በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወንዶች፣ ለክርስቶስ ራስነት ትገዛላችሁ?

እናንት ወንዶች፣ ለክርስቶስ ራስነት ትገዛላችሁ?

እናንት ወንዶች፣ ለክርስቶስ ራስነት ትገዛላችሁ?

“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ [ነው]።”—1 ቆሮ. 11:3

1. ይሖዋ የሁከት አምላክ እንዳልሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?

“ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ እንዲሁም ያሉትም ሆነ የተፈጠሩት በአንተ ፈቃድ ስለሆነ ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል” በማለት ራእይ 4:11 ይናገራል። ይሖዋ አምላክ፣ የሁሉም ነገር ፈጣሪ ስለሆነ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ ነው፤ እንዲሁም በፍጥረታቱ ሁሉ ላይ ሥልጣን አለው። ይሖዋ “የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ” እንዳልሆነ መላእክቱን ካደራጀበት መንገድ በግልጽ መመልከት ይቻላል።—1 ቆሮ. 14:33፤ ኢሳ. 6:1-3፤ ዕብ. 12:22, 23

2, 3. (ሀ) ይሖዋ መጀመሪያ የፈጠረው ማንን ነው? (ለ) የአምላክ የበኩር ልጅ ከይሖዋ አንጻር ያለው ቦታ ምንድን ነው?

2 ማንኛውም ነገር ከመፈጠሩ በፊት አምላክ ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት ብቻውን ይኖር ነበር። አምላክ መጀመሪያ የፈጠረው “ቃል” ተብሎ የሚጠራውን መንፈሳዊ ፍጥረት ሲሆን ይህ ስም የተሰጠው የይሖዋ ቃል አቀባይ በመሆኑ ነው። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ወደ ሕልውና የመጡት “ቃል” በተባለው በዚህ አካል አማካኝነት ነው። ከጊዜ በኋላ ይህ መንፈሳዊ ፍጥረት ፍጹም ሰው ሆኖ ወደ ምድር የመጣ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ ይጠራ ጀመር።—ዮሐንስ 1:1-3, 14ን አንብብ።

3 ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክና የበኩር ልጁ ስላላቸው ቦታ ምን ይላሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ሁሉ ራስ ደግሞ ወንድ፣ የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ እንደሆነ እንድታውቁ እወዳለሁ።” (1 ቆሮ. 11:3) ክርስቶስ በአባቱ የራስነት ሥልጣን ሥር ነው። የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታት መካከል ሰላምና ሥርዓት እንዲሰፍን ከተፈለገ የራስነት ሥልጣን መኖሩ እንዲሁም ፍጥረታት ለዚህ ሥልጣን መገዛታቸው አስፈላጊ ነው። ‘ሌሎች ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በእሱ አማካኝነት’ እንደሆነ የተነገረለት አካልም እንኳ ለአምላክ የራስነት ሥልጣን እንዲገዛ ይጠበቅበታል።—ቆላ. 1:16

4, 5. ኢየሱስ ከይሖዋ አንጻር ስላለው ቦታ ምን አመለካከት ነበረው?

4 ኢየሱስ ለይሖዋ የራስነት ሥልጣን ስለመገዛትና ወደ ምድር ስለመምጣት ምን ተሰምቶት ነበር? ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ይላሉ፦ “[ክርስቶስ ኢየሱስ] በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን ነጥቆ ሊወስደው እንደሚገባ ነገር አድርጎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ አደረገ፤ እንደ ባሪያ ሆኖም በሰው አምሳል መጣ። ከዚህም በላይ በሰው አምሳል በመጣ ጊዜ ራሱን ዝቅ በማድረግ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመከራ እንጨት ላይ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆኗል።”—ፊልጵ. 2:5-8

5 ኢየሱስ ምንጊዜም ለአባቱ ፈቃድ በትሕትና ይገዛ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በራሴ ተነሳስቼ አንድም ነገር ማድረግ አልችልም፤ . . . የራሴን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ መፈጸም ስለምፈልግ የምፈርደው የጽድቅ ፍርድ ነው።” (ዮሐ. 5:30) በተጨማሪም “ሁልጊዜ [አባቴን] ደስ የሚያሰኘውን [አደርጋለሁ]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 8:29) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ” ብሏል። (ዮሐ. 17:4) በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ኢየሱስ የአምላክን የራስነት ሥልጣን መቀበልና ለዚህ ሥልጣን መገዛት ምንም አላስቸገረውም።

የአምላክ ልጅ ለአባቱ መገዛቱ ጥቅም አስገኝቶለታል

6. ኢየሱስ ምን ግሩም ባሕርያት እንዳሉት አሳይቷል?

6 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ብዙ ግሩም ባሕርያት እንዳሉት አሳይቷል። ለአባቱ የነበረውን ጥልቅ ፍቅር እንደ ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። “እኔ አብን [እወደዋለሁ]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:31) ኢየሱስ ለሰዎችም ታላቅ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ማቴዎስ 22:35-40ን አንብብ።) ኢየሱስ ደግና አሳቢ እንጂ ኃይለኛ ወይም ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም ሰው አልነበረም። እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፣ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ምክንያቱም ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነው።” (ማቴ. 11:28-30) በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ በግ መሰል ሰዎች በተለይም በደል የደረሰባቸውና የተጨቆኑ ሰዎች አስደሳች የሆነው የኢየሱስ ባሕርይና መንፈስን የሚያድሰው መልእክቱ ያጽናናቸው ነበር።

7, 8. ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት በሕጉ መሠረት ምን እንድታደርግ አይፈቀድላትም ነበር? ኢየሱስ ግን ይህችን ሴት የያዛት እንዴት ነበር?

7 ኢየሱስ ሴቶችን የያዘበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ወንዶች ሴቶችን ሲጨቁኗቸው ኖረዋል። በጥንቷ እስራኤል የነበሩት የሃይማኖት መሪዎችም ሴቶችን የሚይዙት በዚህ መንገድ ነበር። ኢየሱስ ግን ለሴቶች አክብሮት ነበረው። ለ12 ዓመት ደም ሲፈሳት ለኖረች አንዲት ሴት ያደረገው ነገር ይህን በግልጽ ያሳያል። ይህች ሴት ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ “ብዙ ተሠቃይታ” የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለመዳን ስትል ያላትን ጥሪት ሁሉ ብትጨርስም “ሕመሙ ባሰባት” እንጂ አልተሻላትም። በሕጉ መሠረት ይህች ሴት ርኩስ እንደሆነች ተደርጋ ትታይ ነበር። እሷን የሚነካ ማንኛውም ሰውም ርኩስ ይሆን ነበር።—ዘሌ. 15:19, 25

8 ይህች ሴት ኢየሱስ የታመሙ ሰዎችን እንደሚፈውስ ስትሰማ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ ስላሰበች እሱን ከከበበው ሕዝብ ጋር ተቀላቀለች። ኢየሱስን ስትነካው ወዲያውኑ ዳነች። ኢየሱስ ሴትየዋ ልብሱን መንካት እንዳልነበረባት ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ይህን በማድረጓ አልወቀሳትም። እንዲያውም ደግነት አሳይቷታል። ለበርካታ ዓመታት በሕመም ስትሠቃይ በመኖሯ ስሜቷ ምን ያህል እንደተደቆሰና እርዳታ ለማግኘት ምን ያህል እንደጓጓች ተረድቶ ነበር። ኢየሱስ ርኅራኄ በሚንጸባረቅበት መንገድ “ልጄ ሆይ፣ እምነትሽ አድኖሻል። በሰላም ሂጂ፣ ከሚያሠቃይ ሕመምሽም እረፊ” አላት።—ማር. 5:25-34

9. ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ልጆች ወደ እሱ እንዳይቀርቡ በተከላከሉ ጊዜ ምን አደረገ?

9 ልጆችም እንኳ ከኢየሱስ ጋር መሆን ያስደስታቸው ነበር። በአንድ ወቅት ሰዎች ልጆችን ወደ ኢየሱስ ይዘው በመጡ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ልጆቹ እንዲያስቸግሩት እንደማይፈልግ በማሰብ ሰዎቹን ገሠጿቸው። ኢየሱስ ግን ልጆቹ እንደሚያስቸግሩት አልተሰማውም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ይህን ሲያይ [ደቀ መዛሙርቱን] ተቆጥቶ እንዲህ አላቸው፦ ‘ልጆቹ ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ ምክንያቱም የአምላክ መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ነው።’” “ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ይባርካቸው ጀመር።” ኢየሱስ ልጆችን የሚያቀርበው የግድ ሆኖበት አልነበረም፤ እንዲያውም ሞቅ ባለ ስሜት ተቀብሏቸዋል።—ማር. 10:13-16

10. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያሳያቸውን ባሕርያት ያዳበረው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ያሳያቸውን ባሕርያት ያዳበረው እንዴት ነው? ሰው ከመሆኑ በፊት በሰማይ በቆየባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዘመናት የአባቱን ባሕርያት ያስተዋለ ከመሆኑም ሌላ አባቱ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በመመልከት ትምህርት ይቀስም ነበር። (ምሳሌ 8:22, 23, 30ን አንብብ።) ኢየሱስ በሰማይ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በሁሉም ፍጥረታቱ ላይ የራስነት ሥልጣኑን በፍቅር የሚጠቀምበት እንዴት እንደሆነ የተመለከተ ሲሆን እሱም የአባቱን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ተከትሏል። ኢየሱስ ለአባቱ ሥልጣን ተገዢ ባይሆን ኖሮ የእሱን ምሳሌ ለመከተል ይነሳሳ ነበር? የአምላክ ልጅ ለአባቱ ሥልጣን መገዛት የሚያስደስተው ሲሆን ይሖዋም እንዲህ ዓይነት ልጅ ስላለው ደስተኛ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሰማይ አባቱን ግሩም ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በሰማይ ባለው መንግሥት ላይ እንዲገዛ አምላክ ለሾመው ንጉሥ ማለትም ለክርስቶስ መገዛታችን እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!

የክርስቶስን ባሕርያት አንጸባርቁ

11. (ሀ) ማንን ለመምሰል ጥረት ማድረግ አለብን? (ለ) በተለይ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?

11 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ በተለይም ወንዶች የክርስቶስን ባሕርያት ለማንጸባረቅ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” እንደሆነ ይናገራል። ክርስቶስ የእሱ ራስ የሆነውን እውነተኛውን አምላክ እንደመሰለ ሁሉ ክርስቲያን ወንዶችም ራሳቸው የሆነውን ክርስቶስን ለመምሰል መጣር ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ሲሆን ይህንን አድርጓል። “እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ” በማለት የእምነት ባልንጀሮቹን መክሯቸዋል። (1 ቆሮ. 11:1) ሐዋርያው ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል፦ “የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል።” (1 ጴጥ. 2:21) በተለይ ወንዶች ክርስቶስን እንድንመስል ለተሰጠን ምክር ትኩረት እንዲሰጡት የሚያነሳሳቸው ሌላም ምክንያት አለ። ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚሆኑት እነሱ ናቸው። ኢየሱስ ይሖዋን በመምሰሉ ይደሰት እንደነበረ ሁሉ ክርስቲያን ወንዶችም ክርስቶስን በመምሰልና ባሕርያቱን በማንጸባረቅ ሊደሰቱ ይገባል።

12, 13. ሽማግሌዎች በአደራ የተሰጧቸውን በጎች እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?

12 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች የክርስቶስን አርዓያ ለመከተል ጥረት የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች የሚከተለውን ጥብቅ ምክር ሰጥቷቸዋል፦ “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ ጠብቁ፤ በግዴታ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት፣ የአምላክ ንብረት በሆኑት ላይ ሥልጣናችሁን በማሳየት ሳይሆን ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ።” (1 ጴጥ. 5:1-3) ክርስቲያን ሽማግሌዎች አምባገነን ወይም ፈላጭ ቆራጭ እንዲሁም ምክንያታዊነትና ደግነት የጎደላቸው መሆን የለባቸውም። ሽማግሌዎች የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል በአደራ ለተሰጧቸው በጎች ፍቅርና አሳቢነት ለማሳየት እንዲሁም በጎቹን በትሕትናና በደግነት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ።

13 በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ወንድሞች ፍጽምና የጎደላቸው ናቸው፤ በመሆኑም አቅማቸው ውስን መሆኑን ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ሮም 3:23) እንግዲያው ስለ ኢየሱስ ለመማርና የእሱ ዓይነት ፍቅር ለማንጸባረቅ ከልብ ሊነሳሱ ይገባል። አምላክና ክርስቶስ ሰዎችን በሚይዙበት መንገድ ላይ ማሰላሰልና የእነሱን ምሳሌ ለመከተል መጣር ይኖርባቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ የሚል ምክር ሰጥቶናል፦ “እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥ. 5:5

14. ሽማግሌዎች እስከ ምን ድረስ ሌሎችን ማክበር ይኖርባቸዋል?

14 በጉባኤ ውስጥ የተሾሙ ወንዶች የአምላክን መንጋ በሚይዙበት ጊዜ ግሩም ባሕርያትን ማሳየት ይኖርባቸዋል። ሮም 12:10 እንዲህ ይላል፦ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ለሌሎች አክብሮት ያሳያሉ። እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሁሉ እነዚህ ወንዶችም ‘ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው በትሕትና ማሰብ እንጂ በምቀኝነት ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር ማድረግ’ የለባቸውም። (ፊልጵ. 2:3) ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል። እነዚህ የተሾሙ ወንዶች እንዲህ ሲያደርጉ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር በተግባር ያውላሉ፦ “እኛ ብርቱዎች የሆንን ብርቱ ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት ልንሸከም ይገባል እንጂ ራሳችንን የምናስደስት መሆን የለብንም። እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውን ይኸውም ሊያንጸው የሚችለውን ነገር በማድረግ እናስደስተው። ክርስቶስ እንኳ ራሱን አላስደሰተም።”—ሮም 15:1-3

‘ለሚስቶች ክብር መስጠት’

15. ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?

15 እስቲ አሁን ደግሞ ጴጥሮስ ላገቡ ወንዶች የሰጠውን ምክር እንመልከት። “ባሎች ሆይ፣ . . . ከእናንተ ይበልጥ ተሰባሪ ዕቃ ለሆኑት [ለሚስቶቻችሁ] ክብር በመስጠት ልክ እንደዚሁ ከእነሱ ጋር በእውቀት መኖራችሁን ቀጥሉ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥ. 3:7) አንድን ሰው ማክበር ሲባል ያንን ግለሰብ ከፍ አድርጎ መመልከት ማለት ነው። ስለዚህ የግለሰቡን አመለካከትና ፍላጎት እንዲሁም የሚያስፈልገውን ነገር ከግምት ታስገባለህ፤ እንዲሁም ሐሳቡን እንዳትቀበል የሚያደርግህ በቂ ምክንያት እስከሌለህ ድረስ ከእሱ ፈቃድ ጋር ትስማማለህ። አንድ ባልም ሚስቱን መያዝ ያለበት በዚህ መንገድ ነው።

16. የአምላክ ቃል ሚስቶቻቸውን ከማክበር ጋር በተያያዘ ለባሎች ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?

16 ጴጥሮስ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ ምክር ሲሰጥ “ጸሎታችሁ እንዳይታገድ” የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥቶ ነበር። (1 ጴጥ. 3:7) ይህ አባባል አንድ ወንድ ሚስቱን የሚይዝበትን መንገድ ይሖዋ አክብዶ እንደሚመለከተው በግልጽ ያሳያል። ለሚስቱ አክብሮት የማያሳይ ከሆነ ጸሎቱ ሊታገድ ይችላል። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ ሚስቶች ጥሩ ምላሽ የሚሰጡት ባሎቻቸው በአክብሮት ሲይዟቸው አይደለም?

17. አንድ ባል ሚስቱን እስከ ምን ድረስ ሊወዳት ይገባል?

17 ሚስትን መውደድን በተመለከተ የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል ምክር ይሰጣል፦ “ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ አካላቸው አድርገው ሊወዷቸው ይገባል። . . . ምክንያቱም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም ሰው የለም፤ ከዚህ ይልቅ ይመግበዋል እንዲሁም ይሳሳለታል፤ ክርስቶስም ለጉባኤው ያደረገው እንደዚሁ ነው፤ . . . ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ።” (ኤፌ. 5:28, 29, 33) ባሎች ሚስቶቻቸውን እስከ ምን ድረስ ሊወዷቸው ይገባል? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደና ለእሱ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ሁሉ እናንተም ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።” (ኤፌ. 5:25) በእርግጥም፣ ክርስቶስ ለሰዎች እንዳደረገው ሁሉ አንድ ባልም ሕይወቱን እንኳ ለሚስቱ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆን ይገባል። አንድ ክርስቲያን ባል ለሚስቱ ፍቅርና አሳቢነት የሚያሳያት፣ ትኩረት የሚሰጣት እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ የሚይዛት ከሆነ ሚስቱ ለራስነት ሥልጣኑ መገዛት ቀላል ይሆንላታል።

18. ባሎች በትዳራቸው ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ምን እርዳታ ማግኘት ይችላሉ?

18 ባሎች ለሚስቶቻቸው የዚህን ያህል አክብሮት መስጠት ከአቅማቸው በላይ ነው? አይደለም፣ ይሖዋ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ በፍጹም አይጠይቃቸውም። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ አምላኪዎች በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለውን ኃይል ማለትም የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ማግኘት ይችላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳላችሁ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” (ሉቃስ 11:13) ባሎች በሚጸልዩበት ጊዜ ሚስቶቻቸውን ጨምሮ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲረዳቸው መጠየቅ ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:32ን አንብብ።

19. በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

19 በእርግጥም ወንዶች፣ ለክርስቶስ እንዴት መገዛት እንዳለባቸውና የራስነት ሥልጣኑን የተጠቀመበትን መንገድ እንዴት መከተል እንደሚችሉ በመማር ረገድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ይሁንና ስለ ሴቶች በተለይም ስለ ሚስቶች ምን ማለት ይቻላል? የሚቀጥለው ርዕስ ሴቶች፣ በይሖዋ ዝግጅት ውስጥ ስላላቸው ቦታ ምን አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያብራራል።

ታስታውሳለህ?

• የትኞቹን የኢየሱስ ባሕርያት ልናንጸባርቅ ይገባል?

• ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?

• አንድ ባል ሚስቱን እንዴት መያዝ ይኖርበታል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለሌሎች አክብሮት በማሳየት የክርስቶስን ምሳሌ ተከተሉ