በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ ሃይማኖት ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ያስተምራል

ጥሩ ሃይማኖት ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ያስተምራል

ጥሩ ሃይማኖት መልካም የሆኑ ነገሮችን እንድናስብ እንዲሁም ጠባያችንን እንዴት ማሻሻል እንዳለብን ያስተምረናል። ትክክል የሆነውን ለማድረግ በምናደርገው ትግል የሚረዳን ከመሆኑም በላይ የተሻልን ሰዎች እንድንሆን ያስችለናል። ጥሩ ሃይማኖት በዚህ ረገድ እንደሚረዳን እንዴት እናውቃለን?

ሐዋርያው ጳውሎስ ግሪክ ውስጥ በምትገኘው ቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ ለነበሩ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል። በዚህች ጥንታዊ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሥነ ምግባር የዘቀጠ ሕይወት በመምራት የታወቁ ነበሩ። ጳውሎስ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፦ “ሴሰኞች፣ ወይም ጣዖት አምላኪዎች፣ ወይም አመንዝራዎች፣ ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ፣ ወይም ሌቦች፣ ወይም ስግብግቦች፣ ወይም ሰካራሞች፣ ወይም የሰው ስም አጥፊዎች፣ ወይም ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንዲሁ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና፣ በአምላካችን መንፈስ ከኃጢአት ታጥባችኋል፤ ለእግዚአብሔር የተለየ ቅዱስ ሕዝብ ሆናችኋል፤ ጸድቃችኋልም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9-11 የታረመው የ1980 ትርጉም) ከዚህ ጥቅስ መመልከት እንደምትችለው ጥሩ ሃይማኖት፣ በሥነ ምግባር መሥፈርቶች የማይመሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን ንጹሕና ጻድቅ የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል!

በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦ “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

አንተ የምታውቃቸው ሃይማኖቶች በዚህ ረገድ ያላቸው አቋም ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ይከተላሉ? ወይስ ሰዎች “የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን” ብቻ በማስተማር በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ንጹሕ ምክር ያቃልላሉ?

አንድ ሃይማኖት ጥሩ ፍሬ የሚያፈራ መሆን አለመሆኑን ለይተህ ለማወቅ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች ለምን አታስብባቸውም?

ርዕሰ ጉዳይ፦ ጋብቻ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።”—ዕብራውያን 13:4 የ1954 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንደ ባልና ሚስት አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት በሕግ እንዲጋቡ ያዛል?

ርዕሰ ጉዳይ፦ ፍቺ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? ኢየሱስ ለፍቺ የሚያበቃ ምክንያት ይኖር እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ “አንድ ሰው በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት ቢያገባ አመነዘረ” ብሏል።—ማቴዎስ 19:9 የታረመው የ1980 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ፍቺንና እንደገና ማግባትን ባለመፍቀድ ኢየሱስ የሰጠውን ይህን መመሪያ ያከብራል?

ርዕሰ ጉዳይ፦ የጾታ ሥነ ምግባር።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል።”—1 ቆሮንቶስ 6:18 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

“ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።”—ሮሜ 1:26, 27 የ1954 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታውቀው ሃይማኖት በወንድና በሴትም ሆነ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመው የፆታ ብልግና ኃጢአት እንደሆነ ያስተምራል?

ርዕሰ ጉዳይ፦ አባላቱ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በጥብቅ እንዲከተሉ ይጠብቅባቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “ክርስቲያኖች ተብለው ከሚያመነዝሩ፣ ወይም ከሚስገበገቡ፣ ወይም ጣዖት ከሚያመልኩ፣ ወይም የሰውን ስም ከሚያጠፉ፣ ወይም ከሚሰክሩ፣ ወይም ከቀማኞች ጋር አትተባበሩ። . . . እንደእነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር፣ መብል አብራችሁ አትብሉ።” (1 ቆሮንቶስ 5:11 የታረመው የ1980 ትርጉም) ክርስቲያን ነን የሚሉ ሆኖም ኃጢአት ሠርተው ንስሐ የማይገቡ ሰዎች ምን እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል? የአምላክ ቃል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ” በማለት ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 5:13 የታረመው የ1980 ትርጉም

ጥያቄ፦ አንተ የምታወቀው ሃይማኖት የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ጥሰው ንስሐ የማይገቡ ሰዎችን ከአባልነት ይሰርዛል?

የመጽሐፍ ቅዱስን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ በመከተል ረገድ ጥሩ ስም ያተረፈው የትኛው ሃይማኖት ነው?