን ይሰጠናል፦ “መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ ችግሩ መጸለይ በሚያስፈልገን ጊዜ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤ ሆኖም በቃላት መግለጽ ተስኖን በምንቃትትበት ጊዜ መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል።” ባለፉት ዘመናት የኖሩት የአምላክ አገልጋዮች የጸለዩአቸው ጸሎቶች የእኛን ስሜት የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም ‘ጸሎት ሰሚ’ የሆነው ይሖዋ፣ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ የተመዘገቡትን ጸሎቶች እኛ እንዳቀረብናቸው አድርጎ እንደሚቀበል ከዚህ ጥቅስ መረዳት እንችላለን።—መዝሙር 65:2

አምላክ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ትኩረት እንደሚሰጥ የሚያሳየው ሌላው አሳማኝ ማስረጃ ደግሞ የትንሣኤ ተስፋ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የእሱን ድምፅ ሰምተው እንደሚወጡ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት የግሪክኛ ቃል “መቃብር” ብቻ ከማለት ይልቅ “መታሰቢያ መቃብር” ተብሎ መተርጎሙ ተገቢ ነው። ይህ ጥቅስ አምላክ፣ አንድ ሰው በሕይወት ሳለ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር የሚያስታውስ መሆኑን ይጠቁማል።

እስቲ አስበው፦ አምላክ ለአንድ ሰው እንደገና ሕይወት ለመስጠት ይህ ሰው ምን እንደሚመስል፣ ከወላጆቹ የወረሳቸውንና በሕይወት ዘመኑ ያዳበራቸውን ባሕርያት እንዲሁም በአእምሮው ውስጥ ያከማቸውን መረጃ በሙሉ ጨምሮ ስለ ግለሰቡ ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት። (ማርቆስ 10:27) አምላክ ስለዚህ ሰው የሚያውቃቸውን ነገሮች ከሺህ ዓመታት በኋላም እንኳ ያስታውሳቸዋል። (ኢዮብ 14:13-15፤ ሉቃስ 20:38) በመሆኑም ይሖዋ አምላክ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሙታንን እንደሚያስታውስና ስለ እያንዳንዳቸውም በዝርዝር እንደሚያውቅ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይህ ደግሞ አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልን የሚያረጋግጥ ግሩም ማስረጃ ነው።

ይሖዋ ወሮታ ከፋይ ነው

አምላክ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲያሳየን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ከሁሉ በፊት፣ በእሱ እንደምንታመንና እንደምንታዘዘው እንዲሁም በእሱ እምነት እንዳለን ማሳየት አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አምላክ እንዲያስብልን ከፈለግን እምነት እንዳለን ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ሲገልጽ የሚከተለውን ብሏል፦ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ አምላክ የሚቀርብ ሰው እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።”—ዕብራውያን 11:6

አምላክ የሚደሰትበት እምነት ሁለት ነገሮችን እንደሚያካትት ልብ በል። በመጀመሪያ “እሱ መኖሩን” ማለትም አምላክ እንዳለና የበላይ ገዥያችን እንደሆነ እንዲሁም ልንታዘዘውና ልናመልከው እንደሚገባን ማመን አለብን። ሁለተኛ “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” ማመን ይኖርብናል። እውነተኛ እምነት፣ አምላክ ፈቃዱን ለማድረግ ከልብ የሚፈልጉ ሰዎች ደኅንነት እንደሚያሳስበውና ወሮታ እንደሚከፍላቸውም ማመንን ይጨምራል። አንተም የአምላክን ቃል በማጥናትና እሱን ከሚታዘዙት ጋር በአምልኮ በመተባበር እንዲህ ያለውን እምነት ማዳበር ትችላለህ፤ ይህን ዓይነቱን እምነት ማዳበርህ አምላክ ወሮታ እንዲከፍልህና ከፍቅር የመነጨ አሳቢነት እንዲያሳይህ ያነሳሳዋል።

በዛሬው ጊዜ ብዙዎች አምላክ የሰው ልጆች ሁኔታ እንደማያሳስበው ሲናገሩ ይሰማል። ይሁንና እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ በእሱ ላይ እውነተኛ እምነት እንዳላቸው በተግባር ለሚያሳዩ ሰዎች በጥልቅ እንደሚያስብ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። በዛሬው ጊዜ ሕይወት በሐሳብና በጭንቀት እንዲሁም በብስጭትና በሐዘን የተሞላ ቢሆንም ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ምክንያቱም ይሖዋ አምላክ ያስብልናል። እንዲያውም የእሱን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦልናል። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።”—መዝሙር 55:22

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አምላክ ለአንተ እንደሚያስብ ያለህን እምነት የሚያጠናክሩ ጥቅሶች

“በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉና።”—2 ዜና መዋዕል 16:9

“እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን?”—መዝሙር 56:8

“እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም።”—መዝሙር 23:1

“ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ።”—መዝሙር 65:2

“ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ።”—ኢዮብ 14:15

“ወደ አምላክ የሚቀርብ ሰው እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል።”—ዕብራውያን 11:6

“የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።”—መዝሙር 55:22