በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐዋርያዊ አባቶች—ጽሑፎቻቸው በእርግጥ ከሐዋርያት ትምህርት ጋር ይስማማሉ?

ሐዋርያዊ አባቶች—ጽሑፎቻቸው በእርግጥ ከሐዋርያት ትምህርት ጋር ይስማማሉ?

ሐዋርያዊ አባቶች—ጽሑፎቻቸው በእርግጥ ከሐዋርያት ትምህርት ጋር ይስማማሉ?

በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የሐሰት ትምህርት በንጹሕ ውኃ የተመሰለውን የክርስትናን እውነት ማደፍረስ ጀምሮ ነበር። በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ አስቀድሞ እንደተነገረው ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ አንዳንዶች እውነትን በመተው ወደ “ተረት” ዘወር ብለዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) በ98 ዓ.ም. አካባቢ በሕይወት የነበረው የመጨረሻው ሐዋርያ ዮሐንስ ሲሆን ይህ ሐዋርያ እንደዚህ ስላሉት የተሳሳቱ ትምህርቶችና ታማኝ ክርስቲያኖችን ‘ሊያሳስቱ ስለሚሞክሩ’ ሰዎች አስጠንቅቆ ነበር።—1 ዮሐንስ 2:26፤ 4:1, 6

ዮሐንስ ይህን ካለ ብዙም ሳይቆይ፣ ሐዋርያዊ አባቶች በመባል የሚታወቁት ግለሰቦች ወደ መድረክ ብቅ አሉ። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ ማታለያዎችን በተመለከተ አቋማቸው ምን ነበር? ሐዋርያው ዮሐንስ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመስማት እርምጃ ወስደው ነበር?

ሐዋርያዊ አባቶች እነማን ነበሩ?

“ሐዋርያዊ አባቶች” የሚለው መጠሪያ የሚያመለክተው ከኢየሱስ ሐዋርያት መካከል ከአንዱ ጋር ይተዋወቁ እንደነበረ ወይም ከሐዋርያት የተማሩ ደቀ መዛሙርት እንዳስተማሯቸው የሚገመቱ ሃይማኖታዊ ጸሐፊዎችን ነው። በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ሰዎች የኖሩት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ አንስቶ እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። * ከእነዚህ ጸሐፊዎች መካከል የሮሙ ክሌመንት፣ የአንጾኪያው ኢግኔሸስ፣ የሂራጶሊሱ ፔፒየስ እና የሰምርኔሱ ፖሊካርፕ ይገኙበታል። የክሌመንት ሁለተኛ ደብዳቤም የተጻፈው በዚሁ ጊዜ ነው፤ እንዲሁም ዘ ዲዳሂ፣ ኢፒስል ኦቭ ባርናባስ፣ ማርትርደም ኦቭ ፖሊካርፕ የሚባሉት መጻሕፍትም የተጻፉት በዚህ ወቅት ቢሆንም የጸሐፊዎቹ ስም አይታወቅም።

ሐዋርያዊ አባቶች ያስተማሯቸው ነገሮች ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር ምን ያህል እንደሚስማሙ መለየት በአሁኑ ወቅት አዳጋች ነው። የእነዚህ ግለሰቦች ዓላማ አንድን ዓይነት የክርስትና እምነት ጠብቆ ማቆየት ወይም ማስፋፋት እንደነበረ ግልጽ ነው። ጣዖት አምልኮንና የሥነ ምግባር ብልግናን አውግዘዋል። ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነና ትንሣኤ እንዳገኘ ያምኑ ነበር። ያም ሆኖ ልክ ኃይሉ እየጨመረ እንደሚመጣ የባሕር ሞገድ እየተስፋፋ የነበረውን የክህደት ትምህርት መግታት አልቻሉም። ከዚህ በተቃራኒ አንዳንዶቹ የራሳቸውን የተሳሳቱ ትምህርቶች በመጨመር ማዕበሉ ይበልጥ እንዲባባስ አድርገዋል።

ያደረጓቸው ለውጦች ከቁጥር የማይገቡ ናቸው?

በጥንት ዘመን የነበሩ ክርስቲያን ነን የሚሉ ግለሰቦች የሚያስተምሯቸው አንዳንድ ትምህርቶች ክርስቶስና ሐዋርያቱ ካስተማሯቸው ትምህርቶች የተለዩ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የጌታ እራት ተብሎ በሚጠራው በዓል ላይ ካደረገው በተቃራኒ ዘ ዲዳሂ የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊ፣ ከቂጣው በፊት ወይኑ እንዲዞር ሐሳብ አቅርቧል። (ማቴዎስ 26:26, 27) ይኸው ጸሐፊ፣ አንድን ሰው ውኃ ውስጥ አጥልቆ ለማጥመቅ የሚያስችል ጥልቀት ያለው ውኃ ካልተገኘ በተጠማቂው ራስ ላይ ውኃ ማፍሰስ በቂ እንደሆነ በጽሑፉ ላይ ገልጿል። (ማርቆስ 1:9, 10፤ የሐዋርያት ሥራ 8:36, 38) በዚሁ ጽሑፍ ላይ ክርስቲያኖች በሳምንት ሁለት ቀን እንደ መጾም እንዲሁም አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በቀን ሦስት ጊዜ እንደ መድገም ያሉትን ሥርዓቶች እንዲከተሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል።—ማቴዎስ 6:5-13፤ ሉቃስ 18:12

ኢግኔሸስ ደግሞ የክርስቲያን ጉባኤ አዲስ አደረጃጀት ሊኖረው እንደሚገባ ማለትም “በአምላክ ምትክ” ጉባኤውን የሚመራ አንድ ጳጳስ ሊሾም እንደሚገባ አስተምሮ ነበር። ይህ ጳጳስ በበርካታ ቀሳውስት ላይ ሥልጣን ይኖረዋል። እንዲህ ያሉት የፈጠራ ሐሳቦች ማዕበሉ ይበልጥ እየጨመረ እንዲሄድ ይኸውም ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ትምህርቶች ይበልጥ እንዲስፋፉ መንገድ ከፍተዋል።—ማቴዎስ 23:8, 9

የተጋነኑ ትምህርቶች፣ ሰማዕትነት እንዲሁም ጣዖት አምልኮ

አንዳንድ ሐዋርያዊ አባቶች የተጋንኑ ትምህርቶችን መቀበላቸው በሐሰት ትምህርት ማዕበል እየተገፉ ከእውነት ይበልጥ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። ፔፒየስ ለእውነት ጥማት የነበረው ከመሆኑም በላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያነብ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በትንቢት በተነገረው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የሚበቅሉት የወይን ተክሎች 10,000 ቅርንጫፎች እንደሚኖሯቸው፣ እያንዳንዱ ቅርንጫፍ 10,000 ሌሎች አነስተኛ ቅርንጫፎች እንደሚኖሩት፣ እነዚህ ቅርንጫፎች ደግሞ እያንዳንዳቸው 10,000 ቀንበጦች እንደሚኖሯቸው፣ እያንዳንዱ ቀንበጥ 10,000 ዘለላዎች እንደሚኖሩት፣ እያንዳንዱ ዘለላ ደግሞ 10,000 የወይን ፍሬ እንደሚያፈራ እንዲሁም እያንዳንዱ ፍሬ 1,000 ሊትር የወይን ጠጅ እንደሚያስገኝ ያምን ነበር።

ፖሊካርፕ የክርስትናን እምነት ከመካድ ይልቅ ሰማዕት ሆኖ ለመሞት መርጦ ነበር። ፖሊካርፕን ያስተማሩት ሐዋርያትና ኢየሱስን ያውቁ የነበሩ ሌሎች ሰዎች እንደሆኑ ይነገራል። ይህ ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሶ ያስተምር የነበረ ከመሆኑም ሌላ በክርስቲያናዊ መመሪያዎች መሠረት ለመኖር ጥረት ያደርግ የነበረ ይመስላል።

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ለፖሊካርፕ የነበራቸው ፍቅር ከጣዖት አምልኮ ያልተናነሰ አክብሮት እንዲሰጡት አድርጓቸዋል። ማርትርደም ኦቭ ፖሊካርፕ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ፖሊካርፕ ከሞተ በኋላ “ታማኞቹ” አጽሙን ወሰዱት። የፖሊካርፕን አጽም “ከከበሩ ድንጋዮች ይበልጥ ውድ እንዲሁም ከንጹሕ ወርቅ ይልቅ የጠራ” እንደሆነ አድርገው ተመልክተውት ነበር። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የክህደት ትምህርቶች በንጹሕ ውኃ የተመሰለውን እውነተኛውን የክርስትና ትምህርት መበከል ጀምረው ነበር።

አፖክሪፋ የሚባሉት መጻሕፍት

አንዳንድ ሐዋርያዊ አባቶች አፖክሪፋ የሚባሉትን (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማይካተቱ) መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት እንደተጻፉ አድርገው ተቀብለዋቸው ነበር። የሮሙ ክሌመንት፣ አፖክሪፋ ከሚባሉት መጻሕፍት መካከል መጽሐፈ ጥበብን እና መጽሐፈ ዮዲትን ጠቅሶ ጽፏል። ዚ ኢፒስል ኦቭ ፖሊካርፕ የተባለው መጽሐፍ ጸሐፊ ደግሞ አንድ ሰው ምጽዋት መስጠቱ መዳን እንደሚያስገኝለት የሚገልጸውን ትምህርት ለመደገፍ መጽሐፈ ጦቢትን እንደ ማስረጃ ጠቅሷል።

በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኢየሱስን ሕይወት በተመለከተ ከእውነታው የራቁ ዘገባዎችን የሚያስፋፉ ሐሰተኛ ወንጌሎች ነበሩ፤ ሐዋርያዊ አባቶች ደግሞ እነዚህን ዘገባዎች ትክክለኛ እንደሆኑ አድርገው ከመቀበላቸውም ሌላ በተደጋጋሚ ከእነዚህ መጻሕፍት ይጠቅሱ ነበር። ለምሳሌ ኢግኔሸስ፣ ጎስፔል ኦቭ ዘ ሂብሪውስ በመባል ከሚታወቀው ጽሑፍ ይጠቅስ ነበር። የሮሙን ክሌመንት በተመለከተም አንድ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “ክሌመንት ክርስቶስን ያወቀው በወንጌሎች [ላይ ባነበበው ነገር] ሳይሆን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ በሆኑ ጽሑፎች [ላይ ባነበበው ነገር] ይመስላል።”

የሐሰት ትምህርት ማዕበል

ሐዋርያዊ አባቶች የክርስትናን እምነት ለማብራራት አፈ ታሪኮችን፣ ሚስጥራዊ የሆኑ ሐሳቦችን እንዲሁም ፍልስፍናዎችን በመጠቀማቸው የሐሰት ትምህርት ልክ እንደ ማዕበል እውነተኛውን ክርስትና እንዲያጥለቀልቀው መንገድ ከፍተዋል። ለምሳሌ ክሌመንት የትንሣኤን ትምህርት ለመደገፍ፣ በአፈ ታሪክ የሚታወቀውን የፊኒክስን ታሪክ እንደ ማስረጃ አድርጎ ጠቅሷል። ፊኒክስ የተባለው ወፍ ራሱን ካቃጠለ በኋላ ከአመዱ ውስጥ እንደገና ሌላ ፊኒክስ እንደሚነሳ በአፈ ታሪክ ይነገራል፤ በግብጻውያን አፈ ታሪክ ውስጥ እንደሚነገረው ይህ ወፍ ከፀሐይ አምልኮ ጋር የተያያዘ ነው።

የቅዱሳን ጽሑፎችን እውነት ካቃለሉትና ካጣመሙት ሰዎች መካከል ኢፒስል ኦቭ ባርናባስ የተባለውን መጽሐፍ የጻፈው ሰውም ይገኛል። ይህ ሰው የሙሴ ሕግ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው ገልጿል። ንጹሕ እንደሆኑ የተገለጹት የሚያመሰኩ ወይም የሚያመነዥጉ እና ሰኰናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት የሚያመለክቱት በአምላክ ቃል ላይ የሚያሰላስሉ ወይም የአምላክን ቃል የሚያመነዥጉ ሰዎችን እንደሆነ ገልጿል። ይህ ጸሐፊ፣ የእንስሳው ሰኰና የተሰነጠቀ መሆኑ ጻድቅ ሰው በአንድ በኩል “በዚህ ዓለም” እየኖረ በሌላ በኩል ደግሞ በሰማይ የሚኖረውን ሕይወት እንደሚጠባበቅ የሚያመለክት መሆኑን አብራርቷል። እንደነዚህ ያሉት ማብራሪያዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም።—ዘሌዋውያን 11:1-3

ሐዋርያው ዮሐንስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ

ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋል።” (1 ዮሐንስ 4:1) ይህ ማስጠንቀቂያ ምንኛ ተስማሚ ነበር!

በአንደኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ክርስቲያን ነን የሚሉ በርካታ ሰዎች ኢየሱስና ሐዋርያቱ የሰጡትን ትምህርት መከተል አቁመው ነበር። ሐዋርያዊ አባቶችም እየጨመረ የመጣውን የክህደት ማዕበል ከመግታት ይልቅ ይበልጥ አባብሰውታል። እነዚህ ሰዎች እውነትን ከሐሰት ጋር በመደባለቅ ንጹሕ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በከሉት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንደዚህ ስላሉት ግለሰቦች ሲናገር “አልፎ የሚሄድና በክርስቶስ ትምህርት ጸንቶ የማይኖር ሁሉ አምላክ የለውም” ብሏል። (2 ዮሐንስ 9) ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነትን ለማግኘት ከልባቸው ለሚፈልጉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ መልዕክት የያዘው ማስጠንቀቂያ በዚያ ዘመንም ሆነ ዛሬ የሚያሻማ አይደለም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 አብዛኛውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተብለው የሚጠሩት ጸሐፊዎች፣ የሃይማኖት ምሑራንና ፈላስፎች የኖሩት ከሁለተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ክሌመንትን ጨምሮ አንዳንድ ሐዋርያዊ አባቶች በጽሑፎቻቸው ውስጥ አፈ ታሪኮችን፣ ሚስጥራዊ የሆኑ ሐሳቦችን እንዲሁም ፍልስፍናዎችን ጠቅሰዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፖሊካርፕ ሰማዕት ሆኖ ለመሞት መርጦ ነበር

[የሥዕል ምንጭ]

The Granger Collection, New York