በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ክርስቲያን ለመባል በሥላሴ ማመን ያስፈልጋል?

ክርስቲያን ለመባል በሥላሴ ማመን ያስፈልጋል?

በ2007 የታተመ ዎርልድ ሪሊጅንስ ኢን ዴንማርክ የተባለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሲገልጽ ‘መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ የሚከተል አናሳ የክርስቲያኖች ቡድን’ በማለት ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት በዴንማርክ ካሉት ሃይማኖቶች በአባላት ብዛት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ይሁን እንጂ የዳኒሽ ብሔራዊ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ፣ ጸሐፊዋ ባዘጋጁት የመማሪያ መጽሐፍ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን በመጥቀሳቸው ክፉኛ ተችተዋቸዋል። ለምን? ጳጳሱ እንዲህ ያሉበትን ምክንያት ሲጠቅሱ “[የይሖዋ ምሥክሮችን] ክርስቲያን አድርጎ የሚቆጥር የሃይማኖት ምሑር አጋጥሞኝ አያውቅም። . . . እነሱ የክርስትና ሃይማኖት ዋና መሠረት የሆነውን የሥላሴ ትምህርት ይክዳሉ” በማለት ተናግረዋል።

የመጽሐፉ ደራሲና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያጠኑት አኒካ ህፊታማር እንደገለጹት ከሆነ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ክርስቲያን አድርገው የሚቆጥሩት ለምን እንደሆነ ሲጠየቁ ‘አምላክ ሥላሴ እንደሆነ ስለማምን ነው’ ብለው የሚናገሩ ሰዎች የሉም። ከዚህም በላይ “ክርስቲያን ነህ?” የሚል ርዕስ ያለው የመጽሐፉ ክፍል እንዲህ ይላል፦ “የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለመረዳት አስቸጋሪ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች ሁሉ በጣም አስቸጋሪው ነው።” አክሎም “ምንጊዜም ቢሆን የሃይማኖት ትምህርት ላልተከታተለ ሰው የክርስቲያኖች አምላክ አንድም ሦስትም ናቸው ብሎ ማስረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው” ብሏል።

“የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለመረዳት አስቸጋሪ ከሆኑት የክርስትና ትምህርቶች ሁሉ በጣም አስቸጋሪው ነው”

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክም ሆነ ስለ ክርስቶስ የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽና ቀላል ነው። እንዲሁም ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። “ሥላሴ” የሚለው ቃልም ሆነ ስለ ሥላሴ የሚናገር ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ የበኩር ልጅ እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ቆላስይስ 1:15) በተጨማሪም ኢየሱስ ‘በአምላክና በሰው መካከል የሚገኝ አስታራቂ’ እንደሆነ ይገልጻል። (1 ጢሞቴዎስ 2:5) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ ሲናገር “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ነው” ይላል።—መዝሙር 83:18 NW

የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በኢየሱስ ማመናቸው ወሳኝ ነገር እንደሆነ ያምናሉ። (ዮሐንስ 3:16) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ “‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ በቁም ነገር ይመለከቱታል። (ማቴዎስ 4:10) ከዚህ ለመመልከት እንደሚቻለው አንድ ሰው ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ የሚችለው የኢየሱስን ትእዛዝ ለማክበር ጥረት ካደረገ ብቻ ነው።