በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ማስገር

በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ማስገር

በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ ማስገር

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ በማጥመድ የሚተዳደሩ ሰዎች ኑሯቸው ምን ይመስል ነበር? የዚህ ጥያቄ መልስ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ያሉ በርካታ የወንጌል ዘገባዎችን እንድንረዳ ያስችለናል።

በመሠረቱ ይህ “ባሕር” ወደ 21 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመትና 12 ኪሎ ሜትር የሚያህል ስፋት ያለው ጨው አልባ ሐይቅ ነው። ዓሣ አስጋሪዎች ለረጅም ዘመናት ከዚህ ሐይቅ ላይ በጣም ብዙ ዓሣ ሲያጠምዱ ኖረዋል። የኢየሩሳሌም የዓሣ በር የሚያመለክተው የዓሣ ግብይት የሚካሄድበትን ቦታ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ነህምያ 3:3) በዚህ ገበያ ላይ ከገሊላ ባሕር የሚጠመዱ ዓሦችም ይቀርቡ ነበር።

ሐዋርያው ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ላይ የምትገኘው የቤተሳይዳ ከተማ ሰው ነበር፤ ቤተሳይዳ “የዓሣ አጥማጁ ቤት” የሚል ትርጉም ሳይኖራት አይቀርም። በዚህ ሐይቅ ዳርቻ ላይ የምትገኘው ሌላዋ ከተማ ደግሞ መጌዶን ወይም መጌዶል ስትሆን ኢየሱስ በባሕሩ ላይ ከተራመደ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን ይዞ የሄደው ወደዚህች ከተማ ነበር። (ማቴዎስ 15:39) አንድ ጸሐፊ እንደተናገሩት ከሆነ ይህች ከተማ የምትጠራበት የግሪክኛ ስም “የዓሣ ማቀነባበሪያ ከተማ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። ይህች ከተማ ባሏት በርካታ የዓሣ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተለይታ ትታወቅ ነበር፤ እነዚህ ፋብሪካዎች ከባሕሩ የተጠመዱትን ዓሦች አድርቀው በጨው ካሹ ወይም ከዘፈዘፉ በኋላ የዓሣ ስጎ አዘጋጅተው በሸክላ ገንቦ ያሽጉታል። እነዚህ ምርቶች አንድ ላይ ከታሸጉ በኋላ ወደ ሁሉም የእስራኤል ከተሞች አልፎ ተርፎም ወደሌሎች ቦታዎች በመርከብ ይላካሉ።

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ዓሣ ማስገር፣ ማቀነባበርና ለገበያ ማቅረብ በገሊላ አውራጃ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ንግድ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ በርካታ ሰዎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል መገመት አያዳግትም። እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። የዓሣ ንግድ “በዘመናችን አዲስ ኪዳንን የሚያነቡ ሰዎች ሊገምቱ እንደሚችሉት ‘ነፃ ገበያ’ አልነበረም” በማለት አንድ ምሑር ተናግረዋል። ከዚህ ይልቅ “በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ከነበሩና በጥቂት ሀብታሞች ከተያዙ አትራፊ ድርጅቶች” መካከል አንዱ ነበር።

ሄሮድስ አንቲጳስ፣ በሮም መንግሥት የተሾመ የገሊላ አውራጃ ወይም የአራተኛው ክፍል ገዥ ነበር። ስለሆነም በእሱ የግዛት ክልል ውስጥ የሚገኙትን መንገዶችና ወደቦች እንዲሁም እንደ ማዕድን፣ ደን፣ ግብርና እና ዓሣ ማስገር የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን ይቆጣጠር ነበር። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ለሄሮድስ ዋነኛ የቀረጥ መሰብሰቢያ ምንጭ ሆነውለት ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በገሊላ ይደረግ የነበረውን ቀረጥ የመሰብሰብ ፖሊሲ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ የለንም። ይሁንና ሄሮድስ ይከተለው የነበረው ፖሊሲ፣ የግሪክ ገዥዎች ወይም በስተ ምሥራቅ የሚገኙ ሌሎች አውራጃዎችን የሚያስተዳድሩ ሮማውያን ይከተሉት ከነበረው ፖሊሲ ብዙም እንደማይለይ መገመት እንችላለን። በአካባቢው ከሚደረጉት የንግድ እንቅስቃሴዎችና የተፈጥሮ ሀብትን በመጠቀም ከሚገኘው ትርፍ በአብዛኛው ተጠቃሚ የሚሆኑት ብዙውን ሥራ የሚያከናውኑት ተራ ሰዎች ሳይሆኑ ሀብታሞች ነበሩ።

ከፍተኛ ቀረጥ ይጫንባቸው ነበር

በኢየሱስ ዘመን በገሊላ የሚገኙ ምርጥ የሆኑ ቦታዎች በንጉሡ ይዞታ ሥር የነበሩ ሲሆን ሄሮድስ አንቲጳስ እነዚህን ቦታዎች ከፋፍሎ ለመኳንንቱና ለሌሎች ሰዎች በስጦታ መልክ ይሰጥ ነበር። ሄሮድስ ለሚመራው የተንደላቀቀ ኑሮና ለሚገነባቸው ትላልቅ ሕንፃዎች እንዲሁም ውስብስብ ለሆነው የአስተዳደር ሥርዓቱ የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነውም ሆነ ለወዳጆቹና ለሌሎች ከተሞች የሚሰጠው ድጎማ የሚገኘው በእሱ አገዛዝ ሥር ካሉ ሰዎች ከሚሰበሰበው ቀረጥ ነበር። በወቅቱ ተራው ሕዝብ ከአቅም በላይ የሆነ ግብርና ቀረጥ ይጫንበት እንደነበር ይነገራል።

በተጨማሪም ሄሮድስ በወቅቱ የነበረውን የዓሣ ንግድ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር። በመሆኑም ዓሣ የማስገሩ ንግድ፣ በሄሮድስ አሊያም እሱ በስጦታ መልክ ርስት በሰጣቸው ግለሰቦች የሚተዳደር ትልቅ ሥራ ነበር። ንጉሡ በቀጥታ በሚያስተዳድራቸው ቦታዎች ላይ ሥልጣን የተሰጣቸውና የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ተብለው የሚጠሩት ግለሰቦች፣ ለዓሣ አጥማጆች የሥራ ፈቃድ የመስጠት ሥልጣን አላቸው፤ እነዚህ ሀብታም ግለሰቦች ቀረጥ የመሰብሰብ መብት የሚያገኙት በጨረታ አሸንፈው ነው። ማቴዎስ ቀረጥ የሚሰበስብበት ቦታ የሚገኘው ለዓሣ ንግድ ቁልፍ ቦታ በሆነችው በቅፍርናሆም ስለነበር ማቴዎስ ለእነዚህ ቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቆች “በኮንትራት” የሚሠራ ሳይሆን እንደማይቀር አንዳንድ ተንታኞች ገልጸዋል። *

በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በፓለስቲና ምድር አብዛኛውን ጊዜ ቀረጥ የሚከፈለው በጥሬ ገንዘብ ሳይሆን “በዓይነት” ነበር። በመሆኑም ዓሣ በማስገር ሥራ የተሠማሩ አንዳንድ ሰዎች ካጠመዱት ዓሣ ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚያህለውን ላከራዩአቸው ግለሰቦች ይሰጡ ነበር። የጥንት መዛግብት እንደሚያሳዩት በሮም አገዛዝ ሥር ባሉ አንዳንድ ቦታዎች ዓሣ የማስገሩ ሥራ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበር፤ መንግሥት ሥራውን የሚያካሂደው ተቆጣጣሪዎችን በመሾም ነበር። በጵስድያ ማንም ሰው ዓሣ ያለ ፈቃድ እንዳያጠምድ የሚቆጣጠሩ ፖሊሶች የነበሩ ሲሆን ዓሣ መሸጥ የሚቻለው ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው ወይም ለጅምላ ነጋዴዎች ብቻ ነበር፤ እነዚህንም ነጋዴዎች የሚቆጣጠረው መንግሥት ሲሆን ቀረጥም ይከፍላሉ።

አንድ ተንታኝ እንደገለጸው ከሆነ ይህ ሁሉ ቁጥጥርና የሚሰበሰበው ቀረጥ “ለንጉሡ ወይም ለመሬቱ ባለንብረት ይህ ነው የማይባል ትርፍ ያስገኛል፤ ዓሣ አጥማጆቹ የሚያገኙት ገንዘብ ግን በጣም ጥቂት ነበር።” በተመሳሳይም በሌሎች የንግድ ዘርፎች የተሠማሩ ግለሰቦች ከአቅማቸው በላይ በሆነ ቀረጥ ምክንያት የሚያገኙት ትርፍ በጣም አናሳ ነው። ቀረጥ የሚከፍሉ ሰዎች ለቀረጥ ጥሩ አመለካከት ኖሯቸው አያውቅም። በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ እንደሚስተዋለው ሕዝቡ ለቀረጥ ሰብሳቢዎች ጥላቻ ሊያሳድር የቻለው፣ ታማኝነት የጎደላቸውና ስስታም የሆኑት እነዚህ ግለሰቦች የተቻላቸውን ያህል ተራውን ሕዝብ በመበዝበዝና በመቀማት ሀብት በማካበታቸው እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 3:13፤ 19:2, 8

በወንጌሎች ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ ዓሣ አስጋሪዎች

የወንጌል ዘገባዎች ስምዖን ጴጥሮስ ከሌሎች ጋር ሆኖ ዓሣ በማስገር ሥራ ይተዳደር እንደነበር ይናገራሉ። ጴጥሮስ በተአምር እጅግ ብዙ ዓሣ በያዘ ጊዜ ሊረዱት የመጡት ‘በሌላኛው ጀልባ ላይ ያሉ ባልደረቦቹ’ ነበሩ። (ሉቃስ 5:3-7) ምሑራን እንዳብራሩት ከሆነ “ዓሣ አጥማጆች ጨረታው ላይ ለመቅረብ ‘በማኅበር’ . . . መደራጀት ይችሉ ነበር።” ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ባልደረቦቻቸው የዓሣ ማጥመድ ንግዳቸውን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት በዚህ መንገድ ሳይደራጁ አልቀሩም።

በገሊላ ባሕር ላይ ዓሣ የሚያጠምዱት እነዚህ ሰዎች የሚጠቀሙበት ጀልባም ሆነ ቁሳቁስ የግል ንብረታቸው ይሁን አይሁን ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ አይናገሩም። አንዳንዶች እነዚህ ንብረቶች የዓሣ አስጋሪዎቹ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ኢየሱስ የተሳፈረባት ጀልባ ‘የስምዖን ነበረች።’ (ሉቃስ 5:3) በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን አንድ ርዕስ “በማኅበር የተደራጁ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ጀልባዎች የቀረጥ ሰብሳቢዎቹ አለቆች ንብረት ሊሆኑም ይችላሉ” ብሏል። ይህ አባባል ትክክል ሆነም አልሆነ ቅዱሳን መጻሕፍት ያዕቆብና ዮሐንስ መረባቸውን ሲጠግኑ እንደነበረ ይናገራሉ። በተጨማሪም ዓሣ አስጋሪዎች ያጠመዱትን ዓሣ ለመሸጥ መደራደር ምናልባትም የቀን ሠራተኞችን መቅጠር ያስፈልጋቸው ይሆናል።

በመሆኑም በአንደኛው መቶ ዘመን በገሊላ የሚኖሩ ዓሣ አስጋሪዎች መጀመሪያ ላይ ካሰብከው በላይ ብዙ ሥራ እንዳለባቸው ሳትረዳ አትቀርም። ሥራቸው ውስብስብ የሆነው የንግድ ሥርዓት አንዱ ክፍል ነበር። ይህን በአእምሯችን መያዛችን የወንጌል ዘገባዎችን ብሎም ኢየሱስ ዓሣ ስለማስገርና ስለ ዓሣ አጥማጆች የተናገራቸውን ሐሳቦች በጥልቅ እንድንረዳ ያስችለናል። ከዚህም በላይ ጴጥሮስ፣ እንድሪያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ምን ያህል ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው እንድንገነዘብ ያስችለናል። ዓሣ የማጥመድ ሥራ መተዳደሪያቸው ነበር። ኢየሱስ እነሱን በጠራቸው ጊዜ የነበራቸው የኢኮኖሚ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እነዚህ ሰዎች ቋሚ ሥራቸውን ያለምንም ማንገራገር ትተው “ሰዎችን አጥማጆች” ሆነዋል።—ማቴዎስ 4:19

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ከቤተሳይዳ ወደ ቅፍርናሆም እንደተዛወረ ግልጽ ነው፤ በዚያም ከወንድሙ ከእንድርያስና ከዘብዴዎስ ልጆች ጋር ሆኖ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ተሠማርቷል። ኢየሱስም ለተወሰነ ጊዜ በቅፍርናሆም ኖሮ ነበር።—ማቴዎስ 4:13-16

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የሁላ ሐይቅ

ቤተሳይዳ

ቅፍርናሆም

መጌዶን

የገሊላ ባሕር

ኢየሩሳሌም

የሙት ባሕር

[የሥዕል ምንጭ]

Todd Bolen/Bible Places.com

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Todd Bolen/Bible Places.com