በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት ይቻላል?

የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት ይቻላል?

የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት ይቻላል?

“በቤተሰብ ሆነን እሁድ እሁድ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ ነበረን። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ብዙም የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ አምናለሁ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ የማነበውን ነገር መረዳት በጣም ይከብደኝ ነበር።”—ስቲቨን፣ ብሪታንያ

“የ17 ዓመት ልጅ እያለሁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ሞክሬ ነበር። ሆኖም ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆነብኝ ማንበቤን አቆምኩ።”—ባልባኔራ፣ ስፔን

“ካቶሊክ ስለነበርኩ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር፤ በመሆኑም አንዴ ከዳር እስከ ዳር አንብቤዋለሁ። አንብቤ ለመጨረስም ሦስት ዓመት ፈጅቶብኛል! ይሁንና ካነበብኩት ውስጥ የተረዳሁት በጣም ጥቂቱን ነበር።” —ጆአን፣ አውስትራሊያ

መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ አሁንም በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ እጅግ ታዋቂ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከምንጊዜውም ይበልጥ ብዙ ሰዎች እንደልብ የሚያገኙት መሆኑና በበርካታ ቋንቋዎች መተርጎሙ ብሎም በመጽሐፍ መልክ ብቻ ሳይወሰን በካሴት፣ በሲዲና በዲቪዲ መዘጋጀቱ ከሌሎች መጻሕፍት ይልቅ በብዛት የሚሸጥ በመሆን ረገድ ቀዳሚነቱን ይዞ እንዲቀጥል አድርጎታል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። አንተስ እንዲህ ይሰማሃል?

አምላክ ቃሉን እንድንረዳ ይፈልጋል?

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ አምላክ ነው። ታዲያ አምላክ ቃሉን እንድንረዳ ይፈልጋል? ወይስ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው እንደ ቀሳውስትና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ያሉ የተመረጡ ሰዎች ብቻ እንዲረዱት አድርጎ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይህን በተመለከተ ምን እንደሚል ተመልከት፦

“በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም።”—ዘዳግም 30:11

“የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል።”—መዝሙር 119:130

“በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ።’”—ሉቃስ 10:21

አዎን፣ አምላክ ቃሉን እንድትረዳ ይፈልጋል! ያም ሆኖ በርካታ ቅን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚቸግራቸው መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ሊረዳህ ይችላል? ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ርዕሶች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ልትወስዳቸው የምትችላቸውን ሦስት እርምጃዎች ያብራራሉ።