በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የሮም ወታደሮች የኢየሱስን እጀ ጠባብ በጣም የወደዱት ለምን ነበር?

ኢየሱስን የሰቀሉት አራት ወታደሮች የኢየሱስን መደረቢያዎች ተከፋፍለዋቸው ነበር። “ሆኖም እጀ ጠባቡ ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ” እንደነበር በዮሐንስ 19:23 ላይ ተገልጿል። በመሆኑም ወታደሮቹ እጀ ጠባቡን ከመቅደድ ይልቅ ዕጣ ተጣጥለው አንዳቸው ቢወስዱት እንደሚሻል ተስማሙ። የኢየሱስ እጀ ጠባብ የተሠራው እንዴት ነበር?

እዚህ ላይ የተገለጸው እጀ ጠባብ የሚሠራው ከበፍታ አሊያም ከሱፍ ሲሆን ቁመቱ እስከ ጉልበት ወይም እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርስና እጅጌ የሌለው እንደ ቀሚስ ያለ ልብስ ነው። አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ያሉ ልብሶች የሚሠሩት አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸውን ሁለት ጨርቆች አንድ ላይ ገጣጥሞ በመስፋት ነው። ለአንገትና ለእጅ ማስገቢያ በመተው ጨርቆቹ ከላይ እንዲሁም ከጎንና ከጎን ይሰፋሉ።

ጂሰስ ኤንድ ሂዝ ዎርልድ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከላይ ከተጠቀሰው ልብስ ይበልጥ ውድ ዋጋ ያለው እጀ ጠባብ ደግሞ አሠራሩ ተመሳሳይ ሆኖ “የሚዘጋጀው አንድ ወጥ ከሆነ ጨርቅ ነው፤ ጨርቁ ሁለት ቦታ ከታጠፈ በኋላ እጥፋቱ ላይ ለአንገት ማስገቢያ ቀዳዳ ይበጅለታል።” ከዚያም የአንገቱ ዙሪያ ይዘመዘማል። እንዲህ ያለው ልብስ መሰፋት የሚያስፈልገው ጎንና ጎኑ ላይ ብቻ ነው።

ኢየሱስ የለበሰው ዓይነት ምንም ስፌት የሌለው እጀ ጠባብ ይሠራ የነበረው በፓለስቲና ብቻ ነበር። እንዲህ ያለው ልብስ የሚሠራው በቁም መሸመኛ ነው። ቋሚ በሆኑ ሁለት እንጨቶች አናት ላይ አግድም አንድ እንጨት ከተዘረጋ በኋላ ድሮቹ በአግዳሚው እንጨት ላይ ከፊትና ከጀርባ ወደታች ይወጠራሉ። ሸማኔው ማጉን በያዘው መወርወሪያ በመጠቀም ማጉን ከአንድ ጫፍ ጀምሮ አንድ ድር ከላይ ሌላውን ድር ከታች እያደረገ በማጠላለፍ ከፊትና ከጀርባ የተወጠረውን ድር ይዞረዋል። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው በዚህ መንገድ የተሠራው ልብስ እንደ ከረጢት ዓይነት “ክብ ቅርጽ ይኖረዋል።” ምንም ስፌት ሳይኖረው የተሠራ እጀ ጠባብ በቀላሉ የማይገኝ ልብስ በመሆኑ ሁሉም ወታደሮች ለራሳቸው ፈልገውት ነበር።

በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ንብ አርቢዎች ነበሩ?

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚናገሩት አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ‘ማርና ወተት የምታፈስ ምድር’ እንደሚያወርሳቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘፀአት 3:8) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ ማር የሚገልጹት አብዛኞቹ ዘገባዎች የሚያመለክቱት ከጫካ የሚገኘውን ማር ሳይሆን አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቷ እስራኤል የንብ እርባታ ይካሄድ እንደነበር አይገልጽም። ሆኖም በቅርቡ በእስራኤል በቤትሺአን ሸለቆ የተገኘው ነገር በጥንት ዘመን እስራኤላውያን “የንብ እርባታ በስፋት ያካሂዱ እንደነበር” ይጠቁማል።

በሂብሩ ዩኒቨርሲቲ በኢየሩሳሌም የአርኪኦሎጂ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪዎች፣ ከ900 አንስቶ እስከ 800 ዓ.ዓ. መጀመሪያ አካባቢ (የእስራኤል ንጉሣዊ አገዛዝ በጀመረበት ወቅት) አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር የሚገመቱ የንብ ቀፎዎች የተቀመጡበትን ስፍራ በቴል ሬኮቭ በቁፋሮ አግኝተዋል። በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጥንታዊ የንብ ቀፎዎች ሲገኙ ይህ የመጀመሪያው ነው። የንብ ቀፎዎቹ በተገኙበት ቦታ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀፎዎች እንደነበሩና ቀፎዎቹ አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብረው በሦስት ደርብ በረድፍ የተቀመጡ እንደነበሩ ይገመታል።

ዩኒቨርሲቲው ይህን ግኝት አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ እንደተገለጸው እያንዳንዱ የንብ ቀፎ “ሞላላ ቅርጽ ያለውና ከሸክላ . . . የተሠራ ነው፤ ርዝመቱ 80 ሴንቲ ሜትር ሲሆን የቀፎው አፍ ስፋት 40 ሴንቲ ሜትር ነው። . . . ቦታውን የጎበኙ ተሞክሮ ያላቸው ንብ አርቢዎችና ተመራማሪዎች እንደገመቱት ከእነዚህ የንብ ቀፎዎች በየዓመቱ እስከ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማር ማግኘት ይቻል ነበር።”

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቴል ሬኮቭ የንብ ቀፎዎቹ የተገኙበት ቦታ

[የሥዕል ምንጭ]

Institute of Archaeology/Hebrew University © Tel Rehov Excavations