በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ከልጅነቱ ጀምሮ ማሪዋና እና ትምባሆ ሲያጨስ የነበረ አንድ ሰው ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚያስችለውን ኃይል ያገኘው እንዴት ነው? በአንድ የወሮበሎች ቡድን ውስጥ አባል የነበረ ተደባዳቢ ሰው የቁጠኝነት ባሕርይውን እንዲያስተካክልና ለሌላ ዘር የነበረውን ጥላቻ እንዲያሸንፍ ያስቻለው ምንድን ነው? እስቲ እነዚህ ግለሰቦች የሚሉትን እንስማ።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ሃይንሪክ ማር

ዕድሜ፦ 38

አገር፦ ካዛክስታን

የኋላ ታሪክ፦ የማሪዋና እና የትንባሆ ሱሰኛ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት በደቡብ ካዛክስታን ታሽከንት ከተባለችው ከተማ 120 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ነው። ይህ ቦታ በበጋ ወቅት ደረቅና ሞቃታማ ሲሆን የሙቀቱም መጠን እስከ 45 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል፤ በክረምት ወቅት ደግሞ የቅዝቃዜው መጠን ከዜሮ በታች እስከ 10 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል። ይህ የአየር ጠባይ ወይንንም ሆነ ማሪዋናን ለማብቀል እጅግ ተስማሚ ነው።

የጀርመን ዝርያ ያላቸው ወላጆቼ የኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን አባላት ቢሆኑም ያን ያህል አጥባቂዎች አልነበሩም። ይሁን እንጂ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በቃሌ እንድይዘው አስተምረውኛል። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴና ታላቅ እህቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ነበር። አንድ ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች እናቴን እያስጠኗት ሳለ ቤታችን ከሚገኝ የቆየ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እየጠቀሱ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ሲነግሯት ሰማሁ። የሰማሁት ነገር በጣም አስገረመኝ። እናቴ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቷን ያቆመች ሲሆን እኔም መንፈሳዊ ነገሮችን ለማወቅ ተጨማሪ ጥረት አላደረግሁም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ትምህርት ቤት ሳለሁ አንዲት አስተማሪ መናፍቃን እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩት ስለ የይሖዋ ምሥክሮች የሰማችውን የሐሰት ወሬ በሙሉ ትነግረን ጀመር። የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ከእህቴ ጋር ተገኝቼ ስለነበር አስተማሪያችን የተናገረቻቸው ነገሮች ትክክል አለመሆናቸውን ነገርኳት።

አሥራ አምስት ዓመት ሲሞላኝ በዛሬው ጊዜ ሴንት ፒትስበርግ ተብላ ወደምትጠራው ሌኒንግራድ ወደተባለች ከተማ የሙያ ትምህርት እንድማር ተላክሁ። በትምህርት ቤት ውስጥ አብረውኝ ለሚኖሩት ልጆች ስለ ይሖዋ የማውቃትን ትንሽ ነገር እነግራቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሲጃራ ማጨስ ጀመርኩ። በካዛክስታን ማሪዋና መግዛት ሕጋዊ ባይሆንም እንኳ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ወደዚያ በሄድኩበት ወቅት ያለ ምንም ችግር ማሪዋና ማግኘት እችል ነበር። ከዚህም በላይ ቮድካና ቤት ውስጥ የሚዘጋጅ የወይን ጠጅ ከልክ በላይ እጠጣ ነበር።

የተከታተልኩትን የሙያ ትምህርት ካጠናቀቅኩ በኋላ በሶቪየት የጦር ሠራዊት ውስጥ ለሁለት ዓመት አገለገልኩ። ያም ሆኖ በልጅነቴ ያወቅኳቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከአእምሮዬ አልጠፉም ነበር። አጋጣሚ በማገኝበት ጊዜ ሁሉ አብረውኝ ላሉት ወታደሮች ስለ ይሖዋ እነግራቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳቱ ሐሳቦች በሚሰነዘሩበት ጊዜ ሽንጤን ገትሬ እከራከር ነበር።

ወታደራዊ አገልግሎቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ወደ ጀርመን ሄድኩ። በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ሳለሁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ አገኘሁ። በጉጉት ካነበብኩት በኋላ የያዘው ሐሳብ እውነት ነው ወደሚል መደምደሚያ ደረስኩ። ከትንባሆና ከማሪዋና ሱስ ግን መላቀቅ አልቻልኩም ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካርልዝሩአ በተባለችው ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ አንድ አካባቢ ተዛወርኩ። በዚያም ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር የተገናኘሁ ሲሆን እሱም መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ጀመር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? ለረጅም ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ አምን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳውን መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ደግሞ ቅዱሳን መጻሕፍት በሕይወት ውስጥ ለሚነሱ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎች በሙሉ መልስ እንደሚሰጡ እርግጠኛ ሆንኩ። ያም ሆኖ ከሱሶቼ ለመላቀቅ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር። በኋላም በ2 ቆሮንቶስ 7:1 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ማዋል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ፤ ከዚያም “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሴን ለማንጻት ማለትም ማሪዋና እና ትንባሆ ማጨሴን ለማቆም ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ።

ወዲያውኑ ማለት ይቻላል ማሪዋና ማጨሴን አቆምኩ። ይሁን እንጂ ከትንባሆ ሱስ ለመላቀቅ ሌሎች ስድስት ወራት ወስዶብኛል። አንድ ቀን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናኝ የይሖዋ ምሥክር “የሕይወትህ ዓላማ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ከእሱ ጋር ያደረግነው ውይይት ከትንባሆ ሱሴ ስለመላቀቅ እንዳስብ አደረገኝ። ትንባሆ ማጨሴን ለመተው ለበርካታ ጊዜያት ሞክሬ ነበር። አሁን ግን ሲጃራ አጭሼ አምላክን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ገና ሲጃራውን ከማንሳቴ በፊት ለመጸለይ ወሰንኩ። በ1993 ሲጃራ ማጨሴን የማቆምበትን ቀን ቆረጥኩ፤ በይሖዋ እርዳታ ከዚያን ቀን ጀምሮ አጭሼ አላውቅም።

ያገኘሁት ጥቅም፦ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ገንዘብ ያስወጣኝ ከነበረው ጎጂ ልማድ ይኸውም ከማሪዋና እና ከትንባሆ ሱሴ በመላቀቄ ጤንነቴ በእጅጉ እየተሻሻለ ነው። አሁን ጀርመን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆኜ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት እንደሆነ በመማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ! መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ማወቄ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።

አጭር የሕይወት ታሪክ

ስም፦ ታይተስ ሻንጋዲ

ዕድሜ፦ 43

አገር፦ ናሚቢያ

የኋላ ታሪክ፦ የወሮበላ ቡድን አባል

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት በሰሜን ናሚቢያ በኦሃንግዌና ክልል በምትገኝ አንዲት የገጠር መንደር ውስጥ ነው። በ1980 በዚህ ክልል ውስጥ ተደርጎ በነበረው ጦርነት በመንደራችን የሚኖሩ ሰዎች ተደብድበዋል፤ አልፎ ተርፎም ግድያ ተፈጽሞባቸዋል። ባደግኩበት መንደር አንድ ልጅ እንደ ወንድ የሚታየው ኃይለኛ ተደባዳቢ ከሆነና ሌሎች ልጆችን ካሸነፈ ብቻ ነበር። በመሆኑም ሌሎችን ማጥቃት የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ።

ትምህርቴን ስጨርስ ስፋኮፕመንት በምትባለው የወደብ ከተማ ውስጥ ከሚኖረው አጎቴ ጋር መኖር ጀመርኩ። እዚያ መኖር ከጀመርኩ ብዙም ሳልቆይ የአንድ ወረበሎች ቡድን አባል ሆንኩ። በከተማ ውስጥ ጥቁሮች እንዲገቡባቸው ወዳልተፈቀዱ ሆቴሎችና ቡና ቤቶች ሄደን ብጥብጥ እናስነሳ ነበር። በተለያዩ ጊዜያት ከጥበቃ ሠራተኞችና ከፖሊሶች ጋር ተደባድበናል። ማታ ማታ ስሄድ መንገድ ላይ ባገኘሁት ሰው ሁሉ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ገጀራ እይዝ ነበር።

አንድ ምሽት ከሌላ የወሮበላ ቡድን ጋር በተደባደብንበት ጊዜ ከሞት የተረፍኩት ለጥቂት ነበር። የሌላኛው ቡድን አባል የሆነ አንድ ወሮበላ ከኋላ መጥቶ አንገቴን ሊቆርጠው ትንሽ ነበር የቀረው፤ ከእኛ መካከል ያለ አንድ ጓደኛዬ ይህን ሰው መትቶ ራሱን እንዲስት ባያደርገው ኖሮ በሕይወት አልገኝም ነበር። ከሞት ብተርፍም እንኳ ይበልጥ ዓመፀኛ ሆንኩ። ወንድም ሆነ ሴት ከማንም ሰው ጋር ብጋጭ ሁልጊዜም የመጀመሪያውን ቡጢ የምሰነዝረው እኔ ነበርኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? መጀመሪያ ላይ ያገኘኋት የይሖዋ ምሥክር ከመዝሙር 37 ላይ የተወሰኑ ቁጥሮች አነበበችልኝና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ስለወደፊቱ ጊዜ የሚናገር ሌላ አስደሳች ተስፋ እንደያዘ ነገረችኝ። ይሁንና ይህ አስደሳች ተስፋ የሚገኘው የትኛው ምዕራፍ ላይ እንደሆነ ስላልነገረችኝ ያን ቀን ምሽት ጠቅላላውን የራእይ መጽሐፍ አንብቤ ጨረስኩት። በራእይ 21:3, 4 ላይ የሚገኘውን “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚለውን ተስፋ ሳነብ በጣም ተደሰትኩ። የይሖዋ ምሥክሮቹ እንደገና የመጡ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ያቀረቡልኝን ግብዣ ተቀበልኩ።

በአመለካከቴም ሆነ በአኗኗሬ ላይ ለውጥ ማድረግ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ይሁንና ከሐዋርያት ሥራ 10:34, 35 ላይ ‘አምላክ እንደማያዳላ፣ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው’ ተማርኩ። በተጨማሪም “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለውን የሮም 12:18⁠ን ሐሳብ በተግባር ለማዋል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ።

ቁጣዬን ከመቆጣጠር በተጨማሪ ያለብኝን ከባድ የትንባሆ ሱስ ማቆም ነበረብኝ። በተደጋጋሚ ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳኝ በእንባ ጭምር እለምነው ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋን እርዳታ እጠይቅ የነበረው በተሳሳተ መንገድ ነበር፤ ይኸውም “ለመጨረሻ ጊዜ” ላጭስና ይሖዋ እንዲረዳኝ እጸልያለሁ ብዬ አስብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኝ የነበረችው የይሖዋ ምሥክር ሲጃራ ከማንሳቴ በፊት መጸለይ ያለውን ጥቅም እንድገነዘብ ረዳችኝ። ከዚህም በላይ ሲጃራ ከሚያጨሱ ሌሎች ሰዎች መራቅ ነበረብኝ። በተጨማሪም ማጨስ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ አብረውኝ ለሚሠሩት ሰዎች እንድናገር የተሰጠኝን ምክር በተግባር ማዋል ጀመርኩ። ይህን ማድረጌ በጣም ጠቅሞኛል፤ ምክንያቱም አብረውኝ የሚሠሩት ሰዎች ከዚያ ወዲህ ሲጃራ እንዳጨስ አይጋብዙኝም።

ውሎ አድሮ ሲጃራ ማጨስ ያቆምኩ ሲሆን የቀድሞ አኗኗሬን እርግፍ አድርጌ ተውኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መማርና ተግባራዊ ማድረግ ከጀመርኩ ከስድስት ወራት በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ብቁ ሆንኩ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ የይሖዋ ምሥክሮች የዘርና የቀለም ልዩነት ሳይበግራቸው እርስ በርስ እንደሚዋደዱ መመልከቴ እውነተኛውን ሃይማኖት እንደሚከተሉ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል። ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከመሆኔ በፊት እንኳ የጉባኤ አባል የሆነ አንድ ነጭ ሰው እቤቱ ምግብ ጋብዞኛል። ይህ ለእኔ እንደ ሕልም ነበር። ከነጮች ጋር እቤታቸው ቁጭ ብዬ ምግብ ልበላ ቀርቶ በሰላም ጎን ለጎን ተቀምጬ አላውቅም። አሁን ግን የእውነተኛው የዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አባል ሆኛለሁ።

ቀደም ሲል የጥበቃ ሠራተኞችና ፖሊሶች አመለካከቴንና አኗኗሬን እንዳስተካክል ኃይል ተጠቅመው ሊያሳምኑኝ ሞክረው ነበር፤ ይሁን እንጂ አልተሳካላቸውም። የባሕርይ ለውጥ እንዳደርግና ደስተኛ ሰው እንድሆን ያስቻለኝ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ኃይል ብቻ ነው።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በተደጋጋሚ ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳኝ በእንባ ጭምር እለምነው ነበር”