በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይምጡና ይጎብኙ!

ይምጡና ይጎብኙ!

ይምጡና ይጎብኙ!

መጥተው የሚጎበኙት ምኑን ነው? ብዙውን ጊዜ ቤቴል ተብሎ የሚጠራውን ከይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች አንዱን ነው። በተለያዩ አገሮች ውስጥ 118 ቅርንጫፍ ቢሮዎች አሉ። ጎብኚዎች በቤቴል የሚከናወነውን ነገር ከተመለከቱ በኋላ ልባቸው ስለሚነካ ብዙውን ጊዜ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ።

በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በሜክሲኮ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኘበት ወቅት ይሖዋን በደስታ የሚያገለግሉ በርካታ ትጉ ሠራተኞችን ተመልክቶ በጣም ስለተገረመ “እዚህ ለመኖር ምን ማድረግ አለብኝ?” በማለት ጠይቆ ነበር። “መጀመሪያ መጠመቅ አለብህ። ከዚያም አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ብትሆን ጥሩ ነው” የሚል መልስ ተሰጠው። ወጣቱ የተሰጠውን ሐሳብ ተግባራዊ ስላደረገ ከሁለት ዓመት በኋላ በሜክሲኮ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲያገለግል ተጠራ፤ አሁን በዚያ ማገልገል ከጀመረ 20 ዓመት ሆኖታል።

ቤቴል ምንድን ነው?

“ቤቴል” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ‘የአምላክ ቤት’ የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍ. 28:19 የግርጌ ማስታወሻ) እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማተምና ለማሰራጨት እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ከ100,000 በላይ ለሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ያገለግላሉ። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ቤቴሎች ውስጥ ሙሉ ጊዜ የሚሠሩ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ወደ 20,000 የሚጠጉ ወንዶችና ሴቶች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ይሖዋንና መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውን ያገለግላሉ። በዚህ ክርስቲያናዊ ሥራ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ክርስቲያኖች አፍላ ጉልበት ካላቸው ወጣቶች ጋር በመሆን ይሠራሉ። የቤቴል ቤተሰብ አባላት ምሽት ላይ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ይካፈላሉ። በተጨማሪም ያላቸውን ነፃ ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለመዝናናትና የግል ጉዳዮቻቸውን ለማከናወን ይጠቀሙበታል።

የቤቴል ቤተሰብ አባላት በየወሩ አነስተኛ የወጪ መተኪያ ይሰጣቸዋል። ጣፋጭና ተመጣጣኝ ምግብ የሚመገቡ ሲሆን ንጹሕና ምቹ በሆኑ ሕንፃዎች ውስጥ ይኖራሉ። የቤቴል ቤቶች እጅግ ያጌጡና የተንቆጠቆጡ ባይሆኑም አስፈላጊውን ጥቅም ይሰጣሉ። ጎብኚዎች በደንብ በተያዙት ሕንፃዎች፣ ግቢዎች፣ በተደራጀ ሁኔታ በሚሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን ቤቴላውያን በሚያሳዩት የደግነትና የትብብር መንፈስ ይገረማሉ። ሁሉም ሰው በትጋት የሚሠራ ቢሆንም በሥራ መወጠራቸው ወዳጃዊ ስሜት እንዳያሳዩ አያደርጋቸውም። በቤቴል ውስጥ ማንም ከማንም እንደሚበልጥ ተደርጎ አይታይም፤ እንዲሁም የሥራ ምድብ ልዩነት መኖሩ አንዱ ከሌላው ከፍ ያለ እንደሆነ ተደርጎ እንዲቆጠር አያደርገውም። በቤቴል ውስጥ የሚከናወነው ማንኛውም ሥራ ይኸውም ቤት ማጽዳትም ይሁን አትክልት መንከባከብ፣ ምግብ ማብሰል አሊያም በኅትመት ክፍልና በቢሮዎች ውስጥ መሥራት ሁሉም በጣም አስፈላጊ ነው። ቤቴላውያን ተብለው የሚጠሩት በቤቴል ውስጥ የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን አገልግሎት ለመደገፍ እንደ አንድ ቡድን ሆነው በኅብረት ይሠራሉ።—ቆላ. 3:23

አንዳንድ ቤቴላውያን ምን ይላሉ?

እስቲ ስለ እነዚህ ዓለም አቀፍ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሁኔታ የበለጠ እንመልከት። እነዚህን ሰዎች በቤቴል እንዲያገለግሉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ይህን ለማወቅ የማርዮን ሁኔታ እንመልከት። ማርዮ የይሖዋ ምሥክር በሆነበት ጊዜ በአንድ ስመ ጥር በሆነ የጀርመን የመኪና ድርጅት ውስጥ ይሠራ ስለነበር ጥሩ ይከፈለው ነበር፤ እንዲሁም የበለጠ እድገት የማግኘት አጋጣሚ ነበረው። ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ በአገሩ በሚገኝ ቤቴል ውስጥ ለአንድ ሳምንት ለመሥራት ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ። በኅትመት ክፍል እንዲሠራ ተመደበ። ማርዮ፣ ቤቴል አብሯቸው ይሠራ የነበሩ ሰዎች በሰብዓዊ ሥራው ከሚያገኛቸው ሰዎች ምን ያህል የተለዩ እንደሆኑ መመልከት ችሎ ነበር። በመሆኑም በቤቴል በሙሉ ጊዜ ለማገልገል አመለከተ። በርካታ ዘመዶቹና የሥራ ባልደረቦቹ ያደረገው ውሳኔ ባይገባቸውም በአሁኑ ጊዜ ማርዮ ጀርመን በሚገኘው ቤቴል ውስጥ በደስታ እያገለገለ ነው።

አብዛኞቹ ቤቴላውያን ቤቴል በገቡበት ወቅት የተለየ ትምህርት ወይም ችሎታ አልነበራቸውም። በሜክሲኮ ቤቴል ለ15 ዓመት ያገለገለው የአቤል ሁኔታ ይህንን ያረጋግጥልናል። እንዲህ ብሏል፦ “በቤቴል ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። በጣም ውስብስብ የሆኑ የማተሚያ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ ተምሬያለሁ። ከቤቴል ውጪ ሌላ ቦታ ብሠራ ይህ እውቀት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝልኝ አውቃለሁ፤ ሆኖም እዚህ የማገኘውን ደስታ ላገኝ አልችልም። በሌሎች መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ካለ ጭንቀትና የፉክክር መንፈስ ነፃ ሆኜ የተረጋጋና አስደሳች ሕይወት እየመራሁ ነው። መንፈሳዊነቴንም ሆነ አጠቃላይ እውቀቴን ለማሳደግ የረዳኝ ከሁሉ የተሻለ ትምህርት እንዳገኘሁ ይሰማኛል። ስመ ጥር በሆነ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም እንኳ እንዲህ ዓይነት እውቀት ማግኘት አልችልም።”

ቤቴልን መጎብኘት ያበረታታል

አንድ ሰው ቤቴልን መጎብኘቱ ብቻ በመንፈሳዊነቱ ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ለዚህ እንደ ምሳሌ በሜክሲኮ የሚገኘውን የኦማርን ሁኔታ መመልከት እንችላለን። እናቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ብታስተምረውም በ17 ዓመቱ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትም ሆነ በአገልግሎት መካፈል አቆመ። በመጨረሻም በመጥፎ አኗኗር ውስጥ የተዘፈቀ ከመሆኑም በላይ ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ጀመረ። ኦማር በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሠራ እያለ ድርጅቱ በሜክሲኮ ወደሚገኘው ቤቴል ሄደው አንዳንድ መሣሪያዎችን ለማስተዋወቅ ከመረጣቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነበር። ኦማር እንዲህ ብሏል፦ “መሣሪያዎቻችንን ካስተዋወቅን በኋላ የተቀበለን ሰው ሕንፃውን ያስጎበኘን ጀመር። ያየሁት ነገርም ሆነ የተደረገልኝ ጥሩ አቀባበል ከይሖዋ ተለይቼ ስለምመራው ሕይወት እንዳስብ አደረገኝ። ወዲያውኑ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ቤቴልን ከጎበኘሁ ከስድስት ወር በኋላ ተጠመቅሁ። ቤቴልን ስጎበኝ ልቤ እንዲነሳሳ በማድረጉ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።”

በጃፓን የሚኖረው ማሳሂኮም ያደገው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ የክርስትና መንገድ በጣም ጥብቅ እንደሆነ ይሰማው ነበር። በትምህርት ቤት በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ከመጠን በላይ ከመጠመዱ የተነሳ በስብሰባዎች ላይ መገኘትም ሆነ በስብከቱ ሥራ መካፈል አቆመ። ማሳሂኮ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን ቤተሰባችንና ጥቂት ክርስቲያን ጓደኞቻቸው ቤቴልን ለመጎብኘት ወሰኑ። ቤተሰቤም ከእነሱ ጋር እንድሄድ ስለጎተጎቱኝ አብሬያቸው ሄድኩ። ቤቴልን መጎብኘቴ ከዚህ በፊት በፍጹም ተሰምቶኝ የማያውቅ የመነቃቃት መንፈስ እንዲሰማኝ አደረገኝ። በጉዞ ላይ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መቀራረቤ የይሖዋ ምሥክር ካልሆኑ ጓደኞቼ ጋር ስሆን ፈጽሞ አግኝቼው የማላውቀውን ደስታ እንዳገኝ አድርጎኛል። ክርስቲያናዊውን የሕይወት ጎዳና ለመከተል ያለኝ ፍላጎት በመጨመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርልኝ ለመጠየቅ ወሰንኩ።” ማሳሂኮ በአሁኑ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆኖ እያገለገለ ነው።

በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለሥራ ወደ ሞስኮ ሄደች። በዚያም ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር መገናኘት ስላልቻለች በመንፈሳዊ ተዳከመች። መጥፎ ድርጊት መፈጸም የጀመረች ከመሆኑም በላይ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው አገባች። አንዲት እህት ልትጠይቃት ከፈረንሳይ ወደ ሞስኮ በሄደችበት ጊዜ በሴንት ፒተርስበርግ፣ ሩሲያ የሚገኘውን ቤቴል ለመጎብኘት ሄዱ። እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ቤቴል በተደረገልን ሞቅ ያለ አቀባበል ልቤ ተነካ። ቦታው ሰላም የሰፈነበት ነው። የይሖዋ መንፈስ በዚያ እንዳለ አስተውያለሁ። ከይሖዋ ድርጅት በመራቅ እንዴት እንዲህ ያለ ስህተት እሠራለሁ? ቤቴልን ጎብኝቼ ከተመለስኩ በኋላ ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸሎት አቅርቤ በአዲስ መንፈስ ልጆቼን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመርኩ።” በመንፈሳዊ ደክማ የነበረችው ይህች እህት ከተደረገላት መንፈሳዊ እርዳታ ባሻገር ቤቴልን መጎብኘቷ በእጅጉ አበረታቷታል፤ ከዚያ በኋላም ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርጋለች።

የይሖዋ ምሥክሮችን እምብዛም የማያውቁ ሰዎች ቤቴልን ሲጎበኙ ስለሚሰማቸው ስሜትስ ምን ማለት ይቻላል? በፖለቲካ ውስጥ ተጠላልፎ የነበረው አልቤርቶ በ1988 በብራዚል የሚገኘውን ቤቴል ጎበኘ። የቤቴል ንጽሕና፣ ሥርዓታማነት በተለይም በዚያ የሚሠራው ሥራ በሚስጥር የሚካሄድ አለመሆኑ በጣም አስደነቀው። አልቤርቶ ቤቴልን ከመጎብኘቱ ከጥቂት ጊዜያት በፊት የባለቤቱ ወንድም ቄስ ሆኖ የሚያገለግልበትን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ጎብኝቶ ነበር። አልቤርቶ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት አስተውሎ ነበር። “በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሁሉ ነገር የሚከናወነው በሚስጥር ነበር” ብሏል። ቤቴልን ከጎበኘ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ የተቀበለ ከመሆኑም በላይ በፖለቲካ ውስጥ የሚያደርገውን ተሳትፎ አቆመ፤ አልቤርቶ በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።

ኑና ቤቴልን ጎብኙ!

ብዙዎች በአገራቸው የሚገኘውን ቤቴል ለመጎብኘት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጠይቆባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ፓውሎና አውዤንየ የሚኖሩት በብራዚል የሚገኘው ቤቴል ካለበት 3,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፤ በአገራቸው የሚገኘውን ይህን ቤቴል ለመጎብኘት ሁለት ቀን በአውቶቡስ መጓዝ ስለሚጠይቅባቸው ይህን ወጪ ለመሸፈን ለአራት ዓመት ገንዘብ ማጠራቀም ነበረባቸው። እንዲህ ብለዋል፦ “ያደረግነው ጥረት ሁሉ የሚክስ ነበር። አሁን ስለ ይሖዋ ድርጅት ሰፋ ያለ ግንዛቤ አግኝተናል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በቤቴል ስለሚከናወነው ሥራ ስናብራራላቸው አንዳንድ ጊዜ ‘እዚያ ሄዳችሁ ታውቃላችሁ?’ በማለት ይጠይቁናል። አሁን ‘አዎን’ በማለት መመለስ እንችላለን።”

በአገርህ ወይም በጎረቤት አገር የቅርንጫፍ ቢሮ ወይም የቤቴል ቤት ይገኛል? ይህን ቦታ ሄደህ እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን። ቤቴልን ስትጎበኝ ሞቅ ያለ አቀባበል እንደሚደረግልህና ቤቴልን በመጎብኘትህ ከፍተኛ መንፈሳዊ ጥቅም እንደምታገኝ እርግጠኛ ሁን።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርዮ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቤል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀርመን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጃፓን

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብራዚል