በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ

የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ

የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ

“ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ በመካከላችሁ [ይስፈን]።”—ሮም 15:5

1. የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር መጣር ያለብን ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ እኔ ኑ፣ . . . ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ” የሚል ግብዣ አቅርቧል። (ማቴ. 11:28, 29) ይህ ሞቅ ያለ ግብዣ አፍቃሪ የሆነውን የኢየሱስን አስተሳሰብ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ከሰው ልጆች መካከል ልንከተለው የምንችል ከኢየሱስ የተሻለ ምሳሌ የሚሆን ሰው ማግኘት አይቻልም። ኢየሱስ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን ያለው የአምላክ ልጅ ቢሆንም ለሰዎች በተለይም ችግር ለደረሰባቸው ርኅራኄና አዘኔታ አሳይቷል።

2. ከኢየሱስ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

2 በዚህና በሚቀጥሉት ሁለት የጥናት ርዕሶች ላይ የኢየሱስን አስተሳሰብ ማዳበርና እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ እስከ መጨረሻው ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን፤ ከዚህም በተጨማሪ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ በሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቅ የምንችልባቸውን መንገዶች እንመረምራለን። (1 ቆሮ. 2:16) በእነዚህ የጥናት ርዕሶች ውስጥ በዋነኝነት የምናተኩረው በአምስት ነገሮች ይኸውም ኢየሱስ ባሳየው ገርነትና ትሕትና እንዲሁም በደግነቱ፣ ለአምላክ ታዛዥ በመሆኑ፣ በድፍረቱና ጽኑ በሆነው ፍቅሩ ላይ ነው።

ክርስቶስ ካሳየው ገርነት ትምህርት ማግኘት

3. (ሀ) ኢየሱስ ትሑት ስለ መሆን ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማረባቸው መንገዶች አንዱ የትኛው ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርቱ ድክመት ባሳዩበት ወቅት ኢየሱስ ምን አላቸው?

3 ፍጹም የሆነው የአምላክ ልጅ ኢየሱስ፣ በፈቃደኝነት ወደ ምድር በመምጣት ፍጽምና በጎደላቸውና ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች መካከል አገልግሏል። ኢየሱስ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ እንደሚገድሉት ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ምንጊዜም ደስተኛ የነበረ ከመሆኑም በላይ ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይቷል። (1 ጴጥ. 2:21-23) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ ‘በትኩረት መመልከታችን’ በሌሎች ድክመትና አለፍጽምና የተነሳ በምናዝንበት ወቅት ደስታችንን እንዳናጣና ራሳችንን እንድንገዛ ሊረዳን ይችላል። (ዕብ. 12:2) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ‘ቀንበሩን እንዲሸከሙ’ እና እንዲህ በማድረግ ከእሱ እንዲማሩ ግብዣ አቅርቦላቸዋል። (ማቴ. 11:29) ታዲያ ምን ሊማሩ ይችላሉ? ከኢየሱስ ሊማሩ የሚችሉት አንዱ ነገር ገርነትን ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ይሳሳቱ የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ በትዕግሥት ይዟቸዋል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ ነበር፤ በዚህ ወቅት “ትሑት” በመሆን ረገድ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። (ዮሐንስ 13:14-17ን አንብብ።) በኋላም ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ‘ነቅተው መጠበቅ’ ባቃታቸው ጊዜ ኢየሱስ በደግነት ድክመታቸውን ተገንዝቦላቸው ነበር። ኢየሱስ “ስምዖን፣ ተኝተሃል?” በማለት ጴጥሮስን ከጠየቀው በኋላ እንዲህ አለ፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፣ ጸልዩም። እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”—ማር. 14:32-38

4, 5. ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ሰዎች ስህተት ሲሠሩ ጉዳዩን እንዴት መያዝ እንዳለብን የሚያስተምረን በምን መንገድ ነው?

4 አንድ የእምነት ባልንጀራችን የፉክክር መንፈስ የሚታይበት፣ በቀላሉ የሚቀየም አሊያም “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወይም ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ምክር ቶሎ ሥራ ላይ የማያውል ቢሆን ምን ይሰማናል? (ማቴ. 24:45-47) በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች በአለፍጽምና ምክንያት ስህተት ሲፈጽሙ ብዙም ላይገርመንና እነሱን ይቅር ለማለትም ዝግጁ ልንሆን እንችላለን፤ የወንድሞቻችንን ድክመት መቻል ግን ይከብደን ይሆናል። የሌሎችን ጉድለት ስናይ ቶሎ የሚከፋን ከሆነ “‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ በተሻለ መንገድ ማንጸባረቅ የምችለው እንዴት ነው?” በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ በተወሰነ መጠን በመንፈሳዊ በተዳከሙበት ጊዜም እንኳ እንዳልተበሳጨ ማስታወስ ይኖርብናል።

5 ሐዋርያው ጴጥሮስን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጴጥሮስ ከጀልባው ላይ በመውረድ በውኃ ላይ እየተራመደ ወደ እሱ እንዲመጣ ኢየሱስ በጋበዘው ጊዜ ይህ ሐዋርያ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እንደዚያ ማድረግ ችሎ ነበር። ይሁንና ማዕበሉን ሲያይ መስጠም ጀመረ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ተበሳጭቶ “ዋጋህ ነው! ለወደፊቱ ይህ ትምህርት ይሆንሃል” አለው? በፍጹም! ከዚያ ይልቅ “ኢየሱስ [ወዲያው] እጁን ዘርግቶ ያዘውና ‘አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርክ?’ አለው።” (ማቴ. 14:28-31) እኛስ አንድ ወንድማችን እምነት እንደጎደለው የሚጠቁም እርምጃ ሲወስድ ብንመለከት በምሳሌያዊ መንገድ እጃችንን ልንዘረጋለትና እምነቱን እንዲያጠናክር ልንረዳው እንችላለን? ኢየሱስ ጴጥሮስን በገርነት መንፈስ ከያዘበት መንገድ የምናገኘው ትምህርት ይህ ነው።

6. ኢየሱስ ከፍ ያለ ቦታ ለማግኘት መፈለግን በተመለከተ ለሐዋርያቱ ምን ትምህርት ሰጣቸው?

6 ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በየጊዜው ይከራከሩ የነበረ ሲሆን በዚህ ውዝግብ ጴጥሮስም ተካፋይ ነበር። ያዕቆብና ዮሐንስ በመንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር አንዳቸው በቀኙ አንዳቸው ደግሞ በግራው መቀመጥ ፈልገው ነበር። ጴጥሮስና የቀሩት ሐዋርያት ይህን ሲሰሙ ተቆጡ። ሐዋርያቱ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲያድርባቸው ያደረገው ያደጉበት ማኅበረሰብ እንደሆነ ኢየሱስ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ ገዥዎች በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ። በእናንተ መካከል እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ግን አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባዋል፤ እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባዋል።” ከዚያም የራሱን ሁኔታ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት እንጂ እንዲገለገል አይደለም።”—ማቴ. 20:20-28

7. ሁላችንም ለጉባኤው አንድነት አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ባሳየው ትሕትና ላይ ማሰላሰላችን ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ‘ራሳችንን ከሁሉ እንደምናንስ አድርገን እንድንቆጥር’ ይረዳናል። (ሉቃስ 9:46-48) እንዲህ ማድረጋችን በመካከላችን አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል። ይሖዋ፣ ትልቅ ቤተሰብ እንዳለው አንድ አባት ልጆቹ “ተስማምተው በአንድነት [እንዲኖሩ]” ይፈልጋል። (መዝ. 133:1) ኢየሱስ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አንድነት እንዲኖራቸው ወደ አባቱ ጸልዮአል፤ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲገልጽም “ዓለም አንተ እንደላክኸኝ እንዲሁም እኔን እንደወደድከኝ ሁሉ እነሱንም እንደወደድካቸው ያውቅ ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐ. 17:23) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በመካከላችን አንድነት መኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችን እንዲታወቅ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት አንድነት እንዲኖረን የሌሎችን ድክመት በተመለከተ የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይገባናል። ኢየሱስ ይቅር ባይ ነበረ፤ እኛም ይቅርታ የሚደረግልን ሌሎችን ይቅር ካልን ብቻ እንደሆነ አስተምሯል።—ማቴዎስ 6:14, 15ን አንብብ።

8. ለረጅም ዓመታት አምላክን ያገለገሉ ሰዎች ከተዉት ምሳሌ ምን መማር እንችላለን?

8 ለረጅም ዓመታት የክርስቶስን ምሳሌ ሲከተሉ የኖሩ ሰዎችን እምነት በመከተልም ብዙ መማር እንችላለን። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ልክ እንደ ኢየሱስ የሌሎችን ድክመት ይረዳሉ። የክርስቶስ ዓይነት ርኅራኄ ማሳየት “ብርቱ ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት” ለመሸከም እንደሚረዳ እንዲሁም አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገንዝበዋል። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱን ርኅራኄ ማሳየት መላው ጉባኤ የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲያንጸባርቅ እንደሚረዳ ያውቃሉ። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ወንድሞቻቸውም የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲይዙና አንድነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የተመኘው ይህንኑ ነበር፤ እንዲህ ብሏል፦ “ጽናትንና መጽናኛን የሚሰጠው አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ በመካከላችሁ እንዲሰፍን ያድርግ፤ ይኸውም በአንድ ሐሳብና በአንድ አፍ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።” (ሮም 15:1, 5, 6) በእርግጥም በአንድነት ሆነን ይሖዋን ማምለካችን ለእሱ ውዳሴ ያመጣል።

9. የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል መንፈስ ቅዱስ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

9 ኢየሱስ ‘በልብ ትሑት’ መሆንን ከገርነት ጋር አያይዞ የጠቀሰው ሲሆን ገርነት ደግሞ ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ የተወውን አርዓያ በትክክል መከተል እንድንችል የእሱን ምሳሌ ከማጥናትም በተጨማሪ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልገናል። አምላክ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይ እንዲሁም የመንፈሱን ፍሬ ገጽታዎች ይኸውም ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ጥሩነትን፣ እምነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን’ ለማዳበር መጣር ይኖርብናል። (ገላ. 5:22, 23) በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ የተወውን የትሕትናና የገርነት ምሳሌ በመከተል በሰማይ የሚገኘውን አባታችንን ይሖዋን እናስደስታለን።

ኢየሱስ ሌሎችን በደግነት ይይዝ ነበር

10. ኢየሱስ ደግነት ያሳየው እንዴት ነበር?

10 ደግነትም ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ነው። ኢየሱስ ምንጊዜም ቢሆን ሰዎችን በደግነት ይይዝ ነበር። እሱን በቅንነት የፈለጉት ሁሉ ‘በደግነት እንደተቀበላቸው’ መገንዘብ ችለዋል። (ሉቃስ 9:11ን አንብብ።) ታዲያ ኢየሱስ ካሳየው ደግነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? ደግ የሆነ ሰው ተግባቢ፣ ገር፣ አዛኝና ርኅሩኅ ነው። ኢየሱስ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነበር። ሕዝቡ “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር” እጅግ አዝኖላቸዋል።—ማቴ. 9:35, 36

11, 12. (ሀ) ኢየሱስ ርኅሩኅ ሰው መሆኑን በተግባር ያሳየበትን አንድ ምሳሌ ጥቀስ። (ለ) እዚህ ላይ ከተመለከትነው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?

11 ኢየሱስ ለሰዎች ያለውን አዘኔታና ርኅራኄ በተግባር አሳይቷል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ለአሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች። ይህቺ ሴት በሙሴ ሕግ መሠረት እሷም ሆነች እሷን የነኩ ሰዎች ሁሉ እንደ ረከሱ ስለሚቆጠሩ በአምልኮ ሥርዓቶች መካፈል እንደማይችሉ ታውቅ ነበር። (ዘሌ. 15:25-27) ያም ሆኖ ስለ ኢየሱስ የሰማችው ነገርና ሰዎችን የያዘበት መንገድ እሷን ለመፈወስ ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው እንድታምን ሳያደርጋት አልቀረም። “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ታስብ ስለነበር እንደምንም ራሷን አደፋፍራ ልብሱን ነካች፤ ወዲያውም ከሕመሟ እንደተፈወሰች ታወቃት።

12 ኢየሱስ አንድ ሰው እንደነካው ስለታወቀው ማን እንደነካው ለማወቅ ዘወር ብሎ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ይህች ሴት፣ ሕጉን በመጣሷ እንደሚገሥጻት በመፍራት ሳይሆን አይቀርም እየተንቀጠቀጠች በእግሩ ሥር ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። ታዲያ ኢየሱስ ስትሠቃይ የኖረችውን ይህችን ምስኪን ሴት ገሠጻት? በፍጹም! ከዚያ ይልቅ በሚያጽናና መንገድ እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ።” (ማር. 5:25-34) ሴትየዋ እንዲህ ያለውን ደግነት የተንጸባረቀበት ንግግር ስትሰማ ምን ያህል ተጽናንታ ይሆን!

13. (ሀ) የኢየሱስ አስተሳሰብ ከፈሪሳውያን የተለየ የነበረው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ልጆችን የያዛቸው እንዴት ነበር?

13 ለሰዎች ርኅራኄ ካልነበራቸው ፈሪሳውያን በተለየ መልኩ ክርስቶስ ሥልጣኑን በሌሎች ላይ ተጨማሪ ሸክም ለመጫን ፈጽሞ ተጠቅሞበት አያውቅም። (ማቴ. 23:4) ከዚህ ይልቅ የይሖዋን መንገዶች ለሰዎች በደግነትና በትዕግሥት አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ ለተከታዮቹ አፍቃሪ ወዳጅ ነበር፤ ሁልጊዜ ፍቅርና ደግነትን በማሳየት እውነተኛ ጓደኛ መሆኑን አሳይቷቸዋል። (ምሳሌ 17:17፤ ዮሐ. 15:11-15) ልጆችም እንኳ ኢየሱስን መቅረብ አይከብዳቸውም ነበር፤ እሱም ቢሆን ከልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተው ነበር። የሚሠራውን ትቶ ከልጆች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ፈቃደኛ ነበር፤ ከእነሱ ጋር ለመሆን ጊዜ አጥቶ አያውቅም። በአካባቢያቸው እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸውን ከፍ አድርገው የመመልከት ዝንባሌ የነበራቸው ደቀ መዛሙርቱ በአንድ ወቅት ሰዎች ትንንሽ ልጆቻቸውን ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ወደ እሱ ባመጧቸው ጊዜ ለመከልከል ሞክረው ነበር። ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ባደረጉት ነገር አልተደሰተም። “ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው” አላቸው። ከዚያም ልጆቹን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ጠቃሚ ትምህርት ሰጣቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ የአምላክን መንግሥት እንደ አንድ ትንሽ ልጅ ሆኖ የማይቀበል ሁሉ ፈጽሞ ወደዚህ መንግሥት አይገባም።”—ማር. 10:13-15

14. የጉባኤ አባላት ለልጆች ጤናማ የሆነ አሳቢነት ማሳየታቸው ልጆቹን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

14 ከእነዚያ ልጆች አንዳንዶቹ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አቅፏቸውና እጁን ጭኖ ባርኳቸው’ እንደነበር ከዓመታት በኋላ ትልቅ ሰው ሆነው ሲያስታውሱ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አስብ። (ማር. 10:16) በዛሬው ጊዜም ሽማግሌዎችና ሌሎች የጉባኤው አባላት ለልጆች ጤናማ የሆነ ልባዊ አሳቢነት ካሳዩአቸው ልጆቹ ሲያድጉ ጥሩ ትዝታ ይኖራቸዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የጉባኤው አባላት ለልጆች በለጋ ዕድሜያቸው እንዲህ ዓይነት ልባዊ አሳቢነት ካሳዩአቸው ልጆቹ የይሖዋ መንፈስ በሕዝቦቹ መካከል እንዳለ ይገነዘባሉ።

ደግነት በጎደለው ዓለም ውስጥ ደግነት ማሳየት

15. በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ደግነት የማያሳዩ መሆናቸው ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ለሌሎች ደግነት ለማሳየት ጊዜ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ ሕዝቦች በየዕለቱ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም በጉዞና በአገልግሎት ላይ የዓለም መንፈስ ለሚያሳድረው ተጽዕኖ የተጋለጡ ናቸው። ሰዎች ደግነት የማያሳዩ መሆናቸው ሊያሳዝነን ቢችልም ሊያስገርመን ግን አይገባም። “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸው ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” ሊሆኑ እንደሚችሉ ጳውሎስ በይሖዋ መንፈስ መሪነት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።—2 ጢሞ. 3:1-3

16. በጉባኤ ውስጥ የክርስቶስ ዓይነት ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ደግነት ከጎደለው ከዚህ ዓለም በተቃራኒ በእውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታ መንፈስን የሚያድስ ነው። ሁላችንም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለው ጥሩ መንፈስ እንዲኖር አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች የጤና እክል አሊያም ሌሎች ከባድ ችግሮች አሉባቸው፤ በመሆኑም በጉባኤ ውስጥ መንፈስን የሚያድስ ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ እነዚህን ወንድሞቻችንን በመርዳትና በማበረታታት ነው። “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ እንደነዚህ ያሉት ችግሮች ይበልጥ እየተባባሱ ቢሄዱም እነዚህ ሁኔታዎች አዲስ አይደሉም። በጥንት ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖችም እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟቸው ነበር። በዚያ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እርዳታ ያስፈልጋቸው እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ጳውሎስ፣ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” በማለት ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) ይህም እንደ ክርስቶስ ዓይነት ደግነት እንዳለን በተግባር ማሳየትን ይጨምራል።

17, 18. የኢየሱስ ዓይነት ደግነት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

17 ክርስቲያኖች ለወንድሞቻችን ደግነት የማሳየት፣ ኢየሱስ በሚይዛቸው መንገድ የመያዝ እንዲሁም ለረጅም ዓመታት ለምናውቃቸውም ሆነ አዲስ ለተዋወቅናቸው ወንድሞቻችን ልባዊ አሳቢነት የማሳየት ኃላፊነት ተጥሎብናል። (3 ዮሐ. 5-8) ኢየሱስ በራሱ ተነሳሽነት ለሌሎች ርኅራኄ ያሳይ እንደነበረ ሁሉ እኛም ምንጊዜም ሌሎች ከጭንቀታቸው እረፍት እንዲያገኙ በማድረግ ርኅራኄ ልናሳይ ይገባል።—ኢሳ. 32:2፤ ማቴ. 11:28-30

18 ሁላችንም ስለ ሌሎች ደኅንነት ከልባችን እንደምናስብና ችግራቸውን እንደምንረዳላቸው የሚጠቁም ነገር በማድረግ ደግነት ማሳየት እንችላለን። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉን አጋጣሚዎች መፈለግ ይኖርብናል። ወንድሞቻችንን ለመርዳት ጥረት ልናደርግ ይገባል። ጳውሎስ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” የሚል ማሳሰቢያ ከሰጠ በኋላ አክሎም “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” ብሏል። (ሮም 12:10) ይህም ሲባል የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ሌሎችን በፍቅርና በደግነት መያዝ እንዲሁም ‘ግብዝነት የሌለው ፍቅር’ ማሳየትን መማር ማለት ነው። (2 ቆሮ. 6:6) ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ያሳየውን እንዲህ ያለውን ፍቅር በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም፣ ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም።” (1 ቆሮ. 13:4) በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ ቂም ከመያዝ ይልቅ የሚከተለውን ምክር በተግባር እናውል፦ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌ. 4:32

19. የክርስቶስን ዓይነት ደግነት ማሳየታችን ምን በረከት ያስገኛል?

19 የክርስቶስ ዓይነት ደግነት ለማዳበርና በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ ይህን ባሕርይ ለማንጸባረቅ ጥረት ማድረጋችን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኛል። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋ መንፈስ ምንም ነገር ሳይገድበው በጉባኤው ውስጥ እንዲሠራ የሚያደርግ ሲሆን ይህ ደግሞ እያንዳንዱ የጉባኤው አባል የመንፈስ ፍሬን እንዲያፈራ ይረዳዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የተወውን አርዓያ በመከተልና ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ በመርዳት በደስታና በአንድነት የምናቀርበው አምልኮ ይሖዋን ያስደስተዋል። እንግዲያው ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የኢየሱስን ዓይነት ገርነትና ደግነት ሁልጊዜ ለማንጸባረቅ ጥረት እናድርግ።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ ‘ገርና በልቡ ትሑት’ እንደሆነ ያሳየው እንዴት ነበር?

• ኢየሱስ ደግነት ያሳየው እንዴት ነበር?

• ፍጽምና በጎደለው ዓለም ውስጥ የክርስቶስን ዓይነት ገርነትና ደግነት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጴጥሮስ እንዳጋጠመው ሁሉ አንድ ወንድማችንም እምነት እንደጎደለው የሚጠቁም እርምጃ ሲወስድ ብንመለከት የእርዳታ እጃችንን እንዘረጋለታለን?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጉባኤው ደግነት የሰፈነበት እንዲሆን አስተዋጽኦ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?