በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች ሲያናድዱህ

ሰዎች ሲያናድዱህ

ሰዎች ሲያናድዱህ

ብዙውን ጊዜ ሰዎች “ብቀላ ጣፋጭ ነው” ሲሉ ይደመጣል። ይህ የሆነው አንድ የሚያናድድ ወይም ስሜትን የሚጎዳ ነገር በሚደረግብን ጊዜ የመበሳጨት ተፈጥሯዊ ባሕርይ ስላለን ነው። በተፈጥሯችን ትክክል እና ስህተት የሆነውን ነገር ለይቶ የማወቅ ችሎታ ስላለን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ተስተካክለው ማየት እንፈልጋለን። ታዲያ መስተካከል የሚችሉት እንዴት ነው?

እርግጥ ነው፣ እንድንናደድ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው በጥፊ ሊመታን፣ ሊገፈትረን፣ ሊሰድበን፣ ሊደበድበን፣ ሊዘርፈን ወይም ሌላ በደል ሊፈጽምብን ይችላል። አንተ እንዲህ ያለ በደል ቢደርስብህ ምን ይሰማሃል? በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ከሚወስዱት እርምጃ አንጻር ሲታይ ‘ዋጋውን ነው የምሰጠው!’ የሚሉ ይመስላል።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ፣ አንዳንድ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተግሣጽ የሰጧቸውን መምህራን ለመበቀል ሲሉ በደል እንደተፈጸመባቸው በማስመሰል መምህሮቻቸውን በሐሰት ይከሷቸዋል። የኒው ኦርሊየንስ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ብሬንደ ሚሼል “መምህራኑ አንዴ ክስ ከተመሠረተባቸው በኋላ ስማቸው ይጎድፋል” ብለዋል። የተመሠረተው ክስ ሐሰት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላም እንኳ ስማቸው እንደጎደፈ ሊቀር ይችላል።

በሥራ ቦታ በአሠሪዎቻቸው ያልተደሰቱ ወይም ከሥራ የተባረሩ በርካታ ሠራተኞች አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ከድርጅቱ ኮምፒውተር ውስጥ በማጥፋት አሠሪዎቻቸውን ይበቀላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የድርጅቱን ሚስጥር ሰርቀው ይሸጣሉ ወይም ለሌሎች አሳልፈው ይሰጣሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ሠራተኞች የድርጅቱን ኤሌክትሮኒክ ፋይል ከመስረቅ ባሻገር “ለብቀላ ሲሉ አንዳንድ ዕቃዎችን መውሰዳቸው ዛሬም ድረስ የተለመደ ነገር ነው።” በርካታ ድርጅቶች አንድን ሠራተኛ ከሥራው ሲያሰናብቱት ግለሰቡ ሊፈጽም የሚችለውን የብቀላ እርምጃ ለመከላከል ያሉትን ዕቃዎች ሰብስቦ ሕንፃውን ለቅቆ እስኪወጣ ድረስ የሚከታተለው የደኅንነት ሠራተኛ ይመድባሉ።

በጣም የሚገርመው አብዛኛውን ጊዜ የበቀል እርምጃ ሲፈጸም የሚታየው እርስ በርስ በሚቀራረቡ ሰዎች ማለትም በጓደኛሞች፣ በሥራ ባልደረቦች እና በቤተሰብ አባላት መካከል ነው። አንድ ሰው ሌሎች ደግነት የጎደለው ንግግር ተናግረውት ወይም መጥፎ ነገር አድርገውበት ስሜቱ መጎዳቱ የአጸፋ እርምጃ እንዲወስድ ሊያነሳሳው ይችላል። አንድ ጓደኛህ በቁጣ ሲናገርህ አንተም ጎጂ ቃላት ተጠቅመህ አጸፋውን ትመልሳለህ? ከቤተሰብህ አባላት መካከል አንዱ በሆነ መንገድ ቢያበሳጭህ ብድርህን የምትመልስበት መንገድ ትፈልጋለህ? በተለይ ያናደደን ሰው የምንቀርበው ሰው ከሆነ ብድር መመለስ በጣም እንደሚቀለን የታወቀ ነው!

መበቀል ያለው አደጋ

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ለመበቀል የሚነሳሱት የደረሰባቸው በደል ያስከተለባቸውን የስሜት ሥቃይ ለማስታገስ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የዕብራዊው የያዕቆብ ልጆች፣ ከነዓናዊው ሴኬም እህታቸውን ዲናን እንዳስነወራት በሰሙ ጊዜ እጅግ በጣም ‘እንዳዘኑና ክፉኛ እንደተቈጡ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 34:1-7) ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች በእህታቸው ላይ ለተፈጸመው ድርጊት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ በሴኬምና በቤተሰቡ ላይ ተንኮል ጠነሰሱ። ስምዖንና ሌዊ የጠነሰሱት ሴራ ስለተሳካላቸው ወደ ከነዓናውያን ከተማ በመግባት ሴኬምን ጨምሮ ሁሉንም ወንዶች ገደሉ።—ዘፍጥረት 34:13-27

ታዲያ ስምዖንና ሌዊ ደም ማፍሰሳቸው ሁኔታው እንዲስተካከል አድርጓል? ያዕቆብ ልጆቹ ያደረጉትን ነገር ከሰማ በኋላ እንዲህ በማለት ገሥጿቸዋል፦ “በዚህ አገር በሚኖሩት . . . እንደ ጥምብ አስቈጠራችሁኝ፣ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። . . . ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” (ዘፍጥረት 34:30) አዎን፣ እነዚህ ሰዎች የወሰዱት የበቀል እርምጃ ችግሩ እንዲፈታ አላደረገም፤ እንዲያውም ያዕቆብና ቤተሰቡ ‘ጎረቤቶቻችን መልሰው ይበቀሉናል’ በሚል ስሜት የሰቀቀን ሕይወት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። አምላክ በያዕቆብ ቤተሰብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ አስቦ ሳይሆን አይቀርም ያዕቆብ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ቤቴል እንዲሄድ አዘዘው።—ዘፍጥረት 35:1, 5

ዲና ተገድዳ ከመደፈሯ ጋር በተያያዘ ከተከሰቱት ሁኔታዎች ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። ብቀላ አብዛኛውን ጊዜ ሌላ የበቀል እርምጃ የሚያስከትል ሲሆን እንዲህ ያለው ድርጊት ማቆሚያ ላይኖረው ይችላል። “በቀል በቀልን ይወልዳል” የሚለው የጀርመኖች አባባል ይህን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል።

ማብቂያ የሌለው ብቀላ

የበደለንን ሰው እንዴት አድርገን እንደምንበቀለው ማሰብ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። ይቅር ባይነት—የተፈጸመብህን በደል ረስተህ የራስህን ሕይወት መምራት የምትችልበት መንገድ የተባለው መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሏል፦ “ንዴት ውስጥህን በልቶ ይጨርስሃል። ከዚህ ቀደም ስለተፈጸመብህ በደል ማሰላሰልህ፣ የጎዱህን ሰዎች በልብህ መርገምህና እነሱን የምትበቀልበትን ዘዴ ማፈላለግህ ጊዜህንና ኃይልህን ያሟጥጥብሃል።” መጽሐፍ ቅዱስ ‘ቅናት ዐጥንትን ያነቅዛል’ በማለት በግልጽ ይናገራል።—ምሳሌ 14:30

አንድ ሰው በጥላቻና አፍራሽ በሆኑ ስሜቶች ተሞልቶ እንዴት ደስተኛ ሊሆን ይችላል? አንድ አስተያየት ሰጪ “‘ብቀላ ጣፋጭ ነው’ ብለህ የምታስብ ከሆነ እንዴት እንደሚበቀሉ ለዓመታት ሲያውጠነጥኑ የኖሩ ሰዎችን ፊት ተመልከት” በማለት ተናግረዋል።

የዘርና የሃይማኖት ጥላቻ በነገሠባቸው በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ተመልከት። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ሲገደል ለበቀል ሲባል ሌላ ሰው ይገደላል፤ ይህ ደግሞ ማብቂያ የሌለው ጥላቻና ግድያ ከማስከተል ውጪ ምንም ፋይዳ የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ በአሸባሪዎች የቦንብ ጥቃት 18 ወጣቶች በተገደሉ ጊዜ በሁኔታው ያዘነች አንዲት ሴት “አንድ ሺህ እጥፍ አድርገን መመለስ አለብን!” በማለት በምሬት ተናግራ ነበር። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የጭካኔ ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዲሄዱና በርካታ ሰዎች ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።

“በዐይን ፈንታ ዐይን”

አንዳንድ ሰዎች የሚወስዱት የበቀል እርምጃ ትክክል መሆኑን ለማስረዳት መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ። እነዚህ ሰዎች “መጽሐፍ ቅዱስ ‘በዐይን ፈንታ ዐይን፣ በጥርስ ፈንታ ጥርስ’ በማለት ይናገር የለም?” ይላሉ። (ዘሌዋውያን 24:20) “በዐይን ፈንታ ዐይን” የሚለውን ትእዛዝ ላይ ላዩን ስናየው ብቀላን የሚያበረታታ ሊመስለን ይችላል። በመሠረቱ ግን ይህ ትእዛዝ በጭፍን የሚደረጉ የብቀላ ድርጊቶችን ለመግታት ወይም ለመከላከል የሚያገለግል ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

አንድ እስራኤላዊ የባልንጀራውን ዓይን ቢያጠፋ ሕጉ ተገቢው ቅጣት እንዲበየንበት ያዛል። ይሁንና ጉዳት ባደረሰው ግለሰብም ሆነ በቤተሰቡ አባላት ላይ የቅጣት እርምጃውን የሚወስደው በደል የተፈጸመበት ሰው አይደለም። ሕጉ በደል የተፈጸመበት ግለሰብ ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት ጉዳዩን ሥልጣን በተሰጣቸው ሰዎች ማለትም በተሾሙ ዳኞች ፊት እንዲያቀርብ ያዛል። ሆነ ብሎ ወንጀል የሚፈጽም ሰው እሱ የፈጸመው ድርጊት በራሱ ላይ የሚፈጸምበት መሆኑ ሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገር እንዳይፈጽሙ ለማስጠንቀቅ ያገለግል ነበር። ይሁንና ሕጉ ከዚህም ያለፈ ጥቅም ነበረው።

ይሖዋ አምላክ ከላይ የተመለከትነውን የቅጣት ሕግ ከመስጠቱ በፊት በሙሴ በኩል “ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ . . . ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት” የሚል ትእዛዝ ለእስራኤል ብሔር ሰጥቶ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:17, 18) አዎን፣ “በዐይን ፈንታ ዐይን፣ በጥርስ ፈንታ ጥርስ” የሚለው ትእዛዝ ጠቅላላው ሕግ ካለው አንድምታ አንጻር መታየት ይኖርበታል፤ ኢየሱስ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በሚሉት ሁለት ትእዛዛት ሕጉን ጠቅለል አድርጎ አስቀምጦታል። (ማቴዎስ 22:37-40) ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ሲፈጸምባቸው ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

የሰላምን መንገድ ተከተሉ

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን “የሰላም አምላክ” ብሎ የሚገልጸው ሲሆን እሱን የሚያመልኩ ሰዎችም ‘ሰላምን እንዲፈልጉና እንዲከተሉ’ ያሳስባቸዋል። (ዕብራውያን 13:20፤ 1 ጴጥሮስ 3:11) ይሁንና ሰላምን መፈለግ ጥሩ ውጤት ያስገኛል?

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ተተፍቶበታል፣ ተገርፏል፣ ጠላቶቹ ስደት አድርሰውበታል እንዲሁም የቅርብ ወዳጁ ከድቶታል አልፎ ተርፎም ተከታዮቹ ትተውት ሸሽተዋል። (ማቴዎስ 26:48-50፤ 27:27-31) በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምን እርምጃ ወሰደ? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።”—1 ጴጥሮስ 2:23

ጴጥሮስ፣ “ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 2:21) አዎን፣ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በደል ሲፈጸምበት ያደረገውን ነገር ጨምሮ የእሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። እንዲያውም እሱ ራሱ በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ።”—ማቴዎስ 5:44, 45

የክርስቶስ ዓይነት ፍቅር ያላቸው ሰዎች በደል ሲፈጸምባቸውም ሆነ እንደተፈጸመባቸው ሲሰማቸው ምን እርምጃ ይወስዳሉ? ምሳሌ 19:11 “ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች፤ በደልን ንቆ መተውም መከበሪያው ነው” ይላል። ከዚህም በተጨማሪ “በክፉ አትሸነፍ፤ ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ሮም 12:21) እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ከሚታየው የበቀል መንፈስ ምንኛ የተለየ ነው! ፍቅር ‘የበደል መዝገብ ስለሌለው’ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር የበቀል ስሜትን በማሸነፍ ‘በደልን ንቀን እንድንተው’ ይረዳናል።—1 ቆሮንቶስ 13:5

ይህ ሲባል ሰዎች ወንጀል ቢፈጽሙብን ወይም አንድ ነገር እንደሚያደርጉን በመናገር ቢያስፈራሩን ዝም ብለን መቀበል አለብን ማለት ነው? በፍጹም! ጳውሎስ “ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ” ብሎ ሲናገር አንድ ክርስቲያን ሁልጊዜ ሰማዕት ስለ መሆን ማሰብ አለበት ማለቱ አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ ጥቃት ሲሰነዘርብን ራሳችንን የመከላከል መብት አለን። አንድ ሰው በአንተም ሆነ በንብረትህ ላይ አደጋ ሊያደርስ ቢሞክር ፖሊስ ልትጠራ ትችላለህ። ችግሩ የተነሳው በሥራ ቦታ አሊያም በትምህርት ቤት ከሆነ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጉዳዩን ማሳወቅ ትችላለህ።—ሮም 13:3, 4

ያም ሆኖ በዚህ ሥርዓት ውስጥ እውነተኛ ፍትሕ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። እንዲያውም ፍትሕ ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት የባዘኑ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እነኚህ ሰዎች ያሰቡትን ነገር ማግኘት አለመቻላቸው ካስከተለባቸው ምሬትና ንዴት ውጪ ያተረፉት ነገር የለም።

ሰዎች በበቀልና በጥላቻ ሲናቆሩ ከማየት የበለጠ ሰይጣንን የሚያስደስተው ነገር የለም። (1 ዮሐንስ 3:7, 8) የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሁልጊዜም ማሰባችን ምንኛ የተሻለ ነው፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ይላል ይሖዋ’ ተብሎ ስለተጻፈ ለአምላክ ቁጣ ዕድል ስጡ።” (ሮም 12:19) በደል ሲፈጸምብን ጉዳዩን ለይሖዋ መተዋችን ከስሜት ሥቃይ፣ ከብስጭትና ከሌሎች ጋር ከመጣላት ያድነናል።—ምሳሌ 3:3-6

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” እንዲሁም “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ”

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅር “የበደል መዝገብ የለውም።”—1 ቆሮንቶስ 13:5