በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?

ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?

ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?

“የማመልከው [“የእርሱ የሆንሁት፣” አ.መ.ት.] . . . አምላክ የላከው መልአክ ትናንት ሌሊት አጠገቤ [ቆመ]”።—ሥራ 27:23

1. ለጥምቀት ራሳቸውን ያቀረቡ እጩዎች የትኞቹን እርምጃዎች ወስደዋል? ይህስ የትኞቹን ጥያቄዎች ያስነሳል?

“በኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት በማመን ከኃጢአታችሁ ንስሐ ገብታችሁ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችሁን ወስናችኋል?” ይህ በጥምቀት ንግግር መደምደሚያ ላይ ለጥምቀት እጩዎች ከሚቀርቡላቸው ሁለት ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነው። ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰን ያለባቸው ለምንድን ነው? ለአምላክ ራሳችንን መወሰናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ ካልወሰነ አምልኮቱ ተቀባይነት የማይኖረው ለምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ ራስን መወሰን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ መመርመራችን አስፈላጊ ነው።

2. ራስን ለይሖዋ መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

2 ራስን ለአምላክ መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዴት አድርጎ እንደገለጸው ልብ በል። አደጋ በደረሰባት መርከብ ላይ ተሳፍረው በነበሩ በርካታ ሰዎች ፊት ይሖዋን ‘የእርሱ የሆንሁት አምላክ’ [አ.መ.ት.] በማለት ጠርቶታል። (ሥራ 27:22-24) ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የይሖዋ ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ግን መላው ዓለም “በክፉው ኃይል ሥር ነው።” (1 ዮሐ. 5:19) ክርስቲያኖች የይሖዋ ንብረት የሚሆኑት ተቀባይነት ባለው መንገድ ራሳቸውን ለእሱ መወሰናቸውን በጸሎት ሲገልጹ ነው። ራስን መወሰን አንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ ለይሖዋ የሚገባው ቃል ነው። ከዚያም ግለሰቡ በውኃ ይጠመቃል።

3. የኢየሱስ ጥምቀት ምን ያመለክታል? የእሱ ተከታዮች ምሳሌውን መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ በማድረግ ለእኛ ምሳሌ ትቶልናል። ራሱን ለአምላክ ወስኖ ከነበረው የእስራኤል ብሔር የተወለደ በመሆኑ ቀድሞውንም ቢሆን ራሱን ለአምላክ የወሰነ ነበር። ያም ሆኖ በተጠመቀበት ወቅት ሕጉ ከሚጠብቅበት የበለጠ ነገር አከናውኗል። የአምላክ ቃል፣ ኢየሱስ “እነሆ፣ አምላክ ሆይ፣ . . . ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” በማለት እንደተናገረ ያመለክታል። (ዕብ. 10:7፤ ሉቃስ 3:21) በመሆኑም ኢየሱስ መጠመቁ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ራሱን ማቅረቡን ያመለክታል። የኢየሱስ ተከታዮች ራሳቸውን ለጥምቀት ሲያቀርቡ የእሱን ምሳሌ ይከተላሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በውኃ የሚጠመቁት በጸሎት አማካኝነት ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለሰዎች ይፋ ለማድረግ ነው።

ራሳችንን መወሰናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

4. በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው ጓደኝነት ቃል ስለ መግባት ምን ያስገነዝበናል?

4 ክርስቲያን በመሆን ራስን ለአምላክ መወሰን በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህ እርምጃ እንዲሁ ቃል መግባት ማለት ብቻ አይደለም። ይሁንና ራሳችንን መወሰናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ይህን ለመረዳት ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ቃል መግባታቸው ጥቅም የሚያስገኝላቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ለዚህ አንዱ ምሳሌ በሰዎች መካከል የሚመሠረተው ጓደኝነት ነው። ጓደኛ ማፍራት የሚያስገኘውን ጥቅም ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ጓደኝነት የሚያስከትለውን ኃላፊነት መቀበል አለብህ። ይህም ሲባል ለጓደኛህ ቃል መግባትን ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ስለ ጓደኛህ ደኅንነት የማሰብ ግዴታ እንዳለብህ እንዲሰማህ ያደርጋል ማለት ነው። ወዳጅነትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ታሪኮች ሁሉ ጎላ ብሎ የሚታየው ዳዊትና ዮናታን የነበራቸው ጓደኝነት ነው። እንዲያውም ጓደኝነታቸውን በተመለከተ ቃል ኪዳን ተገባብተው ነበር። (1 ሳሙኤል 17:57 እና 18:1, 3ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያለ ቃል ኪዳን የሚገባቡት ከስንት አንድ ቢሆኑም ጓደኛሞች ቃላቸውን ሲፈጽሙ ወይም አንዳቸው ለሌላው ደኅንነት የማሰብ ግዴታ እንዳለባቸው ሲሰማቸው ጓደኝነታቸው ይጠናከራል።—ምሳሌ 17:17 NW፤ 18:24

5. አንድ አገልጋይ ለዘለቄታው የጌታው ባሪያ በመሆን ዘላቂ ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

5 ሰዎች እርስ በርስ ቃል መገባባታቸው ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው የሚጠቁመውን ሌላውን ምሳሌ ደግሞ አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። አንድ አገልጋይ ጥሩ ለሆነው ጌታው ለዘለቄታው ባሪያ በመሆን ደኅንነት ማግኘት ከፈለገ ዘላቂና ጽኑ የሆነ ስምምነት ማድረግ ይችል ነበር። ሕጉ እንደሚከተለው ይላል፦ “አገልጋዩ፤ ‘ጌታዬን፤ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ ነጻ ሆኜ አልሄድም’ ቢል፣ ጌታው ወደ ዳኞች ይውሰደው፤ ወደ በር ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን የእርሱ አገልጋይ ይሆናል።”—ዘፀ. 21:5, 6

6, 7. (ሀ) ሰዎች ቃል መግባታቸው ጥቅም የሚያስገኝላቸው እንዴት ነው? (ለ) ይህ ሁኔታ ከይሖዋ ጋር ስላለን ግንኙነት ምን ይጠቁማል?

6 ጋብቻ ቃል ኪዳንን ለመጠበቅ ብርቱ ጥረት ማድረግ የሚጠይቅ ግንኙነት ነው። አንድ ሰው ቃሉን የሚጠብቀው ለተፈራረመው ውል ብሎ ሳይሆን ቃል ለገባለት ሰው ሲል ነው። በሕግ ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩ ሰዎች እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው ፈጽሞ ደኅንነት አይሰማቸውም። ይሁንና ቃል ኪዳን በመግባት ክቡር ጋብቻ የፈጸሙ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በፍቅር ለመፍታት የሚገፋፏቸው በቂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች አሏቸው።—ማቴ. 19:5, 6፤ 1 ቆሮ. 13:7, 8፤ ዕብ. 13:4

7 በጥንት ዘመን ሰዎች ከንግድና ከሥራ ጋር በተያያዘ ውል መፈጸማቸው ጥቅም ያስገኝላቸው ነበር። (ማቴ. 20:1, 2, 8) በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ንግድ ከመጀመራችን ወይም በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረን ከመሥራታችን በፊት የጽሑፍ ስምምነት ማድረጋችን ወይም ውል መዋዋላችን ጥቅም ያስገኝልናል። ቃል መገባባት ከጓደኝነት፣ ከትዳርና ከሥራ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩትን ግንኙነቶች የሚያጠናክር ከሆነ ከይሖዋ ጋር ባለህ ግንኙነት ራስህን ለእሱ ሙሉ በሙሉ መወሰንህ የበለጠ ጥቅም እንደሚያስገኝልህ ምንም ጥርጥር የለውም! እስቲ በጥንት ዘመን ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ የወሰኑ ሰዎች እንዴት እንደተጠቀሙና ይህ ውሳኔያቸው ከተራ ቃል ኪዳን ያለፈ ነገር ነበር የምንልበትን ምክንያት እንመርምር።

እስራኤላውያን ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰናቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?

8. ለእስራኤላውያን ራስን ለአምላክ መወሰን ምን ትርጉም ነበረው?

8 መላው የእስራኤል ብሔር ራሱን ለይሖዋ የወሰነው ለአምላክ ቃል በገባበት ወቅት ነው። ይሖዋ እስራኤላውያን በሲና ተራራ አጠገብ እንዲሰበሰቡ ካደረገ በኋላ “በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ። (ዘፀ. 19:4-8) ለእስራኤላውያን ራስን መወሰን አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከመግባት የበለጠ ትርጉም ነበረው። እስራኤላውያን ራሳቸውን ሲወስኑ ሙሉ በሙሉ የይሖዋ ንብረት ሆኑ ማለት ነው፤ ይሖዋም እነሱን ‘እንደ ተወደደ ርስቱ’ አድርጎ መመልከት ጀመረ።

9. እስራኤላውያን ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰናቸው የተጠቀሙት እንዴት ነው?

9 እስራኤላውያን የይሖዋ ንብረት መሆናቸው ጥቅም አስገኝቶላቸዋል። ይሖዋ ለእስራኤላውያን ታማኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ልክ አንድ አፍቃሪ ወላጅ ልጁን እንደሚንከባከብ ሁሉ ይሖዋም እነሱን ተንከባክቧቸዋል። አምላክ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሷ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን [አ]ልረሳሽም።” (ኢሳ. 49:15) ይሖዋ በሕጉ አማካኝነት መመሪያ ሰጥቷቸዋል፣ ነቢያቱን በመላክ አበረታቷቸዋል እንዲሁም በመላእክት በኩል ጥበቃ አድርጎላቸዋል። መዝሙራዊው “ቃሉን ለያዕቆብ፣ ሥርዐቱንና ፍርዱን ለእስራኤል ይገልጣል። ይህን ለማንኛውም ሌላ ሕዝብ አላደረገም” በማለት ጽፏል። (መዝ. 147:19, 20፤ መዝሙር 34:7, 19 እና 48:14ን አንብብ።) ይሖዋ በጥንት ጊዜ የነበሩትን ሕዝቦቹን እንደተንከባከበ ሁሉ በዛሬው ጊዜም ራሳቸውን ለእሱ የሚወስኑ አገልጋዮቹን ይንከባከባቸዋል።

ራሳችንን ለአምላክ መወሰን ያለብን ለምንድን ነው?

10, 11. የተወለድነው በአምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ውስጥ ነው? አብራራ።

10 አንዳንድ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወስነው ስለ መጠመቅ ሲያስቡ ‘ራሴን ለአምላክ ሳልወስን እሱን ማገልገል የማልችለው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ፊት ያለንን አቋም በትክክል መገንዘባችን ምክንያቱን ግልጽ ያደርግልናል። አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ሁላችንም ከአምላክ ቤተሰብ ውጭ እንደተወለድን አስታውስ። (ሮም 3:23፤ 5:12) ስለሆነም የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባል ለመሆን ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችን ወሳኝ ነገር ነው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

11 ማናችንም ብንሆን አምላክ ያቀደውን ዓይነት ፍጹም ሕይወት ሊያወርሰን የሚችል ሰብዓዊ አባት የለንም። (1 ጢሞ. 6:19) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአት ሲሠሩ የሰው ዘር አፍቃሪ ከሆነው አባቱና ፈጣሪው ተለየ፤ በዚህም ምክንያት የአምላክ ልጆች ሆነን መወለድ አልቻልንም። (ከዘዳግም 32:5 ጋር አወዳድር።) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መላው የሰው ዘር የሚኖረው ከይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ቤተሰብ ውጭ ከመሆኑም ሌላ ከአምላክ ርቋል።

12. (ሀ) ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ከመጠመቃችን በፊት የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይገባናል?

12 ይሁንና እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ አምላክ የእሱን ሞገስ ያገኙ አገልጋዮቹን ያቀፈው ቤተሰቡ አባላት አድርጎ እንዲቀበለን መጠየቅ እንችላለን። * ታዲያ እንደ እኛ ያሉ ኃጢአተኞች የአምላክ ቤተሰብ አባላት መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “ጠላቶች ሆነን ሳለን በልጁ ሞት አማካኝነት ከአምላክ ጋር [ታረቅን]” በማለት ጽፏል። (ሮም 5:10) በመሆኑም በምንጠመቅበት ጊዜ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት አምላክ ጥሩ ሕሊና እንዲሰጠን እንጠይቀዋለን። (1 ጴጥ. 3:21) ሆኖም ከመጠመቃችን በፊት ልንወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ። አምላክን ማወቅ፣ በእሱ መታመን፣ ንስሐ መግባትና አኗኗራችንን መለወጥ ይኖርብናል። (ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 3:19፤ ዕብ. 11:6) እንደ አምላክ ቤተሰብ አባል ከመቆጠራችን በፊት ልናደርገው የሚገባ ሌላም ነገር አለ። ይህ ነገር ምንድን ነው?

13. አንድ ሰው፣ የአምላክን ሞገስ ያገኙ አገልጋዮቹን ያቀፈው ቤተሰብ አባል ለመሆን ራሱን ለአምላክ ለመወሰን ቃል ኪዳን መግባት አለበት የምንለው ለምንድን ነው?

13 ከአምላክ የራቀ አንድ ሰው፣ የአምላክን ሞገስ ያገኙ አገልጋዮቹን ያቀፈው ቤተሰብ አባል ከመሆኑ በፊት ለይሖዋ ቃል ኪዳን መግባት ያስፈልገዋል። ይህን ለመረዳት እንድንችል አንድ ምሳሌ እንመልከት፤ አንድ የተከበረ አባት ወላጆቹ የሞቱበትን አንድ ወጣት የቤተሰቡ አባል አድርጎ ለመቀበል ፍላጎት ስላደረበት ልጁን የማደጎ ልጅ አድርጎ ለመውሰድ አሰበ እንበል። ይህ አባት በጥሩነቱ የሚታወቅ ሰው ነው። ያም ሆኖ ይህን ወጣት እንደ ልጁ አድርጎ ከመውሰዱ በፊት ልጁ ቃል እንዲገባለት ፈለገ። በመሆኑም ልጁን “አንተን እንደ ልጄ አድርጌ ከመውሰዴ በፊት እንደ አባትህ አድርገህ እንደምትወደኝና እንደምታከብረኝ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ” አለው። ይህ አባት፣ ልጁን የቤተሰቡ አባል አድርጎ የሚቀበለው ልጁ ቃል ለመግባት ፈቃደኛ ከሆነ ብቻ ነው። አባትየው ይህን መጠየቁ ምክንያታዊ አይደለም? በተመሳሳይም ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት አድርጎ የሚቀበላቸው ራሳቸውን ለእሱ ለመወሰን ቃል ለመግባት ፈቃደኛ የሚሆኑትን ሰዎች ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን ለእሱ ብቻ የተወሰነና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ” ይላል።—ሮም 12:1 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል

የፍቅርና የእምነት መግለጫ

14. ራስን መወሰን የፍቅር መግለጫ የሆነው እንዴት ነው?

14 ራሳችንን ለአምላክ ለመወሰን ቃል መግባታችን ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ፍቅር እንዳለን የሚያሳይ ነው። ይህ ሁኔታ በአንዳንድ መንገዶች ከጋብቻ ቃል ኪዳን ጋር ይመሳሰላል። አንድ ክርስቲያን ሙሽራ ምንም ይምጣ ምን ለሙሽሪት ታማኝ እንደሚሆን ቃል በመግባት ለእሷ ያለውን ፍቅር ይገልጻል። ይህም አንድን ነገር ለማከናወን እንዲሁ ቃል መግባትን ብቻ ሳይሆን ለአንድ ግለሰብ ቃለ መሐላ መፈጸምን የሚያመለክት ነው። አንድ ክርስቲያን ሙሽራ ይህን የጋብቻ ቃል ኪዳን ካልገባ ከሙሽሪት ጋር አብሮ የመኖር መብት ሊኖረው እንደማይችል ያውቃል። በተመሳሳይም ራሳችንን ለአምላክ ለመወሰን ቃል እስካልገባን ድረስ የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም በተሟላ ሁኔታ ልናገኝ አንችልም። ፍጽምና የሚጎድለን ቢሆንም እንኳ የአምላክ መሆን ስለምንፈልግና ምንም ይምጣ ምን ለእሱ ታማኝ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ ስላደረግን ራሳችንን ለአምላክ እንወስናለን።—ማቴ. 22:37

15. ራስን መወሰን የእምነት መግለጫ የሆነው እንዴት ነው?

15 ራስን ለአምላክ መወሰን እምነት እንዳለን ያሳያል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ወደ እሱ መቅረባችን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንድንተማመን ያደርገናል። (መዝ. 73:28) “በጠማማና በወልጋዳ ትውልድ መካከል” እየኖሩ ከአምላክ ጋር መሄድ ሁልጊዜ ቀላል እንዳልሆነ እናውቃለን፤ ይሁንና አምላክ የምናደርገውን ጥረት ሁሉ እንደሚደግፍ በገባው ቃል ላይ እንተማመናለን። (ፊልጵ. 2:15፤ 4:13) ፍጹም እንዳልሆንን እናውቃለን፤ ሆኖም ስህተት በምንሠራበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ በምሕረት ዓይን እንደሚያየን እምነት አለን። (መዝሙር 103:13, 14ን እና ሮም 7:21-25ን አንብብ።) በተጨማሪም ይሖዋ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እንደሚባርከው እንተማመናለን።—ኢዮብ 27:5 NW

ራስን ለአምላክ መወሰን ደስታ ያስገኛል

16, 17. ራስን ለይሖዋ መወሰን ደስታ ያስገኛል የምንለው ለምንድን ነው?

16 ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ሁለንተናችንን ለእሱ መስጠታችን ስለሆነ ደስታ ያስገኝልናል። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት አንድ ሐቅ ተናግሯል። (ሥራ 20:35) ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ ሙሉ በሙሉ አጣጥሟል። ሰዎች የሕይወትን መንገድ እንዲያገኙ ለመርዳት ሲል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ እረፍቱንና ምቾቱን መሥዋዕት ያደረገበት እንዲሁም ያልበላበት ጊዜ ነበር። (ዮሐ. 4:34) ኢየሱስ የአባቱን ልብ ደስ ማሰኘት ደስታ ይሰጠው ነበር። “ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” ብሏል።—ዮሐ. 8:29፤ ምሳሌ 27:11

17 በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹን “ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ” በማለት እርካታ ማግኘት የሚቻልበትን የሕይወት ጎዳና ጠቁሟቸዋል። (ማቴ. 16:24) እኛም እንዲህ ማድረጋችን ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ያደርገናል። ራሳችንን ልንሰጠው የምንችል ከእሱ የበለጠ አሳቢና አፍቃሪ የሆነ ማን አለ?

18. ራሳችንን ለይሖዋ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራችን ለማንኛውም አካል ወይም ለምንም ነገር ራሳችንን ብንወስን ልናገኝ ከምንችለው የበለጠ ደስታ ያስገኝልናል የምንለው ለምንድን ነው?

18 ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንና የእሱን ፈቃድ በማድረግ ከውሳኔያችን ጋር ተስማምተን መኖራችን ለማንኛውም አካል ወይም ለምንም ነገር ራሳችንን ብንወስን ልናገኝ ከምንችለው የበለጠ ደስታ ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ ሰዎች መላ ሕይወታቸውን ቁሳዊ ሀብት ለማሳደድ ይጠቀሙበታል፤ ይሁን እንጂ እውነተኛ ደስታም ሆነ እርካታ አያገኙም። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎች ግን ዘላቂ ደስታ ያገኛሉ። (ማቴ. 6:24) እነዚህ ሰዎች ‘ከአምላክ ጋር አብሮ የመሥራት’ ክቡር መብት ማግኘታቸው ደስታ ያስገኝላቸዋል፤ ያም ሆኖ ራሳቸውን የወሰኑት ለሥራው ሳይሆን አድናቂ ለሆነው አምላካችን ነው። (1 ቆሮ. 3:9) አገልጋዮቹ የሚከፍሉትን መሥዋዕት ከእሱ የበለጠ የሚያደንቅ የለም። ሌላው ቀርቶ ታማኝ አገልጋዮቹ ለዘላለም የእሱን እንክብካቤ እንዲያገኙ ወደ ወጣትነት ይመልሳቸዋል።—ኢዮብ 33:25፤ ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።

19. ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሰዎች ምን መብት ያገኛሉ?

19 ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ከእሱ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖርህ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕ. 4:8፤ መዝ. 25:14) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የይሖዋ ንብረት ለመሆን ባደረግነው ምርጫ መተማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” እስከ ሺው ዓመት ፍጻሜ ድረስ የአምላክ ልጆች አይሆኑም። ይሁን እንጂ ለአምላክ ራሳቸውን ስለወሰኑ አምላክን “አባታችን” ብለው መጥራት ይችላሉ፤ እንዲሁም የይሖዋ አምላኪዎችን ያቀፈው ቤተሰብ አባላት ሆነው መቆጠር ይችላሉ።—ዮሐ. 10:16፤ ኢሳ. 64:8፤ ማቴ. 6:9፤ ራእይ 20:5

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ራስን ለአምላክ መወሰን ሲባል ምን ማለት ነው?

• ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

• ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰን ያለባቸው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከውሳኔያችን ጋር ተስማምተን መኖራችን ዘላቂ ደስታ ያስገኝልናል