በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ብኩርና ምን መብቶችን ያስገኝ ነበር? የሚያስከትላቸው ኃላፊነቶችስ ምን ነበሩ?

ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የአምላክ አገልጋዮች በኩር ለሆኑት ወንዶች ልጆቻቸው ልዩ መብት ይሰጡ ነበር። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አባት ሲሞት የመጀመሪያው ወንድ ልጁ እንደ ቤተሰብ ራስ ተደርጎ ይታይ ነበር። ይህ የበኩር ልጅ የቤተሰቡን ፍላጎት ያሟላል፤ እንዲሁም በተቀሩት የቤተሰቡ አባላት ላይ ሥልጣን ይኖረዋል። በተጨማሪም የበኩር ልጅ በአምላክ ፊት ቤተሰቡን ይወክል ነበር። ሁሉም ወንዶች ልጆች የውርስ መብት ያላቸው ቢሆንም የበኩር ልጅ የሚያገኘው ውርስ ከሌሎች ብልጫ ነበረው። የበኩር ልጅ የሚያገኘው ውርስ ከሌሎቹ ወንዶች ልጆች ጋር ሲነጻጸር በሁለት እጥፍ ይበልጥ ነበር።

በጥንት ጊዜ የመጀመሪያ ልጅ ብኩርናውን ለሌላ ሰው አሳልፎ ሊሰጥ ወይም ሊነጠቅ ይችል ነበር። ለምሳሌ ያህል ዔሳው ብኩርናውን ለታናሽ ወንድሙ ሸጦለታል። (ዘፍጥረት 25:30-34) የመጀመሪያ ልጅ የነበረው ሮቤል የሥነ ምግባር ብልግና በመፈጸሙ ምክንያት ያዕቆብ ከእሱ ብኩርናውን ወስዶ ለዮሴፍ ሰጥቶታል። (1 ዜና መዋዕል 5:1) ይሁንና በሙሴ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ከአንድ በላይ ሚስት ካለው ከአንደኛዋ ሚስቱ ከተወለደው የመጀመሪያ ልጅ የብኩርና መብቱን ወስዶ ወደሚወዳት ወደሌላኛው ሚስቱ የመጀመሪያ ልጅ ማስተላለፍ አይችልም። አንድ አባት የመጀመሪያ ልጁን የብኩርና መብት እንዲያከብር ይጠበቅበት ነበር።—ዘዳግም 21:15-17

ጸሐፍትና ፈሪሳውያን “ክታብ” ያስሩ የነበረው ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ የሆኑትን ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን “ትልቅ ክታብ” በማድረጋቸው ወቅሷቸዋል። (ማቴዎስ 23:2, 5) የጸሐፍትና የፈሪሳውያን ተከታይ የነበሩ ሰዎች ጥቁርና አራት ማዕዘን ወይም ሦስት ማዕዘን ቅርፅ ያለው አነስተኛ ማኅደር በግንባራቸው ላይ ያስሩ ነበር። በተጨማሪም በውስጠኛው የክንዳቸው ክፍል በልባቸው ትክክል ማኅደር ያስሩ ነበር። ማኅደሮቹ ከቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ጥቅሶችን ይዘዋል። ክታብ በመባል የሚታወቁትን ከቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ጥቅሶችን የያዙ እንዲህ ያሉ ማኅደሮችን የማሰር ልማድ የተጀመረው አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጠውን የሚከተለውን ትእዛዝ ቃል በቃል ከመረዳት ነው፦ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። . . . በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ።” (ዘዳግም 6:6-8) ክታቦችን የማሰር ልማድ የጀመረው መቼ እንደሆነ በእርግጠኝነት ባይታወቅም በርካታ ምሑራን ይህ ልማድ የተጀመረው በሦስተኛው ወይም በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. እንደሆነ ይናገራሉ።

ኢየሱስ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ይህን ልማድ አውግዟል። አንደኛው፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት ሲሉ ክታቦቻቸውን ያስተልቁ ስለነበር ነው። ሁለተኛው፣ እነዚህ ሰዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን በውስጡ የያዘውን ማኅደር እነሱን ከክፉ ነገር የሚጠብቃቸው ክታብ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ተርድተውት ነበር። እነዚህን ማኅደሮች የሚያመለክተው ፊላክቴሪዮን የሚለው የግሪክኛ ቃል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ጽሑፎች ላይ “ምሽግ” ወይም “ከክፉ የሚጠብቅ” ተብሎ ተተርጉሟል።