በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ስለ አምላክ ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ አምላክ ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ አምላክ ምን አስተምሯል?

“አብ ማን መሆኑን ከወልድ በቀር፣ ወይም ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድለት ሰው በቀር ሌላ ማንም የሚያውቅ የለም።”—ሉቃስ 10:22 የ1980 ትርጉም

አምላክ የበኩር ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ከአባቱ ጋር የኖረ ሲሆን በመካከላቸውም የጠበቀ ግንኙነት ነበር። (ቆላስይስ 1:15) በመሆኑም ወልድ የአባቱን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ ጠንቅቆ ያውቃል። ከጊዜ በኋላ ወልድ፣ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ሲመጣ ኢየሱስ የተባለ ሲሆን ስለ አባቱ እውነቱን ለማስተማር ከፍተኛ ጉጉት ነበረው። ይህ የአምላክ ልጅ የተናገረውን በማዳመጥ ስለ አምላክ ብዙ መማር እንችላለን።

የአምላክ ስም። ይሖዋ የሚለው መለኮታዊ ስም በኢየሱስ ዘንድ ትልቅ ቦታ ነበረው። ተወዳጅ የሆነው ይህ የአምላክ ልጅ ሌሎችም የአባቱን ስም እንዲያውቁና እንዲጠቀሙበት ይፈልግ ነበር። የኢየሱስ ስም ራሱ “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ስምህን . . . አሳውቄአለሁ” ብሎ መናገር ችሏል። (ዮሐንስ 17:26) ኢየሱስ በአምላክ ስም መጠቀሙና ይህን ስም ለሌሎች ማሳወቁ የሚያስደንቅ አይደለም። ደግሞስ የኢየሱስ አድማጮች የአምላክን ስም እንኳ ሳያውቁና ስሙ ምን ትርጉም እንዳለው ሳይረዱ ስለ ይሖዋ እውነቱን እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? *

የአምላክ ታላቅ ፍቅር። ኢየሱስ በአንድ ወቅት ወደ አባቱ ሲጸልይ “አባት ሆይ፣ . . . ዓለም ከመመሥረቱ በፊት [ወደድከኝ]” ብሏል። (ዮሐንስ 17:24) ኢየሱስ በሰማይ እያለ የአምላክን ፍቅር ስለቀመሰ ወደ ምድር ከመጣ በኋላ ይህ ፍቅር ያሉትን የተለያዩ ገጽታዎች ገልጧል።

ኢየሱስ የይሖዋ ፍቅር ሰፊ እንደሆነ አሳይቷል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐንስ 3:16) “ዓለም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ምድር” ማለት አይደለም። ቃሉ እዚህ ጥቅስ ላይ የተሠራበት ሰዎችን ማለትም የሰው ዘርን በሙሉ ለማመልከት ነው። አምላክ ለሰው ዘር ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ እንዲወጡና የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሲል በጣም የሚወደውን ልጁን ሰጥቷል። የአምላክ ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ አእምሯችን ሊረዳው አይችልም።—ሮም 8:38, 39

ኢየሱስ አንድ በጣም የሚያጽናና እውነት ገልጾልናል፦ ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ በጥልቅ ይወዳቸዋል። ኢየሱስ፣ ይሖዋን እያንዳንዱን በግ ለይቶ እንደሚያውቅና ውድ አድርጎ እንደሚመለከት እረኛ አድርጎ ገልጾታል። (ማቴዎስ 18:12-14) ይሖዋ ሳያውቅ አንዲት ድንቢጥ እንኳ መሬት ላይ እንደማትወድቅ ኢየሱስ ተናግሯል። አክሎም “የራሳችሁ ፀጉር እንኳ አንድ ሳይቀር ተቆጥሯል” ብሏል። (ማቴዎስ 10:29-31) ይሖዋ አንዲት ድንቢጥ በጎጆዋ ውስጥ አለመኖሯን ማስተዋል የሚችል ከሆነ አምላኪው የሆነውን የእያንዳንዱን ሰው እንቅስቃሴ እንደሚያስተውልና ለግለሰቡ እንደሚያስብለት ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በራሳችን ላይ ያለውን እያንዳንዱን ፀጉር መቁጠር የሚችል ከሆነ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚከናወኑት ዝርዝር ጉዳዮች ማለትም ስለ ፍላጎታችን፣ ስለሚያጋጥሙን ችግሮች እንዲሁም ስለሚያስጨንቁን ነገሮች ማወቅ የሚሳነው ነገር ይኖራል?

በሰማይ የሚኖር አባት። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ ነው። በመሆኑም ይህ የአምላክ ተወዳጅ ልጅ ስለ ይሖዋ ሲናገርና ወደ እሱ ሲጸልይ ብዙውን ጊዜ “አባቴ” ማለቱ ምንም አያስገርምም። እንዲያውም ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን የመጀመሪያውን ሐሳብ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ በቤተ መቅደስ ውስጥ በተናገረበት ጊዜ ይሖዋን “አባቴ” ብሎታል። (ሉቃስ 2:49) የወንጌል መጻሕፍት አምላክን ለመግለጽ አባት የሚለውን ቃል 190 ጊዜ ያህል በተለያየ መልኩ ተጠቅመውበታል። ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት ስለ ይሖዋ ሲናገር “አባታችሁ፣” “አባታችን” እና “አባቴ” በሚሉት ቃላት ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 5:16፤ 6:9፤ 7:21) ኢየሱስ እንዲህ ባሉት መጠሪያዎች በተደጋጋሚ መጠቀሙ ፍጽምና የጎደላቸውና ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረትና በእሱ መታመን እንደሚችሉ ያሳያል።

መሐሪና ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ሰፊ የሆነው የይሖዋ ምሕረት እንደሚያስፈልጋቸው ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ በተናገረው ምሳሌ ላይ ይሖዋ ሩኅሩኅና ይቅር ባይ ከሆነ አባት ጋር አመሳስሎታል፤ በምሳሌው ላይ የተገለጸው አባት፣ ንስሐ የገባውን ልጁን እጁን ዘርግቶ ተቀብሎታል። (ሉቃስ 15:11-32) ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ይሖዋ፣ ኃጢአተኛ የሆነው ሰው ልብ መለወጡን የሚያሳይ የሆነ ነገር ለማግኘት እንደሚፈልግና ይህን መሠረት በማድረግ ለግለሰቡ ምሕረት እንደሚያደርግለት ያረጋግጥልናል። ይሖዋ ንስሐ የገባን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለትና ሲመለስ ለማየት ይጓጓል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እላችኋለሁ፣ ልክ እንደዚሁ ሁሉ ንስሐ መግባት ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል።” (ሉቃስ 15:7) እንዲህ ወዳለው መሐሪ አምላክ መቅረብ የማይፈልግ ማነው?

ጸሎት ሰሚ። ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ ከአባቱ ጋር ስለነበር ይሖዋ ‘ጸሎት ሰሚ’ እንደሆነና ታማኝ አምላኪዎቹ በሚያቀርቡት ጸሎት እንደሚደሰት አስተውሎ ነበር። (መዝሙር 65:2) በመሆኑም ስብከቱን በሚያከናውንበት ወቅት አድማጮቹን እንዴት መጸለይ እንደሚችሉ እንዲሁም ስለ ምን ነገር መጸለይ እንዳለባቸው አስተምሯቸው ነበር። “አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” የሚል ምክር ሰጥቷል። እንዲሁም የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው እንዲጸልዩ አድማጮቹን አሳስቧቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለዕለት የሚያስፈልገንን ምግብ እንዲሰጠን፣ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን እንዲሁም ፈተናን ለመቋቋም እንዲረዳን መጸለይ እንችላለን። (ማቴዎስ 6:5-13) ይሖዋ አገልጋዮቹ በእምነት የሚያቀርቡትን ልመና ሰምቶ ልክ እንደ አባት ምላሽ እንደሚሰጣቸው ኢየሱስ አስተምሯል።—ማቴዎስ 7:7-11

ኢየሱስ ስለ ይሖዋ እውነቱን ለማስተማር እንዲሁም ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለማሳወቅ ፍላጎት እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ለማስተማር ይፈልግ የነበረው ሌላም ነገር አለ፤ ይሖዋ ለምድርና በእሷ ላይ ለሚኖሩት የሰው ልጆች ያለውን ዓላማ ዳር ለማድረስ ሲል ዓለም አቀፍ ለውጥ ለማምጣት ስለሚጠቀምበት መሣሪያ አስተምሯል። እንዲያውም ይህ መልእክት የኢየሱስ ስብከት ዋና ጭብጥ ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ወደ 7,000 ጊዜ ገደማ ይገኛል። ይህ ስም “መሆን የሚያስፈልገኝን እሆናለሁ” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፀአት 3:14 NW) አምላክ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል። በመሆኑም ይህ ስም፣ አምላክ ዓላማውን ምንጊዜም እንደሚፈጽምና የገባውን ማንኛውንም ቃል እንደሚጠብቅ ዋስትና ይሰጠናል።