በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ ቤት የምትቀኑ ሁኑ!

ለይሖዋ ቤት የምትቀኑ ሁኑ!

ለይሖዋ ቤት የምትቀኑ ሁኑ!

“የቤትህ ቅንዓት ያንገበግበኛል።”—ዮሐ. 2:17

1, 2. ኢየሱስ በ30 ዓ.ም. በቤተ መቅደሱ ውስጥ ምን አደረገ? ለምንስ?

የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ጊዜው 30 ዓ.ም. የፋሲካ በዓል የሚከበርበት ሰሞን ነው። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ከጀመረ ስድስት ወራት ሆኖታል። አሁን በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ነው። እዚያ በደረሰ ጊዜም በቤተ መቅደሱ የአሕዛብ አደባባይ “ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን” ተመለከተ። ከዚያም በገመድ ጅራፍ ሁሉንም እንስሶች አስወጣ፤ ነጋዴዎቹም እንስሶቻቸውን ተከትለው ወጡ። በተጨማሪም ኢየሱስ የገንዘብ ለዋጮችን ሳንቲሞች በተነ፤ እንዲሁም ጠረጴዛዎቻቸውን ገለባበጠ። ርግብ ሻጮቹንም ንብረታቸውን ይዘው እንዲወጡ አዘዛቸው።—ዮሐ. 2:13-16

2 ኢየሱስ ያደረገው ነገር ለቤተ መቅደሱ ይቆረቆር እንደነበር የሚያሳይ ነው። “የአባቴን ቤት የንግድ ቤት ማድረጋችሁ ይብቃ!” ሲል ተናገረ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲመለከቱ ከዘመናት በፊት በመዝሙራዊው ዳዊት የተጻፈውን “የቤትህ ቅንዓት ያንገበግበኛል” የሚለውን ቃል አስታወሱ።—ዮሐ. 2:16, 17፤ መዝ. 69:9

3. (ሀ) ቅንዓት ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?

3 ኢየሱስ እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳው ለአምላክ ቤት ያለው ቅንዓት ነው። ቅንዓት የሚለው ቃል “አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጉጉትና ጽኑ ፍላጎት ማሳደር” የሚል ትርጉም አለው። በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቤት ቅንዓት እንዳላቸው እያሳዩ ነው። ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ‘ለይሖዋ ቤት ያለኝን ቅንዓት ማሳደግ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እንዲረዳን በመጀመሪያ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ቤት ሲባል ምንን እንደሚያመለክት እንመርምር። ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ለአምላክ ቤት ቅንዓት እንዳላቸው ያሳዩ ታማኝ ሰዎችን ታሪክ እንመለከታለን። እነዚህ ሰዎች የተዉት ምሳሌ የተመዘገበው “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” ተብሎ ስለሆነ ታሪካቸውን መመርመራችን ቅንዓታችንን እንድናሳድግ ሊገፋፋን ይችላል።—ሮም 15:4

የአምላክ ቤት—በጥንት ጊዜና አሁን

4. ሰለሞን የገነባው ቤተ መቅደስ ለምን ዓላማ አገልግሎ ነበር?

4 በጥንቷ እስራኤል፣ የአምላክ ቤት በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ነበር። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ቃል በቃል በዚያ ይኖር ነበር ማለት አይደለም። ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማረፊያ ናት፤ ታዲያ የምትሠሩልኝ ቤት፣ የማርፍበትስ ስፍራ የቱ ነው?” (ኢሳ. 66:1) ያም ቢሆን በሰለሞን የግዛት ዘመን የተገነባው ቤተ መቅደስ ጸሎት የሚቀርብበት ቦታ በመሆኑ የይሖዋ አምልኮ ማዕከል ነበር።—1 ነገ. 8:27-30

5. የሰለሞን ቤተ መቅደስ በዘመናችን ጥላ የሆነለት ነገር ምንድን ነው?

5 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ቤት በኢየሩሳሌምም ሆነ በሌላ ቦታ የሚገኝን አንድ ሕንፃ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ እንድንችል የተደረገልንን ዝግጅት ያመለክታል። በምድር ዙሪያ የሚኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ በዚህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሆነው ይሖዋን በአንድነት ያመልካሉ።—ኢሳ. 60:4, 8, 13፤ ሥራ 17:24፤ ዕብ. 8:5፤ 9:24

6. ለእውነተኛው አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት እንዳላቸው ያሳዩት የይሁዳ ነገሥታት እነማን ናቸው?

6 የእስራኤል መንግሥት በ997 ዓ.ዓ. ለሁለት ከተከፈለ በኋላ፣ በስተ ደቡብ ያለውን የይሁዳን መንግሥት ከገዙት 19 ነገሥታት መካከል 4ቱ ለእውነተኛው አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት እንዳላቸው አሳይተዋል። እነሱም አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ናቸው። እነዚህ ነገሥታት ከተዉት ምሳሌ ምን ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

በሙሉ ልብ የሚቀርብ አገልግሎት በረከት ያስገኛል

7, 8. (ሀ) የይሖዋን በረከት የሚያስገኘው እንዴት ባለ መንፈስ የሚቀርብ አገልግሎት ነው? (ለ) ከንጉሥ አሳ ምሳሌ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 በንጉሥ አሳ የግዛት ዘመን ይሖዋ ሕዝቡ ታማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ለመርዳት ነቢያቱን ልኮላቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አሳ የዖዴድ ልጅ የሆነው ነቢዩ አዛርያስ የሚሰጠውን መመሪያ ይከተል እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 15:1-8ን አንብብ።) አሳ የይሖዋን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ያደረገው ጥረት የይሁዳን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ በተደረገው ታላቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከእስራኤል መንግሥት የመጣውን ታላቅ ሕዝብ ጭምር አንድ አድርጓል። በዚህ ወቅት ሁሉም ይሖዋን በታማኝነት ለማምለክ ያላቸውን ቁርጥ ውሳኔ ገልጸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፦ “በታላቅ ድምፅ፣ በእልልታ፣ በእምቢልታና በመለከት ድምፅ ለእግዚአብሔር ማሉ። በፍጹም ልባቸው ስለማሉም የይሁዳ ሕዝብ በመሐላው ደስ ተሰኙ። እግዚአብሔርን ከልብ ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው።” (2 ዜና 15:9-15) እኛም በተመሳሳይ ይሖዋን በሙሉ ልብ የምናገለግል ከሆነ እንደሚባርከን ምንም ጥርጥር የለውም።—ማር. 12:30

8 የሚያሳዝነው ግን አሳ ከጊዜ በኋላ ባለ ራእዩ አናኒ ምክር ሲሰጠው ተበሳጨ። (2 ዜና 16:7-10) ይሖዋ በክርስቲያን ሽማግሌዎች አማካኝነት ምክር ወይም መመሪያ ሲሰጠን ምን ይሰማናል? ከመበሳጨት ወይም ቅር ከመሰኘት ይልቅ ሽማግሌዎቹ የሚሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተቀብለን ወዲያውኑ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን?

9. ኢዮሣፍጥና የይሁዳ ሕዝብ ምን ስጋት የሚፈጥር ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር? እነሱስ ምን አደረጉ?

9 ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ የገዛው በአሥረኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነበር። በወቅቱ የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች የተባበረ የጦር ኃይል በኢዮሣፍጥም ሆነ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ስጋት ፈጥሮ ነበር። ንጉሡ ፍርሃት አድሮበት የነበረ ቢሆንም ምን አደረገ? እሱም ሆነ የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ለመጸለይ በይሖዋ ቤት ተሰበሰቡ። (2 ዜና መዋዕል 20:3-6ን አንብብ።) ቀደም ሲል ሰለሞን በቤተ መቅደሱ ምረቃ ላይ በተናገረው መሠረት ኢዮሣፍጥ እንዲህ ሲል ይሖዋን ተማጸነ፦ “አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።” (2 ዜና 20:12, 13) ኢዮሣፍጥ ከጸለየ በኋላ፣ ሌዋዊው የሕዚኤል በይሖዋ መንፈስ ተነሳስቶ ሕዝቡ በአምላክ ላይ እንዲተማመን ብሎም እንዲጽናና የሚያደርግ ሐሳብ ተናገረ።—2 ዜና መዋዕል 20:14-17ን አንብብ።

10. (ሀ) ኢዮሣፍጥና የይሁዳ ሕዝብ መመሪያ ያገኙት እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለሚሰጠን መመሪያ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 በዚያን ጊዜ ይሖዋ ለኢዮሣፍጥም ሆነ ለይሁዳ ሕዝብ መመሪያ የሰጠው በየሕዚኤል በኩል ነበር። በዛሬው ጊዜ ደግሞ ማጽናኛና ማበረታቻ የምናገኘው በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል ነው። እኛን ተግተው የሚጠብቁንን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠው መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ጠንክረው የሚሠሩትን የተሾሙ ሽማግሌዎች ልንተባበራቸውና ልናከብራቸው ይገባል።—ማቴ. 24:45፤ 1 ተሰ. 5:12, 13

11, 12. ኢዮሣፍጥና የይሁዳ ሕዝብ ከገጠማቸው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ኢዮሣፍጥና ሕዝቡ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት በአንድነት እንደተሰበሰቡ ሁሉ እኛም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትን ቸል አንበል። አንዳንድ ጊዜ ከባድ ችግር ቢያጋጥመንና ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ ቢገባን ኢዮሣፍጥና የይሁዳ ሕዝብ የተዉትን ግሩም ምሳሌ እንከተል፤ እነሱ እንዳደረጉት በይሖዋ ሙሉ በሙሉ በመተማመን ወደ እሱ እንጸልይ። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ከወንድሞቻችን ጋር መገናኘት የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ ለይሖዋ የምናቀርበው ጸሎት ‘በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ካሉት ወንድሞቻችን’ ጋር አንድ ያደርገናል።—1 ጴጥ. 5:9

12 ኢዮሣፍጥና ሕዝቡ አምላክ በየሕዚኤል በኩል የሰጣቸውን መመሪያ ተከትለዋል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኘ? የተደቀነባቸውን ጦርነት በድል አጠናቅቀው “በታላቅ ደስታ” ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እንዲሁም “በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ።” (2 ዜና 20:27, 28) እኛም ይሖዋ መመሪያ ለማስተላለፍ በሚጠቀምበት መስመር በኩል የሚሰጡንን መመሪያዎች በመከተል ከሌሎች ጋር በአንድነት እሱን እናወድሰዋለን።

የመሰብሰቢያ ቦታዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ ያዙ

13. ሕዝቅያስ፣ በነገሠ በመጀመሪያው ወር ምን ሥራ እንዲከናወን አደረገ?

13 ሕዝቅያስ፣ በነገሠ በመጀመሪያው ወር፣ ተዘግቶ የነበረው ቤተ መቅደስ ታድሶ ሥራ እንዲጀምር በማድረግ ለይሖዋ አምልኮ ቅንዓት እንዳለው አሳይቷል። የአምላክን ቤት እንዲያነጹ ካህናቱንና ሌዋውያኑን አደራጀ። እነሱም በ16 ቀናት ውስጥ ሥራቸውን አጠናቀቁ። (2 ዜና መዋዕል 29:16-18ን አንብብ።) በዚያን ጊዜ የተሠራው ሥራ በአሁኑ ጊዜ መሰብሰቢያ ቦታዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ ለመያዝ ሲባል የሚደረገውን ጥገናና እድሳት የሚያስታውሰን ሲሆን ይህ ደግሞ ለይሖዋ አምልኮ ቅንዓት እንዳለን ያሳያል። ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ባለው ሥራ በቅንዓት ሲካፈሉ የተመለከቱ ሰዎች አድናቆታቸውን እንደገለጹ የሚናገሩ ተሞክሮዎችን ሰምተህ ታውቃለህ? አዎን፣ የእነዚህ ወንድሞች ሥራ ለይሖዋ ክብር አምጥቷል።

14, 15. በዛሬው ጊዜ ለይሖዋ ክብር እያመጣ ያለው የትኛው ሥራ ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ።

14 በሰሜን እንግሊዝ በምትገኝ አንዲት ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤቱ አጠገብ ያለውን የመንግሥት አዳራሽ ለማደስ የሚያደርጉትን ጥረት ተቃወመ። ሆኖም ወንድሞች ሁኔታውን የያዙበት መንገድ ደግነት የተንጸባረቀበት ነበር። የመንግሥት አዳራሹንና የሰውየውን ግቢ የሚያዋስነው አጥር ጥገና እንደሚያስፈልገው ስለተመለከቱ፣ ወንድሞች በራሳቸው ወጪ ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኞች እንደሆኑ ገለጹለት። ወንድሞች ጠንክረው በመሥራት አብዛኛውን የግንቡን ክፍል እንደ አዲስ ገነቡት። ሁኔታውን በጥሩ መንገድ መያዛቸው ጎረቤትየው አመለካከቱን እንዲቀይር አድርጎታል። አሁን ይህ ሰው ለመንግሥት አዳራሹ ደህንነት የሚቆረቆር ሆኗል።

15 የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የግንባታ ሥራ ይካፈላሉ። ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞችና ዓለም አቀፍ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የመንግሥት አዳራሾችን ብቻ ሳይሆን ትልልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችንና የቤቴል ቤቶችን ይገነባሉ። ሳም የተዋጣለት መሃንዲስ ሲሆን እሱና ባለቤቱ ሩት በተለያዩ የአውሮፓና የአፍሪካ አገሮች በተካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተካፍለዋል። በሄዱበት አገር ሁሉ በአካባቢው ካሉ ጉባኤዎች ጋር በስብከቱ ሥራ ይካፈላሉ። እንዲህ ባሉ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲካፈል ያነሳሳው ምን እንደሆነ ሳም ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በተለያዩ አገሮች በሚገኙ የቤቴል ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች የሰጡኝ ማበረታቻ ነው። እነዚህ ወንድሞች ያላቸውን ቅንዓትና ደስታ ስመለከት እኔም በእንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት ለመሰማራት ፍላጎት አደረብኝ።”

መለኮታዊ መመሪያዎችን ታዘዙ

16, 17. የአምላክ ሕዝቦች በየትኛው ልዩ እንቅስቃሴ በቅንዓት ተካፍለዋል? ምን ውጤትስ ተገኝቷል?

16 ሕዝቅያስ ቤተ መቅደሱን ከመጠገን በተጨማሪ ይሖዋ በየዓመቱ እንዲከበር ያዘዘው የፋሲካ በዓል እንደገና መከበር እንዲጀምር አድርጓል። (2 ዜና መዋዕል 30:1, 4, 5ን አንብብ።) ሕዝቅያስና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች መላውን የይሁዳ ብሔር ሌላው ቀርቶ በስተ ሰሜን በሚገኘው የእስራኤል መንግሥት ሥር ያለውን ሕዝብ ጭምር በበዓሉ ላይ እንዲገኝ ጋበዙ። በመላው የአገሪቱ ክፍል የግብዣ ደብዳቤዎችን የሚያደርሱ መልእክተኞች ተላኩ።—2 ዜና 30:6-9

17 እኛም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሥራ አከናውነናል። ኢየሱስ እንድናስበው ያዘዘውን የጌታን እራት በዓል በክልላችን ያሉ ሰዎች ከእኛ ጋር እንዲያከብሩ ለመጋበዝ ማራኪ የሆኑ የግብዣ ወረቀቶችን አሠራጭተናል። (ሉቃስ 22:19, 20) በአገልግሎት ስብሰባችን ላይ በተሰጠን መመሪያ መሠረት በዚህ ሥራ በቅንዓት ተካፍለናል። ይሖዋም ይህን ጥረት በእጅጉ ባርኮታል! ባለፈው ዓመት ሰባት ሚሊዮን ገደማ የምንሆን የይሖዋ ምሥክሮች የግብዣ ወረቀቶችን ያሠራጨን ሲሆን በአጠቃላይ 17,790,631 የሚያህሉ ሰዎች በበዓሉ ላይ መገኘታቸው የሚያስደስት ነው!

18. ለእውነተኛው አምልኮ ቀናተኛ መሆንህ አንተን በግልህ የጠቀመህ እንዴት ነው?

18 ስለ ሕዝቅያስ እንደሚከተለው ተብሎለታል፦ “በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ታመነ፤ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ፣ እንደ እርሱ ያለ አልነበረም። ከእግዚአብሔር ጋር ተጣበቀ፤ እርሱን ከመከተል ወደ ኋላ አላለም፤ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውንም ትእዛዞች ጠበቀ።” (2 ነገ. 18:5, 6) እኛም የሕዝቅያስን ምሳሌ እንከተል። ለአምላክ ቤት ያለን ቅንዓት፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን አሻግረን በመመልከት ‘ከይሖዋ ጋር ተጣብቀን’ እንድንኖር ይረዳናል።—ዘዳ. 30:16

መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣን ሁኑ

19. ወንድሞች ከመታሰቢያው በዓል ጋር በተያያዘ እንዴት ያለ ቅንዓት የተሞላበት ጥረት ያደርጋሉ?

19 ኢዮስያስም ንጉሥ ሆኖ በገዛበት ጊዜ የፋሲካን በዓል ለማክበር ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ነበር። (2 ነገ. 23:21-23፤ 2 ዜና 35:1-19) እኛም ለአውራጃና ለወረዳ ስብሰባዎች እንዲሁም ለልዩ ስብሰባ ቀናትና የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል ለማክበር ጥሩ ዝግጅት እናደርጋለን። በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ መጣል ቢጠይቅባቸውም እንኳ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል። ቀናተኛ የሆኑ ሽማግሌዎች ሁሉም የጉባኤ አባላት በበዓሉ ላይ እንዲገኙ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። አረጋውያንና አቅመ ደካማ የሆኑ ወንድሞች በበዓሉ ላይ እንዲገኙ እርዳታ ይደረግላቸዋል።

20. (ሀ) በንጉሥ ኢዮስያስ የግዛት ዘመን ምን ተከሰተ? ኢዮስያስ ሁኔታውን የያዘው እንዴት ነበር? (ለ) ከኢዮስያስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

20 ንጉሥ ኢዮስያስ እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ለማቋቋም ያደራጀው ሥራ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት፣ ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ “በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።” ከዚያም መጽሐፉን ለንጉሡ ጸሐፊ ለሳፋን የሰጠው ሲሆን ሳፋንም ለኢዮስያስ አነበበለት። (2 ዜና መዋዕል 34:14-18ን አንብብ።) ታዲያ ይህ ሁኔታ ምን ውጤት አስገኘ? ንጉሡ የሕጉን ቃል ሲሰማ በጣም ከማዘኑ የተነሳ ልብሱን ቀደደ፤ እንዲሁም አገልጋዮቹ ይሖዋን እንዲጠይቁ አዘዘ። አምላክ በነቢይቱ ሕልዳና አማካኝነት በይሁዳ ይካሄዱ የነበሩትን አንዳንድ የአምልኮ ሥርዓቶች እንደሚያወግዝ ተናገረ። ያም ሆኖ ኢዮስያስ የጣዖት አምልኮን ለማስወገድ ያደረገውን መልካም ጥረት ይሖዋ ተመልክቶ ስለነበር የይሁዳ ሕዝብ እንደሚጠፋ ትንቢት ቢነገርም እሱ ግን የአምላክን ሞገስ አግኝቷል። (2 ዜና 34:19-28) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የእኛም ፍላጎት ከኢዮስያስ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ክህደት አምልኳችንን እንዲበክል ከፈቀድን ምን ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ፈጣን መሆን አለብን። ይሖዋ ለኢዮስያስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ለእውነተኛው አምልኮ የምናሳየውን ቅንዓት በአድናቆት እንደሚመለከት እርግጠኛ መሆን እንችላለን።

21, 22. (ሀ) ለይሖዋ ቤት ቀናተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

21 ከላይ የተጠቀሱት አራቱ የይሁዳ ነገሥታት ማለትም አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ለአምላክ ቤትና ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆኑናል። እኛም በተመሳሳይ ቅንዓታችን በይሖዋ እንድንታመን እንዲሁም ለእውነተኛው አምልኮ እንድንተጋ ሊያነሳሳን ይገባል። መለኮታዊ መመሪያዎችን መታዘዛችን፣ በጉባኤና በተሾሙ ሽማግሌዎች አማካኝነት ለሚደረግልን ፍቅራዊ እንክብካቤ አመስጋኝ መሆናችን እንዲሁም የሚሰጠንን ምክር መቀበላችን የጥበብ አካሄድ ከመሆኑም ሌላ ደስታ እንደሚያስገኝልን የተረጋገጠ ነው።

22 የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ በስብከቱ ሥራ ቀናተኞች እንድንሆን እንዲሁም ወጣቶች አፍቃሪ የሆነውን አባታችንን በቅንዓት እንዲያገለግሉት የሚያበረታታ ትምህርት ይዟል። በተጨማሪም ሰይጣን አእምሯችንን ለመመረዝ ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች መካከል አንዱን እንዴት መከላከል እንደምንችል እንመረምራለን። መጽሐፍ ቅዱስ “የቤትህ ቅናት በላችኝ” ተብሎ በመዝሙር ላይ የተነገረው በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ይነግረናል። እኛም ከይሖዋ የምናገኛቸውን መመሪያዎች በቅንዓት ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ የይሖዋ ልጅ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለናል ማለት ነው።—መዝ. 69:9፤ 119:111, 129፤ 1 ጴጥ. 2:21

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋን በረከት የሚያስገኘው እንዴት ባለ መንፈስ የሚቀርብ አገልግሎት ነው? ለምንስ?

• በይሖዋ እንደምንተማመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• ቅንዓት መለኮታዊ መመሪያዎችን እንድንታዘዝ የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ለይሖዋ ቤት ቅንዓት እንዳላቸው ያሳዩት እንዴት ነው?