በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን አስተምሯል?

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ምን አስተምሯል?

“የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከ . . . ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር።”—ሉቃስ 8:1

ትልቅ ቦታ ስለምንሰጣቸውና በጣም ስለምንወዳቸው ነገሮች ማውራት ያስደስተናል። ኢየሱስ ራሱ እንደገለጸው “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው።” (ማቴዎስ 12:34) ኢየሱስ የስብከቱን ሥራ ያከናውን በነበረበት ወቅት ከተናገራቸው ነገሮች መረዳት እንደምንችለው ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ ይሰጥ ነበር።

የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት በንጉሥ የሚመራ መስተዳድር ሲሆን ይህን መስተዳድር ያቋቋመው አምላክ ነው። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት በስፋት መናገሩ የመልእክቱ ዋነኛ ጭብጥ ይህ መንግሥት እንደነበር ያሳያል። በአራቱ የወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ስለዚህ መንግሥት ከ110 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ እናገኛለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ያስተማረው በንግግሩ ብቻ አልነበረም። ስለ አምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት ወደፊት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ኢየሱስ ካከናወናቸው ነገሮችም መማር እንችላለን።

ንጉሡ ማን ነው? የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሥልጣኑን የያዘው በሰው ልጆች ተመርጦ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን መሪ የመረጠው አምላክ ራሱ ነው። አምላክ ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው እሱን መሆኑን ኢየሱስ በትምህርቱ ላይ ገልጿል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ እንደተነገረው ተስፋ የተደረገበት መሲሕ የሚያስተዳድረው መንግሥት ዘላለማዊ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። (2 ሳሙኤል 7:12-14፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 26:63, 64) ኢየሱስ፣ እንደሚመጣ አስቀድሞ የተነገረው መሲሕ እሱ መሆኑን በግልጽ እንደተናገረ አስታውስ። ኢየሱስ ይህን ሲል በአምላክ የተሾመው ንጉሥ እሱ መሆኑን መግለጹ ነበር። (ዮሐንስ 4:25, 26) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ “መንግሥቴ” የሚለውን አገላለጽ በተደጋጋሚ መጠቀሙ ተገቢ ነበር።—ዮሐንስ 18:36

በተጨማሪም ኢየሱስ በመንግሥቱ ከእሱ ጋር የሚገዙ ሰዎች እንዳሉ አስተምሯል። (ሉቃስ 22:28-30) ከእሱ ጋር የሚገዙት ቁጥራቸው ጥቂት ስለሆነ “ትንሽ መንጋ” በማለት ጠርቷቸዋል። እንዲሁም “አባታችሁ መንግሥትን ሊሰጣችሁ [ፈቅዷል]” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 12:32) የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት መብት የሚያገኙት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 144,000 እንደሆነ ይናገራል።—ራእይ 5:9, 10፤ 14:1

መንግሥቱ የሚገዛው ከየት ሆኖ ነው? ኢየሱስ ለሮማዊው ገዥ ለጳንጥዮስ ጲላጦስ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” ብሎት ነበር። (ዮሐንስ 18:36) በክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት የሚገዛው በሰብዓዊ ወኪሎች በኩል አይደለም። ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜያት “መንግሥተ ሰማያት” በማለት ጠርቶታል። * (ማቴዎስ 4:17፤ 5:3, 10, 19, 20) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው የአምላክ መንግሥት በሰማይ ያለ መስተዳድር ነው።

ኢየሱስ በምድር ላይ የተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ ወደ ሰማይ እንደሚመለስ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ አብረውት የሚገዙት ከእሱ ጋር እንዲሆኑ ‘ቦታ እንደሚያዘጋጅ’ ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:2, 3

መንግሥቱ ምን ያከናውናል? ኢየሱስ አድማጮቹን እንደሚከተለው ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር፦ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየሆነ ነው። አምላክ ለምድር ያለውን ዓላማ የሚያስፈጽመው በመንግሥቱ አማካኝነት ነው። ይህ መንግሥት የአምላክ ዓላማ እንዲፈጸም በምድር ላይ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ያካሂዳል።

መንግሥቱ በምድር ላይ ምን ያከናውናል? የአምላክ መንግሥት፣ የክፋት ድርጊታቸውን ለመተው ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን በማጥፋት ክፋትን እንደሚያስወግድ ኢየሱስ አስተምሯል። (ማቴዎስ 25:31-34, 46) ይህም ሲባል ማንኛውም ዓይነት ሥነ ምግባራዊ ብልሹነትና ክፋት በሙሉ ይወገዳል ማለት ነው። ምድር ‘ገር፣’ ጻድቅና መሐሪ በሆኑ እንዲሁም ‘ልባቸው ንጹሕ በሆነ’ እና ሰላም ፈጣሪ በሆኑ ሰዎች እንደምትሞላ ኢየሱስ አስተምሯል።—ማቴዎስ 5:5-9

እነዚህ ታማኝ ሰዎች የሚኖሩት በተበከለችው ምድር ላይ ነው? በፍጹም! ኢየሱስ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ወቅት ምድር በአስደናቂ ሁኔታ እንደምትለወጥ ቃል ገብቷል። ከኢየሱስ ጎን የተሰቀለው ሰው “ኢየሱስ ሆይ፣ ወደ መንግሥትህ ስትመጣ አስበኝ” ብሎት ነበር። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መልሶለታል። (ሉቃስ 23:42, 43) የአምላክ መንግሥት ከኤደን የአትክልት ሥፍራ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መላዋን ምድር ገነት ያደርጋታል።

መንግሥቱ ለሰው ልጆች የሚያደርገው ሌላ ምን ነገር አለ? ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ምን እንደሚያደርግ ቃል በመግባት ብቻ አልተወሰነም። ይህ መንግሥት ምን እንደሚያከናውንም በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ በተአምር ብዙዎችን የፈወሰ ሲሆን ይህ ደግሞ ወደፊት በመንግሥቱ ሲገዛ በስፋት የሚያከናውነውን ነገር የሚያሳይ ናሙና ነበር። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የወንጌል ዘገባ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በምኩራቦቻቸው እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።”—ማቴዎስ 4:23

ኢየሱስ የተለያየ በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ፈውሷል። “ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች [ከፍቷል]።” (ዮሐንስ 9:1-7, 32, 33) ኢየሱስ አስከፊ በሆነ የሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቃን አንድ ሰው ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመዳሰስ ፈውሶታል። (ማርቆስ 1:40-42) “ደንቆሮ የሆነና የመናገር እክል ያለበት አንድ ሰው” ወደ እሱ ባመጡለት ጊዜ ግለሰቡን በመፈወስ “ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፣ ዲዳዎችም እንዲናገሩ” ማድረግ እንደሚችል አሳይቷል።—ማርቆስ 7:31-37

ሞትም እንኳ ቢሆን በአምላክ ከተሾመው ንጉሥ አቅም በላይ አልነበረም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስ ሙታንን ያስነሳባቸው ሦስት አጋጣሚዎች ተመዝግበው እናገኛለን። የአንዲት መበለትን አንድያ ልጅ፣ አንዲት የ12 ዓመት ልጅን እንዲሁም የሚወደውን ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት አስነስቷል።—ሉቃስ 7:11-15፤ 8:41-55፤ ዮሐንስ 11:38-44

የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ወደፊት ምን ዓይነት አስደናቂ ሕይወት እንደሚያገኙ ሲገልጽ ኢየሱስ በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል እንዲህ ብሏል፦ “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 1:1፤ 21:3, 4) የሐዘን እንባ፣ ሥቃይ እንዲሁም ሞት የሌለበት ዓለም ምን እንደሚመስል እስቲ አስበው! የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲሆን የምንጸልየው ጸሎት በዚያን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል።

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው? ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ወቅትና “መገኘት” ብሎ የገለጸው ልዩ ወቅት ተመሳሳይ ጊዜ ላይ እንደሚያርፉ አስተምሯል። ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ የሚገኝበትን ጊዜ የሚጠቁሙ ዝርዝር ነገሮችን የያዘ ትንቢት ተናግሯል። ይህ ጊዜ ዓለም አቀፍ ይዘት ባላቸው ችግሮች ተለይቶ የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር ነውጥና ቸነፈር እንዲሁም የክፋት እየበዛ መሄድ ይገኙበታል። (ማቴዎስ 24:3, 7-12፤ ሉቃስ 21:10, 11) እነዚህና ኢየሱስ የተናገራቸው ሌሎች በርካታ የምልክቱ ገጽታዎች በተለይ አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳበት ከ1914 ወዲህ እየታዩ ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በመግዛት ላይ መሆኑን ማወቅ እንችላለን። መንግሥቱ የሚመጣበትና የአምላክ ዓላማ በምድር ላይ እንዲፈጸም የሚያደርግበት ጊዜ ቅርብ ነው። *

የአምላክ መንግሥት መምጣት በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ይህ ለኢየሱስ መልእክት በምትሰጠው ምላሽ ላይ የተመካ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 “መንግሥተ ሰማያት” የሚለው ሐሳብ በማቴዎስ ወንጌል ላይ 30 ጊዜ ያህል ይገኛል።

^ አን.17 የአምላክ መንግሥት የሚመጣበት ጊዜ መቅረቡን እንዴት ማወቅ እንደምንችል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “የምንኖረው ‘በመጨረሻው ዘመን’ ውስጥ ነው?” የሚለውን ምዕራፍ 9⁠ን ተመልከት።