በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ በመላው የእስራኤል ምድር ምሥራቹን ሰብኳል። ታዲያ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አይሁዳውያንና ገዥዎቻቸው ኢየሱስን ያስገደሉት “ባለማወቅ እንደሆነ” የተናገረው ለምንድን ነው?—ሥራ 3:17

ሐዋርያው ጴጥሮስ ተሰብስበው ለነበሩ አይሁዳውያን በሰጠው ንግግር ላይ እነዚህ ሰዎች ለመሲሑ መገደል አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ከገለጸ በኋላ “ገዥዎቻችሁ እንዳደረጉት ሁሉ እናንተም ይህን ያደረጋችሁት ባለማወቅ እንደሆነ አውቃለሁ” ብሎ ነበር። (ሥራ 3:14-17) አንዳንድ አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አልተገነዘቡ ብሎም ትምህርቶቹን አልተረዱ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ መሲሑን ማወቅ ያልቻሉት አምላክን የማስደሰት ፍላጎት ስላልነበራቸው፣ ጭፍን ጥላቻና ቅናት ስላደረባቸው አልፎ ተርፎም የመረረ ጥላቻ ስለነበራቸው ነው።

በርካታ አይሁዳውያን፣ ይሖዋን የማስደሰት ፍላጎት ያልነበራቸው መሆኑ ኢየሱስ ላስተማራቸው ነገሮች በነበራቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ የሚያስተምረው በምሳሌ ሲሆን ይበልጥ ለማወቅ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ሁሉ ምሳሌዎቹን ያብራራላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከአድማጮቹ መካከል አንዳንዶቹ ምሳሌውን ለመረዳት ምንም ጥረት አላደረጉም። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ ኢየሱስ በተጠቀመበት ምሳሌ ቅር ተሰኝተው ነበር። (ዮሐ. 6:52-66) ኢየሱስ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች፣ አድማጮቹ አስተሳሰባቸውንና ድርጊታቸውን ለመለወጥ ምን ያህል ፈቃደኞች መሆናቸውን የሚፈትኑ ናቸው፤ ሰዎቹ ግን ይህን አልተገነዘቡም ነበር። (ኢሳ. 6:9, 10፤ 44:18፤ ማቴ. 13:10-15) ከዚህም ሌላ መሲሑ በሚያስተምርበት ጊዜ በምሳሌዎች እንደሚጠቀም የሚገልጸውን ትንቢት ልብ አላሉም ነበር።—መዝ. 78:2

ሌሎች አይሁዳውያን ደግሞ ለኢየሱስ በነበራቸው ጭፍን ጥላቻ ምክንያት ትምህርቶቹን ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። ኢየሱስ፣ ባደገባት ከተማ በናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ባስተማረበት ወቅት ሕዝቡ ‘ተገርመው’ ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ከመቀበል ይልቅ አስተዳደጉን በተመለከተ እንዲህ በማለት ጠይቀዋል፦ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ያገኘው ከየት ነው? . . . ይህ አናጺው የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለም? እህቶቹስ ከእኛው ጋር አይደሉም?” (ማር. 6:1-3) ኢየሱስ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ትልቅ ቦታ በማይሰጠው ቤተሰብ ውስጥ ማደጉ የናዝሬት ሰዎች ትምህርቱን እንዳይቀበሉ እንቅፋት ሆኖባቸዋል።

ስለ ሃይማኖት መሪዎቹስ ምን ለማለት ይቻላል? ከእነሱም መካከል አብዛኞቹ ለኢየሱስ ጭፍን ጥላቻ ስለነበራቸው ለትምህርቱ ጆሮ አልሰጡም። (ዮሐ. 7:47-52) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስን ትምህርት እንዳይቀበሉ ያደረጋቸው ሌላው ምክንያት የሕዝቡን ትኩረት በማግኘቱ ቅናት አድሮባቸው ስለነበረ ነው። (ማር. 15:10) በተጨማሪም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩ ሰዎች ግብዝና አታላይ መሆናቸውን ኢየሱስ በማጋለጡ ብዙዎቹ እሱን መቀበል ከብዷቸዋል። (ማቴ. 23:13-36) ኢየሱስ፣ ሆነ ብለው እንደማያስተውሉ በመግለጽ እነዚህን ሰዎች እንዲህ ሲል ማውገዙ የተገባ ነበር፦ “እናንተ የሕጉ አዋቂዎች ወዮላችሁ! ምክንያቱም የእውቀትን ቁልፍ ነጥቃችሁ ወስዳችኋል፤ እናንተ ራሳችሁ [ወደ አምላክ መንግሥት] አትገቡም፤ ለመግባት የሚሞክሩትንም ትከለክላላችሁ።”—ሉቃስ 11:37-52

ኢየሱስ በእስራኤል ምድር ለሦስት ዓመት ተኩል ምሥራቹን ሰብኳል። በተጨማሪም ይህን ሥራ እንዲያከናውኑ በርካታ ሰዎችን አሠልጥኗል። (ሉቃስ 9:1, 2፤ 10:1, 16, 17) ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ሥራ እጅግ ውጤታማ ከመሆናቸው የተነሳ ፈሪሳውያን እንደሚከተለው በማለት ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፦ “ተመልከቱ፣ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል።” (ዮሐ. 12:19) በመሆኑም አብዛኞቹ አይሁዳውያን ስለ ኢየሱስ ምንም አያውቁም ማለት አይደለም። ይሁንና ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ‘ሳያውቁ’ ቀርተዋል። ስለ መሲሑ ያላቸውን እውቀት ማሳደግም ሆነ እሱን በጥልቅ መውደድ ይችሉ ነበር። አንዳንዶቹ ኢየሱስን ለመግደል በተጠነሰሰው ሴራ እጃቸውን አስገብተዋል። በመሆኑም ሐዋርያው ጴጥሮስ ብዙዎቹን እንዲህ በማለት መክሯቸዋል፦ “ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሐ ግቡ፣ ተመለሱም፤ ከይሖዋም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤ እንዲሁም ለእናንተ የሾመውን ክርስቶስን ይኸውም ኢየሱስን ይልክላችኋል።” (ሥራ 3:19, 20) ‘በጣም ብዙ ካህናትን’ ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ይህን ምክር የተቀበሉ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። እነዚህ ሰዎች ከዚያ በኋላ ባለማወቅ አልተመላለሱም። ከዚህ ይልቅ ንስሐ ገብተው የይሖዋን ሞገስ አግኝተዋል።—ሥራ 2:41፤ 4:4፤ 5:14፤ 6:7