በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈጽሞ የማይከስመውን ፍቅርን አዳብሩ

ፈጽሞ የማይከስመውን ፍቅርን አዳብሩ

ፈጽሞ የማይከስመውን ፍቅርን አዳብሩ

‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም።’—1 ቆሮ. 13:7, 8

1. (ሀ) ብዙውን ጊዜ ፍቅር የሚገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ብዙ ሰዎች ይበልጥ የሚወዱት ምን ነገሮችን ነው?

ፍቅርን በተመለከተ ብዙ ተብሏል። ሰዎች ፍቅርን አወድሰውታል፤ እንዲሁም ዘፍነውለታል። ፍቅር የሰዎች መሠረታዊ ፍላጎት ነው። ይሁንና መጻሕፍትና ፊልሞች አብዛኛውን ጊዜ የሚያወሱት ልብ ወለድ ስለሆነ ፍቅር ነው፤ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ፊልሞችና መጻሕፍት ደግሞ ገበያውን አጥለቅልቀውታል። ይሁን እንጂ ሰዎች ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ሊኖራቸው የሚገባው እውነተኛ ፍቅር በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ የመጨረሻ ቀን ይፈጸማሉ ብሎ የተናገራቸው ነገሮች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ እየተመለከትን ነው። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ [ሆነዋል]።”—2 ጢሞ. 3:1-5

2. መጽሐፍ ቅዱስ ለተሳሳተ ነገር ፍቅር ስለማሳደር ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

2 ሰዎች ፍቅር የማሳየት ችሎታ አላቸው፤ ሆኖም የአምላክ ቃል ለተሳሳተ ነገር ፍቅር እንዳያድርብን ያስጠነቅቀናል። እንዲህ ያለው ፍቅር በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ሥር ሲሰድ ምን እንደሚከሰት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ዴማስ የጻፈውን ታስታውሳለህ? ዴማስ ከጳውሎስ ጋር አብሮ ይሠራ የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ዓለም የሚያቀርባቸውን ነገሮች ወዷል። (2 ጢሞ. 4:10) ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን አደጋ በተመለከተ ክርስቲያኖችን አስጠንቅቋል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብብ።) አንድ ሰው ዓለምንና በውስጡ ያሉትን አላፊ ነገሮች እያፈቀረ አምላክንና ከእሱ የሚመነጩ ነገሮችን መውደድ አይችልም።

3. ምን ብርቱ ትግል ማድረግ ይኖርብናል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

3 በዓለም ብንኖርም የዚህ ዓለም ክፍል አይደለንም። በመሆኑም ዓለም ስለ ፍቅር ያለው የተዛባ አመለካከት እንዳይጋባብን ብርቱ ትግል ማድረግ ይኖርብናል። ለተሳሳተ ነገር ፍቅር እንዳያድርብን ጥንቃቄ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንግዲያው እውነተኛ ፍቅር ማሳየት ያለብን ለእነማን ነው? ይህንንስ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ሁሉን ነገር በጽናት የሚቋቋመውንና ፈጽሞ የማይከስመውን ፍቅር እንድናዳብር ምን ዝግጅቶች ተደርገውልናል? በእነዚህ ዝግጅቶች መጠቀማችን በአሁኑ ጊዜ ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው? የወደፊት ሕይወታችንንስ የሚነካው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ትክክለኛውን አካሄድ መከተል እንድንችል ለእነዚህ ጥያቄዎች የአምላክን አመለካከት የሚያንጸባርቅ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል።

ለይሖዋ ፍቅር ማዳበር

4. ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ማዳበር የሚለው ቃል የአንድን ነገር እድገት ለማፋጠን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሊያመለክት ይችላል። መሬቱን አለስልሶ ለመዝራት ብርቱ ጥረት ስለሚያደርግ አንድ ገበሬ አስብ። ይህ ገበሬ እንዲህ ያለውን ጥረት ካደረገ በኋላ ዘሩ እንደሚያድግ ተስፋ ያደርጋል። (ዕብ. 6:7) በተመሳሳይም ለአምላክ ያለን ፍቅር ማደግ አለበት። ይሁንና ለአምላክ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የመንግሥቱ እውነት የተዘራበትንና በጥሩ አፈር የተመሰለውን ልባችንን በሚገባ ለማዘጋጀት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ ስለ አምላክ ያለንን እውቀት ለመጨመር ቃሉን በትጋት በማጥናት ነው። (ቆላ. 1:10) በተጨማሪም ዘወትር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንና ተሳትፎ ማድረጋችን እውቀታችን እንዲያድግ ይረዳናል። ታዲያ ጥልቅ እውቀት ለማግኘት በግለሰብ ደረጃ ያላሰለሰ ጥረት እያደረግን ነው?—ምሳሌ 2:1-7

5. (ሀ) ስለ ይሖዋ ዋና ዋና ባሕርያት መማር የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ አምላክ ፍትሕ፣ ጥበብና ኃይል ምን ማለት ትችላለህ?

5 ይሖዋ በቃሉ በኩል ባሕርይውን ገልጾልናል። ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናትና ስለ ይሖዋ ያለንን እውቀት ደረጃ በደረጃ በማሳደግ ለዋና ዋና ባሕርያቱ ይኸውም ለፍትሑ፣ ለኃይሉ፣ ለጥበቡና ከምንም በላይ ደግሞ ከሁሉም ለሚልቀው ፍቅሩ ያለንን አድናቆት መጨመር እንችላለን። ይሖዋ በመንገዶቹ ሁሉ እንዲሁም ፍጹም በሆኑት ሕጎቹ አማካኝነት ፍትሑን ይገልጽልናል። (ዘዳ. 32:4፤ መዝ. 19:7) በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ሁሉ ላይ ማሰላሰልና ታላቅ በሆነው ጥበቡ መደመም እንችላለን። (መዝ. 104:24) በተጨማሪም ጽንፈ ዓለም ይሖዋ ፈጽሞ የማይነጥፍ ኃይል ምንጭ እንደሆነ ማስረጃ ይሰጠናል።—ኢሳ. 40:26

6. አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር የገለጸው እንዴት ነው? የአንተን ሕይወት የሚነካውስ እንዴት ነው?

6 ከአምላክ ባሕርያት ሁሉ ስለሚልቀው ስለ ፍቅሩስ ምን ማለት ይቻላል? የይሖዋ ፍቅር፣ ሁሉን አቀፍ ሲሆን የሁላችንንም ሕይወት ይነካል። አምላክ ለሰው ልጆች ከኃጢአት ነፃ እንዲሆኑ ቤዛውን በማዘጋጀት እንዲህ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። (ሮም 5:8ን አንብብ።) ይህ ዝግጅት በምድር ላይ ለሚገኙ የሰው ዘሮች ሁሉ የቀረበ ቢሆንም ተጠቃሚ የሚሆኑት አምላክ ላሳያቸው ፍቅር ምላሽ የሚሰጡና በልጁ እንደሚያምኑ በተግባር የሚያሳዩ ብቻ ናቸው። (ዮሐ. 3:16, 36) አምላክ ኢየሱስን ለኃጢአታችን ማስተሰረያ እንዲሆን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡ እኛም በምላሹ እሱን እንድንወደው ሊያነሳሳን ይገባል።

7, 8. (ሀ) ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ትእዛዛቱን የሚጠብቁት ምን ዓይነት ሁኔታ እያጋጠማቸውም ጭምር ነው?

7 ብዙ ነገሮች ላደረገልን አምላክ ያለንን ፍቅር በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የሚከተለው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐ. 5:3) አዎን፣ ለይሖዋ አምላክ ያለን ፍቅር ትእዛዛቱን እንድንጠብቅ ይገፋፋናል። ስለ ስሙና ስለ መንግሥቱ ለሰዎች የምንመሠክርበት አንደኛው ምክንያት ይህ ነው፤ ምሥክርነት መስጠታችን ደግሞ ለሰዎቹ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። በልባችን ውስጥ በሞላው ፍቅር ተገፋፍተን ይህን ሥራ ማከናወናችን የአምላክን ትእዛዝ የምንጠብቀው በበጎ ዓላማ ተነሳስተን እንደሆነ ያሳያል።—ማቴ. 12:34

8 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻችን፣ ለመንግሥቱ መልእክት ግድ የለሽ የሆኑ ሰዎች እያጋጠሟቸውም እንዲሁም ቀጥተኛ ተቃውሞ እየደረሰባቸውም እንኳ የአምላክን ትእዛዝ በጽናት እየፈጸሙ ነው። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም። (2 ጢሞ. 4:5) እኛም በተመሳሳይ ስለ አምላክ ያገኘነውን እውቀት ለሰዎች ለመናገር እንዲሁም የአምላክን ትእዛዝ በሙሉ ለመፈጸም እንገፋፋለን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድንወደው የሚያደርገን ምክንያት

9. ክርስቶስ በጽናት የተቋቋማቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳውስ ምንድን ነው?

9 አምላክን ከመውደድ በተጨማሪ ለልጁ ያለንን ፍቅር እንድናዳብር የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ኢየሱስን አይተነው የማናውቅ ቢሆንም እንኳ ስለ እሱ ይበልጥ በተማርን መጠን ለእሱ ያለን ፍቅር እየጨመረ ይሄዳል። (1 ጴጥ. 1:8) ኢየሱስ በጽናት ከተቋቋማቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ሲያደርግ ያለ ምንም ምክንያት ተጠልቷል፣ ስደት ደርሶበታል፣ በሐሰት ተወንጅሏል እንዲሁም ተሰድቧል። ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ሌሎች ነገሮችም ደርሰውበታል። (ዮሐንስ 15:25ን አንብብ።) በሰማይ ለሚገኘው አባቱ ያለው ፍቅር እነዚህን መከራዎች በጽናት እንዲቋቋም አነሳስቶታል። ከዚህም በተጨማሪ በፍቅር ተገፋፍቶ መሥዋዕታዊ ሞት መሞቱ ለብዙዎች ቤዛ አስገኝቷል።—ማቴ. 20:28

10, 11. ክርስቶስ ካደረገልን ነገሮች አንጻር ግባችን ምን መሆን አለበት?

10 ኢየሱስ የተከተለው ጎዳና እኛም ተመሳሳይ ምላሽ እንድንሰጥ ያነሳሳናል። ክርስቶስ ለእኛ ስላደረገልን ነገር ስናስብ ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ተከታዮቹ እንደመሆናችን መጠን የክርስቶስን ዓይነት ፍቅር የማዳበርና ይህን ፍቅር ምንጊዜም በተግባር የማሳየት ግብ ሊኖረን ይገባል፤ እንዲህ ማድረጋችን ስለ መንግሥቱ እንድንሰብክና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ትእዛዝ በጽናት እንድንፈጽም ያስችለናል።—ማቴ. 28:19, 20

11 ክርስቶስ ለመላው የሰው ዘር ያሳየው ፍቅር መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የተሰጠንን ሥራ ከፍጻሜው እንድናደርስ ግድ ይለናል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) ክርስቶስ ያሳየው ፍቅር፣ አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ክርስቶስ ፈለጉን በጥብቅ እንድንከተል የተወልን አርዓያ እያንዳንዳችን በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ድርሻ እንዲኖረን አስችሎናል። ይህ ደግሞ ለአምላክ ያለንን ፍቅር የቻልነውን ያህል እንድናዳብር ይገፋፋናል። (ማቴ. 22:37) ኢየሱስ ያስተማረውን በመጠበቅና ትእዛዛቱን በመፈጸም እንደምንወደው እንዲሁም ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለን ልክ እንደ ኢየሱስ ከአምላክ ሉዓላዊነት ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረግን እናሳያለን።—ዮሐ. 14:23, 24፤ 15:10

ከሁሉ የላቀውን የፍቅርን መንገድ መከታተል

12. ጳውሎስ ‘ከሁሉ የላቀው መንገድ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

12 ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስን አርዓያ ተከትሏል። የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ ተከትሎ ስለነበር ወንድሞቹ የእሱን አርዓያ እንዲከተሉ አፉን ሞልቶ መናገር ችሎ ነበር። (1 ቆሮ. 11:1) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተሰጥተው የነበሩትን እንደ መፈወስና በልሳን እንደ መናገር ያሉ የመንፈስ ስጦታዎችን ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧቸው የነበረ ቢሆንም ሊከተሉት የሚገባ የተሻለ ነገር እንዳለ ገልጾላቸዋል። በ⁠1 ቆሮንቶስ 12:31 ላይ “ደግሞም ከሁሉ የላቀውን መንገድ አሳያችኋለሁ” ብሏቸው ነበር። ከዚያ ቀጥሎ ካሉት ጥቅሶች መረዳት እንደሚቻለው ከሁሉ የላቀ መንገድ የተባለው ፍቅር ነው። ፍቅር ከሁሉ የላቀ መንገድ የተባለው ከምን አንጻር ነው? ጳውሎስ ማለት የፈለገውን ሐሳብ ለመግለጽ በምሳሌ አስረድቷል። (1 ቆሮንቶስ 13:1-3ን አንብብ።) ጳውሎስ አንዳንድ ልዩ ችሎታዎች ቢኖሩት እንዲሁም ታላላቅ ነገሮችን ቢያከናውን ፍቅር ግን ባይኖረው ምን ይጠቅመዋል? ምንም! በአምላክ መንፈስ ተገፋፍቶ ለዚህ ወሳኝ ነጥብ ማብራሪያ ሰጥቷል። ጳውሎስ ይህ ሐሳብ ለእኛ እንዲገባን ለማድረግ እንዴት ያለ ግሩም አገላለጽ ተጠቅሟል!

13. (ሀ) የ2010 የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው? (ለ) ፍቅር ፈጽሞ የማይከስመው እንዴት ነው?

13 ጳውሎስ በመቀጠል ፍቅር የሚያደርገውንና የማያደርገውን ነገር ገልጿል። (1 ቆሮንቶስ 13:4-8ን አንብብ።) እስቲ ትንሽ ቆም በልና ፍቅር ከሚጠይቃቸው ብቃቶች አንጻር ራስህን መርምር። በዋነኝነት በቁጥር 7 መጨረሻ ላይና በቁጥር 8 መጀመሪያ ላይ በሚገኘው ‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም’ በሚለው የ2010 የዓመት ጥቅስ ላይ ትኩረት አድርግ። ጳውሎስ በቁጥር 8 ላይ መተንበይንና በልሳን መናገርን ጨምሮ የክርስቲያን ጉባኤ ጨቅላ እያለ ተሰጥተው የነበሩ የመንፈስ ስጦታዎች ሁሉ የሚያበቁበት ወይም የሚቀሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ተናግሯል። ፍቅር ግን ምንጊዜም ይኖራል። የይሖዋ ዋነኛ ባሕርይ ፍቅር ነው፤ ይሖዋ ደግሞ ዘላለማዊ ነው። በመሆኑም ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም ወይም መጨረሻ የለውም። ፍቅር ዘላለማዊ የሆነው አምላካችን ባሕርይ ሆኖ ለዘላለም ይቀጥላል።—1 ዮሐ. 4:8

ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል

14, 15. (ሀ) ፍቅር መከራን በጽናት እንድንቋቋም ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ወጣት ወንድም በአቋሙ የጸናው ለምንድን ነው?

14 ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸውን መከራ፣ አስቸጋሪ ሁኔታና ፈተና በጽናት እንዲቋቋሙ የሚረዳቸው ምንድን ነው? በዋነኝነት የሚረዳቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነው። እንዲህ ያለው ፍቅር ቁሳዊ ነገሮችን ከመስጠት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ፈቃደኛ እንድንሆን እንዲሁም ለክርስቶስ ስንል ሕይወታችንን መሥዋዕት አድርገን እንድንሰጥ ሊገፋፋን ይችላል። (ሉቃስ 9:24, 25) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት በማጎሪያ ካምፖች፣ የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች እንዲሁም በወኅኒ ቤቶች ሥቃይ የደረሰባቸው ወንድሞች ስለተከተሉት የታማኝነት ጎዳና አስብ።

15 ቪልሄልም የተባለ አንድ ጀርመናዊ የይሖዋ ምሥክር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ይህ ወጣት፣ በአንድ የናዚ ረሻኝ ቡድን የመገደል አደጋ ተጋርጦበት የነበረ ቢሆንም አቋሙን ከማላላት ይልቅ ታማኝነቱን ጠብቋል። ለቤተሰቡ በጻፈው የስንብት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘን ከሁሉም በላይ አምላክን መውደድ አለብን። ከእሱ ጎን ከተሰለፍን ወሮታችንን ይከፍለናል።” አንዲት የቤተሰቡ አባል የተናገረችው የሚከተለው ሐሳብ ከጊዜ በኋላ በአንድ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር፦ “በእነዚያ ቀውጢ ጊዜያት ቤተሰባችን ከምንም ነገር በላይ ለአምላክ ፍቅር ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት አድርጓል።” በዛሬው ጊዜ በአርሜንያ፣ በኤርትራ፣ በደቡብ ኮሪያና በሌሎች አገሮች ታስረው ሥቃይ እየደረሰባቸው ያሉ በርካታ ወንድሞች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። እነዚህ ወንድሞች ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር የተነሳ ጸንተዋል።

16. በማላዊ የሚገኙ ወንድሞቻችን ምን ነገር በጽናት ተቋቁመዋል?

16 በሌሎች በርካታ ቦታዎች ደግሞ ወንድሞች በተለያዩ መከራዎች እምነታቸውና ጽናታቸው ይፈተናል። በማላዊ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥት የጣለባቸውን እገዳ ጨምሮ የደረሰባቸውን ከፍተኛ ተቃውሞና ግፍ ለ26 ዓመታት በጽናት ተቋቁመዋል። ይህ ጽናታቸው ደግሞ በረከት አስገኝቶላቸዋል። ስደቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት በአገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 18,000 ገደማ ነበር። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ቁጥራቸው ከእጥፍ በላይ አድጎ 38,393 ደርሶ ነበር። በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ውጤት ተገኝቷል።

17. የማያምን ቤተሰብ ያላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ያጋጥማቸዋል? እንዲህ ያለውን በደል በጽናት እንዲቋቋሙ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

17 የአምላክ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ የሚያጋጥማቸው ቀጥተኛ ተቃውሞ አንድ ነገር ነው። በግለሰብ ደረጃ ከቤተሰብ አባላት የሚያጋጥማቸው ተቃውሞ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። የቤተሰብ አባላት ወይም የቅርብ ዘመዶች የሚያሳድሩት ጫና ውጥረት ያስከትል ይሆናል። ኢየሱስ ይህ እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ደግሞም ብዙዎች ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት እውነት መሆናቸውን በራሳቸው ሕይወት ተመልክተውታል። (ማቴ. 10:35, 36) በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከማያምኑ ወላጆቻቸው የደረሰባቸውን ተቃውሞ በጽናት ተቋቁመዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ከቤት ተባረዋል፤ ደግነቱ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ተቀብለዋቸዋል። አንዳንዶችን ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ክደዋቸዋል። ታዲያ እነዚህ ክርስቲያኖች የደረሰባቸውን በደል በጽናት እንዲቋቋሙ የረዳቸው ምንድን ነው? ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የረዳቸው ለይሖዋና ለልጁ ያላቸው እውነተኛ ፍቅር ነው።—1 ጴጥ. 1:22፤ 1 ዮሐ. 4:21

18. ሁሉን ነገር በጽናት የሚቋቋመው ፍቅር በትዳር የተሳሰሩ ክርስቲያኖችን ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

18 ሁሉን ነገር በጽናት የሚቋቋመው ፍቅር በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ሌሎች በርካታ ሁኔታዎችንም እንድንቋቋም ይረዳናል። በትዳር የተሳሰሩ ባልና ሚስት እርስ በርስ ፍቅር ማሳየታቸው ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ሲል የተናገረውን ቃል እንዲያከብሩ ይረዳቸዋል። (ማቴ. 19:6) ባለትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች “በሥጋቸው ላይ መከራ” ሲያጋጥማቸው ይሖዋ የትዳራቸው ዋነኛው መሠረት መሆኑን ማስታወስ አለባቸው። (1 ቆሮ. 7:28) ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል’ ስለሚል ይህን ባሕርይ የለበሱ ባልና ሚስት እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር ትዳራቸው ጸንቶ እንዲኖር ማድረግ ይችላሉ።—ቆላ. 3:14

19. የተፈጥሮ አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ምን አድርገዋል?

19 ፍቅር የተፈጥሮ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ሁሉን ነገር በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። ይህ ሁኔታ በፔሩ ደቡባዊ ክፍል የመሬት መንቀጥቀጥ በተከሰተበት ጊዜና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የባሕረ ሰላጤ አካባቢ ካትሪና በተባለችው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በተመታበት ወቅት ታይቷል። በርካታ ወንድሞቻችን በእነዚህ አደጋዎች ምክንያት ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። በዚህ ጊዜ ዓለም አቀፉ ጉባኤ በፍቅር ተገፋፍቶ የእርዳታ ቁሳቁሶችን አቅርቧል፤ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች እንደገና ገንብተዋል እንዲሁም መንግሥት አዳራሾችን ጠግነዋል። እንዲህ ያለው ተግባር ወንድሞቻችን በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ሁኔታ ሥር እርስ በርስ እንደሚዋደዱና እንደሚረዳዱ ያሳያል።—ዮሐ. 13:34, 35፤ 1 ጴጥ. 2:17

ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም

20, 21. (ሀ) ፍቅር ከሁሉ ነገር ይበልጣል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የፍቅርን መንገድ ለመከታተል ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?

20 ከሁሉ የላቀውን የፍቅር መንገድ መከታተል የጥበብ እርምጃ መሆኑን በዛሬው ጊዜ ከሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች መረዳት እንችላለን። በእርግጥም ፍቅር ከማንኛውም ነገር ይበልጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን እውነታ ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። በመጀመሪያ የመንፈስ ስጦታዎች እንደሚቀሩ እንዲሁም ጨቅላ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ወደ ጉልምስና ደረጃ እንደሚደርስ ገልጿል። ከዚያም “ይሁን እንጂ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ እንዳሉ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” በማለት ደምድሟል።—1 ቆሮ. 13:13

21 ወደፊት እምነት ያደረግንባቸው ነገሮች እውን ይሆናሉ፤ ከዚያ በኋላ በእነዚያ ነገሮች ላይ እምነት ማሳደር አስፈላጊ አይሆንም። ሁሉም ነገር አዲስ ሲሆን፣ ለማየት እንናፍቃቸው የነበሩ ተስፋዎች ስለሚፈጸሙ ከዚያ በኋላ በእነዚያ ነገሮች ላይ ተስፋ ማድረግ አያስፈልገንም። ስለ ፍቅርስ ምን ማለት ይቻላል? ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም ወይም መጨረሻ የለውም፤ እንዲያውም ለዘላለም ይኖራል። እኛም ለዘላለም ስለምንኖር የአምላክን ፍቅር የተለያዩ ገጽታዎች ይበልጥ እንደምናይና እንደምንረዳ ምንም ጥርጥር የለውም። አንተም ፈጽሞ የማይከስመውንና ከሁሉ የላቀውን የፍቅር መንገድ በመከታተል የአምላክን ፈቃድ የምትፈጽም ከሆነ ለዘላለም መኖር ትችላለህ።—1 ዮሐ. 2:17

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ለተሳሳተ ነገር ፍቅር እንዳያድርብን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

• ፍቅር ምን ነገሮችን በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል?

• ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም ሲባል ምን ማለት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የ2010 የዓመት ጥቅስ ‘ፍቅር ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም’ የሚል ነው።—1 ቆሮ. 13:7, 8

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለአምላክ ያለን ፍቅር ለሰዎች እንድንመሠክር ይገፋፋናል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፈጽሞ የማይከስመው ፍቅር በማላዊ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የደረሰባቸውን መከራ በጽናት እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል