በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃየን ሚስቱን ያገኘው ከየት ነበር?

ቃየን ሚስቱን ያገኘው ከየት ነበር?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

ቃየን ሚስቱን ያገኘው ከየት ነበር?

“አዳምና ሔዋን የነበሯቸው ቃየንና አቤል የተባሉ ሁለት ልጆች ከሆነ ቃየን ሚስቱን ያገኘው ከየት ነበር?” ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ሰዎችን ለማደናገር እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያነሱ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለማግኘት የሚያስችል በቂ ማብራሪያ ይዟል።

ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 እና 4 ላይ የሚከተሉትን መረጃዎች እናገኛለን፦ (1) ሔዋን “የሕያዋን ሁሉ እናት” ናት። (2) ቃየን በተወለደበትና ወንድሙን አቤልን በገደለበት ጊዜ መካከል የተወሰነ ጊዜ አልፏል። (3) ቃየን “ኰብላይና ተንከራታች” ሆኖ እንዲኖር ሲወሰንበት “የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል” የሚል ስጋት አድሮበት ነበር። (4) አምላክ ቃየን እንዳይገደል ሲል በእሱ ላይ ምልክት ማድረጉ ቃየንን ወንድሞቹና እህቶቹ ወይም ሌሎች ዘመዶቹ ሊገድሉት ይችሉ እንደነበር ይጠቁማል። (5) ቃየን ሚስቱን የተገናኛት ‘በኖድ ምድር’ መኖር ከጀመረ በኋላ ነው።—ዘፍጥረት 3:20፤ 4:3, 12, 14-17

ከላይ በቀረቡት ማስረጃዎች ላይ ተመርኩዘን የቃየን ሚስት የሔዋን ዝርያ እንደነበረች (መቼ እንደተወለደች ባይታወቅም) መደምደም እንችላለን። ዘፍጥረት 5:4 እንደሚጠቁመው አዳም በሕይወት በኖረባቸው 930 ዓመታት ውስጥ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችን” አፍርቷል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የቃየን ሚስት የሆነችው የሔዋን ልጅ እንደሆነች በቀጥታ አይናገርም። እንዲያውም የቃየን ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰችው ቃየን በኖድ ምድር መኖር ከጀመረ በኋላ ነው፤ ይህም ከአዳምና ከሔዋን የልጅ ልጆች መካከል አንዷ ለመሆን የሚያስችላት በቂ ጊዜ ማለፉን ይጠቁማል። ዚ አምፕሊፋይድ ኦልድ ቴስታመንት፣ የቃየንን ሚስት “ከአዳም ዝርያዎች አንዷ” እንደሆነች አድርጎ ይገልጻታል።

የአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት አዳም ክላርክ፣ ቃየን እገደላለሁ የሚል ፍርሃት ያደረበት መሆኑ በወቅቱ የአዳም ዝርያ የሆኑ በርካታ ትውልዶች እንደነበሩና እነሱም “በርካታ መንደሮችን ለማቋቋም” የሚያስችል ብዛት እንደነበራቸው የሚጠቁም ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

ቃየን፣ እህቱን አሊያም የአዳም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተጋብተው የወለዷትን ልጅ ማግባቱ በዛሬው ጊዜ በሚገኙ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ድርጊት በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ነውር ይታያል፤ ወይም በዘር የሚተላለፍ ጉድለት እንዳይከሰት ይፈራል። ያም ሆኖ ፍራንክ ላጋርድ ስሚዝ፣ ዘ ናሬትድ ባይብል ኢን ክሮኖሎጂካል ኦርደር በተባለው ሥራቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ወንድማማቾችና እህትማማቾች እርስ በርስ በጋብቻ የተሳሰሩ ይመስላል፤ እርግጥ ነው፣ ከዚያ በኋላ የመጡት ትውልዶች እንዲህ ያለው ጋብቻ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል።” በተጨማሪም በ1513 ዓ.ዓ. ሙሴ፣ አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ እስከተቀበለበት ጊዜ ድረስ እንዲህ ባሉት የቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸምን የፆታ ግንኙነት የሚከለክል ሕግ እንዳልነበረ ልብ ማለት ይገባል።—ዘሌዋውያን 18:9, 17, 24

በዛሬው ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአንድ ወቅት ከነበራቸው ፍጽምና በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ርቀናል። አሁን እኛን የሚያጠቁን በዘር የሚተላለፉ ችግሮች እነሱ ላይ ተጽዕኖ አልነበራቸው ይሆናል። በተጨማሪም ጆርናል ኦቭ ጄኔቲክ ካውንስሊንግ በተባለው መጽሔት ላይ እንደወጣው ያሉ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአጎት ወይም በአክስት ልጆች መካከል በሚፈጸም ጋብቻ የሚወለዱ ልጆች የሚያጋጥማቸው በዘር የሚተላለፍ ችግር ብዙዎች ከሚያስቡት ያነሰ ነው። አዳም በሕይወት በነበረበት ወቅትም ሆነ ከኖኅ ዘመን በፊት እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ አሳሳቢ እንዳልነበረ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። ስለዚህ የቃየን ሚስት ከቅርብ ዘመዶቹ መካከል አንዷ ነበረች ብለን መደምደም እንችላለን።