በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እሱን ስለ መከተል

እሱን ስለ መከተል

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

እሱን ስለ መከተል

ኢየሱስ፣ ሰዎች በእሱ ላይ እምነት ሲያሳድሩ ብዙ ጊዜ ‘ተከታዬ ሁኑ’ ይላቸው ነበር። (ማቴዎስ 9:9፤ 19:21) ክርስቲያን ማለትም የኢየሱስ ተከታይ መሆን ምን ማድረግን ያካትታል? ለሦስት ዓበይት ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ልብ በል።

ከሌሎች ጋር ያለህ ግንኙነት እንዴት ሊሆን ይገባል?

▪ አንድ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባው ግንኙነት የተሰጡትን መመሪያዎች መከተል አለበት። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል” በማለት ተናግሯል። አንድ ሰው ቢያስቀይምህስ? ኢየሱስ “ክስ ከመሠረተብህ ሰው ጋር . . . ወዲያው እርቅ ለመፍጠር ጥረት አድርግ” ብሏል። በተጨማሪም ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”—ማቴዎስ 5:25፤ 6:15፤ 7:12

ትዳር ላላቸው ሰዎች ኢየሱስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶች አስተሳሰቡንና ልቡን ለመለወጥ ጥረት ያደርጋል።—ማቴዎስ 5:27, 28

እውነተኛ ክርስቲያኖች ሌሎችን ለመርዳት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ። ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ሰው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ እሱና ሐዋርያቱ ለስብከት ረጅምና አድካሚ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ምግብ ለመብላት እንኳ ጊዜ አልነበራቸውም። በመሆኑም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያርፉ ወደ አንድ ገለል ያለ ስፍራ በጀልባ ይዟቸው ሄደ። ይሁንና ሰዎቹ ወዴት እንደሚሄድ ስለሰሙ ከእሱ ቀድመው በቦታው ደረሱ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ከጀልባዋ ሲወርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተመለከተ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለነበሩም በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 6:30-34) በተመሳሳይም ችግር እያለብህም እንኳ አምላክ ከአንተ የሚፈልገውን ነገር በማድረግ ኢየሱስን መምሰል ትችላለህ።

ምሥራቹን ለሌሎች መስበክ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ ተከታዮቹ ምሥራቹን ለሌሎች እንዲያካፍሉ አስተምሯቸዋል። ለሐዋርያቱ “ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ ብላችሁ ስበኩ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:7) የኢየሱስ ተከታዮች ይዘውት የሚሄዱት መልእክት ትልቅ ዋጋ ያለው ነበር። ኢየሱስ ሲጸልይ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተ . . . እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3

ኢየሱስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮቹ ስለሚሠሩት ሥራ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14) ስለ አምላክ መንግሥት የምታውቅ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን የምታምን ከሆነ የምታውቀውን ነገር ለሌሎች ሰዎች በመናገርህ እንደምትደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። በርካታ የኢየሱስ ተከታዮች ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ የጀመሩት ለዘመዶቻቸው በመንገር ነው።—ዮሐንስ 1:40, 41

መጠመቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?

▪ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ “አምላክ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” በማለት ጸልዮ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 10:7) የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የምትፈልግ ከሆነ አንተም መጠመቅ አለብህ። ኢየሱስ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን . . . እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ትእዛዝ ሰጥቷል።—ማቴዎስ 28:19

መጠመቅ ምን ኃላፊነትና በረከት ያስገኛል? የተጠመቁ የኢየሱስ ተከታዮች አምላክን በሙሉ ነፍሳቸው ያገለግሉታል። ኢየሱስ የአምላክን ሕግ ጠቅሶ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:37) በተጨማሪም “ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:24) ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ክዶ የአምላክ ንብረት መሆን እንደሚፈልግ የሚያሳይበት ምልክት ነው። በዚህ መንገድ ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና የመሠረቱ ሰዎች አምላክ ንጹሕ ሕሊና እንዲሰጣቸው መጠየቅ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 3:21

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የዚህን መጽሐፍ ምዕራፍ 18 ተመልከት።