በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ቤተሰብ ሕይወት

ስለ ቤተሰብ ሕይወት

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

ስለ ቤተሰብ ሕይወት

ቤተሰቦች ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ስለ ጋብቻ ምን ዓይነት አመለካከት መያዛቸው ነው?

ጋብቻ ቅዱስ ጥምረት ነው። ኢየሱስ መፋታት ይፈቀድ እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ብሏል፦ “ፈጣሪ ከመጀመሪያውም ወንድና ሴት አድርጎ እንደፈጠራቸው አላነበባችሁም? ‘በዚህ ምክንያት ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ብሎ እንደተናገረስ አላነበባችሁም? በመሆኑም ከዚህ በኋላ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው። . . . በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ምንዝር ይፈጽማል።” (ማቴዎስ 19:4-6, 9) ባልና ሚስት የኢየሱስን ምክር በተግባር ካዋሉና አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ከሆኑ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የደኅንነት ስሜት የሚሰማቸው ከመሆኑም በላይ ደስተኞች ይሆናሉ።

ለአምላክ ፍቅር ማዳበር ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርገው እንዴት ነው?

ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው።” ከዚህኛው ቀጥሎ ያለው ትእዛዝስ የትኛው ነው? ኢየሱስ “ባልንጀራህን [አብረውህ የሚኖሩትን ማለትም ቤተሰብህን ይጨምራል] እንደ ራስህ ውደድ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:37-39) ስለዚህ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ነው፤ ምክንያቱም ለእሱ ያለን ፍቅር እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ያነሳሳናል።

ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት ነው?

ባሎች የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ ሚስቶቻቸውን ማስደሰት ይችላሉ። ኢየሱስ ለምሳሌያዊ ሚስቱ ማለትም ለጉባኤው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነበረው። (ኤፌሶን 5:25) ኢየሱስ “የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገል . . . እንጂ እንዲገለገል አይደለም” ብሏል። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ በእሱ ሥር ያሉትን አምባገነንነት በሚንጸባረቅበት ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ በፍጹም አልያዛቸውም፤ ከዚህ ይልቅ እረፍት ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 11:28) በመሆኑም ባሎች ሥልጣናቸውን ለሁሉም የቤተሰቡ አባላት ጥቅም በሚያመጣና ደግነት በተሞላበት መንገድ ሊጠቀሙበት ይገባል።

ሚስቶችም ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ሊጠቀሙ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የክርስቶስ ራስ አምላክ እንደሆነ’ ይናገራል። “የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ” እንደሆነ ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ኢየሱስ ለአምላክ መገዛቱ ዝቅ ሊያደርገው እንደሚችል አልተሰማውም። ለአባቱ ጥልቅ አክብሮት ነበረው። ኢየሱስ “ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:29) አንዲት ሚስት ለአምላክ ካላት ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ለባሏ የራስነት ሥልጣን የምትገዛ ከሆነ ለቤተሰቡ ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ታበረክታለች።

ወላጆች፣ ኢየሱስ ለልጆች ካለው አመለካከት ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

ኢየሱስ ከልጆች ጋር ጊዜ ያሳልፍ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ለመረዳት ይጥር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ኢየሱስ ሕፃናቱን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አለ፦ ‘ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ።’” (ሉቃስ 18:15, 16) በአንድ ወቅት አንዳንድ ልጆች በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት ሲገልጹ ሰዎች ነቀፏቸው። ሆኖም ኢየሱስ እነሱን ይነቅፉ የነበሩትን ሰዎች “‘ከሕፃናትና ከሚጠቡ አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” በማለት በተናገራቸው ጊዜ ለልጆቹ ያለውን አድናቆት ገልጿል።—ማቴዎስ 21:15, 16

ልጆች ከኢየሱስ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ነገር ፍላጎት ማዳበርን በተመለከተ ለልጆች ግሩም ምሳሌ ትቷል። የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ወላጆቹ “ቤተ መቅደሱ ውስጥ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ሲጠይቃቸው [እንዳገኙት]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እንዲህ ማድረጉ ምን ውጤት አስገኘ? “በዚያ የነበሩት ሰዎችም ሁሉ በማስተዋል ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው ያዳምጡት ነበር።” (ሉቃስ 2:42, 46, 47) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያካበተው እውቀት ኩራተኛ እንዲሆን አላደረገውም። ከዚህ ይልቅ ወላጆቹን እንዲያከብር አነሳስቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ወትሮውም ይታዘዛቸው ነበር” ይላል።—ሉቃስ 2:51

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።