በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ካልቪኒዝም በ500 ዓመት ውስጥ ምን ማከናወን ችሏል?

ካልቪኒዝም በ500 ዓመት ውስጥ ምን ማከናወን ችሏል?

ካልቪኒዝም በ500 ዓመት ውስጥ ምን ማከናወን ችሏል?

ዣን ኮቨን (ጆን ካልቪን) በ1509 በኗዮኝ፣ ፈረንሳይ ተወለደ። ካልቪን በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች፣ በአሜሪካ አህጉራት፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች ቦታዎች በሚኖሩ በርካታ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ አካሂዷል። በምዕራቡ ዓለም ታሪክ ውስጥ ከዋነኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ አራማጆች አንዱ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።

ካልቪኒዝም (የካልቪን ንድፈ ሐሳቦችና ትምህርቶች) ካልቪን ከተወለደ ከ500 ዓመት በኋላ በዛሬው ጊዜም እንኳ እንደ ፕሬስባይቲሪያን፣ ኮንግርጌሽናል፣ የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያንና ፒዩሪታን ባሉት እንዲሁም በሌሎች በፕሮቴስታንት ሥር የሚታቀፉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በተለያየ መልኩ ተጽዕኖ ያሳድራል። የዓለም የተሃድሶ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እስካለፈው መስከረም ድረስ በ107 አገሮች ውስጥ 75 ሚሊዮን ተከታዮች እንዳሉት ገልጿል።

ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረው ግጭት

የካልቪን አባት፣ በኗዮኝ የነበረው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃና ፀሐፊ ነበር። የሥራው ባሕርይ በዘመኑ በነበሩት ቀሳውስት ዘንድ በስፋት የሚታየውን ምግባረ ብልሹነት ለመመልከት አጋጣሚ ሳይሰጠው አልቀረም። የጆን አባትና ታላቅ ወንድሙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንዲቃወሙና እንዲያቃልሉ ያነሳሳቸው ምክንያት ይህ ይሁን ሌላ በእርግጠኝነት ማወቅ ባንችልም ከጊዜ በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ እነዚህን ሰዎች አውግዛቸዋለች። ጆን አባቱ ሲሞት የክርስቲያን መቀበሪያ ቦታ ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። ጆን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ የነበረውን ጥርጣሬ ይበልጥ ያጠናከረው ይህ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም።

ስለ ካልቪን የተጻፉ በርካታ ሥነ ጽሑፎች በባሕርዩ ዝምተኛና ጭምት እንደነበረ ከመግለጽ ውጭ ስለ ወጣትነት ሕይወቱ ብዙም የሚናገሩት ነገር የለም። በፓሪስ፣ በኦሌኦኝና በቡርዥ ተማሪ በነበረበት ጊዜ እንኳ ብዙ ጓደኞች የነበሩት አይመስልም። ይሁን እንጂ ካልቪን ፈጣን አእምሮና አስደናቂ የሆነ የማስታወስ ተሰጥኦ ነበረው። በዚህ ተሰጥኦው ላይ ሠርቶ የማይደክም ሰው መሆኑ (በየቀኑ ከማለዳው 11 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ያጠና ነበር) ታክሎበት 23 ዓመት ሳይሆነው በሕግ ሙያ የዶክተርነት ማዕረግ ማግኘት ቻለ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሲል ዕብራይስጥ፣ ግሪክኛና ላቲን ተማረ። ይሁን እንጂ ካልቪን በዋነኝነት የሚታወቀው ጥሩ የሥራ ባሕል ያለው ታታሪ ሰው በመሆኑ ነው፤ ዛሬም ቢሆን ብዙዎች ይህንን ባሕርይ ከካልቪኒዝም ጋር ያያይዙታል።

ካልቪን በኖረበት ዘመን አጎራባች አገር በሆነችው በጀርመን ማርቲን ሉተር፣ በሥነ ምግባር ብልሹ በመሆኗ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችን በማስተማሯ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በይፋ መተቸት ጀምሮ ነበር። በ1517 ማርቲን ሉተር ቤተ ክርስቲያኗ ለውጥ እንድታደርግ ለማሳሰብ 95 የተቃውሞ ነጥቦችን በዊትንበርግ ይገኝ በነበረ አንድ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ እንደለጠፈ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። ሉተር ያነሳው ሐሳብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ የተሃድሶው እንቅስቃሴ በመላው አውሮፓ በፍጥነት ተሰራጨ። ይህ እንቅስቃሴ በብዙ ቦታዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲነሳ ያደረገ ሲሆን ፕሮቴስታንቶቹ ወይም ተቃዋሚዎቹ አመለካከታቸውን በማስፋፋታቸው ችግር ይደርስባቸው ነበር። በ1533 የካልቪን ወዳጅ የነበረው ኒኮላ ኮፕ፣ ሉተርን የሚደግፍ ንግግር በፓሪስ አቀረበ፤ ካልቪን ይህን ንግግር በማዘጋጀት ኮፕን ረድቶት ስለነበረ ሁለቱም ሕይወታቸውን ለማዳን አገር ጥለው ለመሸሽ ተገደዱ። ካልቪን ከዚያ በኋላ በፈረንሳይ አልኖረም።

ካልቪን የፕሮቴስታንት እምነት ዋነኛ ማስተማሪያ የሆነውን የክርስትና ሃይማኖት መመሪያዎች (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ በ1536 አሳተመ። ይህን መጽሐፍ የጻፈው ለንጉሥ ቀዳማዊ ፍራንሲስ ሲሆን በመጽሐፉ ላይ የፈረንሳይ ፕሮቴስታንቶችን (ከጊዜ በኋላ ሂውገነቶች ተብለዋል) የሚደግፍ ሐሳብ አቅርቧል። ካልቪን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች የተቃወመ ከመሆኑም ሌላ የእምነቱ ዋነኛ መሠረት የሆነውን የአምላክን ሉዓላዊነት በመደገፍ ጽፏል። የካልቪን መጽሐፍ በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ካሳደረው ተጽዕኖ በተጨማሪ ለፈረንሳይኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መዳበር ባደረገው አስተዋጽኦ ይታወቃል። ካልቪን ዋነኛና ግንባር ቀደም ከሆኑት የተሃድሶ አራማጆች አንዱ እንደሆነ ተቆጥሮ አድናቆት ተችሮታል። ከጊዜ በኋላ መኖሪያውን በጄኔቫ ከተማ ስዊዘርላንድ ያደረገ ሲሆን ከ1541 በኋላ ይህችን ከተማ የተሃድሶ እንቅስቃሴው ዋነኛ ማዕከል አደረጋት።

የተሃድሶ እንቅስቃሴውን በጄኔቫ ማስፋፋት

ካልቪን በጄኔቫ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ካልቪን ለመልካም ሥነ ምግባርና ለጽድቅ ትልቅ ቦታ ይሰጥ ስለነበር ጄኔቫን “በመጥፎ ምግባሯ መታወቋ ቀርቶ ነዋሪዎቿ በሙሉ . . . ጥብቅ በሆነ የሥነ ምግባር ደንብ የሚመሩባት ከተማ” እንድትሆን እንዳደረጋት ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪልጅን ገልጿል። በሌሎች መንገዶችም የተካሄዱ ለውጦች ነበሩ። በበርሊን የሚገኘው የጀርመን የታሪክ ቤተ መዘክር አስተዳዳሪ የሆኑት ዶክተር ዛቢኔ ቪት “በፈረንሳይ በተደረጉት ሃይማኖታዊ ጦርነቶች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ፕሮቴስታንት ስደተኞች [ወደ ጄኔቫ] በመጉረፋቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ብዛት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ አደገ” በማለት ተናግረዋል። እንደ ካልቪን ሥራ ወዳድ የነበሩት ሂውገነቶች፣ ጄኔቫ ሰዓት በመሥራትና ኅትመት በማካሄድ የታወቀች ከተማ እንድትሆን በማድረግ ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ ደረጃ አሳደጉት።

ፕሮቴስታንቶች ከንግሥት ቀዳማዊት ሜሪ ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው የነበረበትን እንግሊዝን ጨምሮ ከብዙ አገሮች የተሰደዱ ሰዎች ወደ ጄኔቫ መጥተዋል። በአብዛኛው ተሰድደው ከመጡ ትናንሽ ቡድኖች የተውጣጡት ካልቪኒስቶች ክሪስት ኢን ዴር ጌገንቫርት (ዘመናዊው ክርስቲያን) የተባለው ሃይማኖታዊ መጽሔት “የስደተኞች ቲኦሎጂ” ብሎ የጠራውን ትምህርት አዳበሩ። ስደተኞቹ በ1560 ጄኔቫ ባይብል የተባለውን የመጀመሪያውን በቁጥሮች የተከፋፈለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ አሳተሙ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በመጠኑ አነስ ያለ በመሆኑ የአምላክን ቃል በግል ለማጥናት አመቺ ነበር። ፒዩሪታኖች በ1620 ወደ ሰሜን አሜሪካ በተሰደዱበት ጊዜ ይዘው የሄዱት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሳይሆን አይቀርም።

ይሁን እንጂ ጄኔቫ ወደ እሷ የመጡትን ሁሉ እጇን ዘርግታ አልተቀበለችም። በ1511 በስፔን የተወለደው ማይክል ሰርቪተስ ግሪክኛ፣ ላቲን፣ ዕብራይስጥና የሕክምና ሙያ ያጠና ሲሆን ከካልቪን ጋር የተገናኘው ሁለቱም በፓሪስ ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት ሊሆን ይችላል። ሰርቪተስ መጽሐፍ ቅዱስን ሲመረምር የሥላሴ ትምህርት የቅዱሳን መጻሕፍት ድጋፍ እንደሌለው ተገነዘበ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከካልቪን ጋር ለመወያየት ደብዳቤ የጻፈለት ቢሆንም ካልቪን ሰርቪተስን እንደ ወዳጅ ሳይሆን እንደ ጠላት አድርጎ ተመለከተው። ሰርቪተስ በፈረንሳይ ካቶሊኮች ስደት ስላደረሱበት የካልቪን ከተማ ወደነበረችው ወደ ጄኔቫ ሸሸ። ሆኖም በዚያ እንደጠበቀው ጥሩ አቀባበል አልተደረገለትም፤ ከዚህ ይልቅ የታሰረ ሲሆን በመናፍቅነት ተከስሶ በ1553 በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ተቃጠለ። የታሪክ ምሑር የሆኑት ፍሪድሪክ ኦህኒንገ “የሰርቪተስ መገደል ታላቅ የተሃድሶ አራማጅ በነበረው [በካልቪን] ሕይወትና ሥራዎች ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል” ብለዋል።

ካልቪን የተሃድሶ ሥራውን እያከናወነ በርካታ ጽሑፎችን ጽፏል። ከ100 የሚበልጡ የማመሳከሪያ ጽሑፎችንና 1,000 ደብዳቤዎችን እንደጻፈ እንዲሁም 4,000 የሚያህሉ ስብከቶችን በጄኔቫ እንዳቀረበ ይነገርለታል። በእነዚህ ሁሉ መንገዶች ካልቪን ክርስትና ምን መምሰል እንዳለበት ያለውን አመለካከት ያስፋፋ ከመሆኑም ሌላ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ይገባል ብሎ የሚያስበውን የአኗኗር ዘይቤ በተለይ የአምላክ ከተማ እንድትሆን ያልማት በነበረችው በጄኔቫ ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። *

ካልቪን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በጄኔቫ ያካሄደው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ምን ውጤት አስገኝቷል? የስዊስ ፌደራል ስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት ባወጣው ዘገባ መሠረት በ2000 የተሃድሶ (ካልቪኒስት) ቤተ ክርስቲያን አባላት ከጠቅላላው የጄኔቫ ነዋሪዎች 16 በመቶ ብቻ ሲሆኑ በዚህች ከተማ ውስጥ ከካልቪኒስቶች ይልቅ የካቶሊኮች ቁጥር ይበልጣል።

ሃይማኖታዊ መከፋፈል ተስፋፋ

በተሃድሶው ምክንያት የተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች የካቶሊክን፣ የሉተራንን ወይም የካልቪኒስትን ቤተ ክርስቲያን እንደሚደግፉ በመግለጻቸው በአውሮፓ ሃይማኖታዊ መከፋፈል ነገሠ። የተሃድሶው አራማጆች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በመተቸት ረገድ አንድነት ይኑራቸው እንጂ እርስ በርሳቸው ግን ስምምነት አልነበራቸውም። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዶክተር ቪት “በፕሮቴስታንቶቹ መካከል እንኳ ሳይቀር ሃይማኖታዊ ውዝግብ ነበር” ብለዋል። የክርስትና እምነት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሚገባው ሁሉም ቢቀበሉም በሚያስተምሩት ትምህርት ረገድ ግን ቀላል የማይባል ልዩነት ነበራቸው። በወቅቱ አንገብጋቢ የነበረው ጉዳይ የጌታ እራትና የክርስቶስ መገኘት ትርጉም ነበር። ከጊዜ በኋላ ካልቪን እጅግ አወዛጋቢ ከሆኑት መሠረተ ትምህርቶቹ አንዱ የሆነውን የሰው ዕድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ማስተማር ጀመረ።

በዚህ መሠረተ ትምህርት ትርጉም ላይ ብዙ ክርክር ተደርጓል። አንደኛው የካልቪኒስቶች ቡድን፣ የሰው ልጆች ኃጢአት ከመሥራታቸው አስቀድሞ የተመረጡ ጥቂት ሰዎች በክርስቶስ በኩል መዳን እንዲያገኙና የቀሩት ግን ዕጣ ፈንታቸው ጥፋት እንዲሆን አምላክ እንደወሰነ ይሰማው ነበር። ስለሆነም ይህ ቡድን፣ መዳን በአምላክ የሚወሰን ነገር እንደሆነና ሁሉም ሰዎች በእሱ ፊት እኩል እንዳልሆኑ ያምናል። ሌሎች ካልቪኒስቶች ደግሞ መዳን ለሁሉም ሰው እንደቀረበና ይህን መቀበል ወይም አለመቀበል ለግለሰቡ ምርጫ የተተወ እንደሆነ ያምናሉ። ይህም መዳን በሰው ልጅ ነፃ ምርጫ ላይ የተመካ ነው ማለት ነው። ካልቪን ከሞተ ከብዙ ጊዜ በኋላ እንኳ ካልቪኒስቶች ስለ አምላክ ውሳኔ፣ ስለ ሰዎች ነፃ ምርጫና የሰው ልጆች በአምላክ ፊት እኩል ስለመሆናቸው የተነሱትን ውዝግቦች መፍታት አልቻሉም ነበር።

ካልቪኒዝም ያስከተለው ውጤት

በ20ኛው መቶ ዘመን፣ የካልቪንን ትምህርት የምትከተለው የደች ተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድልዎ ለመደገፍ ስትል አምላክ የሰው ልጆችን ዕጣ አስቀድሞ እንደወሰነ ገልጻ ነበር። የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት የሆኑት ኔልሰን ማንዴላ የነጮችን የበላይነት ስለሚያራምደው የመንግሥት ፖሊሲ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የደች የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ፖሊሲ ትደግፍ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያኗ አፍሪካነሮች (ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን) የአምላክ ምርጥ ሕዝብ ሲሆኑ ጥቁሮች ግን ዝቅተኛ ዝርያዎች እንደሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ በማስተላለፍ አፓርታይድ ሃይማኖታዊ ድጋፍ እንዲኖረው አድርጋለች። በአፍሪካነሮች አመለካከት አፓርታይድና ቤተ ክርስቲያን እጅና ጓንት ናቸው።”

የደች የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን አፓርታይድን በመደገፏ በ1990ዎቹ በይፋ ይቅርታ ጠይቃለች። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች በይፋ ባወጡት የሩስተንበርክ መግለጫ ላይ “አንዳንዶቻችን አፓርታይድ ትክክል መሆኑን ለማሳመን በመጽሐፍ ቅዱስ አላግባብ መጠቀማችን ብዙ ሰዎች ይህ ፖሊሲ የአምላክ ድጋፍ እንዳለው እንዲያምኑ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል። ባለፉት በርካታ ዓመታት ቤተ ክርስቲያኒቱ አፓርታይድን አስመልክቶ የነበራት አቋም፣ በዘር መድልዎ ምክንያት ለደረሰው መከራ አስተዋጽኦ ከማድረግም አልፎ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው አምላክ ነው የሚል አመለካከት እንዲፈጠር አድርጓል!

ጆን ካልቪን በ1564 በጄኔቫ ሞተ። ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ ባልደረቦቹ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች “ምንም ዓይነት ክብር ለማይገባው ሰው ይህን ያህል ክብር [በመስጠታቸው]” ካመሰገናቸው በኋላ ግልፍተኛና ትዕግሥት የለሽ በመሆኑ ይቅርታ እንዲያደርጉለት እንደጠየቀ ይነገራል። ጆን ካልቪን እንደዚህ ዓይነት ጉድለቶች ቢኖሩትም እንኳ ታታሪነት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ኃላፊነትን በትጋት መወጣት የሚንጸባረቅበት የፕሮቴስታንቶች የሥራ ባሕል ከእሱ ባሕርይና እሴቶች ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል መካድ አይቻልም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የሰው ዘር አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 321-325 ተመልከት።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በተሃድሶው ምክንያት የተለያዩ ከተሞችና ግዛቶች የካቶሊክን፣ የሉተራንን ወይም የካልቪኒስትን ቤተ ክርስቲያን እንደሚደግፉ በመግለጻቸው በአውሮፓ ሃይማኖታዊ መከፋፈል ነገሠ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ስፔን

ፈረንሳይ

ፓሪስ

ኗዮኝ

ኦሌኦኝ

ቡርዥ

ስዊዘርላንድ

ጄኔቫ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስትና ሃይማኖት መመሪያዎች (1536) የተባለው የካልቪን መጽሐፍ ለፕሮቴስታንት እምነት መሠረት ጥሏል

[ምንጭ]

© INTERFOTO/Alamy

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰርቪተስ መገደል በካልቪን ሕይወትና ሥራዎች ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሏል

[ምንጭ]

© Mary Evans Picture Library

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጄኔቫ ባይብል” (1560) የመጀመሪያው በቁጥሮች የተከፋፈለ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው

[ምንጭ]

Courtesy American Bible Society

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

French town: © Mary Evans Picture Library