በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በድፍረት በመስበክ ኢየሱስን ምሰሉ

በድፍረት በመስበክ ኢየሱስን ምሰሉ

በድፍረት በመስበክ ኢየሱስን ምሰሉ

‘የአምላክን ምሥራች ለእናንተ ለመናገር እንደምንም ብለን ድፍረት አገኘን።’—1 ተሰ. 2:2

1. ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ምሥራች በጣም አስደሳች ነው የምንለው ለምንድን ነው?

ምሥራች መስማት እንዴት ያስደስታል! ከሁሉ የላቀው ምሥራች ደግሞ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው መልእክት ነው። ይህ ምሥራች መከራ፣ ሕመም፣ ሥቃይ፣ ሐዘንና ሞት እንደሚቀሩ ያረጋግጥልናል። ምሥራቹ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን መንገድ የሚከፍትልን ከመሆኑም ሌላ ስለ አምላክ ዓላማ እንድናውቅ ይረዳናል፤ እንዲሁም ከእሱ ጋር በፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝምድና መመሥረት የሚቻልበትን መንገድ ያሳየናል። ኢየሱስ ለሰው ዘሮች የተናገረውን ይህን ምሥራች ሁሉም ሰው በደስታ እንደሚቀበለው ታስብ ይሆናል። የሚያሳዝነው ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነው።

2. ኢየሱስ ‘እኔ የመጣሁት ለመለያየት ነው’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

2 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በምድር ላይ ሰላም ለማስፈን የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ የመጣሁት ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አይደለም። እኔ የመጣሁት ወንድ ልጅን ከአባቱ፣ ሴት ልጅን ከእናቷ እንዲሁም ሙሽሪትን ከአማቷ ለመለያየት ነው። በእርግጥም የሰው ጠላቶቹ የገዛ ቤተሰቦቹ ይሆናሉ።” (ማቴ. 10:34-36) በርካታ ሰዎች ምሥራቹን በደስታ ከመቀበል ይልቅ ሲቃወሙት ይታያሉ። አንዳንዶች የቅርብ የቤተሰባቸው አባላትንም እንኳ ምሥራቹን በማወጃቸው ይጠሏቸዋል።

3. የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ምን ያስፈልገናል?

3 በዛሬው ጊዜ የምናውጀው ኢየሱስ የሰበከውን እውነት ሲሆን ሰዎች ምሥራቹን ሲሰሙ የሚሰጡት ምላሽም በዚያን ጊዜ ብዙዎች ለኢየሱስ ከሰጡት ምላሽ ጋር ይመሳሰላል። ይህም የሚጠበቅ ነገር ነው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኳችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል።” (ዮሐ. 15:20) በብዙ አገሮች ቀጥተኛ ስደት ባያጋጥመንም ሰዎች ለመልእክታችን ንቀት የሚያሳዩ ከመሆኑም ሌላ ግዴለሾች ናቸው። በመሆኑም ምሥራቹን ያለ ፍርሃት በመስበክ ለመጽናት እንድንችል እምነትና ድፍረት ያስፈልገናል።—2 ጴጥሮስ 1:5-8ን አንብብ።

4. ጳውሎስ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ‘እንደምንም ብሎ ድፍረት ማግኘት’ ያስፈለገው ለምን ነበር?

4 አንዳንድ ጊዜ በስብከቱ ሥራ መካፈል ይከብድህ ይሆናል፤ ወይም በአንድ ዓይነት የአገልግሎቱ ዘርፍ መካፈል ሊያስፈራህ ይችላል። ሌሎች ታማኝ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም እንዲህ ይሰማቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እውነትን በሚገባ የተረዳ ደፋር ሰባኪ ነበር፤ ያም ሆኖ እሱም ለመስበክ አልፎ አልፎ ትግል ማድረግ አስፈልጎታል። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል፦ “በመጀመሪያ (እናንተም እንደምታውቁት) በፊልጵስዩስ መከራ ከተቀበልንና እንግልት ከደረሰብን በኋላ የአምላክን ምሥራች በከፍተኛ ትግል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን እርዳታ እንደምንም ብለን እንዴት ድፍረት እንዳገኘን ታውቃላችሁ።” (1 ተሰ. 2:2) ጳውሎስና ጓደኛው ሲላስ በፊልጵስዩስ በነበሩበት ወቅት ባለሥልጣናቱ በበትር ከደበደቧቸው በኋላ እስር ቤት አስገቧቸው፤ ከዚያም እግራቸውን በእግር ግንድ አጥብቀው አሰሯቸው። (ሥራ 16:16-24) ያም ቢሆን ጳውሎስና ሲላስ በስብከቱ ሥራቸው ለመቀጠል ‘እንደምንም ብለው ድፍረት አግኝተዋል።’ እኛስ በድፍረት መስበክ የምንችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት፣ በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ስለ ይሖዋ እውነቱን በድፍረት ለመናገር የረዳቸው ምን እንደሆነ እንመልከት፤ እንዲሁም የእነሱን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደምንችል እንመርምር።

ጠላትነትን ለመቋቋም ድፍረት አስፈልጓቸዋል

5. የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ምንጊዜም ቢሆን ድፍረት ማሳየት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

5 ደፋር በመሆንና ያለ ፍርሃት በመስበክ ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ሁሉም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ድፍረት ማሳየት አስፈልጓቸዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በኤደን ከተነሳው ዓመጽ በኋላ ይሖዋ እሱን በሚያገለግሉትና ሰይጣንን በሚያገለግሉት መካከል ጠላትነት እንደሚኖር ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ዘፍ. 3:15) ብዙም ሳይቆይ ቃየን፣ ጻድቅ ሰው የነበረውን ወንድሙን አቤልን ሲገድለው ይህ ጠላትነት በግልጽ ታይቷል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይህ ጠላትነት ከጥፋት ውኃ በፊት በኖረው ሔኖክ በተባለ ታማኝ ሰው ላይ አነጣጠረ። አምላክ፣ ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክቱ ጋር ፈሪሃ አምላክ በሌላቸው ሰዎች ላይ ለመፍረድ እንደሚመጣ ሔኖክ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ይሁዳ 14, 15) አብዛኞቹ ሰዎች በዚህ መልእክት እንዳልተደሰቱ ምንም ጥያቄ የለውም። ሰዎቹ ሔኖክን የጠሉት ሲሆን ይሖዋ ባይወስደው ኖሮ ይገድሉት እንደነበረ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ሔኖክ እንዴት ያለ ታላቅ ድፍረት ነበረው!—ዘፍ. 5:21-24

6. ሙሴ፣ ፈርዖንን ለማነጋገር ድፍረት አስፈልጎት የነበረው ለምንድን ነው?

6 ሙሴ፣ ፈርዖንን ባነጋገረበት ወቅት ያሳየውን ድፍረትም እንመልከት፤ ራ የተባለው የፀሐይ አምላክ ልጅ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ የነበረው ፈርዖን የአማልክት ወኪል ሳይሆን እሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ ይታሰብ ነበር። እንደ ሌሎች ፈርዖኖች ሁሉ ይህ ንጉሥም የራሱን ምስል ሳያመልክ አልቀረም። ፈርዖን፣ እሱ የተናገረው ነገር ሁሉ እንዲፈጸም የሚጠብቅ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ነበር። ኃያል፣ እብሪተኛና ግትር የነበረው ፈርዖን የሚያደርገውን ነገር ሌሎች እንዲነግሩት አይፈልግም ነበር። በእረኝነት ሥራ የተሰማራውና ትሑት ሰው የነበረው ሙሴ ሳይጋበዝ እንዲሁም ፈርዖን ሊያየው እንደማይፈልግ እያወቀ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይህን ንጉሥ ማነጋገር ነበረበት። ሙሴ የሚናገረው መልእክት ምን ነበር? በግብጽ ላይ አውዳሚ መቅሰፍቶች እንደሚመጡ መናገር ነበረበት። ንጉሡን የጠየቀውስ ምን ነበር? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የፈርዖን ባሪያዎች አገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ፈቃድ እንዲሰጣቸው ፈልጎ ነበር! ታዲያ ሙሴ ይህን መልእክት ለመናገር ደፋር መሆን አስፈልጎት ነበር? ምንም ጥርጥር የለውም!—ዘኍ. 12:3፤ ዕብ. 11:27

7, 8. (ሀ) በጥንት ዘመን የኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምን ዓይነት ችግሮች አጋጥመዋቸዋል? (ለ) ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት የኖሩት የአምላክ አገልጋዮች ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍና ለማስፋፋት የሚያስችላቸውን ድፍረት ያገኙት ከየት ነበር?

7 ከዚያ በኋላ ባሉት ዘመናት ሁሉ ነቢያትና ሌሎች የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በመቆም ድፍረት የተሞላበት አቋም ወስደዋል። የሰይጣን ዓለምም ብዙ መከራ አድርሶባቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “በድንጋይ ተወግረዋል፣ ተፈትነዋል፣ በመጋዝ ተሰንጥቀዋል፣ በሰይፍ ተቀልተው ሞተዋል፤ እየተቸገሩ፣ መከራ እየተቀበሉና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ተንከራተዋል።” (ዕብ. 11:37) እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንዲጸኑ የረዳቸው ምንድን ነው? ሐዋርያው ከላይ ያለውን ከመጻፉ ቀደም ብሎ ባሉት ቁጥሮች ላይ አቤል፣ አብርሃም፣ ሣራ እንዲሁም ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ለመጽናት የሚያስችላቸውን ብርታት የሰጣቸው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ሁሉ የተስፋውን ቃል ፍጻሜ ባያገኙም . . . [በእምነት] ከሩቅ አይተው በደስታ ተቀበሉት።” (ዕብ. 11:13) በተመሳሳይም፣ ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት የኖሩትና ከእውነተኛው አምልኮ ጎን በድፍረት የቆሙት እንደ ኤልያስና ኤርምያስ ያሉ ነቢያት እንዲሁም ሌሎች ታማኝ አገልጋዮች እንዲጸኑ የረዳቸው ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ቲቶ 1:2

8 ከክርስትና በፊት በነበሩት ዘመናት የኖሩት እነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ወደፊት ብሩህና አስደሳች ሕይወት እንደሚያገኙ ይጠብቁ ነበር። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ትንሣኤ ካገኙ በኋላ፣ ክርስቶስ ኢየሱስና 144,000ዎቹ በሚያከናውኑት የክህነት አገልግሎት አማካኝነት ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና የሚደርሱ ከመሆኑም ሌላ “ከመበስበስ ባርነት ነፃ [ይወጣሉ]።” (ሮም 8:21) ከዚህም በተጨማሪ ኤርምያስና በጥንት ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ደፋር የአምላክ አገልጋዮች ያለ ፍርሃት እንዲያገለግሉ የረዳቸው ይሖዋ የሰጣቸው ማረጋገጫ ነበር፤ ይሖዋ ለኤርምያስ እንዲህ በማለት ቃል ገብቶለት ነበር፦ “ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም።” (ኤር. 1:19) ዛሬም በተመሳሳይ፣ አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሰጠን ተስፋ እንዲሁም መንፈሳዊ ጥበቃ እንደሚያደርግልን በገባው ቃል ላይ ስናሰላስል ብርታት እናገኛለን።—ምሳሌ 2:7፤ 2 ቆሮንቶስ 4:17, 18ን አንብብ።

ፍቅር ኢየሱስ በድፍረት እንዲሰብክ አነሳስቶታል

9, 10. ኢየሱስ (ሀ) በሃይማኖት መሪዎቹ፣ (ለ) በወታደሮቹ፣ (ሐ) በሊቀ ካህናቱ፣ (መ) በጲላጦስ ፊት ድፍረት ያሳየው በምን መንገድ ነው?

9 ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ደፋር መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አሳይቷል። ለአብነት ያህል፣ በወቅቱ ሥልጣንና ተደማጭነት የነበራቸው ሰዎች ይጠሉት የነበረ ቢሆንም አምላክ ለሰዎች እንዲናገር የላከውን መልእክት አለሳልሶ ለማቅረብ አልሞከረም። ኃይለኛ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ ራሳቸውን እንደሚያመጻድቁ እንዲሁም የሐሰት ትምህርት እንደሚያስተምሩ በድፍረት አጋልጧል። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ግልጽ በሆነ መንገድ ፊት ለፊት አውግዟቸዋል። በአንድ ወቅት እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ከውጭ አምረው የሚታዩ ከውስጥ ግን በሙታን አፅምና በብዙ ዓይነት ርኩሰት የተሞሉ፣ ኖራ የተቀቡ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ወዮላችሁ! እናንተም ከውጭ ስትታዩ ጻድቅ ትመስላላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በግብዝነትና በዓመፅ የተሞላ ነው።”—ማቴ. 23:27, 28

10 በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ አንድ የወታደሮች ቡድን ኢየሱስን ሊይዝ በመጣበት ወቅት ኢየሱስ በድፍረት ራሱን አሳውቋል። (ዮሐ. 18:3-8) ከዚያም በሳንሄድሪን ፊት ሊቀ ካህናቱ ጥያቄዎች ያቀርብለት ጀመር። ኢየሱስ፣ ሊቀ ካህናቱ እሱን ለመግደል ሰበብ እየፈለገ እንደነበረ ቢያውቅም ክርስቶስና የአምላክ ልጅ መሆኑን በድፍረት ተናግሯል። አክሎም “በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ” እንደሚያዩት ገለጸላቸው። (ማር. 14:53, 57-65) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስን አስረው በጲላጦስ ፊት አቀረቡት። ጲላጦስ ሊፈታው ይችል የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ የተሰነዘሩበትን ክሶች ለማስተባበል አልሞከረም። (ማር. 15:1-5) ይህ ሁሉ ከፍተኛ ድፍረት ይጠይቅ ነበር።

11. ድፍረት ማሳየት ከፍቅር ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?

11 እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ለጲላጦስ እንዲህ ብሎታል፦ “እኔ የተወለድኩትና ወደ ዓለም የመጣሁት ስለ እውነት እንድመሠክር ነው።” (ዮሐ. 18:37) ይሖዋ ለኢየሱስ ምሥራቹን የመስበክ ተልእኮ የሰጠው ሲሆን ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን ስለሚወደው ይህንን ማድረግ ያስደስተዋል። (ሉቃስ 4:18, 19) ኢየሱስ ለሰዎችም ፍቅር ነበረው። በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ያውቅ ነበር። በተመሳሳይ እኛም በድፍረትና ያለ ፍርሃት የምንመሠክረው ለአምላክና ለሰዎች ጥልቅ ፍቅር ስላለን ነው።—ማቴ. 22:36-40

መንፈስ ቅዱስ በድፍረት እንድንሰብክ ኃይል ይሰጠናል

12. የጥንቶቹን ደቀ መዛሙርት እንዲደሰቱ ያደረጋቸው የትኛው ክንውን ነበር?

12 ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በነበሩት ሳምንታት ይሖዋ አዳዲስ ክርስቲያኖች እንዲጨመሩ ስላደረገ ደቀ መዛሙርቱ ተደስተው ነበር። የጴንጤቆስጤን በዓል ለማክበር ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት አይሁዳውያንና ወደ አይሁድ እምነት የተቀየሩ ሰዎች መካከል በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 3,000 ያህል ተጠመቁ! ይህ ሁኔታ በመላው ኢየሩሳሌም የመወያያ ርዕስ ሆኖ እንደነበር መገመት አያዳግትም! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በእያንዳንዱም ነፍስ ላይ ፍርሃት ወደቀ፤ ሐዋርያቱም ብዙ ድንቅ ነገሮችና ተአምራዊ ምልክቶች ያደርጉ ጀመር።”—ሥራ 2:41, 43

13. ወንድሞች ድፍረት ለማግኘት የጸለዩት ለምን ነበር? ምን ውጤትስ አገኙ?

13 የሃይማኖት መሪዎቹ በዚህ ሁኔታ በጣም ስለ ተቆጡ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ይዘው ወኅኒ ቤት አሳደሯቸው፤ ከዚያም ስለ ኢየሱስ እንዳይናገሩ አስጠነቀቋቸው። እነዚህ ሐዋርያት ከእስር ሲፈቱ የደረሰባቸውን ነገር ለወንድሞች ከነገሯቸው በኋላ ያጋጠማቸውን ተቃውሞ በተመለከተ ሁሉም እንዲህ በማለት ጸለዩ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ . . . ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።”—ሥራ 4:24-31

14. መንፈስ ቅዱስ በአገልግሎታችን የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ቃል በድፍረት እንዲናገሩ የረዳቸው ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ ልብ በል። ለሰዎች ሌላው ቀርቶ መልእክታችንን ለሚቃወሙትም እንኳ እውነትን ለመናገር የሚያስችለንን ድፍረት የሚሰጠን ይሖዋ እንጂ በራሳችን የምናገኘው ነገር አይደለም። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን ከጠየቅነው ሊሰጠን ይችላል፤ ደግሞም ይሰጠናል። እኛም የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ዓይነት ተቃውሞ በይሖዋ እርዳታ በድፍረት መቋቋም እንችላለን።—መዝሙር 138:3ን አንብብ።

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በድፍረት ይሰብካሉ

15. በዘመናችን እውነት በሰዎች መካከል መለያየት እንዲኖር የሚያደርገው እንዴት ነው?

15 በጥንት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም እውነት በሰዎች መካከል መለያየት እንዲኖር ያደርጋል። አንዳንዶች ምሥራቹን የሚቀበሉ ሲሆን ሌሎች ግን እውነትን ለመረዳት ፍላጎት የላቸውም፤ አምልኳችንንም አያከብሩልንም። ሌሎች ደግሞ ይነቅፉናል፣ ያፌዙብናል ወይም ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ይጠሉናል። (ማቴ. 10:22) አንዳንድ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን ስለ እኛ የተሳሳተ መረጃ ያቀርባሉ፤ እንዲሁም በተንኮል የተሸረበ ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ። (መዝ. 109:1-3) ያም ቢሆን የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ ምሥራቹን በድፍረት ያውጃሉ።

16. ድፍረት የምንሰብክላቸውን ሰዎች አመለካከት ሊለውጠው እንደሚችል የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

16 ድፍረት፣ የምንሰብክላቸው ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ያላቸውን አመለካከት እንዲለወጡ ሊያደርጋቸው ይችላል። በኪርጊስታን የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “በስብከቱ ሥራ ላይ እያለሁ አንድ ሰው እንዲህ አለኝ፦ ‘በአምላክ የማምን ቢሆንም በክርስቲያኖች አምላክ ግን አላምንም። ሁለተኛ ቤቴ ድርሽ ብትይ ውሻዬን ነው የምለቅብሽ!’ ከሰውየው በስተጀርባ በሠንሠለት የታሰረ ትልቅ ውሻ ነበር። ይሁንና ‘የሐሰት ሃይማኖት የሚጠፋበት ጊዜ ቀርቧል!’ የሚል ርዕስ ያለው የመንግሥት ዜና ቁጥር 37 በሚሰራጭበት ወቅት ሌሎች የቤተሰቡን አባላት ላገኝ እንደምችል ስላሰብኩ ወደዚህ ሰው ቤት ተመልሼ ለመሄድ ወሰንኩ። ይሁን እንጂ በሩን የከፈተው ሰውዬው ራሱ ነበር። ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ እንዲህ አልኩት፦ ‘ጤና ይስጥልኝ፣ ከሦስት ቀናት በፊት የተነጋገርነውን አስታውሳለሁ፤ ውሻህንም አልረሳሁትም። ሆኖም ልክ እንደ አንተ እኔም አንድ እውነተኛ አምላክ እንዳለ ስለማምን ይህን ትራክት ልሰጥህ አሰብኩ። አምላክ በቅርቡ እሱን የማያስከብሩ ሃይማኖቶችን ይቀጣቸዋል። ይህንን ትራክት በማንበብ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ ትችላለህ።’ የሚገርመው ይህ ሰው ትራክቱን ተቀበለኝ። እኔም አገልግሎቴን ቀጠልኩ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሰውየው የመንግሥት ዜናውን ይዞ እየሮጠ ወደ እኔ በመምጣት ‘ትራክቱን አንብቤዋለሁ፤ በአምላክ ቁጣ እንዳልጠፋ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ በማለት ጠየቀኝ።” ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ዝግጅት የተደረገለት ሲሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ጀምሯል።

17. አንዲት እህት ያሳየችው ድፍረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ ፍርሃቷን እንድታሸንፍ የረዳት እንዴት ነው?

17 በተጨማሪም፣ ድፍረት ማሳየታችን ሌሎችም ደፋሮች እንዲሆኑ ሊያበረታታቸው ይችላል። በሩሲያ የምትኖር አንዲት እህት በአውቶቡስ እየተጓዘች ሳለ አጠገቧ ለነበረች ሴት መጽሔት አሳየቻት። በዚህ ወቅት አንድ ሰው ከተቀመጠበት ዘሎ በመነሳት መጽሔቱን ከእህት ከቀማት በኋላ ጨምድዶ መሬት ላይ ጣለው። ሰውየው ድምፁን ከፍ አድርጎ እህትን በመሳደብ አድራሻዋን እንድትነግረው ጠየቃት፤ እንዲሁም በመንደሩ ውስጥ እንዳትሰብክ አስጠነቀቃት። እህት ይሖዋ እንዲረዳት ከጸለየች በኋላ “ሥጋን የሚገድሉትን . . . አትፍሩ” የሚለውን የኢየሱስን ምክር አስታወሰች። (ማቴ. 10:28) ከዚያም ከመቀመጫዋ በመነሳት “አድራሻዬን አልነግርህም፤ በመንደሩ ውስጥ መስበኬንም አላቆምም” በማለት በእርጋታ ከመለሰችለት በኋላ ከአውቶቡሱ ወረደች። ይህች እህት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ በአውቶቡሱ ውስጥ እንደነበረች አላወቀችም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ ሰዎችን ስለምትፈራ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አትገኝም ነበር። ይሁንና ሴትየዋ፣ እህታችን ያሳየችውን ድፍረት ከተመለከተች በኋላ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወሰነች።

18. እንደ ኢየሱስ በድፍረት ለመስበክ ምን ሊረዳህ ይችላል?

18 ከአምላክ በራቀው በዚህ ዓለም ውስጥ ምሥራቹን ለመስበክ እንደ ኢየሱስ ድፍረት ማሳየት ያስፈልጋል። እንዲህ ያለ ድፍረት ለማዳበር ምን ሊረዳህ ይችላል? ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስብ። ለአምላክና ለሰዎች ያለህ ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ጥረት አድርግ። ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጥህ ጸልይ። ኢየሱስ ከአንተ ጋር በመሆኑ፣ ምንጊዜም ብቻህን እንዳልሆንክ አስታውስ። (ማቴ. 28:20) መንፈስ ቅዱስ ብርታት ይሰጥሃል። ይሖዋም ጥረትህን ይባርከዋል እንዲሁም ይደግፍሃል። እንግዲያው “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” በማለት በሙሉ ልብ መናገር እንችላለን።—ዕብ. 13:6

መልስህ ምንድን ነው?

• የአምላክ አገልጋዮች ደፋር መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

• ድፍረትን በማሳየት ረገድ . . .

ከጥንት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣

ከኢየሱስ ክርስቶስ፣

ከቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች፣

በዛሬ ጊዜ ካሉት የእምነት ባልንጀሮቻችን

ምን ትምህርት እናገኛለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ፣ የሃይማኖት መሪዎቹን ያለ ፍርሃት አጋልጧቸዋል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ለመስበክ የሚያስችለንን ድፍረት ይሰጠናል