በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚስዮናውያን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተላኩ

ሚስዮናውያን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተላኩ

127ኛው የጊልያድ ምረቃ

ሚስዮናውያን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተላኩ

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ሄደው እንዲመሠክሩ ተልዕኮ ሰጥቷቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ በቁም ነገር ይመለከቱታል።

እንዲያውም በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሥልጠና ያገኙ ሚስዮናውያን ከ65 ለሚበልጡ ዓመታት ይህን የስብከት ሥራ ከ200 በሚበልጡ አገሮች በግንባር ቀደምትነት ሲሠሩ ቆይተዋል። ቅዳሜ፣ መስከረም 12, 2009 ደግሞ ተሞክሮ ያላቸው ሌሎች 56 አገልጋዮች በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት አምስት ወር ከሠለጠኑ በኋላ ተመርቀዋል።

በዓይነ ሕሊና መመልከት ያለው ጥቅምና ጉዳት

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባልና የምረቃ ፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት “በዓይነ ሕሊናችሁ የመሳል ችሎታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት” በሚል ጭብጥ ለተመራቂዎቹ ንግግር አቀረበ። በመጀመሪያ ተመራቂዎቹ በዓይነ ሕሊናቸው መሳል የሌለባቸውን አራት ነገሮች ተናገረ። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦ (1) ቁሳዊ ነገሮች ዘላቂ ጥበቃ ያስገኝልናል ብላችሁ አታስቡ፣ (2) ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ነገሮች በዓይነ ሕሊናችሁ አትሳሉ እንዲሁም (3) ነገ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል በዓይነ ሕሊናችሁ በመሳል ከሚገባው በላይ አትጨነቁ። (ምሳሌ 18:11፤ ማቴዎስ 5:28፤ 6:34) ወንድም ሌት፣ ሦስተኛውን ነጥብ አስመልክቶ ሲናገር አንድ ሰው ከመጠን በላይ የሚጨነቅ ከሆነ በትላንትናው ጭንቀት ላይ የዛሬውን ይጨምርና የነገውን ደግሞ ስቦ ወደ ዛሬ ለማምጣት እንደሚንጠራራ ያህል እንደሆነ ገልጿል። “ይህ ደግሞ ለመሸከም በጣም ከባድ ይሆናል” በማለት ተናግሯል። አራተኛው ነጥብስ ምንድን ነው? ወንድም ሌት፣ ተመራቂዎቹ ሚስዮናዊ ከመሆናቸው በፊት የነበራቸው ሕይወት የተሻለ እንደነበር አድርገው በዓይነ ሕሊናቸው እንዳይስሉ አስጠንቅቋል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ በአዲሱ ምድባቸው ሊያገኙት የሚችሉትን ደስታ ያጣሉ።

ወንድም ሌት በመቀጠል ተመራቂዎቹ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አራት ነገሮችን በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ አበረታታቸው። እንዲህ አለ፦ (1) መንፈሳዊ ወይም አካላዊ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን አስቀድማችሁ ተመልክታችሁ ሊደርስባችሁ የሚችለውን አደጋ አስወግዱ፣ (2) የምታነቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በዓይነ ሕሊናችሁ ሳሉ፤ እንዲሁም ራሳችሁን የታሪኩ አካል አድርጋችሁ ሳሉ፣ (3) በአዲሱ ምድባችሁ ውስጥ የምታነጋግሩት እያንዳንዱ ሰው የይሖዋ አገልጋይ ሊሆን እንደሚችል አስቡ እንዲሁም (4) ራሳችሁን በምትሰብኩላቸው ሰዎች ቦታ አድርጋችሁ በማሰብ ለእነሱ ርኅራኄ አሳዩ።—ምሳሌ 22:3

ሌሎችን ማሠልጠን ያለው ጠቀሜታ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን በ2 ጢሞቴዎስ 2:2 ላይ የተመሠረተ “እነዚህን ነገሮች ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ” የሚል ንግግር አቀረበ። ሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን እንዲያሠለጥን ለጢሞቴዎስ በነገረው ጊዜ ጳውሎስ አስቦ የነበረው ጢሞቴዎስ ለእነዚህ ሰዎች እውነትን እንዲያስተምር ብቻ ሳይሆን እነሱም ለሌሎች ሰዎች ሥልጠና እንዲሰጡ እንዲያበረታታቸው ነበር። ወንድም ስፕሌን፣ ለተመራቂዎቹ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት የሚካፈሉ ወንዶች በጣም እንደሚያስፈልጉ ተናገረ። እነዚህ ወንዶች የሚሠለጥኑት መቼና እንዴት ነው? ወንድም ስፕሌን፣ ሚስዮናውያኑ ወደ ምድብ ቦታቸው ሄደው ወንድ ጥናቶችን እንዳገኙ ወዲያው ሥልጠና መስጠት እንዲጀምሩ አበረታታቸው።

ሚስዮናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸው ለሌሎች ታማኝ ምሳሌ እንዲሆኑ ማሠልጠን የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ወንድም ስፕሌን በርካታ መንገዶችን ተናግሯል። ሚስዮናውያን፣ ተማሪዎቻቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በደንብ እንዲዘጋጁ ሊያሠለጥኗቸው ይገባል። ተማሪዎቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምሩ ደግሞ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለሚቀርበው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት እንዴት አስቀድመው መዘጋጀት እንዳለባቸው መሠልጠን ያስፈልጋቸዋል። ወንድም ስፕሌን፣ “አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በግሉ ካላጠና ሌሎችን በፍጹም ማስተማር አይችልም” በማለት ተናገረ። አክሎም ሚስዮናውያን ጥናቶቻቸው ሰዓት አክባሪ እንዲሆኑ፣ የስብከቱን ሥራ በገንዘብ እንዲደግፉና አመራር ለሚሰጡ ወንድሞች ታዛዥ እንዲሆኑ ማበረታታት እንደሚችሉ ገልጿል። ይህን የመሰለውን ሥልጠና መስጠት የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ በመገኘት እንደሆነ ተናግሯል።

የይሖዋ ምሥክር መሆን ልዩ መብት ነው

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ ደግሞ ኢየሱስ በሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ በተናገረው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ “ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚል ንግግር አቀረበ። ወንድም ፒርስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን የይሖዋ ምሥክር የመሆን መብታቸውን እንዳጡ ለተመራቂዎቹ ተናገረ። ይህ መብት የመንግሥቱን ፍሬ ለሚያፈራ ሕዝብ ተሰጠ። (ማቴዎስ 21:43) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ይህ ሕዝብ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈው ጉባኤ ነው። ወንድም ፒርስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ቅዱስ ብሔር” የተባለው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን የይሖዋን ድንቅ ባሕርያት ‘በስፋት እንደሚያስታውቅ’ ተናግሮ እንደነበር ገለጸ። (1 ጴጥሮስ 2:6-9) እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቲያኖች ስለ ይሖዋ መመሥከራቸውን ትተው ስለ እሱ ብቻ ይመሠክራሉ ማለቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ደግሞም ኢየሱስ ራሱ “የታመነ ምሥክር” ተብሎ ተጠርቷል። (ራእይ 1:5፤ 3:14) ኢየሱስ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የይሖዋ ምሥክር ነው፤ እኛም የእሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 2:21

ወንድም ፒርስ፣ ኢየሱስ በሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ የተናገራቸው ቃላት በዘመናችን ትልቅ ትርጉም እንዳላቸው ለተመራቂዎቹ ተናገረ። እንዲህ ያለው ለምን ነበር? በራእይ 11:15 ላይ የሚገኘው ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ትንቢት ፍጻሜውን ስላገኘ ነው! የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ተቋቁሟል። በአሁኑ ጊዜ ምሥክርነት የመስጠቱ ሥራ ቃል በቃል “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እየተሠራ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) ወንድም ፒርስ፣ ሚስዮናውያን መመሥከር ያለባቸው ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ እንጂ ስለ ራሳቸው፣ ስለ ቀድሞ አኗኗራቸው፣ ስለ ባሕላቸውና ስለ አገራቸው መሆን እንደሌለበት ጎላ አድርጎ ገለጸ። ተመራቂዎቹን “በቀረው ጊዜ የተቻላቸውን ያህል ብዙ ሰዎችን” እንዲያስተምሩ አበረታቷቸዋል።

የፕሮግራሙ ጎላ ያሉ ሌሎች ገጽታዎች

በሕትመት ኮሚቴ ውስጥ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም አሊክስ ራይንሙለር “ይሖዋ ድፍረት ይሰጣችኋል” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ሚስዮናውያን በይሖዋ ኃይል የሚተማመኑ ከሆነ እሱ ጠንካራ ጎናቸውን እንዲያውቁ፣ ድክመታቸውን አምነው እንዲቀበሉ፣ ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉና ለአምላክ ምርጣቸውን እንዲሰጡ እንደሚረዳቸው ተናገረ።

ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን በሚከታተለው ክፍል ውስጥ የሚሠሩት ወንድም ሳም ሮበርሰን እና ወንድም ዊልያም ሳሙኤልሰን የተባሉ አስተማሪዎች ለተማሪዎቹ ንግግር አቅርበዋል። ወንድም ሮበርሰን በኢሳይያስ 41:10 ላይ የተመሠረተ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” የሚል ንግግር አቀረበ። ወንድም ሮበርሰን፣ ሚስዮናውያን ብዙ አስደሳች ነገሮች እንደሚኖሯቸው ገለጸ። እንዲሁም ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ተናገረ። ይሁንና አፍቃሪ አባቱ እንዲረዳው በጸሎት የጠየቀውን የንጉሥ ዳዊትን ምሳሌ የሚከተሉ ከሆነ እነሱም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም ይችላሉ። (መዝሙር 34:4, 6, 17, 19) ወንድም ሳሙኤልሰን ያቀረበው ንግግር የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላ ነበር። ሚስዮናውያን እንዲህ ማድረጋቸው ደስ የማይል አስተያየት ሲሰነዘርባቸው አጸፋውን እንዳይመልሱ እንዲሁም በቀላሉ እንዳይበሳጩ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 2:10, 11

በጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ ውስጥ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ጂም ማንትስ፣ በጆርጂያ ሪፑብሊክና በሆንዱራስ ውስጥ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሆነው ለሚያገለግሉ ሁለት ወንድሞች እንዲሁም የታጂኪስታን ሪፑብሊክ የአገር ኮሚቴ አባል ለሆነው ወንድም ቃለ መጠይቅ አደረገ። እነዚህ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ሚስዮናውያኑ ‘ክፉውን በመልካም በማሸነፍ’ ኃይለኛ የሆኑ ሰዎችን እንዴት ወዳጅ ማድረግ እንደሚችሉ ምክር ሰጡ። (ሮም 12:21) የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር፣ ተማሪዎቹ በጊልያድ በቆዩባቸው ወራት ሲያገለግሉ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች እንዲናገሩ ቃለ ምልልስ አደረገላቸው። ቃለ ምልልሱ “አቤት፣ ምን ልርዳዎት?” የሚል ስሜት ቀስቃሽ ጭብጥ ነበረው።

ሊቀ መንበሩ ከአዲሱ የመዝሙር መጽሐፍ ላይ “ራስህን ሁሉም ነገር አዲስ በሆነበት ሥርዓት ውስጥ ሳል” የሚለውን መዝሙር አንዳንድ ስንኞች በመጥቀስ ፕሮግራሙን ደመደመ። በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት 6,509 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች “እስከ ምድር ዳር ድረስ” የይሖዋና የልጁ ምሥክሮች ለመሆን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ወደየመጡበት ሄደዋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገን ሰንጠረዥ/​ካርታ]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

8 የተውጣጡባቸው አገሮች

56 ተማሪዎች

28 ባልና ሚስት

33.6 አማካይ ዕድሜ

18.3 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፉት ዓመታት በአማካይ

13.6 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ

[ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ተመራቂዎቹ የተመደቡት ከታች ወደሚገኙት 22 አገሮች ነው

ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገሮች

አልባኒያ

ቦሊቪያ

ቡሩንዲ

ካምቦዲያ

ቺሊ

ኮንጎ ዲሞ. ሪፑ.

ኮስታ ሪካ

ኮት ዲቩዋር

ኩራሳኦ

ጋያና

ሄይቲ

ጃማይካ

ሞልዶቫ

ሞዛምቢክ

ኔፓል

ኒካራጓ

ፓናማ

ፓራጓይ

ፔሩ

ሰርቢያ

ታንዛኒያ

ኡጋንዳ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ127ኛው ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ማርሸል ታራ፣ ፕሩደንት ሎሪ፣ ማሽበርን አላነ፣ ሮዘንስትሮም ሳኒ፣ ቴስታ አሊግዛንድረ፣ ታኪያማ ሚሼል፣ ሲስክ ሞኒካ

(2) ግሩምስ ካረ፣ ሚውረ ሳዩሪ፣ ካማቾ ማይደር፣ ሮሳስ ሱሳና፣ ቡርክ ማሪየላ፣ ሜሳ ኢሊያና፣ ያንግ ግሎሪያ፣ ጌረት ሻነን

(3) ቦኒያ ክላሪስ፣ ክናለር ደኒዝ፣ ፓራለስ ሪቸል፣ ሆቴ ሱቪ፣ ታካዳ ኤሚ፣ ቱርናድ ሚርያም፣ ሶፔል ክሪስቲና

(4) ሚውረ ዩኢኪሮ፣ ፓራለስ ኬነዝ፣ ፕሩደንት ካርኖቭ፣ ኮልበርን ሻነን፣ ዊለስ ሊያ፣ ቫረነን አና፣ ሲስክ ብራድሊ፣ ታካዳ ሪቻርድ

(5) ግሩምስ ጆ፣ ቫረነን ማርኩስ፣ ጌረት ብራየን፣ ስታክሃውስ ሩት፣ ዊልሰን ኤሚ፣ ቦኔል ኤስትሬለ፣ ካማቾ ዴቪድ፣ ሜሳ ራነልድ፣ ቦኔል ማኒ

(6) ታኪያማ ሺንጂ፣ ቴስታ ጁልያኖ፣ ኮልበርን ትሬ፣ ማሽበርን ኮሪ፣ ዊለስ ዊሊ፣ ቱርናድ ሎራን፣ ቡርክ ዮኤል፣ ስታክሃውስ ጆርዳን

(7) ዊልሰን ጄምስ፣ ያንግ ጆሹዋ፣ ማርሸል ኤሪክ፣ ሮሳስ ማርኮስ፣ ክናለር ጃን፣ ሆቴ ኒኮ፣ ሮዘንስትሮም አስኮ፣ ሶፔል ጆ፣ ቦኒያ ኦስካር