በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን የለወጠው ኢየሱስ

ዓለምን የለወጠው ኢየሱስ

ዓለምን የለወጠው ኢየሱስ

በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህች ምድር ላይ ኖረው አልፈዋል። ብዙዎቹ በታሪክ ውስጥ ትተውት ያለፉት አሻራ የለም። በጣም ጥቂት ሰዎች ግን የዓለምን ታሪክ የሚቀይር ምናልባትም በዕለት ተዕለት ሕይወትህ ላይ ለውጥ የሚያመጣ ነገር አከናውነዋል።

በጠዋት ተነስተህ ወደ ሥራ ለመሄድ ጉድ ጉድ እያልክ ነው እንበል። ከእንቅልፍህ ተነስተህ በምትዘገጃጅበት ጊዜ መብራት ማብራትህ አይቀርም። ምናልባትም በአውቶቡስ ስትጓዝ የምታነበው መጽሐፍ ወይም መጽሔት ትይዝ ይሆናል። ለሕመምህ ተብሎ የታዘዘልህን አንቲባዮቲክ መድኃኒት መውሰድ እንዳለብህም አልዘነጋህም። ቀኑ ገና ከመጀመሩ እውቅ የሆኑ ሰዎች ከፈለሰፏቸው ነገሮች ብዙ ጥቅም አግኝተሃል።

ሚካኤል ፋራዳይ። በ1791 የተወለደው ይህ እንግሊዛዊ የፊዚክስ ባለሞያ የኤሌክትሪክ ሞተርና ዲናሞ በመፈልሰፉ ይታወቃል። የፋራዳይ ግኝት አብዛኛው ሰው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል።

ዛይ ሉን። በቻይና ቤተ መንግሥት ውስጥ ከነበሩት ባለሥልጣናት አንዱ የሆነው ሴይ ለን በ105 ዓ.ም. ገደማ ላይ ወረቀትን ማዘጋጀት የሚቻልበትን ዘዴ እንደፈጠረ ይታመናል፤ ይህም ወረቀትን በብዛት ለማምረት አስችሏል።

ዮሐንስ ጉተንበርግ። ይህ ጀርመናዊ በ1450 ገደማ የመጀመሪያውን የማተሚያ መሣሪያ ፈለሰፈ። እሱ የፈለሰፈው ማተሚያ በአነስተኛ ወጪ የሕትመት ሥራዎችን ለማከናወን ያስቻለ ሲሆን ይህም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ መረጃን በስፋት ለማሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል።

አሌክሳንደር ፍሌሚንግ። እኚህ ስኮትላንዳዊ ተመራማሪ በ1928 ባክቴሪያን ለመዋጋት የሚረዳ ንጥረ ነገር (አንቲባዮቲክ) የፈለሰፉ ሲሆን ይህን ንጥረ ነገር ፔኒሲሊን ብለው ሰየሙት። አንቲባዮቲክ በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም በአሁኑ ጊዜ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።

ጥቂት ሰዎች የፈለሰፏቸው ነገሮችና የደረሱባቸው ግኝቶች በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በአንዳንድ ዘርፎች ጥቅም እንዲያገኙ ወይም ጤንነታቸው እንዲሻሻል አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ምንም ጥርጥር የለውም።

ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሰዎች ሁሉ ለየት ብሎ የሚጠቀስ አንድ ታላቅ ሰው አለ። ይህ ሰው የሚታወቀው አንድ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ በመድረሱ ወይም በሕክምናው መስክ ታላቅ ሥራ በማከናወኑ አይደለም። ዝቅተኛ ኑሮ ካለው ቤተሰብ የመጣውና ከ2,000 ዓመታት በፊት የኖረው ይህ ሰው ለሰው ልጆች ተስፋ የሚፈነጥቅና ማጽናኛ የሚሰጥ ታላቅ መልእክት ትቶ አልፏል። ብዙዎች መልእክቱ በዓለም ዙሪያ በሚኖሩ ሰዎች ላይ ምን ያህል በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ሲመለከቱ በእርግጥም ይህ ሰው ዓለምን የለወጠው ታላቅ ሰው እንደሆነ ይስማማሉ።

ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ምንድን ነው? መልእክቱስ በአንተ ሕይወት ውስጥ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?