በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድር ሁልጊዜ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ይኖራት ይሆን?

ምድር ሁልጊዜ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ይኖራት ይሆን?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ምድር ሁልጊዜ ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ይኖራት ይሆን?

▪ ውብ የሆነችው ፕላኔቷ ምድራችን ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችል አስደናቂ አቅም አላት። ይሁንና የሕዝብ ብዛት በፍጥነት እየጨመረ ሲመጣና የምድር ሀብት በአስደንጋጭ ፍጥነት ሲበዘበዝ ‘ያልተጠበቀ ነገር ይከሰት ይሆን?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በእርግጥም ምድር ሁልጊዜ በቂ የሆነ ምግብና የተፈጥሮ ሀብት ማቅረብ ትችል ይሆን?

በዚህ ጥያቄ ላይ ስናሰላስል አምላክ ከ4,000 ዓመታት በፊት “ምድር እስካለች ድረስ፣ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት፣ አይቋረጡም” በማለት ለሰው ዘር የገባው ቃል ያጽናናናል። (ዘፍጥረት 8:22) በመሆኑም ፀሐይ በየዕለቱ እንደምትወጣ በእርግጠኝነት እንደምንጠብቀው ሁሉ ምድር ሕይወት እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስፈልገውን ነገር መስጠቷ የሚያቆምበት ጊዜ እንደማይኖር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

“ፕላኔቷ ትመግበን ይሆን?” በሚል ርዕስ በ2004 በወጣ አንድ ሪፖርት ላይ አሊክስ ከርቢ የተባሉ የአካባቢ ጥበቃ ዜና ዘጋቢ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ዓለም ሁሉንም ሰው ለመመገብ የሚያስችል በቂ ምግብ ታመርታለች። ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ ምግቡ የሚገኘው በተሳሳተ ቦታ ነው፤ ወይም ዋጋው ውድ ነው። አሊያም ለረጅም ጊዜ መቀመጥ የማይችል ነው። ስለሆነም ሁሉም ሰው በቂ ምግብ እንዲያገኝ የማድረጉ ሁኔታ የተመካው በሳይንስ ላይ ሳይሆን በፖለቲካ ላይ ነው።” ምድር ተገቢው ክትትል ከተደረገላትና የምድር ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ እጥረት ያጋጥማል ብለን የምንሰጋበት ምክንያት አይኖርም። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንቷ የእስራኤል ዘመን አምላክ መሬትን በአግባቡ መጠቀምን በተመለከተ ግልጽ የሆነ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። በዘሌዋውያን 25:4 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አምላክ ለእስራኤላውያን “በሰባተኛው ዓመት ግን ምድሪቱ የዕረፍት ሰንበት ታድርግ፤ . . . በዕርሻህ ላይ አትዝራ” ብሏቸው ነበር። በሰባት ዓመት አንዴ ምድሪቱን ባያርሱም እንኳ አምላክ ለሕዝቡ የተትረፈረፈ ምርት እንደሚያገኝና የምግብ እጥረት ያጋጥመናል የሚል ስጋት እንደማይገባው ቃል ገብቶ ነበር።—ዘሌዋውያን 26:3-5

ምንም እንኳ በዛሬው ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በቅንነት ተነሳስተው በምድርና በተፈጥሮ ሀብቷ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማስተካከል ጥረት ቢያደርጉም ብዙዎች እንዲህ ዓይነቱ ጥረት ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንደሚባለው ዓይነት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ራእይ 11:18 ዘላቂ የሆነው ብቸኛ መፍትሔ ከየት ሊገኝ እንደሚችል ይጠቁማል። እዚህ ጥቅስ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን እንደሚያጠፋ’ ይናገራል። ይሖዋ ምድርንም ሆነ የተፈጥሮ ሀብቷን ያላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎችን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ምድር ለነዋሪዎቿ በሙሉ የሚበቃ የተትረፈረፈ ምግብ እንድታመርት ያደርጋል። ከዚያ በኋላ የአምላክን ዓላማ ሆን ብለው ችላ የሚሉም ሆኑ የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ምድርን የሚበዘብዙ ሰዎች አይኖሩም። በሌላ በኩል ግን የይሖዋን አገዛዝ በፈቃደኝነት የሚደግፉ ሰዎች በመዝሙር 72:16 ላይ የሚገኘው ‘በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዛል’ የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ ይመለከታሉ።

ይሖዋ ፈጽሞ በማይከስመው ፍቅሩና በጥበቡ ተገፋፍቶ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንዲኖሩ ብሎም መኖሪያቸውን እንዲንከባከቡ የማድረግ ዓላማ አውጥቷል። (ዘፍጥረት 1:28) በእሱ አገዛዝ ሥር ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የምድርን የተፈጥሮ ሀብት ሳያባክኑ እንዴት በጥበብ መጠቀም እንደሚችሉ ይማራሉ። የሕያዋን ፍጥረታትን ፍላጎት ሁሉ የሚያረካ እንዲህ ያለ አፍቃሪ ሰጪ ያለን በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን!—መዝሙር 145:16

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሁሉም ሰው በቂ ምግብ እንዲያገኝ የማድረጉ ሁኔታ የተመካው በሳይንስ ላይ ሳይሆን በፖለቲካ ላይ ነው”