በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለመልካም ሥራ የምትቀኑ’ ሁኑ!

‘ለመልካም ሥራ የምትቀኑ’ ሁኑ!

‘ለመልካም ሥራ የምትቀኑ’ ሁኑ!

“ክርስቶስ እኛን ከማንኛውም ዓይነት ዓመፅ ለማዳንና ለመልካም ሥራ የሚቀና የእሱ ብቻ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ራሱን ለእኛ ሰጥቷል።”—ቲቶ 2:14

1. ኢየሱስ በኒሳን 10, 33 ዓ.ም. ቤተ መቅደሱ ሲደርስ ምን ተከሰተ?

ዕለቱ ኒሳን 10, 33 ዓ.ም. ሲሆን የፋሲካ በዓል ሊከበር የቀረው ጥቂት ቀናት ብቻ ነው። ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ አካባቢ ለአምልኮ የተሰባሰቡ ሰዎች በዓሉ የሚከበርበትን ጊዜ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ ምን ይከሰት ይሆን? ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ የተባሉት የወንጌል ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ አባረረ። በተጨማሪም የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎች ገለባበጠ። (ማቴ. 21:12፤ ማር. 11:15፤ ሉቃስ 19:45) ኢየሱስ ከሦስት ዓመት በፊት ተመሳሳይ እርምጃ በወሰደበት ጊዜ የነበረው ቅንዓት አሁንም አልቀዘቀዘም።—ዮሐ. 2:13-17

2, 3. የኢየሱስ ቅንዓት ቤተ መቅደሱን ከማጽዳት ያለፈ ነገር እንዲያደርግ አነሳስቶታል እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

2 የማቴዎስ ዘገባ እንደሚያሳየው የኢየሱስ ቅንዓት ቤተ መቅደሱን ከማጽዳት ያለፈ ነገር እንዲያደርግ አነሳስቶታል። በዚህ ወቅት ወደ እሱ የመጡትን ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ፈውሷል። (ማቴ. 21:14) የሉቃስ ዘገባ ደግሞ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ሌሎች ተግባራት ሲገልጽ “በየዕለቱ በቤተ መቅደሱ ማስተማሩን ቀጠለ” ይላል። (ሉቃስ 19:47፤ 20:1) ስለሆነም የኢየሱስ ቅንዓት በአገልግሎቱ ጉልህ ሆኖ ታይቷል።

3 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ እንዲህ በማለት ጽፎለታል፦ “ክርስቶስ እኛን ከማንኛውም ዓይነት ዓመፅ ለማዳንና ለመልካም ሥራ የሚቀና የእሱ ብቻ የሆነ ሕዝብ ለራሱ ለማንጻት ራሱን ለእኛ ሰጥቷል።” (ቲቶ 2:14) በዛሬው ጊዜ ‘ለመልካም ሥራ የምንቀና’ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? አራቱ የይሁዳ ነገሥታት የተዉት ጥሩ ምሳሌ ለመልካም ሥራ ቀናተኛ እንድንሆን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ቀናተኛ ሁኑ

4, 5. አራቱ የይሁዳ ነገሥታት ለመልካም ሥራ ቀናተኛ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?

4 አሳ፣ ኢዮሣፍጥ፣ ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ጣዖት አምልኮን ከይሁዳ ጠራርጎ ለማጥፋት ዘመቻ አካሂደዋል። አሳ “ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብታዎችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም ቈራረጠ።” (2 ዜና 14:3) ኢዮሣፍጥ ለይሖዋ አምልኮ የነበረው ከፍተኛ ቅንዓት “ማምለኪያ ኰረብታዎችንና የአሼራ ዐምዶችን ከይሁዳ [እንዲያስወግድ]” አነሳስቶታል።—2 ዜና 17:6፤ 19:3 *

5 ሕዝቅያስ በኢየሩሳሌም ያዘጋጀው የፋሲካ በዓል ለሰባት ቀን ከተከበረ በኋላ ‘በዚያ የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ይሁዳ ከተሞች ወጥተው፣ የማምለኪያ ድንጋዮችን ሰባበሩ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈረጡ፤ እንዲሁም በመላው ይሁዳና በብንያም፣ በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን የኰረብታ መስገጃዎችና መሠዊያዎች አጠፉ።’ (2 ዜና 31:1) ወጣቱ ኢዮስያስ ንጉሥ የሆነው ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ ‘በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ።’ (2 ዜና 34:3) እስካሁን እንደተመለከትነው አራቱም ነገሥታት ለመልካም ሥራ ቀናተኛ መሆናቸውን አሳይተዋል።

6. በዛሬው ጊዜ የምናካሂደው አገልግሎት ታማኞቹ የይሁዳ ነገሥታት ካካሄዷቸው ዘመቻዎች ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

6 በዛሬው ጊዜም የይሁዳ ነገሥታት ከወሰዱት እርምጃ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሰዎች ጣዖት አምልኮን ጨምሮ ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ነፃ እንዲሆኑ በመርዳቱ ሥራ በትጋት እንካፈላለን። ከቤት ወደ ቤት የምናደርገው አገልግሎት ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ያገናኘናል። (1 ጢሞ. 2:4) የእስያ ተወላጅ የሆነች አንዲት ወጣት፣ እናቷ በቤት ውስጥ ባሉ በርካታ ምስሎች ፊት የአምልኮ ሥርዓት ስትፈጽም ትመለከት ነበር። ሁሉም ምስሎች እውነተኛውን አምላክ ሊወክሉ እንደማይችሉ ስለተሰማት እውነተኛውን አምላክ ማወቅ እንድትችል አዘውትራ ትጸልይ ነበር። አንድ ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ የእሷን ቤት አንኳኩ፤ ከዚያም እውነተኛው አምላክ ልዩ የሆነ ስም እንዳለውና ስሙም ይሖዋ እንደሆነ አስረዷት። ስለ ጣዖታት እውነተኛውን ነገር በማወቋም በጣም ተደሰተች። ይህች ወጣት በአሁኑ ጊዜ ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት በስብከቱ ሥራ በትጋት በመካፈል ከፍተኛ ቅንዓት እንዳላት እያሳየች ነው።—መዝ. 83:18 NW፤ 115:4-8፤ 1 ዮሐ. 5:21

7. ኢዮሣፍጥ በገዛበት ዘመን በይሁዳ ከተማ ሁሉ በመዘዋወር ሕዝቡን ያስተማሩትን ሰዎች እንዴት ልንመስላቸው እንችላለን?

7 ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል የተሰጠንን ክልል ምን ያህል አጣርተን እንሸፍናለን? ኢዮሣፍጥ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የወሰደው እርምጃ ትኩረት የሚስብ ነው። በይሁዳ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ የይሖዋን ሕግ ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ አምስት ሹማምት፣ ዘጠኝ ሌዋውያንና ሁለት ካህናት ላከ። እነዚህ ሰዎች ያከናወኑት ሥራ በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሳ በዙሪያቸው የነበሩት ብሔራት ይሖዋን ፈሩ። (2 ዜና መዋዕል 17:9, 10ን አንብብ።) እኛም በተለያየ ቀንና ሰዓት ከቤት ወደ ቤት የምንሄድ ከሆነ የተለያዩ የቤተሰብ አባላትን ማግኘት እንችላለን።

8. የአገልግሎታችንን አድማስ ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?

8 በዘመናችን የሚገኙ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች ቤታቸውን ትተው ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ለመዛወር ፈቃደኞች ሆነዋል። አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ? አንዳንዶቻችን ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አንችል ይሆናል፤ ይሁንና በአካባቢያችን ለሚኖሩ ከእኛ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ለመመሥከር ጥረት ልናደርግ እንችላለን። ወንድም ራን በክልላቸው ውስጥ የተለያዩ ዜጎችን ስለሚያገኙ በ81 ዓመታቸው በ32 ቋንቋዎች እንዴት ሰላምታ መስጠት እንደሚቻል ተምረዋል! በቅርቡ መንገድ ላይ ሲያገለግሉ አፍሪካውያን ባልና ሚስት አገኙና በዮሩባ ቋንቋ ሰላምታ ሰጧቸው። ከዚያም እነዚህ ባልና ሚስት ወንድም ራን አፍሪካ ሄደው ያውቁ እንደሆነ ጠየቋቸው። ወንድም ራንም “ሄጄ አላውቅም” ሲሉ መለሱ፤ በዚህ ጊዜ ‘ታዲያ አፍ መፍቻ ቋንቋችንን እንዴት ሊያውቁ ቻሉ?’ ብለው ወንድምን ጠየቋቸው። ይህ ሁኔታ ለወንድም ራን ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ከፈተላቸው። እነዚህ ባልና ሚስት መጽሔቶችን በደስታ የተቀበሉ ከመሆኑም ሌላ አድራሻቸውን ሰጡ፤ ወንድም ራንም ባልና ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርላቸው በአካባቢያቸው ለሚገኘው ጉባኤ አድራሻቸውን አስተላለፉ።

9. በአገልግሎታችን ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን ማንበባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 በመላው ይሁዳ እየተዘዋወሩ ሕዝቡን እንዲያስተምሩ ኢዮሣፍጥ የላካቸው ሰዎች ‘የይሖዋን ሕግ መጽሐፍ’ ይዘው ነበር። በተመሳሳይም በየትኛውም የዓለም ክፍል የምንገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማስተማር እንጥራለን። በአገልግሎታችን ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን ለማንበብ ልዩ ጥረት እናደርጋለን። ሊንዳ የተባለች የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አንዲት ሴት አገኘች፤ ሴትየዋም ባለቤቷ ታሞ ቤት እንደተኛና የእሷን እንክብካቤ እንደሚፈልግ ገለጸችላት። ከዚያም “አምላክ ይህ መከራ በእኔ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ምን ብበድል እንደሆነ አላውቅም” በማለት በሐዘን ተናገረች። ሊንዳም “ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ሁኚ” አለቻትና ያዕቆብ 1:13 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አነበበችላት። አክላም “የምንወዳቸው ሰዎችም ሆኑ እኛ መከራ የሚደርስብን አምላክ እየቀጣን ስለሆነ አይደለም” አለቻት። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ምስጋናዋን ለመግለጽ ሊንዳን አቀፈቻት። ሊንዳ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚያጽናና ሐሳብ ላሳያት ችያለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናነብላቸውን ጥቅስ ከዚያ ቀደም ሰምተውት እንኳ አያውቁም።” ይህ ውይይት ሴትየዋ በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የሚያስችላትን አጋጣሚ ከፍቶላታል።

በቅንዓት የሚያገለግሉ ወጣቶች

10. ኢዮስያስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያን ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

10 እስቲ ቀደም ሲል የተመለከትነውን የኢዮስያስን ምሳሌ ደግመን እናንሳ፤ ኢዮስያስ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ እውነተኛውን አምልኮ የተከተለ ሲሆን በ20 ዓመቱ ደግሞ የጣዖት አምልኮን ለማጥፋት ሰፊ ዘመቻ አካሂዷል። (2 ዜና መዋዕል 34:1-3ን አንብብ።) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች በአገልግሎት ቀናተኛ መሆናቸውን አሳይተዋል።

11-13. በዘመናችን ይሖዋን በቅንዓት እያገለገሉ ካሉ ወጣቶች ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 በእንግሊዝ የምትኖረው ሃና የ13 ዓመት ልጅ በነበረችበት ወቅት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ከተማ ውስጥ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚመራ ቡድን መቋቋሙን ሰማች፤ በዚያን ጊዜ በትምህርት ቤት ፈረንሳይኛ ቋንቋ ትማር ነበር። ቡድኑ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ መገኘት ስለፈለገችም አባቷ አብሯት ለመሄድ ተስማማ። አሁን 18 ዓመት የሆናት ሃና የዘወትር አቅኚ ሆና በፈረንሳይኛ ቋንቋ በቅንዓት ትሰብካለች። አንተስ ሌላ ቋንቋ ተምረህ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ መርዳት ትችል ይሆን?

12 ሬቸል ደግሞ አምላክን የሚያስከብር ግብ ላይ ለመድረስ ተጣጣሩ የሚለውን የቪዲዮ ፊልም መመልከቷ በጣም አስደስቷታል። በ1995 ይሖዋን ማገልገል በጀመረችበት ወቅት የነበራትን አመለካከት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “በመንፈሳዊ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለሁ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ይህን ፊልም ከተመለከትኩ በኋላ ግን ለበርካታ ዓመታት መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማድረግ ብቻ ረክቼ እኖር እንደነበር ተገነዘብኩ። እውነትን ይበልጥ አጥብቄ መያዝ እንዲሁም አገልግሎቴንና የግል ጥናቴን የማከናውንበትን መንገድ በተመለከተ በቁም ነገር ማሰብና ትጋት ማሳየት እንዳለብኝ ተረዳሁ።” በአሁኑ ጊዜ ሬቸል ይሖዋን ይበልጥ በቅንዓት እያገለገለች እንደሆነ ይሰማታል። ታዲያ ይህ ምን በርከት አስገኝቶላታል? “ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ተጠናክሯል። ጸሎቴ ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል፤ የግል ጥናቴም ጥልቀት ያለውና ይበልጥ አስደሳች ሆኖልኛል፤ እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማነባቸው ታሪኮች ከበፊቱ የበለጠ ሕያው ሆነው ይታዩኛል። በዚህም ምክንያት አገልግሎቴ በጣም አስደሳች ሆኖልኛል፤ ከዚህም ሌላ የይሖዋ ቃል ሌሎችን እንዴት እንደሚያጽናና መመልከት እውነተኛ እርካታ አስገኝቶልኛል።”

13 ሉክ የተባለ አንድ ወጣት፣ የወጣቶች ጥያቄሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል? የተሰኘውን ፊልም መመልከቱ አበረታቶታል። ሉክ ይህን ፊልም ከተመለከተ በኋላ የተሰማውን ሲገልጽ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሕይወቴን እንዴት እየተጠቀምኩበት እንዳለሁ እንዳስብ አድርጎኛል። መንፈሳዊ ግቦች ላይ ትኩረት ከማድረጌ በፊት ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝልኝ ሥራ ለመያዝ የሚያስችለኝን ከፍተኛ ትምህርት እንድከታተል ተጽዕኖ ይደረግብኝ ነበር። እንዲህ ያለው ጫና ደግሞ አንድ ሰው በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ አይረዳውም፤ እንዲያውም ያዳክመዋል።” ወጣት የሆናችሁ ወንድሞችና እህቶች፣ በትምህርት ቤት የምትማሩትን ነገር ልክ እንደ ሃና አገልግሎታችሁን ለማስፋት ልትጠቀሙበት ትችሉ እንደሆነ እስቲ አስቡ። በተጨማሪም አምላክን የሚያስከብር ግብ ላይ ለመድረስ በቅንዓት በመጣጣር የሬቸልን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። ለብዙ ወጣቶች ወጥመድ እየሆነ ያለውን አደጋ በመሸሽ የሉክን ምሳሌ ተከተሉ።

ማስጠንቀቂያዎችን ሰምታችሁ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ቀናተኛ ሁኑ

14. በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምን ዓይነት አምልኮ ነው? በዛሬው ጊዜ ይህን ከባድ የሚያደርገው ምንድን ነው?

14 የአምላክ ሕዝቦች አምልኳቸው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ንጹሕ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ኢሳይያስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “እናንት የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ፣ ተለዩ፤ ተለዩ፤ ከዚያ ውጡ፤ ርኵስ ነገር አትንኩ፤ ከዚያ [ከባቢሎን] ውጡ ንጹሓንም ሁኑ።” (ኢሳ. 52:11) ኢሳይያስ ይህን ከመጻፉ ከብዙ ዓመታት በፊት ንጉሥ አሳ የሥነ ምግባር ብልግናን ከይሁዳ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ጠንካራ እርምጃ ወስዶ ነበር። (1 ነገሥት 15:11-13ን አንብብ።) ከበርካታ ዘመናት በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ኢየሱስ “ለመልካም ሥራ የሚቀና የእሱ ብቻ የሆነ ሕዝብ” እንዲሆኑ ተከታዮቹን ለማንጻት ራሱን እንደሰጠ ገልጿል። (ቲቶ 2:14) በሥነ ምግባር ባዘቀጠው በዛሬው ዓለም ውስጥ የሥነ ምግባር ንጽሕናን ጠብቆ መመላለስ በተለይ ለወጣቶች ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ወጣት አዋቂ ሳይል የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ በትላልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የሚለጠፉ የጾታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ሥዕሎችን እንዲሁም በቴሌቪዥን፣ በፊልሞችና በተለይ በኢንተርኔት የሚተላለፉ የብልግና ምስሎችን በመመልከት አእምሯቸው እንዳይመረዝ ከፍተኛ ትግል ማድረግ አለባቸው።

15. ክፉ ወይም መጥፎ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ እንድናዳብር ምን ሊረዳን ይችላል?

15 አምላክ የሚሰጠንን ማስጠንቀቂያዎች ሰምተን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ቀናተኞች መሆናችን ክፉ ወይም መጥፎ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ እንድናዳብር ይረዳናል። (መዝ. 97:10፤ ሮም 12:9) አንድ ክርስቲያን እንደገለጸው ከሆነ “እንደ ማግኔት ያለ ከፍተኛ የሆነ የመሳብ ኃይል ያለውን የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ እርግፍ አድርጎ ለመተው” እንዲህ ያለውን ልማድ መጸየፍ ይኖርብናል። ሁለት የተጣበቁ ማግኔቶችን ለማለያየት ከተፈለገ ሁለቱን ብረቶች ካጣበቃቸው የበለጠ ኃይል መጠቀም ያስፈልጋል። በተመሳሳይም የብልግና ምስሎችን መመልከት ያለውን የማታለል ኃይል ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። ያም ሆኖ የብልግና ምስሎች ምን ያህል ጉዳት ሊያስከትሉብን እንደሚችሉ መገንዘባችን ለእነዚህ ነገሮች ጥላቻ እንድናዳብርና እንድንጸየፋቸው ይረዳናል። አንድ ወንድም የብልግና ምስሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች በኢንተርኔት የመመልከት ልማዱን ለማሸነፍ ብርቱ ትግል ማድረግ አስፈልጎታል። ወንድም ኮምፒውተሩን መላው ቤተሰብ በቀላሉ ሊያየው በሚችለው ቦታ ላይ አስቀመጠ። ከዚህም ባሻገር ራሱን ከዚህ ርኩስ ልማድ ለማንጻትና መልካም ሥራዎችን በመሥራት ቀናተኛ ለመሆን ከመቼውም በበለጠ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ይሁንና በዚህ ብቻ አልተወሰነም። ሰብዓዊ ሥራው ኢንተርኔት እንዲጠቀም ቢያስገድደውም ባለቤቱ አጠገቡ ተቀምጣ ካልሆነ በስተቀር ኢንተርኔት ላለመጠቀም ወሰነ።

መልካም ምግባር ማሳየት ያለው ጥቅም

16, 17. ጥሩ ክርስቲያናዊ ምግባር ማሳየታችን በሚመለከቱን ሰዎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል? ምሳሌ ስጥ።

16 በይሖዋ አገልግሎት የሚተጉ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ የሚመለከቷቸውን ሰዎች የሚማርክ እንዴት ያለ ግሩም መንፈስ አላቸው! (1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።) አንድ ሰው በለንደን ቤቴል ውስጥ የማተሚያ ማሽን በመጠገን ሙሉ ቀን ካሳለፈ በኋላ ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ባለቤቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናች የነበረ ሲሆን የባሏ አመለካከት እንደተለወጠ ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደባትም። ቀደም ሲል ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ እንዲመጡ አይፈልግም ነበር። ቤቴል ለሥራ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ ግን በዚያ ያሉ ወንድሞች ስላሳዩት ደግነት አውርቶ አይጠግብም። ጸያፍ ቃላት የሚናገር አንድም ሰው እንዳልነበረ፣ ሁሉም ሰው ትዕግሥተኛ እንደሆነና በመካከላቸውም ሰላማዊ መንፈስ እንዳለ ማስተዋሉን ተናግሯል። ከሁሉ የበለጠ ያስደነቀው ግን ወጣት ወንድሞችና እህቶች ምሥራቹን ለማዳረስ የሚረዱ ጽሑፎችን ለማተሙ ሥራ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኝነት በመስጠት ያለ ክፍያ በቅንዓት ሲሠሩ መመልከቱ ነበር።

17 በተመሳሳይም ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ሲሉ ሰብዓዊ ሥራ የሚሠሩ ወንድሞችና እህቶች ሥራቸውን በሙሉ ነፍስ ያከናውናሉ። (ቆላ. 3:23, 24) ጠንቃቃና ትጉ ሠራተኞች መሆናቸው በአሠሪዎቻቸው ዘንድ አድናቆት ስለሚያተርፍላቸው እንዲሁም ተፈላጊ እንዲሆኑ ስለሚያደርጋቸው በአብዛኛው ሥራቸውን የማጣታቸው አጋጣሚ አነስተኛ ነው።

18. ‘ለመልካም ሥራ የምንቀና’ ሰዎች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 በይሖዋ መታመን፣ መመሪያዎቹን መታዘዝና መሰብሰቢያ ቦታዎቻችንን በጥሩ ሁኔታ መያዝ ለይሖዋ ቤት የምንቀና መሆናችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በተቻለን መጠን የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ እንፈልጋለን። ወጣት አዋቂ ሳይል ሁላችንም ይሖዋ ከሚጠብቅብን ንጹሕ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ብርቱ ትግል የምናደርግ ከሆነ የተትረፈረፈ በረከት እናጭዳለን። እንዲሁም “ለመልካም ሥራ የሚቀና” ሕዝብ ሆነን መቀጠል እንችላለን።—ቲቶ 2:14

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 አሳ የሐሰት አምልኮ ይካሄድባቸው የነበሩ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ሲያስወግድ ሕዝቡ ይሖዋን ያመልክባቸው የነበሩትን ኰረብታዎች አላጠፋ ይሆናል። ወይም ደግሞ የማምለኪያ ኰረብታዎቹ በእሱ የግዛት ዘመን መጨረሻ አካባቢ በድጋሚ የተገነቡና በኋላ ላይ ልጁ ኢዮሣፍጥ ያጠፋቸው ሊሆኑ ይችላሉ።—1 ነገ. 15:14፤ 2 ዜና 15:17

ከመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ከዘመናችን ከተመለከትናቸው ምሳሌዎች . . .

• በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ቀናተኛ መሆንህን ማሳየት ስለምትችልበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• ክርስቲያን ወጣቶች ‘ለመልካም ሥራ የሚቀኑ’ መሆን ስለሚችሉበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

• አእምሮን ከሚመርዙ ልማዶች መላቀቅ ስለሚቻልበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎታችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራችሁ ትጠቀማላችሁ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትምህርት ቤት ሌላ ቋንቋ መማራችሁ አገልግሎታችሁን ማስፋት የምትችሉበት አጋጣሚ ሊከፍትላችሁ ይችላል