በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለኮታዊ ትምህርት ያለው የላቀ ዋጋ

መለኮታዊ ትምህርት ያለው የላቀ ዋጋ

መለኮታዊ ትምህርት ያለው የላቀ ዋጋ

“ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት የተነሳ ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ።”—ፊልጵ. 3:8

1, 2. አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ መርጠዋል? ለምንስ?

ሮበርት ከልጅነቱ ጀምሮ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበር። ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ከአስተማሪዎቹ አንዷ ወደ ቤቱ በመሄድ ባለው ችሎታ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል ገለጸችለት። ሲያድግ ሐኪም እንዲሆን ምኞቷ እንደሆነ ተናገረች። ሮበርት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባጠናቀቀበት ወቅት ያገኘው ውጤት በአገሪቱ ታዋቂ ከሆኑት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በፈለገው ውስጥ ገብቶ ለመማር የሚያስችለው ነበር። ይሁን እንጂ ሮበርት የዘወትር አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ሲል ብዙዎች በሕይወት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ሊገኝ የሚችል እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩትን ይህን አጋጣሚ ለመተው መርጧል።

2 እንደ ሮበርት ሁሉ ወጣትም ሆነ አዋቂ የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያስችል አጋጣሚ ይቀርብላቸዋል። አንዳንዶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ሲሉ በእነዚህ አጋጣሚዎች ሙሉ በሙሉ ላለመጠቀም መርጠዋል። (1 ቆሮ. 7:29-31) እንደ ሮበርት ያሉ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ በትጋት እንዲካፈሉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር ቢሆንም መለኮታዊ ትምህርት ያለውን የላቀ ዋጋ መገንዘባቸውም ይህንን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። እውነትን ባታውቅ ኖሮ ሕይወትህ ምን ሊመስል እንደሚችል በቅርብ ጊዜ ውስጥ አስበህ ታውቃለህ? ከይሖዋ በመማራችን ካገኘናቸው የላቁ ጥቅሞች መካከል በአንዳንዶቹ ላይ ማሰላሰላችን ምንጊዜም ለምሥራቹ አድናቆት እንዲኖረን እንዲሁም ይህንን የምሥራች ለሌሎች በቅንዓት እንድንሰብክ ይረዳናል።

ከአምላክ የተማሩ መሆን ታላቅ መብት ነው

3. ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ለማስተማር ፈቃደኛ እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

3 ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸውን የሰው ልጆች ለማስተማር ፈቃደኛ በመሆን ጥሩነቱን አሳይቷል። ቅቡዓን ክርስቲያኖችን በተመለከተ በ⁠ኢሳይያስ 54:13 ላይ “ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል” የሚል ትንቢት ተናግሯል። ይህ ጥቅስ በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ ለክርስቶስ ‘ሌሎች በጎችም’ ይሠራል። (ዮሐ. 10:16) በዘመናችን እየተፈጸመ ያለ አንድ ትንቢት ይህንን በግልጽ ያሳያል። ኢሳይያስ ከሕዝቦች ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ ሲጎርፉ በራእይ ተመልክቷል። እነዚህ ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲህ በማለት እንደሚነጋገሩ ገልጿል፦ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱ መንገዱን ያስተምረናል፤ በጐዳናውም እንሄዳለን።” (ኢሳ. 2:1-3) ከአምላክ የተማሩ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

4. ከይሖዋ ለመማር የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው?

4 ከመለኮታዊ ትምህርት ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ዋነኛው ብቃት ትሑትና ለመማር ፈቃደኛ መሆን ነው። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤ . . . ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 25:8, 9) ኢየሱስም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለገለጥክላቸው በሕዝብ ፊት አወድስሃለሁ።” (ሉቃስ 10:21) አምላክ ‘ለትሑታን ጸጋን እንደሚሰጥ’ ማወቅህ ወደ እሱ ለመቅረብ አይገፋፋህም?—1 ጴጥ. 5:5

5. አምላክን ማወቅ እንድንችል የረዳን ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው?

5 እውነትን አውቀን የይሖዋ አገልጋዮች መሆን የቻልነው በራሳችን ችሎታ ወይም ጥበብ ነው ማለት እንችላለን? አንችልም። እንዲያውም በራሳችን ቢሆን ኖሮ ፈጽሞ አምላክን ማወቅ አንችልም ነበር። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም” ብሏል። (ዮሐ. 6:44) ይሖዋ ‘የሕዝቦች ሀብት ሁሉ’ የተባሉትን በግ መሰል ሰዎች በስብከቱ ሥራና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እየሳባቸው ነው። (ሐጌ 2:7) ይሖዋ፣ ወደ ልጁ ከሳባቸው መካከል መሆንህ አመስጋኝ እንድትሆን አያነሳሳህም?—ኤርምያስ 9:23, 24ን አንብብ።

የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል አለው

6. ሰዎች የአምላክን እውቀት መቅሰማቸው ምን አስገራሚ ውጤት አስገኝቷል?

6 የኢሳይያስ ትንቢት በጣም ግሩም የሆነ ምሳሌያዊ አገላለጽ በመጠቀም በዘመናችን ሰዎች የሚያደርጉትን የባሕርይ ለውጥ ገልጿል። ቀደም ሲል ዓመፀኛ የነበሩ ሰዎች ሰላማውያን ሆነዋል። (ኢሳይያስ 11:6-9ን አንብብ።) የተለያየ ዜግነት፣ ዘር ወይም ጎሳ ስላላቸው አሊያም በሌሎች የባሕል ልዩነቶች የተነሳ ከዚህ ቀደም እርስ በርስ ይጠላሉ የነበሩ ሰዎች በአንድነት አብረው መኖርን ተምረዋል። እነዚህ ሰዎች በምሳሌያዊ አገላለጽ ‘ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ አድርገዋል።’ (ኢሳ. 2:4) እንዲህ ዓይነት አስገራሚ ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? የአምላክን እውቀት መቅሰማቸውና የተማሩትን በሕይወታቸው ተግባራዊ ማድረጋቸው ነው። የአምላክ አገልጋዮች ፍጽምና የጎደላቸው ቢሆኑም እውነተኛ የሆነ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት ፈጥረዋል። ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት ማግኘቱና መልካም ፍሬ ማፍራቱ መለኮታዊ ትምህርት የላቀ ዋጋ እንዳለው ይመሠክራል።—ማቴ. 11:19

7, 8. (ሀ) መለኮታዊ ትምህርት “ምሽግ” ተብለው ከተገለጹት ነገሮች መካከል የትኞቹን እንዲያፈርሱ ሰዎችን ረድቷቸዋል? (ለ) መለኮታዊ ትምህርት ለይሖዋ ውዳሴ እንደሚያመጣ የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

7 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የአምላክ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ከመንፈሳዊ ጦርነት ጋር አመሳስሎታል። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው። የአምላክን እውቀት የሚጻረሩ የመከራከሪያ ነጥቦችንና ይህን እውቀት ለማገድ የሚገነባውን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን።” (2 ቆሮ. 10:4, 5) መለኮታዊ ትምህርት እንደ “ምሽግ” ተደርገው ከተገለጹት ከየትኞቹ ነገሮች ሰዎችን ነፃ አውጥቷቸዋል? በሰዎች ላይ ሸክም የሆኑት የሐሰት ትምህርቶች፣ አጉል እምነቶችና ሰብዓዊ ፍልስፍናዎች ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። (ቆላ. 2:8) መለኮታዊ ትምህርት ሰዎች መጥፎ ልማዶችን እንዲያሸንፉና አምላካዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። (1 ቆሮ. 6:9-11) የቤተሰብ ሕይወት የተሻለ እንዲሆን ያደርጋል። ተስፋ አጥተው የነበሩ ሰዎች ሕይወታቸው እውነተኛ ዓላማ ያለው እንዲሆን ይረዳል። በዛሬው ጊዜ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው እንዲህ ዓይነት ትምህርት ነው።

8 አምላክ ሕዝቦቹ እንዲያዳብሩ ከሚረዳቸው ባሕርያት አንዱ ሐቀኝነት ነው፤ የሚከተለው ተሞክሮ ይህንን ያሳያል። (ዕብ. 13:18) በሕንድ የምትኖር አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን ከጊዜ በኋላ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። አንድ ቀን በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ስትካፈል ቆይታ ወደ ቤቷ ስትመለስ ስምንት መቶ የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የወርቅ ጌጥ በአውቶቡስ ተራ አካባቢ ወድቆ አገኘች። ይህች ሴት ኑሮዋ ዝቅተኛ ቢሆንም ወርቁን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስዳ አስረከበች። እዚያ የነበረው ፖሊስ ሴትየዋ ያደረገችውን ነገር ማመን አልቻለም! ቆየት ብሎም ሌላ ፖሊስ “ወርቁን ለማስረከብ የወሰንሽው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቃት። እሷም “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ባሕርዬን እንድለውጥ ረድቶኛል፤ አሁን ሐቀኛ ሰው ሆኛለሁ” በማለት መለሰችለት። ፖሊሱ በዚህ በመገረም አብሯት ወደ ፖሊስ ጣቢያው ለሄደው የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ አለው፦ “በዚህ ግዛት ውስጥ ከ38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። አሥር ሰዎች እንደዚህች ሴት እንዲለወጡ መርዳት ከቻላችሁ ትልቅ ነገር አከናወናችሁ ማለት ነው።” ታዲያ መለኮታዊው ትምህርት ሕይወታቸው የተሻለ እንዲሆን የረዳቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳሉ ማወቃችን ይሖዋን ይበልጥ ለማወደስ አያነሳሳንም?

9. ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው ምንድን ነው?

9 ሰዎችን የመለወጥ ኃይል ያለው የአምላክ ቃል እንዲሁም ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የሚሰጠው እርዳታ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። (ሮም 12:2፤ ገላ. 5:22, 23) ቆላስይስ 3:10 እንዲህ ይላል፦ “ከፈጣሪው አምሳል ጋር በሚስማማ ሁኔታ በትክክለኛ እውቀት አማካኝነት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ስብዕና ልበሱ።” የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት፣ የአንድ ሰው ውስጣዊ ማንነት ግልጽ ሆኖ እንዲታይ የማድረግ ኃይል ያለው ከመሆኑም ሌላ የግለሰቡን አስተሳሰብና ሌላው ቀርቶ ለነገሮች ያለውን ስሜት እንኳ መቀየር ይችላል። (ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።) አንድ ሰው ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ እውቀት በመቅሰምና ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ በመኖር የአምላክ ወዳጅ መሆን እንዲሁም ለዘላለም የመኖር ተስፋ ማግኘት ይችላል።

ለወደፊቱ ጊዜ ያዘጋጀናል

10. (ሀ) ለወደፊቱ ጊዜ እንድንዘጋጅ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በቅርቡ በመላው ዓለም ላይ ምን ከፍተኛ ለውጥ ይከናወናል?

10 ለወደፊቱ ጊዜ እንድንዘጋጅ ሊረዳን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም ወደፊት ምን እንደሚመጣ የሚያውቀው እሱ ነው። የሰው ዘር የወደፊት ሕይወት ምን እንደሚሆን የሚወስነው ይሖዋ ነው። (ኢሳ. 46:9, 10) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ” እንደሆነ ይገልጻል። (ሶፎ. 1:14) “በቍጣ ቀን ሀብት ፋይዳ የለውም፤ ጽድቅ ግን ከሞት ትታደጋለች” የሚለው በ⁠ምሳሌ 11:4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነተኝነት በዚያ ቀን ይታያል። ይሖዋ በሰይጣን ዓለም ላይ የሚፈርድበት ጊዜ ሲመጣ ትልቅ ቦታ የሚኖረው የአምላክን ሞገስ ማግኘታችን ነው። በዚያን ጊዜ ገንዘብ ምንም ዋጋ አይኖረውም። እንዲያውም ሕዝቅኤል 7:19 “ብራቸውን በየጐዳናው ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም እንደ ርኵስ ነገር ይቈጠራል” ይላል። ይህንን አስቀድመን ማወቃችን በአሁኑ ጊዜ የጥበብ እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል።

11. መለኮታዊ ትምህርት ለወደፊቱ ጊዜ እንድንዘጋጅ ከሚያደርግባቸው መንገዶች አንዱ የትኛው ነው?

11 መለኮታዊ ትምህርት ከፊታችን ላለው የይሖዋ ቀን እንድንዘጋጅ ከሚያደርግባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ የሚረዳን መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፎለታል፦ “አሁን ባለው ሥርዓት ውስጥ ሀብታም የሆኑት ሰዎች፣ ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዳይመለከቱ እንዲሁም ተስፋቸውን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን . . . [በአምላክ] ላይ እንዲጥሉ እዘዛቸው።” ሀብታም ባንሆንም እንኳ በአምላክ መንፈስ መሪነት ከተጻፈው ከዚህ ምክር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ይህን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ምን ማድረግ ይኖርብናል? ቁሳዊ ንብረት ለማከማቸት ከመሞከር ይልቅ ‘መልካም ነገር ለማድረግና በመልካም ሥራዎች ባለጸጋ ለመሆን’ መጣር ይኖርብናል። በሕይወታችን ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ‘ለራሳችን ውድ ሀብት ማከማቸት ይኸውም ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆን መልካም መሠረት መጣል’ እንችላለን። (1 ጢሞ. 6:17-19) የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ እንዲህ ዓይነት አካሄድ መከተላችን አስተዋዮች እንደሆንን ይጠቁማል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንደተናገረው “አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” (ማቴ. 16:26, 27) የይሖዋ ቀን በጣም ቅርብ ከመሆኑ አንጻር እያንዳንዳችን ‘ሀብት የማከማቸው የት ነው? ባሪያ የሆንኩት ለአምላክ ነው ወይስ ለሀብት?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።—ማቴ. 6:19, 20, 24

12. አንዳንዶች አገልግሎታችንን ቢያቃልሉብንም ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብን ለምንድን ነው?

12 በአምላክ ቃል ውስጥ ለክርስቲያኖች ከተሰጧቸው “መልካም ሥራዎች” መካከል ትልቁን ቦታ የሚይዘው ሕይወት አድን የሆነው የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም አንዳንድ ሰዎች አገልግሎታችንን ያቃልሉት ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 1:18-21ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ የመልእክቱን ክብደት ዝቅ አያደርገውም፤ እንዲሁም ጊዜው ከማብቃቱ በፊት እያንዳንዱ ሰው በምሥራቹ ላይ እምነት እንዲያሳድር አጋጣሚ የመስጠቱን አስፈላጊነት አይቀንሰውም። (ሮም 10:13, 14) ሰዎች ከመለኮታዊው ትምህርት እንዲጠቀሙ ስንረዳቸው እኛም ብዙ በረከቶች እናገኛለን።

መሥዋዕት በመክፈላቸው ተባርከዋል

13. ሐዋርያው ጳውሎስ ለምሥራቹ ሲል ምን ዓይነት መሥዋዕትነት ከፍሎ ነበር?

13 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በአይሁድ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ለመድረስ እየሠለጠነ ነበር። የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ እያለ ሳይሆን አይቀርም በዚያን ጊዜ ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጠውና የሕግ አስተማሪ ከሆነው ከገማልያል ለመማር የትውልድ ከተማው የሆነችውን ጠርሴስን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። (ሥራ 22:3) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ጳውሎስ ከእኩዮቹ ልቆ መታየት የጀመረ ሲሆን በያዘው ጎዳና ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ በአይሁድ እምነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊኖረው ይችል ነበር። (ገላ. 1:13, 14) ሆኖም ጳውሎስ ምሥራቹን ተቀብሎ የስብከቱን ሥራ ሲጀምር ያንን ሁሉ ተወው። ባደረገው ውሳኔ ተጸጽቶ ይሆን? በፍጹም። እንዲያውም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት የተነሳ ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ። ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ።”—ፊልጵ. 3:8

14, 15. “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” በመሆናችን ምን በረከቶች እናገኛለን?

14 እንደ ጳውሎስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ለምሥራቹ ሲሉ መሥዋዕትነት ይከፍላሉ። (ማር. 10:29, 30) እንዲህ በማድረጋችን የሚቀርብን ነገር አለ? በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደስታና እርካታ ያስገኘልኝ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ‘ቸር መሆኑን ቀምሼ ለማየት’ አስችሎኛል። መንፈሳዊ ግቦችን ለማስቀደም ስል ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት ሳደርግ ምንጊዜም ይሖዋ ከተውኩት የበለጠ በመስጠት ይባርከኛል። ምንም ነገር መሥዋዕት ያላደረግሁ ያህል ነው። እንዲያውም የበለጠ አግኝቻለሁ!” ሌሎች ብዙዎችም የሮበርትን ስሜት ይጋራሉ።—መዝ. 34:8፤ ምሳሌ 10:22

15 አንተም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ እየተካፈልክ ከሆነ ይሖዋ ቸር መሆኑን ቀምሰህ ለማየት የሚያስችሉህ አጋጣሚዎች እንዳገኘህ ምንም ጥርጥር የለውም። ምሥራቹን በምትሰብክበት ጊዜ የአምላክን መንፈስ እርዳታ እንዳገኘህ ሆኖ የተሰማህ ጊዜ አለ? ሰዎች ለመልእክቱ ትኩረት እንዲሰጡ ይሖዋ ልባቸውን ሲከፍትላቸው ፊታቸው በደስታ ሲያበራ ተመልክተህ ታውቃለህ? (ሥራ 16:14) ይሖዋ የተለያዩ እንቅፋቶችን እንድትወጣ ምናልባትም አገልግሎትህን ለማስፋት የሚያስችል አጋጣሚ እንድታገኝ ረድቶሃል? ኃይልህ እንደተሟጠጠ በተሰማህ ጊዜ እሱን ማገልገልህን እንድትቀጥል በመርዳት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንድትቋቋም አግዞሃል? (ፊልጵ. 4:13) አገልግሎታችንን በምናከናውንበት ወቅት የይሖዋን እርዳታ በግለሰብ ደረጃ ስናገኝ ይሖዋ የበለጠ እውን ይሆንልናል፤ እንዲሁም ወደ እሱ ይበልጥ እንደቀረብን ይሰማናል። (ኢሳ. 41:10) ታላቅ በሆነው መለኮታዊውን ትምህርት የማስተማር ሥራ “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን በረከት አይደለም?—1 ቆሮ. 3:9

16. ከመለኮታዊው ትምህርት ጋር በተያያዘ ስለምታደርገው ጥረትና ስለምትከፍለው መሥዋዕትነት ምን ይሰማሃል?

16 ብዙ ሰዎች ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ አንድ ነገር በሕይወታቸው ውስጥ ለማከናወን ይመኛሉ። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ በዓለም ላይ ታላቅ የሚባሉ ሥራዎች እንኳ ብዙም ሳይቆይ ሲረሱ ተመልክተናል። ይሖዋ ስሙን ከማስቀደስ ጋር በተያያዘ በዘመናችን እያከናወናቸው ያሉት ሥራዎች ግን በአምላክ ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ምንጊዜም እንደማይረሱ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ሥራዎች ለዘላለም ይታወሳሉ። (ምሳሌ 10:7፤ ዕብ. 6:10) መለኮታዊውን ትምህርት ለሌሎች በማስተማሩ ታሪካዊ ሥራ የመካፈል መብታችንን ከፍ አድርገን እንመልከተው።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ከይሖዋ ለመማር የሚያስፈልገው ብቃት ምንድን ነው?

• መለኮታዊው ትምህርት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

• ሰዎች ከመለኮታዊው ትምህርት እንዲጠቀሙ ስንረዳቸው እኛም በረከት የምናገኘው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከይሖዋ የተማሩ ሰዎች እውነተኛ የሆነ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ኅብረት ፈጥረዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን በረከት አይደለም?