በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሲሑ አምላክ ያዘጋጀው የመዳን መንገድ ነው

መሲሑ አምላክ ያዘጋጀው የመዳን መንገድ ነው

መሲሑ አምላክ ያዘጋጀው የመዳን መንገድ ነው

“ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ልክ እንደዚሁም ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።”—1 ቆሮ. 15:22

1, 2. (ሀ) እንድርያስና ፊልጶስ ኢየሱስን ካገኙ በኋላ ምን አደረጉ? (ለ) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በተመለከተ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከነበራቸው የበለጠ ማስረጃ አለን የምንለው ለምንድን ነው?

እንድርያስ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ የአምላክ ቅቡዕ መሆኑን ስላመነ ለወንድሙ ለጴጥሮስ “መሲሑን አገኘነው” በማለት ነገረው። ፊልጶስም የኢየሱስን መሲሕነት ስላመነ ወዳጁን ናትናኤልን ፈልጎ ካገኘው በኋላ “ሙሴ በሕጉ እንዲሁም ነቢያት ስለ እሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስ አገኘነው” አለው።—ዮሐ. 1:40, 41, 45

2 አንተስ ኢየሱስ፣ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ይኸውም ‘ለመዳን የሚያበቃ የይሖዋ ዋና ወኪል’ እንደሆነ በሚገባ ታምናለህ? (ዕብ. 2:10) ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በተመለከተ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች ከነበራቸው የበለጠ ማስረጃ አለን። ከኢየሱስ ልደት እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለውን ታሪክ የሚዘግበው የአምላክ ቃል፣ ኢየሱስ በእርግጥ ክርስቶስ እንደነበረ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ይሰጠናል። (ዮሐንስ 20:30, 31ን አንብብ።) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከሄደም በኋላ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና እንደሚቀጥል ይናገራል። (ዮሐ. 6:40፤ 1 ቆሮንቶስ 15:22ን አንብብ።) አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ካገኘኸው እውቀት በመነሳት ‘መሲሑን እንዳገኘኸው’ መናገር ትችላለህ። በቅድሚያ ግን በጥንት ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት መሲሑን ማግኘታቸውን በእርግጠኝነት እንዲናገሩ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ እንመልከት።

ስለ መሲሑ የተነገረው “ቅዱስ ሚስጥር” ደረጃ በደረጃ ተገለጠ

3, 4. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት ‘መሲሑን ያገኙት’ እንዴት ነበር? (ለ) ስለ መሲሑ የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ ሊፈጽም የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው የምትለው ለምንድን ነው?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የኢየሱስ ተከታዮች እሱ መሲሕ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር የቻሉት እንዴት ነበር? ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የመሲሑን መምጣት የሚያሳውቁ አንዳንድ ምልክቶችን ደረጃ በደረጃ ገልጦ ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር ይህን ሁኔታ የተለያዩ የእብነ በረድ ቁርጥራጮችን በማገጣጠም ከተሠራ ሐውልት ጋር አመሳስለውታል። ከዚህ በፊት እርስ በርስ የማይተዋወቁ በርካታ ሰዎች እያንዳንዳቸው የሐውልቱን አንድ አንድ ቁራጭ ይዘው ወደ አንድ ክፍል ገቡ እንበል። እነዚህ ቁርጥራጮች ተገጣጥመው የተሟላ የሐውልቱን ቅርጽ ቢያስገኙ አንድ ሰው ሐውልቱን በተሟላ ሁኔታ ከሠራ በኋላ ቁርጥራጮቹን ለእያንዳንዱ ሰው ልኮ መሆን አለበት ብለህ እንደምትደመድም ምንም ጥርጥር የለውም። ልክ እንደ እያንዳንዱ የሐውልቱ ቁርጥራጭ ሁሉ ስለ መሲሑ የተነገረው እያንዳንዱ ትንቢት መሲሑን በሚመለከት አስፈላጊ መረጃ ይሰጣል።

4 ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ በአንድ ሰው ላይ ፍጻሜያቸውን የማግኘታቸው አጋጣሚ ምን ያህል ነው? አንድ ተመራማሪ፣ እነዚህ መሲሐዊ ትንቢቶች በሙሉ በአንድ ሰው ላይ በአጋጣሚ የመፈጸማቸው ዕድል “በጣም ጠባብ” እንደሆነ ተናግረዋል። አክለውም “በታሪክ ዘመናት ሁሉ እነዚህን ትንቢቶች መፈጸም የቻለው ኢየሱስና ኢየሱስ ብቻ ነው” ብለዋል።

5, 6. (ሀ) በሰይጣን ላይ የተበየነው የቅጣት ፍርድ የሚፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ የሚመጣበትን የዘር ሐረግ ደረጃ በደረጃ የገለጠው እንዴት ነው?

5 ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች፣ ዘርፈ ብዙ የሆነ አጽናፈ ዓለማዊ ጠቀሜታ ባለው “ቅዱስ ሚስጥር” ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። (ቆላ. 1:26, 27፤ ዘፍ. 3:15) ይህ ቅዱስ ሚስጥር ከሚያካትታቸው ነገሮች መካከል “የመጀመሪያው እባብ” የተባለውና የሰው ልጆችን በኃጢአትና በሞት አዘቅት ውስጥ በከተታቸው በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ የተነገረው የቅጣት ፍርድ ይገኝበታል። (ራእይ 12:9) ይህ የቅጣት ፍርድ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ይሖዋ “ሴቲቱ” የምታስገኘው ‘ዘር’ የሰይጣንን ራስ እንደሚቀጠቅጥ ትንቢት ተናግሯል። አስቀድሞ የተነገረለት ‘ዘር’ የእባቡን ራስ በመቀጥቀጥ የዓመፅ፣ የሕመምና የሞት መንስኤ የሆነውን ሰይጣንን ያጠፋዋል። ይሁን እንጂ ከዚያ በፊት ሰይጣን የሴቲቱን ‘ዘር’ ምሳሌያዊ ተረከዝ እንዲያቆስል አምላክ ይፈቅድለታል።

6 ይሖዋ ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ ማን እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ገልጧል። አምላክ “የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ” በማለት ለአብርሃም ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍ. 22:18) ሙሴ ይህ ዘር “ነቢይ” እንደሚሆንና ከራሱ ከሙሴ እንደሚበልጥ ከረጅም ጊዜ በፊት ተናግሮ ነበር። (ዘዳ. 18:18, 19) ዳዊት ደግሞ መሲሑ በእሱ ዘር በኩል እንደሚመጣና ዙፋኑን ለዘላለም እንደሚወርስ ቃል ተገብቶለት የነበረ ሲሆን ነቢያትም ከጊዜ በኋላ ይህንኑ ሐቅ አረጋግጠዋል።—2 ሳሙ. 7:12, 16፤ ኤር. 23:5, 6

ኢየሱስ መሲሕ መሆን እንደሚችል የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች

7. ኢየሱስ በአምላክ ሚስት ከተመሰለችው ‘ሴት’ የመጣው እንዴት ነው?

7 አምላክ በሚስት መሰል ድርጅቱ ውስጥ ከታቀፉት መንፈሳዊ ፍጥረታቱ መካከል በኩር የሆነውን ልጁን ተስፋ የተደረገበት ‘ዘር’ እንዲሆን ወደ ምድር ልኮታል። ይህ ደግሞ የአምላክ አንድያ ልጅ፣ በሰማይ ከነበረው ሕይወት ጋር በተያያዘ “ራሱን ባዶ” ማድረግና ፍጹም ሰው ሆኖ መወለድ ጠይቆበታል። (ፊልጵ. 2:5-7፤ ዮሐ. 1:14) በማርያም ላይ መንፈስ ቅዱስ ‘ማረፉ’ የሚወለደው ልጅ “ቅዱስ፣ የአምላክ ልጅ” እንደሚሆን ዋስትና የሚሰጥ ነበር።—ሉቃስ 1:35

8. ኢየሱስ በውኃ ለመጠመቅ ራሱን ባቀረበበት ጊዜ ስለ መሲሑ የተነገረውን ትንቢት የፈጸመው እንዴት ነበር?

8 ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ኢየሱስ መቼና የት እንደሚወለድ ጠቁመው ነበር። በትንቢት በተነገረው መሠረት ኢየሱስ በቤተልሔም ተወለደ። (ሚክ. 5:2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን የመሲሑን መምጣት በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ከጉጉታቸው የተነሳ አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስን በተመለከተ “ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን?” ብለው ይጠይቁ ነበር። ዮሐንስ ግን ‘ከእኔ የሚበረታ ይመጣል’ በማለት መለሰላቸው። (ሉቃስ 3:15, 16) በ29 ዓ.ም. በበልግ ወራት ኢየሱስ በ30 ዓመቱ ወደ ዮሐንስ ሄዶ በመጠመቅ በተወሰነው ጊዜ ራሱን መሲሕ አድርጎ አቀረበ። (ዳን. 9:25) ከዚያም “የተወሰነው ጊዜ ተፈጽሟል፤ የአምላክ መንግሥት ቀርቧል” በማለት ብዙ ነገሮች ያከናወነበትን አገልግሎቱን ጀመረ።—ማር. 1:14, 15

9. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በወቅቱ የተሟላ ግንዛቤ ባይኖራቸውም እንኳ ምን የጸና እምነት ነበራቸው?

9 ይሁን እንጂ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ አመለካከታቸውን ማስተካከል ነበረባቸው። ኢየሱስን ንጉሥ አድርገው መቀበላቸው የተገባ ነበር፤ ይሁን እንጂ ንጉሥ ሆኖ የሚገዛው ከጊዜ በኋላ በሰማይ መሆኑን በወቅቱ ሙሉ በሙሉ አልተገነዘቡም ነበር። (ዮሐ. 12:12-16፤ 16:12, 13፤ ሥራ 2:32-36) ይሁንና ኢየሱስ “እኔን ማን ትሉኛላችሁ?” ብሎ በጠየቀበት ወቅት ጴጥሮስ ምንም ሳያመነታ “አንተ መሲሑ፣ የሕያው አምላክ ልጅ ነህ” በማለት መለሰለት። (ማቴ. 16:13-16) ከጊዜ በኋላ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ባስተማረው ትምህርት ተሰናክለው እሱን መከተላቸውን ባቆሙበት ጊዜም ጴጥሮስ ተመሳሳይ መልስ ሰጥቷል።—ዮሐንስ 6:68, 69ን አንብብ።

መሲሑን መስማት

10. ይሖዋ ልጁን የመስማትን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው?

10 የአምላክ አንድያ ልጅ በሰማይ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ ይኖር ነበር። በምድር ላይ ደግሞ “የአብ ተወካይ” ሆኖ አገልግሏል። (ዮሐ. 16:27, 28) “የማስተምረው ትምህርት የራሴ ሳይሆን ከላከኝ የመጣ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 7:16) ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ወቅት ይሖዋ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ “እሱን ስሙት” ብሏል። (ሉቃስ 9:35) አዎን፣ ይሖዋ የመረጠውን ኢየሱስን መስማት ወይም መታዘዝ ያስፈልጋል። ይህም እምነት እንዲሁም መልካም ሥራዎችን ማድረግ ይጠይቃል፤ እነዚህ ደግሞ አምላክን ለማስደሰትም ሆነ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ወሳኝ ነገሮች ናቸው።—ዮሐ. 3:16, 35, 36

11, 12. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ያልተቀበሉት ለምን ነበር? (ለ) በኢየሱስ ያመኑት እነማን ነበሩ?

11 ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ አይሁዳውያን አልተቀበሉትም። ለምን? ኢየሱስ ከሮም ጭቆና ነፃ የሚያወጣ የፖለቲካ መሲሕ ይሆናል የሚለውን አስተሳሰብ ጨምሮ ስለ መሲሑ መሠረት የሌላቸው ሌሎች አመለካከቶች ስለነበሯቸው ነው። (ዮሐንስ 12:34ን አንብብ።) በሰዎች እንደሚናቅና እንደሚጠላ፣ የሕማም ሰው እንደሚሆንና ሥቃይ እንደማይለየው በመጨረሻም እንደሚገደል የሚናገሩ ትንቢቶችን የሚፈጽም መሲሕ መቀበል አልሆነላቸውም። (ኢሳ. 53:3, 5) ሌላው ቀርቶ አንዳንድ የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንኳ ፖለቲካዊ ነፃነት ስላላመጣላቸው ቅር ብሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በታማኝነት የጸኑ ሲሆን ከጊዜ በኋላም ትክክለኛ ግንዛቤ አግኝተዋል።—ሉቃስ 24:21

12 በሌላ በኩል ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተስፋ የተደረገበት መሲሕ አድርገው ያልተቀበሉት ትምህርቶቹ ለመረዳት ከባድ ስለሆኑባቸው ነበር። ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ‘ራስን መካድ፣’ ‘የኢየሱስን ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት፣’ ‘ዳግመኛ መወለድ’ እንዲሁም ‘የዓለም ክፍል ከመሆን’ መቆጠብ ያስፈልጋል። (ማር. 8:34፤ ዮሐ. 3:3፤ 6:53፤ 17:14, 16) ትዕቢተኛ፣ ሀብታምና ግብዝ የሆኑ ሰዎች እነዚህን ብቃቶች ማሟላት በጣም ከባድ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ይሁን እንጂ “ይህ ሰው በእርግጥ የዓለም አዳኝ [ነው]” እንዳሉት አንዳንድ ሳምራውያን ሁሉ ትሑት የሆኑ አይሁዳውያንም ኢየሱስን መሲሕ አድርገው ተቀብለውታል።—ዮሐ. 4:25, 26, 41, 42፤ 7:31

13. ኢየሱስ በምሳሌያዊ ሁኔታ ተረከዙ የቆሰለው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ የካህናት አለቆች እንደሚፈርዱበት፣ አሕዛብ እንደሚሰቅሉት ሆኖም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሳ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 20:17-19) በሳንሄድሪን ፊት ቀርቦ “የአምላክ ልጅ ክርስቶስ” እንደሆነ መናገሩ አምላክን እንደ መሳደብ ተቆጥሮበታል። (ማቴ. 26:63-66) ጲላጦስ “ለሞት የሚያበቃ ምንም ነገር” ባያገኝበትም አይሁዳውያን ዓመፅ ያነሳሳል የሚል ክስም ሰንዝረውበት ስለነበር ጲላጦስ “እንደ ፍላጎታቸው አሳልፎ ሰጠው።” (ሉቃስ 23:13-15, 25) በአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ “የሕይወትን ዋና ወኪል” በዚህ መንገድ ‘ክደው’ ለሞት አሳልፈው ሰጥተውታል። (ሥራ 3:13-15) በትንቢት በተነገረው መሠረት መሲሑ በ33 ዓ.ም. በፋሲካ በዓል ዕለት በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ‘ተገደለ።’ (ዳን. 9:26, 27፤ ሥራ 2:22, 23) ኢየሱስ እንዲህ ባለ አሰቃቂ ሁኔታ በመገደሉ በ⁠ዘፍጥረት 3:15 ላይ በትንቢት በተነገረው መሠረት “ተረከዙ” ቆስሏል።

መሲሑ መሞት የነበረበት ለምንድን ነው?

14, 15. (ሀ) ይሖዋ ኢየሱስ እንዲሞት የፈቀደው በየትኞቹ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ምን አደረገ?

14 ይሖዋ፣ ኢየሱስ እንዲሞት የፈቀደው በሁለት ዓበይት ምክንያቶች የተነሳ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆኑ ‘ከቅዱሱ ሚስጥር’ ጋር በተያያዘ ለተነሳ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ምላሽ አስገኝቷል። ፍጹም የሆነ ሰው፣ ሰይጣን በጣም ከባድ ፈተና ቢያመጣበትም እንኳ ምንጊዜም ‘ለአምላክ ያደረ’ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ከአምላክ ሉዓላዊነት ጎን እንደሚቆም በማያዳግም መንገድ አረጋግጧል። (1 ጢሞ. 3:16) በሁለተኛ ደረጃ ኢየሱስ እንደተናገረው ‘የሰው ልጅ የመጣው በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ለመስጠት’ ነው። (ማቴ. 20:28) ይህ “ተመጣጣኝ ቤዛ” በአዳም ዘሮች ላይ የተጣለውን የኃጢአት ቅጣት የሚያስቀር ከመሆኑም በላይ አምላክ በኢየሱስ አማካኝነት ያደረገውን የመዳን ዝግጅት ለሚቀበሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያስገኝላቸዋል።—1 ጢሞ. 2:5, 6

15 ክርስቶስ ለሦስት ቀን መቃብር ውስጥ ከቆየ በኋላ ከሞት ተነሳ፤ ከዚያም ሕያው መሆኑን ለማረጋገጥ ለ40 ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ የታየ ሲሆን ተጨማሪ መመሪያም ሰጣቸው። (ሥራ 1:3-5) ይህ ከሆነ በኋላ ውድ የሆነው መሥዋዕቱ የሚያስገኘውን ዋጋ ለይሖዋ ለማቅረብ ወደ ሰማይ አረገ፤ በዚያም መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበትን የተወሰነውን ጊዜ መጠባበቅ ጀመረ። ይህ እስከሚሆን ጊዜ ድረስ ግን ብዙ የሚሠራው ነገር ነበረው።

መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ከፍጻሜ ማድረስ

16, 17. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ መሲሕ ሆኖ ያከናወናቸውን ነገሮች ግለጽ።

16 ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ባሉት መቶ ዓመታት የክርስቲያን ጉባኤን ንጉሥ ሆኖ እያስተዳደረ ሲሆን ይህ ጉባኤ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በታማኝነት ሲቆጣጠር ቆይቷል። (ቆላ. 1:13) የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ይጀምራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችና በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ክስተቶች እንደሚያረጋግጡት ኢየሱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” በጀመረበት በ1914 ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል። (ማቴ. 24:3፤ ራእይ 11:15) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር በመሆን ሰይጣንንና አጋንንቱን ከሰማይ አባሯቸዋል።—ራእይ 12:7-10

17 ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. የጀመረው የመስበክና የማስተማር ሥራ ወደ ታላቅ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። በቅርቡ በሕያዋን ሁሉ ላይ ይፈርዳል። በዚያ ጊዜ እሱን የይሖዋ የመዳን ዝግጅት እንደሆነ አድርገው የሚቀበሉ በግ መሰል ሰዎችን ‘ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላቸውን መንግሥት እንዲወርሱ’ ይነግራቸዋል። (ማቴ. 25:31-34, 41) የኢየሱስን ንጉሥነት የማይቀበሉ ሰዎችን ደግሞ ከሰማይ ሠራዊቱ ጋር ሆኖ ክፉዎችን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ያስወግዳቸዋል። በመጨረሻም ኢየሱስ ሰይጣንን አስሮ እሱንና አጋንንቱን ወደ “ጥልቁ” ይወረውራቸዋል።—ራእይ 19:11-14፤ 20:1-3

18, 19. ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ በሚጫወተው ሚና ምን ነገሮችን ያከናውናል? ይህስ ታዛዥ ለሆኑት የሰው ልጆች ምን ያስገኝላቸዋል?

18 በሺህ ዓመት ግዛቱ ወቅት ኢየሱስ “ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል” በመሆን የሚያከናውነውን ተግባር ሙሉ በሙሉ ይፈጽማል። (ኢሳ. 9:6, 7) በእሱ የግዛት ዘመን ከሞት የሚነሱትን ጨምሮ ሰዎች ሁሉ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። (ዮሐ. 5:26-29) መሲሑ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን “ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ” ይመራቸዋል፤ ይህ ደግሞ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከይሖዋ ጋር ሰላማዊ የሆነ ዝምድና እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። (ራእይ 7:16, 17ን አንብብ።) ከመጨረሻው ፈተና በኋላ ሰይጣንንና አጋንንቱን ጨምሮ ሁሉም ዓመፀኞች ‘ወደ እሳቱ ሐይቅ ይወረወራሉ’፤ በዚህ መንገድ ‘እባቡ’ ራሱ ተቀጥቅጦ ይጠፋል።—ራእይ 20:10

19 ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ የሚጫወተውን ሚና አስደናቂና እንከን የለሽ በሆነ መንገድ ወደ ፍጻሜው ያደርሰዋል። ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ሰዎች ምድርን ይሞላሉ፤ እነዚህ ሰዎች ፍጹም ጤንነትና ደስታ አግኝተው ለዘላለም ይኖራሉ። የይሖዋ ቅዱስ ስም ከነቀፋ ሁሉ ነፃ ይሆናል፤ እንዲሁም አጽናፈ ዓለምን የመግዛት መብቱ ሙሉ በሙሉ ይረጋገጣል። የአምላክን ቅቡዕ የሚታዘዙ ሁሉ እንዴት ያለ ታላቅ በረከት ከፊታቸው ተዘርግቶላቸዋል!

መሲሑን አግኝተኸዋል?

20, 21. ለሌሎች ስለ መሲሑ እንድትናገር የሚያነሳሳህ ምን ምክንያት አለህ?

20 ከ1914 ጀምሮ የምንኖረው በክርስቶስ ፓሩሲያ ወይም መገኘት ወቅት ነው። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መገኘቱ ለሰው ልጆች የማይታይ ቢሆንም ፍጻሜያቸውን ከሚያገኙት ትንቢቶች ይህን በግልጽ መረዳት ይቻላል። (ራእይ 6:2-8) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሰዎችም ስለ መሲሑ መገኘት የሚናገሩትን ማስረጃዎች ችላ ብለዋል። እነዚህ ሰዎችም የሚፈልጉት ፖለቲካዊ መሲሕ ወይም በሰብዓዊ የፖለቲካ አገዛዝ ውስጥ ገብቶ ለውጥ የሚያመጣ መሲሕ ነው። አንተ ግን ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ እንደሚገኝ ታውቃለህ። ታዲያ ይህን በማወቅህ አልተደሰትክም? “መሲሑን አገኘነው” ብለው እንደተናገሩት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት ሁሉ አንተም እንዲህ ብለህ ለመናገር እንደተገፋፋህ ጥርጥር የለውም።

21 አሁንስ ለሰዎች ስለ እውነት ስትናገር ኢየሱስ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርገህ ትገልጻለህ? እንዲህ ማድረግህ መሲሑ ከዚህ በፊት ለአንተ ስላደረገልህ እንዲሁም አሁንም ሆነ ወደፊት ስለሚያደርግልህ ነገር ያለህ አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። አንተም እንደ እንድርያስና ፊልጶስ ሁሉ ለዘመዶችህና ለወዳጆችህ ስለ መሲሑ እንደተናገርክ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ አሁንም በአዲስ መንፈስ ተነሳስተህ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ይኸውም አምላክ ያዘጋጀው የመዳን መንገድ መሆኑን ለምን አትነግራቸውም?

ልታብራራ ትችላለህ?

• በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ደቀ መዛሙርት ‘መሲሑን ያገኙት’ እንዴት ነበር?

• ኢየሱስ የሞተው በየትኞቹ ሁለት ዓበይት ምክንያቶች የተነሳ ነው?

• ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ በሚጫወተው ሚና ወደፊት ምን ነገሮችን ያከናውናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ሊያውቁ የቻሉት እንዴት ነበር?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች ስለ እውነት ስትናገር ኢየሱስ መሲሕ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርገህ ትገልጻለህ?