በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክርስቲያን ቤተሰቦች የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ!

ክርስቲያን ቤተሰቦች የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ!

ክርስቲያን ቤተሰቦች የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ!

‘ክርስቶስ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችኋል።’—1 ጴጥ. 2:21

1. (ሀ) የአምላክ ልጅ በፍጥረት ሥራ ላይ ምን ሚና ተጫውቷል? (ለ) ኢየሱስ ለሰው ዘር ምን ዓይነት ስሜት አለው?

አምላክ ሰማይና ምድርን ሲፈጥር የበኩር ልጁ ከጎኑ በመሆን “ዋና ባለሙያ” ሆኖ ይሠራ ነበር። ይሖዋ በምድር ላይ ያሉትን የተለያየ ዝርያ ያላቸው እንስሳትና ተክሎች ንድፍ ሲያወጣና ሲፈጥር እንዲሁም በይሖዋ መልክና አምሳል ለተሠሩት ፍጥረታት መኖሪያ የምትሆን ገነት ሲያዘጋጅ የአምላክ ልጅ ከአባቱ ጋር ተባብሯል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ተብሎ የተጠራው የአምላክ ልጅ ለሰው ዘር ጥልቅ ፍቅር ነበረው። “በሰው ልጆች ደስ [ይሰኝ] ነበር።”—ምሳሌ 8:27-31፤ ዘፍ. 1:26, 27

2. (ሀ) ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ለመርዳት ምን ዝግጅት አድርጓል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ከሚሰጥባቸው የሕይወት ዘርፎች አንዱ የትኛው ነው?

2 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆነውን የሰው ዘር ለማዳን የሚያስችለውን ዝግጅት በዓላማው ውስጥ አካተተው። ይሖዋ የሰው ዘርን ከኃጢአት ለመዋጀት የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አዘጋጀ። (ሮም 5:8) ከዚህም በተጨማሪ የሰው ዘር የወረሰው አለፍጽምና ቢኖርበትም እንኳ ሕይወቱን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችለውን መመሪያ እንዲያገኝ ይሖዋ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶታል። (መዝ. 119:105) ሰዎች የቤተሰባቸው ሕይወት ጠንካራና አስደሳች ሆኖ እንዲቀጥል የሚረዳቸውን መመሪያ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ አስፍሯል። የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ጋብቻ ሲናገር ሰው ‘ከሚስቱ ጋር መጣመር እንዳለበትና ሁለቱም አንድ ሥጋ መሆን እንዳለባቸው’ ይገልጻል።—ዘፍ. 2:24

3. (ሀ) ኢየሱስ ጋብቻን አስመልክቶ ምን ትምህርት ሰጥቷል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹ ነጥቦች ይብራራሉ?

3 ኢየሱስ፣ ጋብቻ ከመጀመሪያውም ቢሆን ዘላቂ ጥምረት እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመ ዝግጅት እንደሆነ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ጎላ አድርጎ የገለጸ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯል። ቤተሰቦች እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋቸው ትዳራቸውን የሚያናጉ ወይም የቤተሰባቸውን ደስታ የሚያደፈርሱ አመለካከቶችንና ድርጊቶችን ለማስወገድ ይረዳቸዋል። (ማቴ. 5:27-37፤ 7:12) ባሎች፣ ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች ኢየሱስ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና በምድር ሳለ የተወውን ምሳሌ መከተላቸው ደስተኛና አርኪ ሕይወት ለመምራት የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።

ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአክብሮት እንደሚይዛት የሚያሳየው እንዴት ነው?

4. ኢየሱስና ክርስቲያን ባሎች ያላቸው ቦታ የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ የጉባኤ ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የቤተሰብ ራስ እንዲሆን አምላክ ሾሞታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ክርስቶስ አካሉ ለሆነውና አዳኙ ለሆነለት ጉባኤ ራስ እንደሆነ ሁሉ ባልም የሚስቱ ራስ ነው። ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:23, 25) በእርግጥም፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን የያዘበት መንገድ ክርስቲያን ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው እንደሚገባ አርዓያ የሚሆን ነው። ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ሥልጣን እንዴት እንደተጠቀመበት የሚያሳዩ አንዳንድ ሁኔታዎችን እስቲ እንመልከት።

5. ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተያያዘ ሥልጣኑን የተጠቀመበት እንዴት ነበር?

5 ኢየሱስ ‘ገርና በልቡ ትሑት ነበር።’ (ማቴ. 11:29) ኢየሱስ የተግባር ሰውም ነበር። ኃላፊነቱን ፈጽሞ ችላ ብሎ አያውቅም። (ማር. 6:34፤ ዮሐ. 2:14-17) ደቀ መዛሙርቱ ተደጋጋሚ ስሕተት ቢሠሩም እንኳ በደግነት ምክር ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 20:21-28፤ ማር. 9:33-37፤ ሉቃስ 22:24-27) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በቁጣ ወይም ክብራቸውን ዝቅ በሚያደርግ መንገድ ተናግሯቸው አያውቅም፤ እንዲሁም የማይወደዱ እንደሆኑ ወይም እሱ ያስተማራቸውን ነገሮች ለመፈጸም ብቃቱ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አላደረገም። ከዚህ በተለየ መልኩ ደቀ መዛሙርቱን አመስግኗቸዋል እንዲሁም አበረታቷቸዋል። (ሉቃስ 10:17-21) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በፍቅርና በርኅራኄ ይይዛቸው ስለነበር የእነሱን አክብሮት ማትረፉ ምንም አያስገርምም!

6. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከያዘበት መንገድ አንድ ባል ምን ትምህርት ሊያገኝ ይችላል? (ለ) ጴጥሮስ ለባሎች ምን ማበረታቻ ሰጥቷቸዋል?

6 ባሎች ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ ክርስቲያናዊ የራስነት ሥልጣናቸውን ሚስቶቻቸውን ለመጨቆን አይጠቀሙበትም። ከዚህ ይልቅ በአክብሮት ይይዟቸዋል፤ እንዲሁም የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለእነሱ ፍቅር እንዳላቸው ያሳዩአቸዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ባሎች ፍቅር በማንጸባረቅ ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል እነሱም ‘ልክ እንደዚሁ’ ለሚስቶቻቸው ‘ክብር በመስጠት ከእነሱ ጋር እንዲኖሩ’ አበረታቷል። (1 ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ።) ታዲያ ባሎች አምላክ የሰጣቸውን ሥልጣን እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል? ከዚህ ጎን ለጎን ሚስቶቻቸውን በአክብሮት እንደሚይዟቸው ማሳየት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

7. አንድ ባል ሚስቱን እንደሚያከብር በምን መንገድ ማሳየት ይችላል? አብራራ።

7 ባሎች ሚስቶቻቸውን በአክብሮት እንደሚይዟቸው የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ቤተሰባቸውን የሚመለከት ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት የሚስቶቻቸውን አመለካከትና ስሜት ከግምት በማስገባት ነው። ለምሳሌ የመኖሪያ አካባቢን ወይም ሥራን መቀየርን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ ለእረፍት የሚሄዱበትን ቦታ መምረጥን ወይም የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም በቤተሰቡ በጀት ላይ ማስተካከያ ማድረግን የመሳሰሉ ከዕለታዊ ሕይወት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል። እነዚህ ነገሮች ቤተሰቡን የሚመለከቱ በመሆኑ አንድ ባል ሚዛኑን የጠበቀ ብሎም ይበልጥ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ላይ መድረስ እንዲችልና ሚስቱም ደስ ብሏት ውሳኔውን መደገፍ እንድትችል የእሷን ሐሳብ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። እንዲህ ማድረጉ ለቤተሰቡ ጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ ደግነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው። (ምሳሌ 15:22) ሚስቶቻቸውን የሚያከብሩ ክርስቲያን ባሎች የሚስቶቻቸውን ፍቅርና አክብሮት ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ ያገኛሉ።—ኤፌ. 5:28, 29

አንዲት ሚስት ለባሏ ጥልቅ አክብሮት እንዳላት የምታሳየው እንዴት ነው?

8. ሚስቶች የሔዋንን ምሳሌ መከተል የሌለባቸው ለምንድን ነው?

8 ለሥልጣን በመገዛት ረገድ ኢየሱስ ለክርስቲያን ሚስቶች ፍጹም አርዓያ ትቶላቸዋል። ኢየሱስ ለሥልጣን የነበረው አመለካከት የመጀመሪያዋ ሚስት ከነበራት አመለካከት ምንኛ የተለየ ነው! ሔዋን ለሚስቶች ጥሩ ምሳሌ አይደለችም። ይሖዋ አዳምን በእሷ ላይ ራስ አድርጎ የሾመው ከመሆኑም ሌላ ሔዋን መመሪያ የምታገኘው በእሱ በኩል ነበር። ይሁን እንጂ ሔዋን ለዚህ ዝግጅት አክብሮት አላሳየችም። አዳም የነገራትን የይሖዋን መመሪያ ሳትታዘዝ ቀረች። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:3፤ 1 ቆሮ. 11:3) በእርግጥ ሔዋን ይህን ያደረገችው ተታልላ ነበር፤ ያም ቢሆን ‘አምላክ የሚያውቀውን’ ነገር እየገለጸላት እንዳለ አድርጎ ያናገራትን አካል ከመታዘዟ በፊት ምን ማድረግ እንደሚኖርባት አዳምን ማማከር ነበረባት። ሔዋን ግን ያለ ቦታዋ በመግባት ባሏን እሷ በፈለገችው አቅጣጫ መራችው።—ዘፍ. 3:5, 6፤ 1 ጢሞ. 2:14

9. ለሥልጣን በመገዛት ረገድ ኢየሱስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

9 ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ፣ ራሱ ለሆነው ለይሖዋ በመገዛት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ኢየሱስ ከነበረው አመለካከትና ከአኗኗሩ ማየት እንደሚቻለው “ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን ነጥቆ ሊወስደው እንደሚገባ ነገር አድርጎ አላሰበም።” ይልቁንም ‘ራሱን ባዶ በማድረግ እንደ ባሪያ ሆኖ’ መጥቷል። (ፊልጵ. 2:5-7) ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ ቢሆንም ይህ አመለካከቱ ዛሬም አልተቀየረም። በማንኛውም ነገር ለአባቱ በትሕትና የሚገዛ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ራስነት ያከብራል።—ማቴ. 20:23፤ ዮሐ. 5:30፤ 1 ቆሮ. 15:28

10. አንዲት ሚስት የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደምታከብር እንዴት ልታሳይ ትችላለች?

10 አንዲት ክርስቲያን ሚስት የባሏን የራስነት ሥልጣን በማክበር የኢየሱስን ምሳሌ ልትከተል ይገባል። (1 ጴጥሮስ 2:21፤ 3:1, 2ን አንብብ።) የራስነት ሥልጣንን እንደምታከብር ማሳየት ከምትችልባቸው ሁኔታዎች አንዱን እንመልከት። አንድ ልጅ፣ የወላጆቹን ፈቃድ ማግኘት የሚያስፈልገውን አንድ ነገር ለማድረግ እናቱን ፈቃድ ጠየቀ እንበል። ወላጆቹ ጉዳዩን ከዚያ ቀደም ስላልተወያዩበት እናትየው “አባትህን ጠይቀኸው ነበር?” ማለቷ ተገቢ ነው። ልጁ ይህን ካላደረገ ውሳኔ ከማድረጓ በፊት ከባሏ ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየት ይኖርባታል። ከዚህም በተጨማሪ አንዲት ክርስቲያን ሚስት በልጆቻቸው ፊት የባሏን ሐሳብ መቃወም ወይም ከእሱ ጋር ሙግት መግጠም የለባትም። ከባሏ ጋር በአንድ ጉዳይ ካልተስማማች ብቻቸውን ሲሆኑ ጉዳዩን አንስታ ልታነጋግረው ትችላለች።—ኤፌ. 6:4

ኢየሱስ ለወላጆች የተወው ምሳሌ

11. ኢየሱስ ለወላጆች ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል?

11 ኢየሱስ ትዳር መሥርቶ ልጆች ባይወልድም ለክርስቲያን ወላጆች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። እንዴት? ኢየሱስ አፍቃሪና ታጋሽ በመሆን ደቀ መዛሙርቱን በቃልም ሆነ በድርጊት አስተምሯቸዋል። የሰጣቸውን ተልእኮ እንዴት እንደሚወጡ አሳይቷቸዋል። (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድና ለእነሱ የነበረው አመለካከት እነሱም አንዳቸው ሌላውን እንዴት ሊይዙ እንደሚገባ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።—ዮሐንስ 13:14-17ን አንብብ።

12, 13. ወላጆች፣ ልጆቻቸው ፈሪሃ አምላክ እንዲያድርባቸው ከፈለጉ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

12 ልጆች፣ የወላጆቻቸው ምሳሌ ጥሩም ይሁን መጥፎ እነሱን የመከተል ዝንባሌ አላቸው። በመሆኑም ወላጆች እንደሚከተለው በማለት ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ቴሌቪዥን በማየትና በመዝናኛ የምናጠፋው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት እንዲሁም በአገልግሎት በመካፈል ከምናሳልፈው ጊዜ ጋር ሲወዳደር ለልጆቻችን ምን ዓይነት ምሳሌ እየሆንን ነው? ቤተሰባችን ቅድሚያ የሚሰጠው ለየትኞቹ ነገሮች ነው? በሕይወታችን ውስጥ ለእውነተኛው አምልኮ ቅድሚያ በመስጠት ለልጆቻችን ጥሩ ምሳሌ እየተውን ነው?’ ወላጆች ልጆቻቸው ፈሪሃ አምላክ እንዲያድርባቸው ከፈለጉ መጀመሪያ እነሱ ራሳቸው የአምላክን ሕግ በልባቸው ውስጥ መያዝ ይኖርባቸዋል።—ዘዳ. 6:6

13 ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በተግባር ለማዋል ልባዊ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ ልጆቻቸው ይህን ያስተውላሉ። ይህም ወላጆች ለልጆቻቸው የሚነግሯቸውም ሆነ የሚያስተምሯቸው ነገር በልጆቻቸው ላይ ተጽእኖ የማሳደር ኃይል እንዲኖረው ያደርጋል። ይሁን እንጂ ወላጆች፣ ከልጆቻቸው የሚጠብቁትን ነገር እነሱ ራሳቸው እንደማያደርጉት ልጆቹ ካስተዋሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆኑ ወይም ለእነሱ እንደማይሠሩ ሊሰማቸው ይችላል። ይህም ልጆቹ ዓለም በሚያሳድርባቸው ተጽዕኖ በቀላሉ እንዲሸነፉ ሊያደርጋቸው ይችላል።

14, 15. ወላጆች ልጆቻቸው ምን ዓይነት ግብ የማውጣት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ሊያበረታቷቸው ይገባል? ወላጆች እንዲህ ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድስ የትኛው ነው?

14 ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆችን ማሳደግ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ከማሟላት የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ይረዳሉ። በመሆኑም ልጁ ቁሳዊ ጥቅም የሚያስገኝለትን ግብ ብቻ እንዲያወጣ ማበረታታት ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው። (መክ. 7:12) ኢየሱስ ከሁሉ አስቀድመው የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን እንዲፈልጉ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:33) እንግዲያው ክርስቲያን ወላጆች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን የማውጣት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለመርዳት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

15 ወላጆች እንዲህ ማድረግ የሚችሉበት አንዱ መንገድ ልጆቻቸው ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ከአቅኚዎች ወይም ከወረዳ የበላይ ተመልካቹና ከባለቤቱ ጋር መቀራረብ ምን ያህል እንደሚያበረታታቸው አስቡ። ወደ ቤታችሁ የምትጋብዟቸው ሚስዮናውያን፣ ቤቴላውያን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የግንባታ ሠራተኞች ይሖዋን በማገልገል ያገኙትን ደስታ ከልብ በመነጨ ስሜት ሲናገሩ ልጆቻችሁ ሊያዳምጡ ይችላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች አስደሳች ተሞክሮዎች እንደሚኖሯቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሰማሩት እነዚህ ወንድሞች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ የሚያከናውኑት አገልግሎት ልጆቻችሁ ጥበብ ያለው ውሳኔ ለማድረግ፣ ከአምላክ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ግቦችን ለማውጣት እንዲሁም ራሳቸውን እየረዱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለመውሰድ እንዲነሳሱ ግሩም ምሳሌ ሊሆንላቸው ይችላል።

ልጆች—የኢየሱስን ምሳሌ እንድትከተሉ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

16. ኢየሱስ ለምድራዊ ወላጆቹም ሆነ በሰማይ ላለው አባቱ አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነበር?

16 ልጆች፣ ኢየሱስ ለእናንተም ግሩም ምሳሌ ትቶላችኋል። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ተንከባክበው እንዲያሳድጉት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን እሱም ይታዘዝላቸው ነበር። (ሉቃስ 2:51ን አንብብ።) ኢየሱስ ወላጆቹ ፍጹማን ባይሆኑም እሱን እንዲንከባከቡ አምላክ ኃላፊነት እንደሰጣቸው ተገንዝቦ ነበር። በዚህም ምክንያት ወላጆቹን ሊያከብራቸው ይገባ ነበር። (ዘዳ. 5:16፤ ማቴ. 15:4) ኢየሱስ ካደገም በኋላ ሁልጊዜም በሰማይ የሚኖረውን አባቱን የሚያስደስተውን ነገር ያደርግ ነበር። ይህም ፈተናዎችን መቋቋምን ይጨምራል። (ማቴ. 4:1-10) እናንት ልጆች፣ አንዳንድ ጊዜ የወላጆቻችሁን ትእዛዝ ለመጣስ ትፈተኑ ይሆናል። ታዲያ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንድትችሉ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

17, 18. (ሀ) ልጆች በትምህርት ቤት ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያጋጥማቸዋል? (ለ) ልጆች ምን ነገር ማስታወሳቸው ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ ሊረዳቸው ይችላል?

17 አብረውህ ከሚማሩት ልጆች አብዛኞቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች እምብዛም አክብሮት ላይኖራቸው ይችላል። አጠያያቂ በሆኑ እንቅስቃሴዎች እንድትካፈል ተጽዕኖ ያደርጉብህ ብሎም እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ በማትሆንበት ጊዜ ያፌዙብህ ይሆናል። አብረውህ የሚማሩ ልጆች ከእነሱ ጋር በአንድ ዓይነት ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆንህ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ተናግረውህ ያውቃሉ? ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ምላሽ ሰጠህ? በፍርሃት ተሸንፈህ የእነሱን አካሄድ ብትከተል ወላጆችህም ሆኑ ይሖዋ እንደሚያዝኑብህ ታውቃለህ። አብረውህ የሚማሩትን ልጆች አካሄድ ብትከተል ምን የሚደርስብህ ይመስልሃል? አቅኚ ወይም የጉባኤ አገልጋይ የመሆን፣ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ክልል ሄደህ የማገልገል አሊያም ቤቴላዊ የመሆን ግብ አውጥተህ ይሆናል። አብረውህ ከሚማሩ ልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እነዚህ ግቦች ላይ እንድትደርስ ሊረዳህ ይችላል?

18 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምትገኙ እናንት ልጆች፣ እምነታችሁን የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሟችሁ ያውቃል? ታዲያ ፈተናውን እንዴት ተወጣችሁት? ምሳሌያችሁ የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። ኢየሱስ ለቀረበለት ፈተና አልተሸነፈም፤ ከዚህ ይልቅ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቆራጥ አቋም ወስዷል። ይህንን ማስታወሳችሁ፣ ስሕተት እንደሆነ የምታውቁትን ነገር ለማድረግ አብረዋችሁ ከሚማሩት ልጆች ጋር እንደማትተባበሩ በግልጽ ለመናገር የሚያስችላችሁን ድፍረት እንድታገኙ ይረዳችኋል። ልክ እንደ ኢየሱስ፣ ይሖዋን በማገልገልና እሱን በመታዘዝ በሚገኘው ዘላለማዊ ደስታ ላይ አተኩሩ።—ዕብ. 12:2

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፍ የሆነው ነገር

19. በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን ምንድን ነው?

19 ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆች ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ፍጹማን ባንሆንም እንኳ በተወሰነ መጠን ደስታ ማግኘት እንችላለን። (ኢሳ. 48:17, 18፤ ማቴ. 5:3) ኢየሱስ፣ የሰው ዘር ደስታ እንዲያገኝ የሚረዱ መለኮታዊ እውነቶችን አስተምሯል። ይሁንና በዚህ ብቻ ሳይወሰን ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሚዛናዊ የሆነ ሕይወት ለመምራትና ሚዛናዊ አመለካከት ለማዳበር የሚረዳ ምሳሌ ትቷል። በቤተሰብ ውስጥ ያለን ድርሻ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንግዲያው ባሎች፣ ሚስቶች፣ ወላጆችና ልጆች የኢየሱስን ምሳሌ ተከተሉ! በእርግጥም፣ ደስታና እርካታ የሚያስገኝ የቤተሰብ ሕይወት ለመምራት ቁልፉ የኢየሱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግና ምሳሌውን መከተል ነው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ባሎች አምላክ የሰጣቸውን የራስነት ሥልጣን እንዴት ሊጠቀሙበት ይገባል?

• ሚስቶች የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

• ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከያዘበት መንገድ ወላጆች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

• ልጆች ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ የሆነ ባል ቤተሰቡን የሚመለከት ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ምን ያደርጋል?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ሚስት የባሏን የራስነት ሥልጣን እንደምታከብር በምን መንገድ ማሳየት ትችላለች?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች የወላጆቻቸውን መልካም ምሳሌ የመከተል ልማድ አላቸው