በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለውጦች ቢያጋጥሙም የአምላክን ሞገስ ሳያጡ መኖር

ለውጦች ቢያጋጥሙም የአምላክን ሞገስ ሳያጡ መኖር

ለውጦች ቢያጋጥሙም የአምላክን ሞገስ ሳያጡ መኖር

በሕይወትህ ውስጥ ለውጦች አጋጥመውሃል? እነዚህን ለውጦች መቀበልስ አስቸጋሪ ሆኖብሃል? አብዛኞቻችን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞናል ወይም ወደፊት ያጋጥመን ይሆናል። በጥንት ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ አጋጥሟቸው የነበረውን ነገር እንደ ምሳሌ መመልከታችን በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ባሕርያትን እንድናውቅ ያስችለናል።

ለምሳሌ ያህል፣ በሕይወቱ ውስጥ በርካታ ለውጦች አጋጥመውት የነበሩትን ዳዊትን እንመልከት። ዳዊት፣ ንጉሥ እንዲሆን በሳሙኤል በተቀባበት ወቅት እረኛ ነበር። ዳዊት ገና ልጅ እያለ ጎልያድ የተባለን ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ ለመግጠም ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ። (1 ሳሙ. 17:26-32, 42) ወጣቱ ዳዊት በንጉሥ ሳኦል ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዲኖር ተጋበዘ፤ ከዚያም የሠራዊቱ አለቃ እንዲሆን ተሾመ። ዳዊት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ያጋጥሙኛል ብሎ አስቦ ላያውቅ ይችላል፤ ወይም ከዚያ በኋላ ስለሚያጋጥሙት ነገሮች ምንም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

ከጊዜ በኋላ ዳዊት ከሳኦል ጋር የነበረው ግንኙነት በጣም ሻከረ። (1 ሳሙ. 18:8, 9፤ 19:9, 10) ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን ለበርካታ ዓመታት በስደት ለመኖር ተገዷል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በተለይ ደግሞ ምንዝር ፈጽሞ ይህን ኃጢአቱን ለመሸፋፈን ሲል ሰው ከገደለ በኋላ ሁኔታዎቹ በእጅጉ ተለዋውጠው ነበር። ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት የቤተሰቡን ሕይወት አመሰቃቅሎበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጁ አቤሴሎም በእሱ ላይ ዓምፆአል። (2 ሳሙ. 12:10-12፤ 15:1-14) ያም ሆኖ ዳዊት ለፈጸመው ምንዝርና ግድያ ንስሐ ገብቶ ይሖዋ ይቅር ካለው በኋላ የአምላክን ሞገስ እንደገና ማግኘት ችሏል።

አንተም በሕይወትህ ውስጥ የተለያዩ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። የጤና መቃወስ፣ የኢኮኖሚ ወይም የቤተሰብ ችግር አልፎ ተርፎም የምንወስዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ያስከትሉብን ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በተሻለ መልኩ ለመቋቋም የትኞቹ ባሕርያት ሊረዱን ይችላሉ?

ትሕትና ይረዳናል

ትሕትና የእሺ ባይነትን መንፈስ ማሳየትን ይጨምራል። እውነተኛ ትሕትና የራሳችንንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ትክክለኛ ማንነት እንድናስተውል ይረዳናል። ሌሎች ያሏቸውን ባሕርያትና ያገኟቸውን ስኬቶች አለማጣጣላችን ስለ ማንነታቸውም ሆነ ስላደረጉት ነገር የበለጠ እንድንረዳ ያስችለናል። በተመሳሳይም ትሕትና አንድ ነገር ለምን እንደደረሰብንና ምን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን እንድናስተውል ያስችለናል።

የሳኦል ልጆ የሆነው ዮናታን በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ዮናታን ከእሱ ቁጥጥር ውጪ በተከናወኑ ነገሮች ምክንያት የነበረበት ሁኔታ ተለውጧል። ሳሙኤል ይሖዋ መንግሥቱን ከእሱ እንደሚወስድ ለሳኦል በነገረው ጊዜ ዮናታን ንጉሥ እንደሚሆን የተናገረው ነገር አልነበረም። (1 ሳሙ. 15:28፤ 16:1, 12, 13) አምላክ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ መምረጡ ዮናታንን ለንጉሥነት እንደማይፈልገው የሚያሳይ ነበር። የሳኦል ታዛዥ አለመሆን በሆነ መንገድ በዮናታን ላይ መጥፎ ውጤት አስከትሎ ነበር። ዮናታን ያጠፋው ነገር ባይኖርም እንኳ በአባቱ ምትክ ንጉሥ እንዲሆን ሳይመረጥ ቀርቷል። (1 ሳሙ. 20:30, 31) ታዲያ ዮናታን ምን ተሰማው? ንጉሥ የመሆን አጋጣሚ ስላመለጠው በዳዊት ላይ ቀንቶ ቂም ይዞበታል? በፍጹም። ዮናታን ከዳዊት በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ በጣም የሚበልጥ ቢሆንም በታማኝነት ዳዊትን ደግፏል። (1 ሳሙ. 23:16-18) ዮናታን ትሑት መሆኑ አምላክ የመረጠው ማንን እንደሆነ እንዲረዳ ስላስቻለው “ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ” እንዳይመለከት ረድቶታል። (ሮም 12:3) ይሖዋ ከእሱ የሚጠብቀውን ነገር የተረዳ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ የወሰነውን ውሳኔም ተቀብሏል።

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ለውጦች አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። በአንድ ወቅት ዮናታን ለእሱ ቅርብ ከነበሩ ሁለት ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮበት ነበር። አንደኛው የወደፊቱ ንጉሥና በይሖዋ የተመረጠው ጓደኛው ዳዊት ነበር። ሌላው ደግሞ ይሖዋ የተወውና ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ የነበረው አባቱ ሳኦል ነበር። ይህ ሁኔታ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ይጥር በነበረው በዮናታን ላይ ውጥረት ፈጥሮበት መሆን አለበት። እኛም በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን አንዳንድ ለውጦች ጭንቀትና ፍርሃት ያስከትሉብን ይሆናል። ሆኖም የይሖዋን አመለካከት ለመረዳት የምንጥር ከሆነ ለውጡ የሚያስከትልብንን ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመን ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን መቀጠል እንችላለን።

ልክን ማወቅ ያለው ጠቀሜታ

አንድ ሰው ልኩን ማወቁ አስፈላጊ ነው። ይህ ባሕርይ ከትሕትና ጋር ሊምታታብን አይገባም። አንድ ሰው ትሑት ቢሆንም ልኩን ወይም አቅሙን ሙሉ በሙሉ ላይረዳ ይችላል።

ዳዊት ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ንጉሥ እንዲሆን በይሖዋ የተመረጠ ቢሆንም ለብዙ ዓመታት ዙፋን ላይ መውጣት አልቻለም ነበር። ዳዊት ሥልጣን የሚይዝበት ጊዜ የዘገየበትን ምክንያት ይሖዋ እንደነገረው የሚገልጽ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አናገኝም። ይህ ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢመስልም እንኳ አልተረበሸም። ዳዊት ልኩን ያውቅ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሁኔታውን የፈቀደው ይሖዋ ስለሆነ ለጉዳዩ እልባት እንደሚሰጥ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ዳዊት ሕይወቱን ለማዳን በሚል ሰበብ እንኳ ሳኦልን ለመግደል አልተነሳም፤ እንዲያውም ወዳጁ የሆነው አቢሳ ሳኦልን ለመግደል ሲሞክር ከልክሎታል።—1 ሳሙ. 26:6-9

አንዳንድ ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ አንድ ያልገባን ነገር ይፈጸም ወይም ከእኛ አመለካከት አንጻር በተሻለ መንገድ ሊሠራ ይችል እንደነበረ የሚሰማን ነገር ይከሰት ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ልካችንን በማወቅ ኢየሱስ የጉባኤው ራስ እንደሆነና አመራር ለመስጠት በተሾሙ ሽማግሌዎች አማካኝነት እንደሚጠቀም አምነን እንቀበላለን? የይሖዋን ሞገስ እንዳገኘን ለመቀጠል ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚወስደውን እርምጃ መጠበቅ እንዳለብን በመገንዘብ ልካችንን የምናውቅ ሰዎች መሆናችንን እናሳያለን? ይሖዋ የሚወስደውን እርምጃ መጠበቅ ተፈታታኝ ቢሆንም እንኳ ልካችንን በማወቅ እንደዚያ እናደርጋለን?—ምሳሌ 11:2

ገርነት አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል

ገርነት ወይም የዋህነት የሚደርስብንን ጉዳት ሳንበሳጭ፣ ቅሬታ ሳይሰማንና ቂም ሳንይዝ በትዕግሥት እንድንወጣው ያስችለናል። ገርነትን ማዳበር ቀላል አይደለም። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ‘ገሮች ምድርን ይወርሳሉ’ በማለት ይህን ባሕርይ እንድናዳብር ያበረታታናል። (ማቴ. 5:5) ገርነት ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከትሕትናና ልክን ከማወቅ ጋር ተዛማጅነት አለው፤ ይሁን እንጂ እንደ ጥሩነትና የዋህነት ያሉ ባሕርያትንም ሊያጠቃልል ይችላል። ገር የሆነ ሰው ለመማር ፈቃደኛ ስለሆነና ለመቀረጽ ጥረት ስለሚያደርግ በመንፈሳዊ እድገት ማድረግ ይችላል።

ገርነት በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ለውጦች እንዳመጣጣቸው እንድናስተናግድ የሚረዳን እንዴት ነው? ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው ለውጦች ጥሩ አመለካከት እንደሌላቸው ሳታስተውል አትቀርም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ለውጦች በይሖዋ ይበልጥ ለመሠልጠን የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱልናል። የሙሴ ሕይወት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

ሙሴ የ40 ዓመት ሰው እያለም በጣም ግሩም ባሕርያት ነበሩት። የአምላክ ሕዝቦች ደኅንነት ያሳስበው የነበረ ከመሆኑም ሌላ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንደነበረው አሳይቷል። (ዕብ. 11:24-26) ያም ሆኖ እስራኤላውያንን ከግብፅ እየመራ የማውጣት ኃላፊነት ከይሖዋ ከማግኘቱ በፊት የገርነት ባሕርይውን ይበልጥ ለማዳበር አንዳንድ ለውጦችን ማስተናገድ ነበረበት። ከግብፅ ሸሽቶ በመሄድ እረኛ ሆኖ ማንም ልብ በማይለው በምድያም ምድር ለ40 ዓመት መኖር ነበረበት። ታዲያ ውጤቱ ምን ነበር? በሕይወቱ ውስጥ የተከሰተው ይህ ለውጥ የተሻለ ሰው እንዲሆን አድርጎታል። (ዘኍ. 12:3) ከራሱ ጥቅም ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም እንዳለበት ተምሯል።

ይሖዋ ታዛዥ ያልነበረውን ብሔር አጥፍቶ የሙሴን ዘር ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርግ በነገረው ጊዜ የተከሰተውን ነገር መመልከታችን ሙሴ ገር እንደነበር እንድንረዳ ያስችለናል። (ዘኍ. 14:11-20) በዚህ ጊዜ ሙሴ ይሖዋ እስራኤላውያንን እንዳያጠፋቸው ማለደ። ሙሴ ከተናገረው ሐሳብ ይበልጥ ያሳሰበው የራሱ ጥቅም ሳይሆን የአምላክ ስምና የወንድሞቹ ደኅንነት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። የእስራኤልን ብሔር ለመምራትና አስታራቂ ሆኖ ለማገልገል ገር የሆነ ሰው ያስፈልግ ነበር። ማርያምና አሮን በሙሴ ላይ ባጉረመረሙ ጊዜ ሙሴ “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘኍ. 12:1-3, 9-15) ሙሴ፣ ማርያምና አሮን በነቀፉት ጊዜ ነገሩን በገርነት መንፈስ የያዘው ይመስላል። ሙሴ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ባይዘው ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስብ።

በአንድ ወቅት ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ትንቢት እንዲናገሩ የይሖዋ መንፈስ ወረደባቸው። የሙሴ አገልጋይ የነበረው ኢያሱ እነዚህ እስራኤላውያን ተገቢ ነገር እንዳላደረጉ ተሰምቶት ነበር። በሌላ በኩል ግን ገር የነበረው ሙሴ ነገሩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር የተመለከተው ሲሆን ሥልጣኔን አጣለሁ ብሎ አልተጨነቀም። (ዘኍ. 11:26-29) ሙሴ ገር ባይሆን ኖሮ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ የተደረገውን ይህን ለውጥ ይቀበል ነበር?

ሙሴ ገር መሆኑ አምላክ የሰጠውን ትልቅ ሥልጣንና ኃላፊነት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠቀምበት አስችሎታል። ይሖዋ ወደ ኮሬብ ተራራ እንዲወጣና በሕዝቡ ፊት እንዲቆም ነገረው። አምላክ በአንድ መልአክ አማካኝነት ሙሴን ያናገረው ሲሆን የቃል ኪዳኑ መካከለኛ እንዲሆንም ሾመው። ሙሴ ገር መሆኑ በሥልጣን ረገድ የተደረገውን ትልቅ ለውጥ እንዲቀበልና የአምላክን ሞገስ ሳያጣ እንዲኖር አስችሎታል።

እኛስ እንዴት ነን? ገርነት በግለሰብ ደረጃ ለምናደርገው እድገት ወሳኝ ነገር ነው። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ኃላፊነትና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ገር መሆን ያስፈልጋቸዋል። ገር መሆናችን በሕይወታችን ውስጥ ለውጦች ሲያጋጥሙን ኩራት እንዳይሰማንና ነገሮችን በትክክለኛ መንገድ እንድንይዝ ያስችለናል። ለውጥ ሲያጋጥመን የሚሰማን ስሜት ወሳኝ ነገር ነው። ለውጡን ለመቀበል ፈቃደኛ ነን? ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን? ይህ ለውጥ የገርነት ባሕርይን እንድናዳብር ልዩ አጋጣሚ ይከፍትልን ይሆናል!

ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ለውጦች ይከሰታሉ። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ለውጦች ለምን እንደተከሰቱ መረዳት ቀላል ላይሆንልን ይችላል። ያሉብን ችግሮችና በወቅቱ የሚሰማን ውጥረት ነገሩን በይሖዋ ዓይን መመልከት አስቸጋሪ እንዲሆንብን ሊያደርጉ ይችላሉ። ያም ሆኖ እንደ ትሕትና፣ ልክን ማወቅና ገርነት ያሉት ባሕርያት በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰቱትን ለውጦች እንድንቀበልና የአምላክን ሞገስ ሳናጣ እንድንኖር ይረዱናል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እውነተኛ ትሕትና የራሳችንን ትክክለኛ ማንነት እንድናስተውል ይረዳናል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ገርነት በግለሰብ ደረጃ ለምናደርገው እድገት ወሳኝ ነገር ነው

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሴ የገርነት ባሕርይውን ይበልጥ ለማዳበር አንዳንድ ለውጦችን ማስተናገድ ነበረበት