በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ

ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ

ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ

“ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።”—ኤፌ. 4:25

1, 2. ብዙዎች ለእውነት ምን አመለካከት አላቸው?

እውነት ለዘመናት ሰዎችን ሲያወዛግብ የኖረ ጉዳይ ነው። “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” የሚል የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር አለ። ይህ አባባል አንድ ሰው እውነተኛ ስሜቱን አውጥቶ የሚናገረው ከመጠን በላይ ጠጥቶ ብዙ ሲያወራ እንደሆነ ይጠቁማል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ጳንጥዮስ ጲላጦስ የተባለ ሮማዊ አገረ ገዥም፣ ኢየሱስን “እውነት ምንድን ነው?” በማለት በምጸት መጠየቁ እውነትን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት እንደነበረው ያሳያል።—ዮሐ. 18:38

2 በዘመናችን እውነትን በተመለከተ እርስ በርስ የሚቃረኑ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ። ብዙ ሰዎች “እውነት” የሚለው ቃል የተለያየ ትርጉም እንደሚሰጠው ይሰማቸዋል፤ ወይም እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚል አመለካከት አላቸው። ሌሎች ደግሞ እውነትን የሚናገሩት ጥቅም የሚያስገኝላቸው ወይም ችግር የማያስከትልባቸው ከሆነ ብቻ ነው። መዋሸት ያለው ጥቅም (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሐቀኝነት፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ባሕርይ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይህ ባሕርይ ለመኖርና ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚደረገው የሞት ሽረት ትግል ላይ እምብዛም ጥቅም የለውም። በዚህ ረገድ የሰው ልጅ ብዙ ምርጫ የለውም፤ ለመኖር መዋሸት አለበት።”

3. ኢየሱስ እውነትን በመናገር በኩል ግሩም ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

3 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ያላቸው አመለካከት ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው! እውነትን በተመለከተ ከላይ የተገለጹት ሐሳቦች ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከነበረው አመለካከት ጋር ይቃረናሉ። ኢየሱስ ምንጊዜም ቢሆን እውነትን ይናገር ነበር። ጠላቶቹም እንኳ “መምህር፣ አንተ እውነተኛ እንደሆንክና የአምላክን መንገድ በትክክል እንደምታስተምር . . . እናውቃለን” ብለውታል። (ማቴ. 22:16) ዛሬም በተመሳሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ይከተላሉ። ምንጊዜም ቢሆን እውነትን ከመናገር ወደኋላ አይሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ውሸትን ስላስወገዳችሁ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸውን ምክር በሙሉ ልባቸው ይቀበላሉ። (ኤፌ. 4:25) እስቲ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር ከሦስት አቅጣጫዎች እንመርምር። አንደኛ፣ ባልንጀራችን ማን ነው? ሁለተኛ፣ እውነትን መናገር ሲባል ምን ማለት ነው? ሦስተኛ፣ ይህንን ምክር በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ባልንጀራችን ማን ነው?

4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ባልንጀራን በተመለከተ ምን አስተሳሰብ ነበራቸው? ኢየሱስ ከዚህ በተለየ መልኩ የይሖዋን አመለካከት ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ “ባልንጀራ” ተብሎ ሊጠራ የሚገባው አይሁዳዊ የሆነ ሰው ወይም የቅርብ ጓደኛቸው ብቻ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ኢየሱስ ግን የአባቱን ባሕርይና አስተሳሰብ ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) አምላክ አንድን ዘር ወይም ብሔር ከሌላው እንደማያስበልጥ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷቸዋል። (ዮሐ. 4:5-26) በተጨማሪም ‘አምላክ እንደማያዳላ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው’ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ገልጦለታል። (ሥራ 10:28, 34, 35) በመሆኑም ሁሉንም ሰው እንደ ባልንጀራችን አድርገን መመልከት እንዲሁም ለሚጠሉንም ጭምር ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል።—ማቴ. 5:43-45

5. ከባልንጀሮቻችን ጋር እውነትን መነጋገር ሲባል ምን ማለት ነው?

5 ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከባልንጀሮቻችን ጋር እውነትን መነጋገር እንዳለብን ሲገልጽ ምን ማለቱ ነበር? እውነትን መናገር፣ ከማታለል የጸዳ ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍን ይጨምራል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎችን ለማሳሳት ሐቁን አያጣምሙም ወይም አያዛቡም። ከዚህ ይልቅ ‘ክፉ የሆነውን ነገር ይጸየፋሉ’ እንዲሁም ‘ጥሩ የሆነውን ነገር አጥብቀው ይይዛሉ።’ (ሮም 12:9) “የእውነት አምላክ” የሆነውን የይሖዋን ምሳሌ በመከተል በድርጊታችንም ሆነ በንግግራችን ሁሉ ሐቀኞች ለመሆን መጣር እንዲሁም መረጃዎችን አድበስብሰን ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። (መዝ. 15:1, 2፤ 31:5) የሚያሳፍሩ ወይም ደስ የማይሉ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ የምንናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ በመምረጥ ሳንዋሽ ጉዳዩን በዘዴ መፍታት እንችላለን።—ቆላስይስ 3:9, 10ን አንብብ።

6, 7. (ሀ) እውነትን መናገር ሲባል ጥያቄ ለሚያቀርብልን ሰው ሁሉ ስለ ግል ጉዳያችንም ጭምር በዝርዝር እንናገራለን ማለት ነው? አብራራ። (ለ) ዝርዝር መረጃ መስጠት የሚገባን ለእነማን ነው?

6 እውነትን መናገር ሲባል ስለ አንድ ጉዳይ ለጠየቀን ለማንኛውም ሰው የምናውቀውን በሙሉ እንናገራለን ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት፣ ለአንዳንድ ሰዎች ቀጥተኛ መልስ መስጠት ወይም አንዳንድ መረጃዎችን መናገር ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ አሳይቷል። ግብዝ የሆኑት ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ምልክቶችንና ተአምራትን የሚያከናውነው በማን ኃይል ወይም ሥልጣን እንደሆነ ሲጠይቁት ኢየሱስ “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ” አላቸው። ጸሐፍትና ሽማግሌዎች ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ኢየሱስ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” ብሏቸዋል። (ማር. 11:27-33) እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ምግባረ ብልሹና እምነት የለሽ ስለነበሩ ኢየሱስ ለጥያቄያቸው መልስ መስጠት እንደሚገባው አልተሰማውም። (ማቴ. 12:10-13፤ 23:27, 28) በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ሕዝቦች ከከሃዲዎች እንዲሁም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የማታለያ ዘዴና በተንኮል የተወጠነ አሳሳች ሐሳብ ከሚያመነጩ ሌሎች ክፉ ሰዎች መራቅ ይኖርባቸዋል።—ማቴ. 10:16፤ ኤፌ. 4:14

7 ጳውሎስም በተመሳሳይ ለአንዳንድ ሰዎች ዝርዝር መረጃ መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል። ሐዋርያው “ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ” ሰዎች “ማውራት የማይገባቸውን ነገር [እንደሚያወሩ]” ተናግሯል። (1 ጢሞ. 5:13) በእርግጥም ሰዎች፣ በሌሎች ጉዳይ ጣልቃ ለሚገቡ ወይም ሚስጥር መጠበቅ ለማይችሉ ግለሰቦች ስለ ግል ጉዳያቸው መናገር አይፈልጉም። ጳውሎስ “በጸጥታ ለመኖር፣ በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት . . . እንድትጣጣሩ እናሳስባችኋለን” በማለት በመንፈስ ተመርቶ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ምንኛ የተሻለ ነው። (1 ተሰ. 4:11) ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ሲሉ ስለ ግል ጉዳያችን መጠየቅ ይኖርባቸው ይሆናል። በዚህ ጊዜ እውነቱን በመናገር ከእነሱ ጋር መተባበራችንን የሚያደንቁት ከመሆኑም ሌላ ለሥራቸው ከፍተኛ እገዛ ያበረክታል።—1 ጴጥ. 5:2

በቤተሰብ ውስጥ እውነትን ተነጋገሩ

8. የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ እውነትን መነጋገራቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

8 ከቤተሰባችን አባላት የበለጠ የምንቀርበው ሰው የለም ማለት ይቻላል። ከቤተሰባችን ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ እንድንችል እርስ በርሳችን እውነትን መነጋገራችን በጣም አስፈላጊ ነው። በምንነጋገርበት ወቅት ግልጽና ሐቀኞች መሆናችን እንዲሁም ሐሳባችንን ደግነት በተሞላበት መንገድ መግለጻችን በመካከላችን የሚፈጠሩ ችግሮችንና አለመግባባቶችን ለመቀንስ ወይም ለማስወገድ ያስችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሠራነውን ስህተት ለትዳር ጓደኛችን፣ ለልጆቻችን ወይም ለሌሎች የቅርብ የቤተሰባችን አባላት ከመናገር ወደኋላ እንላለን? ለሠራነው ስህተት ከልብ ይቅርታ መጠየቃችን በቤተሰባችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍንና አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።—1 ጴጥሮስ 3:8-10ን አንብብ።

9. እውነትን መናገራችን፣ ለሌሎች ስሜት ሳንጠነቀቅ እንዳመጣልን ለመናገር ሰበብ የማይሆነው ለምንድን ነው?

9 እውነትን እንናገራለን ሲባል ለሌሎች ስሜት ሳንጠነቀቅ እንዳመጣልን እንናገራለን ማለት አይደለም። አንድ ሰው የሚናገረው ነገር እውነት ቢሆንም እንኳ አክብሮት በጎደለው መንገድ መናገሩ ንግግሩ ክብደት እንዳይሰጠው ሊያደርግ ይችላል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “የመረረ ጥላቻ፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ ጩኸትና ስድብ ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ መካከል ይወገድ። ይልቁንም አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌ. 4:31, 32) ደግነትና ክብር በሚንጸባረቅበት መንገድ መናገራችን የምንናገረው ነገር ክብደት እንዲኖረው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ለምናነጋግራቸው ሰዎች አክብሮት እንዳለን ያሳያል።—ማቴ. 23:12

ከጉባኤ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እውነትን ተነጋገሩ

10. ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ኢየሱስ እውነትን በመናገር ረገድ ከተወው ግሩም ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

10 ኢየሱስ፣ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲነጋገር ሐሳቡን ግልጽ በሆነና ባልተድበሰበሰ መንገድ ይነግራቸው ነበር። ምክር የሚሰጣቸው ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ቢሆንም አድማጮቹን ለማስደሰት ሲል ሐቁን አለሳልሶ አልተናገረም። (ዮሐ. 15:9-12) ለምሳሌ ይህል፣ ሐዋርያቱ ከመካከላቸው የሚበልጠው ማን እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜያት በተከራከሩበት ወቅት ኢየሱስ የትሕትናን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ሆኖም በትዕግሥት አስረድቷቸዋል። (ማር. 9:33-37፤ ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24-27፤ ዮሐ. 13:14) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለጽድቅ ጠንካራ አቋም ቢኖራቸውም በአምላክ መንጋ ላይ ሥልጣናቸውን አያሳዩም። (ማር. 10:42-44) ከዚህ ይልቅ ‘አንዳቸው ለሌላው ደግነት’ በማሳየትና ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ‘ከአንጀት የሚራሩ’ በመሆን የክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ።

11. ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር አንደበታችንን ከምንጠቀምበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?

11 ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ሐሳባችንን በሐቀኝነት መናገር ቢኖርብንም የተሰማንን ሁሉ መናገር አለብን ማለት አይደለም፤ ይህም ወንድሞቻችንን በማያስቀይም መንገድ ሐሳባችንን ለመግለጽ ያስችለናል። በእርግጥም ማናችንም ብንሆን አንደበታችን “እንደ ሰላ ምላጭ” እንዲሆን አንፈልግም፤ በሌላ አነጋገር የሚያቆስልና የሚያዋርድ ነገር በመናገር የሌሎችን ስሜት መጉዳት አንፈልግም። (መዝ. 52:2፤ ምሳሌ 12:18) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ‘አንደበታችንን ከክፉ ነገር እንድንከለክልና ከንፈራችንንም ከሽንገላ እንድንጠብቅ’ ይገፋፋናል። (መዝ. 34:13) እንዲህ በማድረግ አምላክን እናስከብራለን እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እናበረክታለን።

12. በፍርድ ኮሚቴ የሚታየው ምን ዓይነት ውሸት ነው? አብራራ።

12 ሽማግሌዎች፣ ተንኮል ያዘሉ ውሸቶችን ከሚናገሩ ሰዎች ጉባኤውን ለመጠበቅ ጠንክረው ይሠራሉ። (ያዕቆብ 3:14-16ን አንብብ።) ተንኮል ያዘለ ውሸት የሚነገረው አንድን ሰው ለመጉዳት ታስቦ ነው፤ ዓላማውም ግለሰቡ እንዲያዝንና ስሜቱ እንዲጎዳ ወይም ችግር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ውሸት ብዙም ጉዳት የሌለው የሚመስል ነገር ከመናገር፣ የሚያሳስት ሐሳብ ከመሰንዘር ወይም ሐቁን አጋንኖ ከመግለጽ የተለየ ነው። ሁሉም ውሸት ስህተት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ሆኖም አንድ ሰው እውነት ያልሆነ ነገር ስለተናገረ ብቻ በፍርድ ኮሚቴ ፊት ይቀርባል ማለት አይደለም። በመሆኑም ሽማግሌዎች፣ ግለሰቡ በፍርድ ኮሚቴ ሊታይ የሚገባው የታሰበበትና ተንኮል ያዘለ ውሸት የመናገር ልማድ ይኖረው እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ሚዛናዊ፣ ምክንያታዊና አስተዋዮች መሆን ይኖርባቸዋል። አለዚያ ግን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ጠንከር ያለና ፍቅር የሚንጸባረቅበት ምክር መስጠቱ በቂ ሊሆን ይችላል።

ከሥራችሁ ጋር በተያያዘ እውነትን ተናገሩ

13, 14. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ለአሠሪያቸው ሐቀኞች የማይሆኑት በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) በሥራ ላይ ሐቀኛ መሆንና እውነትን መናገር ምን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

13 በዘመናችን ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸም በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው፤ በመሆኑም ለአሠሪያችን ሐቀኛ እንዳንሆን ፈተና የሚሆኑብንን ሁኔታዎች መቋቋም አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ብዙዎች ሥራ ለመቀጠር በሚያመለክቱበት ጊዜ ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የተሻለ ወይም ከፍተኛ ደሞዝ ያለው ሥራ ለማግኘት ሲሉ የሥራ ልምዳቸውን ወይም የትምህርት ደረጃቸውን በተመለከተ ከእውነታው የራቀ መረጃ ያቀርባሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ሠራተኞች ከድርጅቱ ደንብ ጋር የሚጋጭ ቢሆንም በሥራ ሰዓት የግል ጉዳያቸውን ያከናውናሉ። ሥራቸውን እያከናወኑ እንዳሉ በማስመሰል ከሥራቸው ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ጽሑፎችን ያነባሉ፣ ለግል ጉዳያቸው ስልክ ይደውላሉ፣ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት መልእክት ይለዋወጣሉ ወይም ኢንተርኔት ይጠቀማሉ።

14 እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ሐቀኛ መሆንና እውነትን መናገር ለግለሰቦች ምርጫ የተተወ ነገር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። (ምሳሌ 6:16-19ን አንብብ።) ጳውሎስ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]” ብሏል። (ዕብ. 13:18) በመሆኑም ክርስቲያኖች ከአሠሪያቸው ጋር በተዋዋሉት መሠረት ለሚከፈላቸው ደሞዝ የሚጠበቅባቸውን ያህል መሥራት እንደሚገባቸው ይገነዘባሉ። (ኤፌ. 6:5-8) ክርስቲያኖች ሥራችንን በትጋት ማከናወናችን በሰማይ ለሚኖረው አባታችንም ውዳሴ ያመጣል። (1 ጴጥ. 2:12) ለምሳሌ ያህል፣ በስፔን የሚኖረው ሮቤርቶ ሐቀኛና ኃላፊነት የሚሰማው ሠራተኛ መሆኑ የአሠሪውን ምስጋና አስገኝቶለታል። ሮቤርቶ ጥሩ ባሕርይ ያለው ሠራተኛ በመሆኑ ድርጅቱ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ቀጥሯል። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮችም ግሩም ሠራተኞች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። ባለፉት ዓመታት ውስጥ ሮቤርቶ 23 የይሖዋ ምሥክሮችንና 8 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስቀጥሯል!

15. በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ክርስቲያን ሐቀኛ መሆኑን እንዴት ማሳየት ይችላል?

15 የራሳችንን ሥራ የምንሠራ ከሆነ ደግሞ ከሥራችን ጋር በተያያዘ በማንኛውም ጉዳይ ሁልጊዜ እውነትን እንናገራለን? ወይስ አንዳንድ ጊዜ ለባልንጀሮቻችን እውነት ያልሆነ ነገር እንናገራለን? በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ክርስቲያን ደምበኞቹን የሚያሳስት ሐሳብ መናገር አይኖርበትም፤ ከዚህም በተጨማሪ ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል የለበትም። ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር እኛም ልናደርግላቸው እንፈልጋለን።—ምሳሌ 11:1፤ ሉቃስ 6:31

ለመንግሥት ባለሥልጣናት እውነትን ተናገሩ

16. ክርስቲያኖች (ሀ) ለመንግሥት ባለሥልጣናት (ለ) ለይሖዋ ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል?

16 ኢየሱስ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” ብሏል። (ማቴ. 22:21) ለቄሳር ማለትም ለመንግሥት ባለሥልጣናት መስጠት የሚገባን “ነገር” ምንድን ነው? ኢየሱስ ይህንን የተናገረው ግብር ከመክፈል ጋር በተያያዘ ነበር። ስለሆነም በአምላክም ሆነ በሰዎች ፊት ጥሩ ሕሊና እንዲኖረን ግብር መክፈልን ጨምሮ የአገራችንን ሕግ ሁሉ እንታዘዛለን። (ሮም 13:5, 6) ያም ቢሆን ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነው የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ይሖዋ እንደሆነ ስለምንገነዘብ እሱን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ አእምሯችንና ኃይላችን እንወደዋለን። (ማር. 12:30፤ ራእይ 4:11) በመሆኑም ያለ ምንም ገደብ ለይሖዋ አምላክ እንገዛለታለን።—መዝሙር 86:11, 12ን አንብብ።

17. የይሖዋ ሕዝቦች መንግሥት የሚሰጠውን እርዳታ ስለመቀበል ምን አመለካከት አላቸው?

17 በርካታ አገሮች የተቸገሩ ዜጎቻቸውን ለመርዳት የሚያስችሉ አንዳንድ ዝግጅቶች አሏቸው። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን እርዳታ ለመቀበል የሚያስፈልገውን መሥፈርት የሚያሟላ ከሆነ እርዳታውን ቢቀበል ምንም ስህተት የለውም። እንዲህ ያለውን እርዳታ ለማግኘት ስንል ለመንግሥት ባለሥልጣናት የሚያሳስት መረጃ የምንሰጥ ከሆነ ለባልንጀሮቻችን እውነትን እየተናገርን ነው ልንል አንችልም።

እውነትን መናገር የሚያስገኘው በረከት

18-20. ከባልንጀሮቻችን ጋር እውነትን መነጋገራችን ምን በረከቶች ያስገኛል?

18 እውነትን መናገር ብዙ በረከት ያስገኛል። እውነት የምንናገር ከሆነ ንጹሕ ሕሊና የሚኖረን ሲሆን ይህም የአእምሮ ሰላምና የተረጋጋ ልብ እንዲኖረን ያደርጋል። (ምሳሌ 14:30፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ንጹሕ ሕሊና በአምላክ ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ነገር እውነተኛ ከሆንን፣ የሠራነው ነገር ይታወቅብናል ወይም እንጋለጣለን ብለን አንፈራም።—1 ጢሞ. 5:24

19 እውነትን መናገር የሚያስገኘውን ሌላ በረከትም እንመልከት። ጳውሎስ ‘እውነተኛ ንግግርን’ ጨምሮ “በሁሉም መንገድ ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮ. 6:4, 7) በብሪታንያ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ አድርጓል። ይህ ወንድም መኪናውን ሊገዛ ለመጣ አንድ ሰው በግልጽ የማይታየውን የመኪናውን ጉድለት ጨምሮ የመኪናውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን ነገረው። ሰውየው የመኪናውን ሁኔታ ለመፈተሽ ከነዳ በኋላ ወንድምን ‘የይሖዋ ምሥክር ነህ?’ ብሎ ጠየቀው። ይህ ሰው እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? ሰውየው የወንድምን ሐቀኝነትና ሥርዓታማ አለባበስ አስተውሎ ነበር። ያደረጉት ውይይት ወንድም ለዚህ ሰው ጥሩ ምሥክርነት እንዲሰጥ አስችሎታል።

20 እኛም በተመሳሳይ ምንጊዜም ሐቀኞች በመሆንና እውነቱን በመናገር ለፈጣሪያችን ውዳሴ ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “አሳፋሪ የሆኑትን ስውር ነገሮች ትተናል፤ በተንኮል አንመላለስም።” (2 ቆሮ. 4:2) እንግዲያው ከባልንጀሮቻችን ጋር እውነትን ለመነጋገር የቻልነውን ሁሉ እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን በሰማይ ላለው አባታችንም ሆነ ለሕዝቦቹ ክብር ያመጣል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ባልንጀራችን ማን ነው?

• ከባልንጀራችን ጋር እውነትን መነጋገር ሲባል ምን ማለት ነው?

• እውነትን መናገር ለአምላክ ክብር የሚያመጣው እንዴት ነው?

• እውነትን መናገር ምን በረከቶች ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቃቅን ስህተቶች ስትሠራ ጥፋትህን አምነህ ትቀበላለህ?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥራ ለመቀጠር ስታመለክቱ እውነቱን ትናገራላችሁ?