በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳሳተ ትምህርት 6፦ አምላክ ሥዕሎችንና ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ይደግፋል

የተሳሳተ ትምህርት 6፦ አምላክ ሥዕሎችንና ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን ይደግፋል

ይህ የተሳሳተ ትምህርት የመነጨው ከየት ነው?

“በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም አይታወቅም ነበር። . . . ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የጀመረው በ4ኛው እና በ5ኛው መቶ ዘመን ሲሆን ለዚህ እንደ ምክንያት የሚቀርበው ላልተማሩ ሰዎች ስለ ክርስትና ለማስተማር በስብከት ወይም በመጻሕፍት ከመጠቀም ይልቅ በምስል መጠቀም የተሻለ ነው የሚለው ሐሳብ ነው።”—በማክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለዚያስቲካል ሊትሬቸር ጥራዝ 4፣ ገጽ 503 እና 504

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ነገሮች በማናቸውም ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። አትስገድላቸው፤ አታምልካቸውም።” (ዘፀአት 20:4, 5) ሐዋርያው ዮሐንስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች “ልጆቼ ሆይ፣ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ” በማለት ጽፎላቸዋል።—1 ዮሐንስ 5:21

አብያተ ክርስቲያናት እንደሚሉት ምስሎች የሚወክሉትን አካል ለማክበርና ወደዚህ አካል ለመቅረብ ከመርዳት ያለፈ ትርጉም የላቸውም ማለት ይቻላል? ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን እንዲህ ይላል፦ “መጀመሪያ ላይ ምስሎች በዋነኝነት ያገለግሉ የነበረው ለማስተማርና ለጌጥነት ሊሆን ይችላል፤ በምስሎች መጠቀም ትክክል መሆኑን ለማሳመን ይቀርብ የነበረው ማስረጃ ይህ ነው። ብዙም ሳይቆይ ግን ለአምልኮ ማገልገል እንደጀመሩ የማይካድ ነገር ነው። በተለይም ደግሞ በምሥራቅ ኦርቶዶክስ [ቤተ ክርስቲያን] ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ምስሎች ጋር በተያያዘ ይህ ሁኔታ እውነት ሆኖ እናገኘዋለን።” ይሁንና ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?” የሚል ተገቢ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።—ኢሳይያስ 40:18

እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አወዳድር፦ ኢሳይያስ 44:13-19፤ የሐዋርያት ሥራ 10:25, 26፤ 17:29፤ 2 ቆሮንቶስ 5:7

እውነታው፦

አምላክ ሥዕሎችንና ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን አይደግፍም

የተሳሳቱ ትምህርቶችን በመተው እውነትን አጥብቀህ ያዝ

ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዛሬው ጊዜም ስለሚያስተምሯቸው የተሳሳቱ ትምህርቶች ካደረግነው አጠር ያለ ምርምር በመነሳት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? እነዚህ ‘በብልሃት የተፈጠሩ ተረቶች’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ቀላልና የሚያጽናኑ እውነቶች ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም።—2 ጴጥሮስ 1:16 የ1954 ትርጉም

እንግዲያው አእምሮህን ክፍት በማድረግ፣ የተማርካቸውን ነገሮች የእውነት ምንጭ ከሆነው ከአምላክ ቃል ጋር እንድታወዳድር እናበረታታሃለን። (ዮሐንስ 17:17) እንዲህ ካደረግህ ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” በማለት የገባው ቃል በአንተ ላይ ይፈጸማል።—ዮሐንስ 8:32