በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳሳቱ ትምህርቶችን ከእውነቱ መለየትኢየሱስን በተመለከተ እውነቱን ማወቅ

የተሳሳቱ ትምህርቶችን ከእውነቱ መለየትኢየሱስን በተመለከተ እውነቱን ማወቅ

የተሳሳቱ ትምህርቶችን ከእውነቱ መለየት​—ኢየሱስን በተመለከተ እውነቱን ማወቅ

የሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች እውነት ናቸው ወይስ ስህተት?

ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ነው።

ሦስት ጠቢባን ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ሊጠይቁት መጥተው ነበር።

ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች አልነበሩትም።

ኢየሱስ በሰው አምሳል የተገለጠ አምላክ ነበር።

ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረ አንድ ጥሩ ሰው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች የተለየ ነበር።

ብዙዎች ከላይ የቀረቡት ዓረፍተ ነገሮች በሙሉ እውነት እንደሆኑ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ መልሱን በእርግጠኝነት ማወቅ አስቸጋሪ እንዲያውም የማይቻል ነገር እንደሆነ ይገልጹ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ እስካመንክ ድረስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ይሰማቸው ይሆናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ ሐሳብ ይዟል። “ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ . . . ትክክለኛ እውቀት” እንድናገኝ ያበረታታናል። (2 ጴጥሮስ 1:8) እንዲህ ያለ እውቀት የምናገኘው ወንጌሎችን በመመርመር ነው። የወንጌል ዘገባዎች ስለ ኢየሱስ እውነቱን እንድናውቅ በመርዳት ስህተት የሆነውን ትምህርት ከእውነቱ ለመለየት ያስችሉናል። እንግዲያው ከላይ የተጠቀሱትን እምነቶች በተመለከተ የወንጌል ዘገባዎች ምን እንደሚሉ እስቲ እንመርምር።

እምነት፦ ኢየሱስ የተወለደው ታኅሣሥ 25 (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ነው።

መልሱ፦ ስህተት።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የተወለደበትን ወር ወይም ቀን በተመለከተ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። ታዲያ ኢየሱስ ታኅሣሥ 25 (እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ታኅሣሥ 29) ተወለደ የሚለው ትምህርት የመጣው ከየት ነው? ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው ይህ ቀን የተመረጠው ክርስቲያን ነን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የተወለደበት ቀን “የሮማውያን አረማዊ ክብረ በዓል [ከሚከበርበት ጊዜ] ጋር እንዲገጣጠም ስለፈለጉ ይመስላል። . . . በዚህ ክብረ በዓል ላይ የቅዝቃዜው ወቅት መጋመስ የሚከበር ሲሆን ይህም ቀኖቹ እንደገና መርዘም የሚጀምሩበትና ፀሐይዋ አናት ላይ ለመሆን ጉዞ የምትጀምርበት ወቅት ነው።” ይኸው ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው ከገና በዓል ጋር የተያያዙት ብዙዎቹ ልማዶች የመነጩት “አረማውያን በቅዝቃዜው ወቅት አጋማሽ ላይ ከሚያከብሩት የእርሻና የፀሐይ በዓል” ነው።

ኢየሱስ ልደቱ በመከበሩ የሚስማማ ይመስልሃል? እስቲ አስበው፦ ኢየሱስ የተወለደበት ቀን አይታወቅም። የኢየሱስን ልደት እንድናከብር የሚያዝ መመሪያ አሊያም የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዳደረጉ የሚያሳይ ማስረጃ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የለም። ከዚህ በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የሞተበትን ትክክለኛ ቀን የሚገልጽ ሲሆን የኢየሱስ ተከታዮች ይህንን ቀን እንዲያከብሩት ታዘዋል። * (ሉቃስ 22:19) ኢየሱስ በልደቱ ላይ ሳይሆን መሥዋዕታዊ ሞቱ ባለው ዋጋ ላይ ትኩረት እንዲደረግ እንደፈለገ ከዚህ በግልጽ መመልከት እንችላለን።—ማቴዎስ 20:28

እምነት፦ ሦስት ጠቢባን (ወይም አንዳንዶች እንደሚናገሩት ሦስት ነገሥታት) ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ሊጠይቁት መጥተው ነበር።

መልሱ፦ ስህተት።

ሕፃኑ ኢየሱስ በግርግም ውስጥ ተኝቶና ስጦታዎችን የያዙ ሦስት ጠቢባን በዙሪያው ቆመው የሚያሳዩ ሥዕሎችን ወይም ትዕይንቶችን ተመልክተህ ታውቅ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ሐሳብ የፈጠራ ታሪክ እንጂ እውነት አይደለም።

ከምሥራቅ አገር የመጡ ሰዎች አክብሮታቸውን ለመግለጽ ትንሽ ልጅ ወደነበረው ወደ ኢየሱስ መሄዳቸው እውነት ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ሰብአ ሰገል ወይም ኮከብ ቆጣሪዎች ነበሩ። (ማቴዎስ 2:1 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስን ያገኙት በግርግም ውስጥ ነበር? አይደለም፤ ሊጠይቁት በመጡ ጊዜ ኢየሱስ ቤት ውስጥ ነበር። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች የመጡት ኢየሱስ ከተወለደ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ነበር።—ማቴዎስ 2:9-11

ኢየሱስን ሊጠይቁት የመጡት ስንት ሰዎች ነበሩ? ሁለት ይሁኑ ሦስት ወይም ሠላሳ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጸው ነገር የለም። ሰዎቹ ሦስት እንደነበሩ የሚታሰበው ሦስት ዓይነት ስጦታዎች ስለያዙ ሊሆን ይችላል። * (ማቴዎስ 2:11) እንዲያውም ጠቢባን የሚባሉት እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው የተለያዩ ዘሮችን እንደሚወክሉ የሚናገሩም አሉ። ይሁንና ይህ ሐሳብ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አይገኝም። ከዚህ በተቃራኒ እንዲህ ያለው የተሳሳተ ትምህርት “በስምንተኛው መቶ ዘመን የኖረ አንድ ታሪክ ጸሐፊ የፈጠራ ሐሳብ” መሆኑን በወንጌሎች ላይ ትንታኔ የሚሰጡ አንድ ሰው ገልጸዋል።

እምነት፦ ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች አልነበሩትም።

መልሱ፦ ስህተት።

የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት በግልጽ ያሳያሉ። የሉቃስ ወንጌል ኢየሱስ የማርያም ‘የበኩር ልጅ’ እንደሆነ ይናገራል፤ ይህም ማርያም ከኢየሱስ በኋላ ሌሎች ልጆችን እንደወለደች ይጠቁማል። * (ሉቃስ 2:7) የማርቆስ ወንጌል ደግሞ በናዝሬት ከተማ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስን ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ለይተው እንዳልተመለከቱት ያሳያል። ሰዎቹ ስለ ኢየሱስ ሲናገሩ “የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለም? እህቶቹስ ከእኛው ጋር አይደሉም?” ብለው ነበር።—ማርቆስ 6:3፤ ማቴዎስ 12:46፤ ዮሐንስ 7:5

የወንጌል ዘገባዎች እንዲህ ቢሉም በርካታ የሃይማኖት ምሑራን ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች አልነበሩትም በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል። አንዳንዶች የኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች የተባሉት የኢየሱስ የአክስት ወይም የአጎት ልጆች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ። * ሌሎች ደግሞ የዮሴፍ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ። ይሁንና እስቲ አስበው፦ ማርያም የወለደችው ኢየሱስን ብቻ ቢሆን ኖሮ የናዝሬት ሰዎች ከላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ይናገሩ ነበር? ከዚህ በተቃራኒ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ፣ ማርያም ሌሎች ልጆች እንደወለደች የዓይን ምሥክሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ማርያም ከወለደቻቸው በርካታ ልጆች አንዱ መሆኑን በደንብ ያውቁ ነበር።

እምነት፦ ኢየሱስ በሰው አምሳል የተገለጠ አምላክ ነበር።

መልሱ፦ ስህተት።

አምላክ በሰው አምሳል ወደ ምድር በመምጣት ኢየሱስ ሆኖ ተገልጧል የሚለው ለሥላሴ ትምህርት ዋና መሠረት የሆነ አመለካከት ለረጅም ጊዜ ሲታመንበት የኖረ ቢሆንም ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የመነጨ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “ሥላሴ የሚለው ቃልም ሆነ ይህን መሠረተ ትምህርት የሚደግፍ ሐሳብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፈጽሞ አይገኝም። . . . ይህ ትምህርት ቀስ በቀስ እየዳበረ የመጣው ከበርካታ መቶ ዘመናትና ከብዙ ክርክር በኋላ ነው።”

ኢየሱስ በሰው አምሳል የተገለጠ አምላክ እንደሆነ የሚያስተምሩ ሃይማኖቶች ኢየሱስን እያዋረዱት ነው ሊባል ይችላል። * እንዴት? አንድ ምሳሌ እንመልከት። የአንድ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ተቆጣጣሪያቸውን አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው ሲጠይቁት ግለሰቡ የጠየቁትን ለማድረግ ሥልጣኑ እንደሌለው ገለጸላቸው። ግለሰቡ የተናገረው ነገር እውነት ከሆነ ይህን ማለቱ ቦታውን የሚያውቅ ሰው እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የተናገረው ነገር እውነት ካልሆነ ይኸውም እንዲህ ዓይነት ምላሽ የሰጠው የጠየቁትን ነገር ማድረግ እየቻለ ስላልፈለገ ከሆነ ግን ግለሰቡ እያታለላቸው ነው።

ከሐዋርያት ሁለቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ የሰጣቸውን መልስ እስቲ እንመልከት፦ “በቀኜ ወይም በግራዬ የመቀመጡ ጉዳይ . . . አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” አላቸው። (ማቴዎስ 20:23) ኢየሱስ በእርግጥ አምላክ ከነበረ እንዲህ ማለቱ መዋሸት አይሆንበትም? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችለው ከእሱ የበለጠ ሥልጣን ያለው አካል መሆኑን በመግለጹ ቦታን በማወቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ ሆኗል፤ በዚህ መንገድም ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እኩል እንዳልሆነ አሳይቷል።

እምነት፦ ኢየሱስ በምድር ላይ የኖረ አንድ ጥሩ ሰው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች የተለየ ነበር።

መልሱ፦ እውነት።

ኢየሱስ ጥሩ ሰው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች የተለየ እንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። “የአምላክ ልጅ ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 10:36) እርግጥ ነው፣ ማንም ሰው የአምላክ ልጅ እንደሆነ መናገር ይችላል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህን ያለው ውሸቱን ከሆነ ይህ ስለ እሱ ማንነት ምን ይገልጻል? ጥሩ ሰው ሳይሆን የወጣለት አታላይ ሊሆን ነው ማለት ነው!

ስለ ኢየሱስ ከሁሉ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ምሥክርነት የሰጠው አምላክ ራሱ ነው። ኢየሱስን በተመለከተ ሁለት ጊዜ “ልጄ ይህ ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5) እስቲ አስበው፦ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የራሱ የአምላክ ድምፅ በምድር ላይ እንደተሰማ የሚገልጽ ሐሳብ ተመዝግቦ የምናገኘው ጥቂት ቦታዎች ላይ ብቻ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ በሁለቱ ወቅቶች አምላክ፣ ኢየሱስ ልጁ እንደሆነ ተናግሯል! ኢየሱስ ስለ ማንነቱ የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን የሚያረጋግጠው ከሁሉ የላቀው ማስረጃ ይህ ነው።

ይህ ርዕስ ከዚህ በፊት ስለ ኢየሱስ የማታውቃቸውን እውነታዎች አስገንዝቦሃል? ከሆነ በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን የወንጌል ዘገባዎች ለምን ይበልጥ አትመረምርም? እንዲህ ያለው ጥናት አስደሳች ከመሆኑም በላይ የሚክስ ሆኖ ታገኘዋለህ። ደግሞም ኢየሱስ፣ ስለ እሱና ስለ አባቱ መማር “የዘላለም ሕይወት” እንደሚያስገኝ ተናግሯል።—ዮሐንስ 17:3

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ኢየሱስ የሞተው በፋሲካ በዓል ዕለት ወይም በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14 ነው።—ማቴዎስ 26:2

^ አን.18 ሰዎቹ ‘ዕቃቸውን ከፍተው’ ወርቅ፣ ነጭ ዕጣንና ከርቤ በስጦታ መልክ ለኢየሱስ እንዳቀረቡለት ማቴዎስ ዘግቧል። እነዚህ ውድ ስጦታዎች ለኢየሱስ የቀረቡለት በጥሩ ጊዜ ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም ዝቅተኛ ኑሮ የነበራቸው የኢየሱስ ወላጆች ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሌላ አገር ለመሰደድ ተገድደው ነበር።—ማቴዎስ 2:11-15

^ አን.21 ማርያም ኢየሱስን የፀነሰችው በተአምራዊ መንገድ ቢሆንም ሌሎቹን ልጆቿን የወለደችው ከባሏ ከዮሴፍ ነው።—ማቴዎስ 1:25

^ አን.22 ጀሮም በ383 ዓ.ም. ገደማ የደገፈው ይህ ጽንሰ ሐሳብ ማርያም ሕይወቷን ሙሉ ድንግል ሆና ኖራለች ብለው በሚያምኑ ብዙ ሰዎች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። ከጊዜ በኋላ ጀሮም ይህን ጽንሰ ሐሳብ እንደሚጠራጠረው የገለጸ ቢሆንም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ብዙዎች በዚህ ሐሳብ ጸንተዋል።

^ አን.26 ከሥላሴ መሠረተ ትምህርት ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? የሚለውን ብሮሹር ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከዚህ በታች የቀረቡትን እውነታዎች ብታውቅ ትገረም ይሆናል

ኢየሱስ በምድር ላይ እያለ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ማኅበራዊ ግንኙነት የማይወድ፣ ስሜቱን የማይገልጽና የማይቀረብ ከመሆኑ የተነሳ የተራውን ሕዝብ ስሜት ለመረዳት የሚቸገር ሰው ነበር? አንዳንዶች አዎን ብለው ይመልሱ ይሆናል። በመሆኑም ኢየሱስ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነገሮች እንዳደረገ ሲያውቁ ይገረሙ ይሆናል፦

• አስደሳች በሆኑ ማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ተገኝቷል።—ዮሐንስ 2:1-11

• ለሌሎች ያለውን አድናቆት ገልጿል።—ማርቆስ 14:6-9

• ከልጆች ጋር መሆን ያስደስተው ነበር።—ማርቆስ 10:13, 14

• በሰው ፊት አልቅሷል።—ዮሐንስ 11:35

• ለሰዎች ይራራ ነበር።—ማርቆስ 1:40, 41