በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ ክርስቶስ ታዛዦችና ደፋሮች ሁኑ

እንደ ክርስቶስ ታዛዦችና ደፋሮች ሁኑ

እንደ ክርስቶስ ታዛዦችና ደፋሮች ሁኑ

“አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐ. 16:33

1. ኢየሱስ ለአምላክ ታዛዥ የሆነው እስከ ምን ድረስ ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ ምንጊዜም የአምላክን ፈቃድ ያደርግ ነበር። በሰማይ የሚገኘውን የአባቱን ትእዛዝ ለመጣስ ፈጽሞ አስቦ አያውቅም። (ዮሐ. 4:34፤ ዕብ. 7:26) እርግጥ ነው፣ በምድር ላይ እያለ ያጋጠሙት ነገሮች መታዘዝ ቀላል እንዲሆንለት የሚያደርጉ አልነበሩም። ኢየሱስ የስብከት ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሰይጣንም ሆነ ሌሎች ጠላቶቹ፣ የሚያሳምን ሐሳብ በማቅረብና በማስገደድ ወይም በዘዴ በማጥመድ ታማኝነቱን እንዲያጎድል ለማድረግ ሞክረዋል። (ማቴ. 4:1-11፤ ሉቃስ 20:20-25) እነዚህ ጠላቶች በኢየሱስ ላይ ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ፣ የስሜትና የአካል ሥቃይ አድርሰውበታል። በመጨረሻም በመከራ እንጨት ላይ ሰቅለው ገድለውታል። (ማቴ. 26:37, 38፤ ሉቃስ 22:44፤ ዮሐ. 19:1, 17, 18) ኢየሱስ ይህ ሁሉ ሥቃይ ቢደርስበትም “እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።”—ፊልጵስዮስ 2:8⁠ን አንብብ።

2, 3. ኢየሱስ መከራ ቢደርስበትም ታዛዥ መሆኑ ምን ትምህርት ይሰጠናል?

2 ኢየሱስ፣ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት ታዛዥነትን በተለየ መንገድ እንዲማር አስችሎታል። (ዕብ. 5:8) ይሖዋን በማገልገል ረገድ ኢየሱስ ሊማር የሚችለው ነገር የሚኖር አይመስል ይሆናል። ኢየሱስ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበረው ከመሆኑም ሌላ በፍጥረት ወቅት የአምላክ “ዋና ባለሙያ” ነበር። (ምሳሌ 8:30) ያም ቢሆን ሰው ሆኖ መከራ ሲደርስበት በታማኝነት መጽናቱ ንጹሕ አቋሙን ሙሉ በሙሉ እንደጠበቀ የሚያረጋግጥ ነበር። ይህ ሁኔታ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ በመንፈሳዊ እንዲያድግ ረድቶታል። ኢየሱስ ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

3 ኢየሱስ ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ታዛዥ በመሆን ረገድ በራሱ አልተማመነም። እስከ መጨረሻው ታዛዥ ለመሆን እንዲረዳው ወደ አምላክ ጸልዮአል። (ዕብራውያን 5:7ን አንብብ።) እኛም ታዛዦች ሆነን ለመቀጠል ከፈለግን ትሑት መሆንና የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ዘወትር መጸለይ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ራሱን ዝቅ በማድረግ . . . እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ” የሆነው “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር” በማለት ክርስቲያኖችን የመከራቸው ለዚህ ነው። (ፊልጵ. 2:5-8) ኢየሱስ ይህን በማድረግ፣ ሰዎች በክፋት በተሞላ ኅብረተሰብ ውስጥ ቢኖሩም እንኳ ታዛዥ መሆን እንደሚችሉ አረጋግጧል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር፤ ታዲያ ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም ታዛዥ መሆን እንችላለን

4. ይሖዋ ሲፈጥረን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል ሲባል ምን ማለት ነው?

4 አምላክ አዳምንና ሔዋንን፣ የመምረጥ ነፃነትና የማሰብ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጎ ፈጥሯቸዋል። እኛም የእነሱ ልጆች እንደመሆናችን መጠን የመምረጥ ነፃነት አለን። ይህን ስንል ምን ማለታችን ነው? መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ጎዳና ለመከተል የራሳችንን ውሳኔ ማድረግ እንችላለን ማለት ነው። በሌላ አባባል አምላክ እሱን ለመታዘዝም ሆነ ላለመታዘዝ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። እንዲህ ያለው ታላቅ ነፃነት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያስከትላል። በእርግጥም የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሕይወት ሊያስገኙልን ወይም ሞት ሊያስከትሉብን ይችላሉ። ከዚህም በላይ ውሳኔያችን የሚቀርቡንን ሰዎችም ይነካል።

5. ሁላችንም ምን ትግል አለብን? ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

5 በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት መታዘዝ ይከብደናል። የአምላክን ሕግጋት መታዘዝ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ጳውሎስ በዚህ ረገድ ትግል ማድረግ አስፈልጎት እንደነበር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋና በአካሌ ክፍሎች ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” (ሮም 7:23) በእርግጥ መሥዋዕት መክፈል በማይጠይቁ፣ ሥቃይ በማያስከትሉ ወይም ምቹ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ታዛዥ መሆን ቀላል ነው። ይሁን እንጂ አምላክን ለመታዘዝ ባለን ፍላጎት እና ‘በሥጋችን ምኞት ብሎም በዓይናችን አምሮት’ መካከል ግጭት ቢፈጠር ምን እናደርጋለን? እነዚህ የተሳሳቱ ፍላጎቶች በውስጣችን የሚኖሩት ፍጽምና የጎደለን ስለሆንን እንዲሁም በዙሪያችን ያለው ‘የዓለም መንፈስ’ ተጽዕኖ ስለሚያሳድርብን ነው፤ እነዚህ ምኞቶች በእኛ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል አላቸው። (1 ዮሐ. 2:16፤ 1 ቆሮ. 2:12) እነዚህን ምኞቶች ለመቋቋም እንድንችል ችግሮች ከመምጣታቸው ወይም ለፈተና ከመዳረጋችን በፊት ‘ልባችንን ማቅናት’ ወይም ማዘጋጀት እንዲሁም ምንም ይምጣ ምን ይሖዋን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። (መዝ. 78:8) አስቀድመው ልባቸውን በማዘጋጀታቸው ፈተናዎችን በተሳካ ሁኔታ ማሸነፍ የቻሉ የበርካታ ሰዎችን ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማግኘት እንችላለን።—ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም፤ ዳን. 1:8

6, 7. የግል ጥናት፣ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

6 ልባችንን ማዘጋጀት የምንችልበት አንዱ መንገድ ቅዱሳን መጻሕፍትንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት ማጥናት ነው። ራስህን በሚከተለው ሁኔታ ውስጥ ለማስቀመጥ ሞክር። በዚህ ምሽት የግል ጥናት የማድረግ ፕሮግራም አለህ እንበል። ከይሖዋ ቃል የተማርከውን ነገር በሥራ ለማዋል የአምላክ መንፈስ እንዲረዳህ ጸልየሃል። በቀጣዩ ቀን በቴሌቪዥን የሚተላለፍ አንድ ፊልም ለማየት አስበሃል። ይህ ፊልም ጥሩ እንደሆነ ሲወራ ብትሰማም በፊልሙ ላይ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ዓመፅና የሥነ ምግባር ብልግና እንደሚታይ ታውቅ ይሆናል።

7 በኤፌሶን 5:3 ላይ የሚገኘው ጳውሎስ የሰጠው የሚከተለው ምክር ወደ አእምሮህ ይመጣል፦ “ለቅዱሳን የማይገባ ስለሆነ ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።” ከዚህም በተጨማሪ በፊልጵስዩስ 4:8 (አንብብ።) ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር ታስታውሳለህ። በመንፈስ መሪነት በተጻፉት በእነዚህ ምክሮች ላይ በምታሰላስልበት ጊዜ ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ትጠይቃለህ፦ ‘ይህን ፕሮግራም መመልከት አደጋ እንዳለው እያወቅሁ አእምሮዬንና ልቤን ለመጥፎ ነገር የማጋልጥ ከሆነ ኢየሱስ አምላክን ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ረገድ የተወውን ምሳሌ እየተከተልኩ ነው ማለት ይቻላል?’ ምን ውሳኔ ታደርጋለህ? ይህንን ሁሉ ካሰብክም በኋላ ፊልሙን ለማየት ትወስናለህ?

8. ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አቋማችንን ላለማላላት መጠንቀቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

8 ብልግናና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን መዝናኛዎች ጨምሮ ክፉ ባልንጀርነት የሚያስከትለውን መጥፎ ተጽዕኖ መቋቋም እንደምንችል በማሰብ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ አቋማችንን ማላላት ስህተት ነው። ከዚህ ይልቅ የሰይጣን መንፈስ ከሚንጸባረቅባቸው እንዲህ ካሉ በካይ ተጽዕኖዎች ራሳችንንም ሆነ ልጆቻችንን መጠበቅ ይኖርብናል። በኮምፒውተር የሚጠቀሙ ሰዎች ቫይረሶች ወደ ኮምፒውተራቸው እንዳይገቡ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ቫይረሶች ወደ ኮምፒውተራቸው ከገቡ በውስጡ ያለውን መረጃ ሊያጠፉ፣ ኮምፒውተራቸው በደንብ እንዳይሠራ ሊያደርጉ አልፎ ተርፎም ኮምፒውተሩን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠሩና በዚህ ኮምፒውተር በመጠቀም ሌሎች ኮምፒውተሮችንም ጭምር ሊበክሉ ይችላሉ። ታዲያ እኛስ ከሰይጣን “መሠሪ ዘዴዎች” ራሳችንን ለመጠበቅ ከዚህ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አይገባንም?—ኤፌ. 6:11

9. በየዕለቱ ይሖዋን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

9 በየዕለቱ ማለት ይችላል፣ ነገሮችን ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ መምረጥ ይኖርብናል። መዳን ለማግኘት አምላክን መታዘዝና ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር ተስማምተን መኖር ይገባናል። የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል “እስከ ሞት ድረስ” እንኳ ታዛዥ በመሆን ትክክለኛ እምነት እንዳለን እናሳያለን። በታማኝነት ጎዳና ላይ ለመመላለስ በመምረጣችን ይሖዋ ወሮታ ይከፍለናል። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የጸና ግን እሱ ይድናል” በማለት ቃል ገብቷል። (ማቴ. 24:13) በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው እስከ መጨረሻው ለመጽናት ኢየሱስ ያሳየው ዓይነት ትክክለኛ ድፍረት ሊኖረን ይገባል።—መዝ. 31:24

ኢየሱስ—ድፍረት በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ

10. ምን ዓይነት ተጽዕኖዎች ሊደርሱብን ይችላሉ? እኛስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 የዚህን ዓለም አመለካከትና ዝንባሌ በሚያንጸባርቁ ሰዎች የተከበብን እንደመሆናችን መጠን በዚህ ላለመበከል ድፍረት ማሳየት ያስፈልገናል። ክርስቲያኖች፣ የይሖዋን የጽድቅ ጎዳና ከመከተል ዘወር እንዲሉ ሊያደርጉ የሚችሉ ከሥነ ምግባር፣ ከማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ከገንዘብና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ተጽዕኖዎች ይደርሱባቸዋል። ሌሎች በርካታ ክርስቲያኖች ደግሞ የቤተሰብ ተቃውሞ ያጋጥማቸዋል። በአንዳንድ አገሮች የትምህርት ተቋማት የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያስፋፉ ከመሆኑም በላይ አምላክ የለም የሚለው አመለካከት በዓለም ላይ ይበልጥ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። እንዲህ ዓይነት ተጽዕኖዎች ሲደርሱብን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም። እነዚህን ተጽዕኖዎች ለመቋቋምና ራሳችንን ከአደጋ ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ እንዴት ሊሳካልን እንደሚችል ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

11. ኢየሱስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ይበልጥ ድፍረት እንድናገኝ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሏቸው ነበር። (ዮሐ. 16:33) ኢየሱስ ለዓለም ተጽዕኖ ፈጽሞ አልተሸነፈም። የተሰጠውን የስብከት ተልእኮ ከመፈጸም ዓለም እንዲያግደው አልፈቀደም፤ እንዲሁም በዓለም ተጽዕኖ ተሸንፎ ከእውነተኛው አምልኮና ከትክክለኛው የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር በተያያዘ ያለውን የአቋም ደረጃ ዝቅ አላደረገም። እኛም የእሱን ምሳሌ ልንከተል ይገባል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” ብሏል። (ዮሐ. 17:16) ድፍረት በማሳየት ረገድ ክርስቶስ ያሳየውን ምሳሌ ማጥናታችንና በዚያ ላይ ማሰላሰላችን ከዓለም የተለየን ሆነን ለመኖር የሚያስፈልገንን ድፍረት እንድናገኝ ይረዳናል።

ድፍረት ማሳየትን ከኢየሱስ ተማሩ

12-14. ኢየሱስ ደፋር እንደነበረ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።

12 ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ ታላቅ ድፍረት አሳይቷል። የአምላክ ልጅ በመሆኑ ያለውን ሥልጣን በመጠቀም በድፍረት “ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ [አስወጥቷል]፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም [ገለባብጧል]።” (ማቴ. 21:12) ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር ላይ ባሳለፈው በመጨረሻው ምሽት ወታደሮች ሊያስሩት በመጡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል ከመካከላቸው በድፍረት በመውጣት “የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” ብሏል። (ዮሐ. 18:8) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሰይፉን ወደ ሰገባው እንዲመልሰው ለጴጥሮስ ነግሮታል፤ ይህም ኢየሱስ የሚተማመነው በይሖዋ እንጂ በሰው ሠራሽ መሣሪያ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።—ዮሐ. 18:11

13 ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ለሰዎች ፍቅር ያልነበራቸው ሐሰተኛ አስተማሪዎችም ሆነ ስህተት የሆነውን ትምህርታቸውን ያላንዳች ፍርሃት አጋልጧል። ኢየሱስ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፤ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ!” ብሏቸዋል። በተጨማሪም እንዲህ በማለት አውግዟቸዋል፦ “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ ትላላችሁ። . . . ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጡ ግን ቅሚያና ስግብግብነት የሞላበት ነው።” (ማቴ. 23:13, 23, 25) ሐሰተኛ የሆኑ የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ስለሚያሳድዷቸውና አንዳንዶቹንም ስለሚገድሏቸው ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስ ዓይነት ድፍረት ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው።—ማቴ. 23:34፤ 24:9

14 ኢየሱስ አጋንንትን እንኳ በድፍረት ተቃውሟል። በአንድ ወቅት አጋንንት ያደሩበትና በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ማንም በሰንሰለት ሊያስረው ያልቻለ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጣ። ኢየሱስ ሰውየውን ተቆጣጥረውት የነበሩትን በርካታ አጋንንት ያላንዳች ፍርሃት አስወጣቸው። (ማር. 5:1-13) በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ተአምራት እንዲፈጽሙ አምላክ ኃይል አልሰጣቸውም። ያም ቢሆን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ አማካኝነት እኛም ‘የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ ባሳወረው’ በሰይጣን ላይ መንፈሳዊ ጦርነት ማካሄድ አለብን። (2 ቆሮ. 4:4) እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም “የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም፤” ይሁን እንጂ እንደ ምሽግ ያሉ ሥር የሰደዱ የተሳሳቱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን “ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው።” (2 ቆሮ. 10:4) እነዚህን መንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች በመጠቀም ረገድ ከኢየሱስ ምሳሌ ብዙ መማር እንችላለን።

15. የኢየሱስ ድፍረት በምን ላይ የተመሠረተ ነበር?

15 የኢየሱስ ድፍረት ጀብደኝነት የሚንጸባረቅበት ሳይሆን በእምነት ላይ የተመሠረተ ነበር። የእኛም ድፍረት በእምነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። (ማር. 4:40) ትክክለኛ እምነት እንዲኖረን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድም ቢሆን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ኢየሱስ የቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቅ እውቀት የነበረው ከመሆኑም በላይ በአምላክ ቃል ላይ ሙሉ እምነት ነበረው። ኢየሱስ ቃል በቃል ሰይፍ ባይመዝም እንደ መሣሪያ የተጠቀመው የመንፈስን ሰይፍ ማለትም የአምላክን ቃል ነበር። በተደጋጋሚ ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ ለትምህርቱ ድጋፍ ያቀርብ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ አንድ ነገር ሲናገር የአምላክን ቃል በመጥቀስ “ተብሎ ተጽፏል” በማለት ይናገር ነበር። *

16. እምነታችን እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በመሆናችን የሚመጣብንን መከራ ለመቋቋም የሚያስችለንን እምነት ለመገንባት፣ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና በማጥናት እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ለእምነታችን መሠረት የሚሆነውን እውነት ወደ አእምሯችን ማስገባት ያስፈልገናል። (ሮም 10:17) ከዚህም በተጨማሪ በተማርነው ነገር ላይ በጥልቀት በማሰላሰል ትምህርቱ ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ ማድረግ ይኖርብናል። ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ለመውሰድ የምንችለው እምነታችን ሕያው ከሆነ ብቻ ነው። (ያዕ. 2:17) ከዚህም ሌላ እምነት የመንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ በመሆኑ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ አለብን።—ገላ. 5:22

17, 18. አንዲት ወጣት እህት በትምህርት ቤት ድፍረት ያሳየችው እንዴት ነው?

17 ኪቲ የተባለች አንዲት እህት፣ ትክክለኛ የሆነ እምነት ድፍረት የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ በሕይወቷ ካጋጠማት ሁኔታ ተመልክታለች። ይህች ወጣት በትምህርት ቤት ‘በምሥራቹ ማፈር’ እንደሌለባት ከልጅነቷ ጀምሮ ትገነዘብ የነበረ ከመሆኑም ሌላ አብረዋት ለሚማሩት ልጆች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት ከልቧ ትፈልግ ነበር። (ሮም 1:16) ምሥራቹን ለሌሎች ለመስበክ በየዓመቱ ቁርጥ ውሳኔ ብታደርግም ድፍረት በማጣቷ ይህን ከማድረግ ወደኋላ ትል ነበር። ኪቲ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ስትጠጋ ሌላ ትምህርት ቤት ገባች። በዚህ ወቅት “ከዚህ በፊት ሳልጠቀምባቸው ያለፉት አጋጣሚዎች አሁን ሊያመልጡኝ አይገባም” ብላ አሰበች። ኪቲ የክርስቶስ ዓይነት ድፍረትና ማስተዋል እንዲሰጣት እንዲሁም ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ እንድታገኝ እንዲረዳት ወደ ይሖዋ ጸለየች።

18 ትምህርት በተጀመረበት ዕለት ተማሪዎቹ አንድ በአንድ ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ተጠየቁ። በርካታ ተማሪዎች ሃይማኖታቸውን ከተናገሩ በኋላ እምነታቸውን በቁም ነገር እንደማይዙት ገለጹ። ኪቲ፣ ለመመሥከር የሚያስችል አጋጣሚ እንዲሰጣት ወደ ይሖዋ ያቀረበችው ጸሎት መልስ ይህ እንደሆነ ተገነዘበች። የእሷ ተራ ሲደርስ “እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ፤ በመንፈሳዊም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ጉዳዮች ረገድ መመሪያ የሚሆነኝ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት በድፍረት ተናገረች። ንግግሯን ስትቀጥል አንዳንዶቹ ተማሪዎች እንዳልተደሰቱ በፊታቸው ላይ ይታይ ነበር። ይሁን እንጂ ሌሎቹ በትኩረት ያዳመጧት ከመሆኑም ሌላ በኋላ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አቀረቡላት። እንዲያውም መምህሯ፣ ኪቲ ለእምነቷ ጥብቅና በመቆም ረገድ ጥሩ ምሳሌ እንደምትሆን ገለጸ። ኪቲ የኢየሱስን የድፍረት ምሳሌ በመከተሏ በጣም ተደሰተች።

የክርስቶስ ዓይነት እምነትና ድፍረት አሳዩ

19. (ሀ) ትክክለኛ የሆነ እምነት ማዳበር ምንን ይጨምራል? (ለ) ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

19 ሐዋርያትም ድፍረት የተሞላበት እርምጃ እንዲወስዱ የሚያነሳሳቸው እምነት ሊሆን እንደሚገባ ተገንዝበው ነበር። ኢየሱስን “እምነት ጨምርልን” በማለት ለምነውታል። (ሉቃስ 17:5, 6ን አንብብ።) ትክክለኛ እምነት ለማዳበር አምላክ እንዳለ ከማመን የበለጠ ነገር ያስፈልገናል። አንድ ትንሽ ልጅ ደግና አፍቃሪ ከሆነው አባቱ ጋር ያለው ዓይነት የጠበቀ ወዳጅነት ከይሖዋ ጋር መመሥረት ይኖርብናል። ሰለሞን በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ልጄ ሆይ፤ ልብህ ጠቢብ ቢሆን፣ የእኔም ልብ ሐሤት ያደርጋል፤ ከንፈሮችህ ትክክሉን ቢናገሩ፣ ውስጣዊ ሁለንተናዬ ሐሤት ያደርጋል።” (ምሳሌ 23:15, 16) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መልኩ እኛም የጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በድፍረት ማክበራችን ይሖዋን ያስደስተዋል፤ ይህንን ማወቃችን ደግሞ ድፍረት ይጨምርልናል። እንግዲያው ጽድቅን በመከተል ረገድ ድፍረት የተሞላበት አቋም በመውሰድ ምንጊዜም የኢየሱስን ምሳሌ እንከተል!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ለምሳሌ ያህል፣ በ⁠ማቴዎስ 4:4, 7, 10፤ 11:10፤ 21:13፤ 26:31፤ በ⁠ማርቆስ 9:13፤ 14:27፤ በ⁠ሉቃስ 24:46፤ በ⁠ዮሐንስ 6:45፤ 8:17 ላይ የሚገኙትን ሐሳቦች ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ብንሆንም ታዛዦች ሆነን ለመኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

• ትክክለኛ የሆነ እምነት በምን ላይ የተመሠረተ ነው? እንዲህ ያለው እምነት ደፋሮች እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

• ታዛዦች መሆናችንና የክርስቶስ ዓይነት ድፍረት ማሳየታችን ምን ውጤት ያስገኛል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈተናዎችን ለመቋቋም እንድትችል ‘ልብህን እያዘጋጀህ’ ነው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም በእምነት ላይ የተመሠረተ ድፍረት ማሳየት እንችላለን