በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1. አምላክን እንዲረዳህ ጠይቀው

1. አምላክን እንዲረዳህ ጠይቀው

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?

1. አምላክን እንዲረዳህ ጠይቀው

“ከመተኛቴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ ነበረኝ” በማለት በጣሊያን የምትኖረው ኒንፋ ተናግራለች። አክላም እንደሚከተለው ብላለች፦ “እንዲህ የማደርገው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አውቅ ስለነበረ ነው፤ ማንበቡ የሚያስደስተኝ ባይሆንም አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን እንዳስጻፈ የማወቅ ፍላጎት ነበረኝ። በመሆኑም መጽሐፉን አንብቤ የመጨረስ ግብ አወጣሁ። መጀመሪያ አካባቢ ማንበቡ ብዙም አልከበደኝም ነበር፤ ይሁንና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ዘገባዎች ጋ ስደርስ ማንበቤን አቆምኩ።”

አንተስ እንደ ኒንፋ ይሰማሃል? ብዙዎች እንዲህ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ አምላክ ቃሉን እንድትረዳ ይፈልጋል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ አምላክን እንዲረዳህ መጠየቅ ነው።

የኢየሱስ ሐዋርያት የረቢዎች ትምህርት ቤት ገብተው ሃይማኖታዊ ትምህርት ስላልተከታተሉ “ያልተማሩ ተራ ሰዎች” እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 4:13) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ የአምላክን ቃል መረዳት እንደሚችሉ አረጋግጦላቸዋል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል” በማለት ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 14:26) አምላክ ይህን ቅዱስ መንፈስ ተጠቅሞ ምድርንና በእሷ ላይ ያለውን ሕይወት በሙሉ ፈጥሯል። (ዘፍጥረት 1:2) በተጨማሪም 40 የሚያህሉ ሰዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሐሳብ እንዲጽፉ በመንፈስ ቅዱስ መርቷቸዋል። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚፈልጉ ሰዎችም ይህንኑ መንፈስ ማግኘት ይችላሉ።

ታዲያ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው? መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት በእምነት መለመን አለብህ። እንዲያውም ሳታቋርጥ መጠየቅ ሊኖርብህ ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ . . . ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ሉቃስ 11:9, 13) ይሖዋ በቅንነት ለሚለምኑት ሰዎች መንፈስ ቅዱስን አብዝቶ ለመስጠት ፈቃደኛ ነው። ይህ መንፈስ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ለመረዳት ያስችልሃል። በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ ከፍተኛ ኃይል ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሕይወትህ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችልህን ጥበብ ሊሰጥህ ይችላል።—ዕብራውያን 4:12፤ ያዕቆብ 1:5, 6

እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ ሁሉ ቃሉን እንድትረዳ የሚያስችልህን ቅዱስ መንፈስ እንዲሰጥህ ወደ አምላክ ጸልይ።