በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎት—ስለ ምን ጉዳይ?

ጸሎት—ስለ ምን ጉዳይ?

ኢየሱስ ያስተማረው የናሙና ጸሎት ክርስቲያኖች ከሚያቀርቧቸው ጸሎቶች ሁሉ በጣም እንደሚደጋገም ይነገርለታል። ይህ አስተያየት እውነት ሆነም አልሆነ፣ አንዳንድ ጊዜ የጌታ ጸሎት ወይም አባታችን ሆይ ተብሎ የሚጠራውን የዚህን ጸሎት ትርጉም ብዙ ሰዎች እንዳልተረዱት የተረጋገጠ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን ጸሎት በየዕለቱ ምናልባትም በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ በቃላቸው ይደግሙታል። ኢየሱስ ግን ይህን ጸሎት ያስተማረው ሰዎች በዚህ መንገድ እንዲጠቀሙበት ብሎ አልነበረም። ይህን እንዴት እናውቃለን?

ኢየሱስ ይህን ጸሎት ከማስተማሩ ጥቂት ቀደም ብሎ “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 6:7) ታዲያ ኢየሱስ ተሸምድዶ የሚደገም ጸሎት በመስጠት ራሱ ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነገር ያደርጋል? እንዲህ እንደማያደርግ የተረጋገጠ ነው! በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ስለ ምን ጉዳይ መጸለይ እንደምንችል ማስተማሩ አልፎ ተርፎም በምንጸልይበት ጊዜ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡንን ጉዳዮች በግልጽ መናገሩ ነበር። እስቲ ያስተማረውን ጸሎት ጠለቅ ብለን እንመርምር። ጸሎቱ በማቴዎስ 6:9-13 ላይ ይገኛል።

“በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ።”

ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ሲናገር ሁሉም ጸሎት መቅረብ ያለበት ለአባቱ ለይሖዋ መሆኑን ለተከታዮቹ እያስገነዘባቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነውና መቀደስ ያስፈለገው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

በሰው ልጆች ታሪክ መጀመሪያ ላይ የአምላክ ቅዱስ ስም ጎድፏል። የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን፣ ይሖዋን ውሸታምና በፍጥረቶቹ ላይ የመግዛት መብት የሌለው ራስ ወዳድ ገዥ እንደሆነ አድርጎ በመናገር ስሙን አጥፍቷል። (ዘፍጥረት 3:1-6) ብዙ ሰዎች አምላክ ስሜት አልባ፣ ጨካኝና በቀለኛ ነው ብለው በማስተማር አሊያም እስከነጭራሹ ፈጣሪነቱን በመካድ ከሰይጣን ጋር አብረዋል። ሌሎች ደግሞ ይሖዋ የሚለውን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው በማስወጣት ብሎም ሰዎች እንዳይጠቀሙበት በመከልከል ቃል በቃል በስሙ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።

አምላክ ይህን ሁሉ የፍትሕ መዛባት እንደሚያስተካክል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሕዝቅኤል 39:7 NW) በዚህ ጊዜ አምላክ የሚያስፈልጉህ ነገሮች ሁሉ እንዲሟሉልህ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ችግሮችህን በመሉ ያስወግድልሃል። እንዴት? ኢየሱስ ባስተማረው ጸሎት ላይ ቀጥሎ የተጠቀሰው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

“መንግሥትህ ይምጣ።”

በዛሬው ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች የአምላክን መንግሥት በተመለከተ የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ግራ መጋባት ፈጥረዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩት የኢየሱስ አድማጮች፣ የአምላክ ነቢያት ከረጅም ጊዜ በፊት ትንቢት የተናገሩለት መሲሕ ማለትም አምላክ የመረጠው አዳኝ ዓለምን በሚለውጥ መንግሥት ላይ እንደሚገዛ ያውቁ ነበር። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 2:44) ይህ መንግሥት የሰይጣንን ውሸቶች በማጋለጥ እንዲሁም ሰይጣንንም ሆነ ሥራዎቹን በሙሉ በማስወገድ የአምላክ ስም እንዲቀደስ ያደርጋል። የአምላክ መንግሥት ጦርነትን፣ በሽታን፣ ረሃብን ሌላው ቀርቶ ሞትን እንኳ ያስወግዳል። (መዝሙር 46:9፤ 72:12-16፤ ኢሳይያስ 25:8፤ 33:24) የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ በምትጸልይበት ጊዜ እነዚህ ተስፋዎች ሁሉ እንዲፈጸሙ ጸሎት እያቀረብክ ነው።

“ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።”

ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት፣ የአምላክ ፈቃድ እሱ በሚኖርበት በሰማይ እንደተፈጸመ ሁሉ በምድርም ላይ መፈጸሙ እንደማይቀር ይጠቁማሉ። የአምላክ ፈቃድ በሰማይ ምንም ነገር ሳያግደው ተፈጽሟል፤ የአምላክ ልጅ ሰይጣንንና ግብረ አበሮቹን ተዋግቶ ከሰማይ ወደ ምድር ወርውሯቸዋል። (ራእይ 12:9-12) እንደ መጀመሪያዎቹ ሁለት ልመናዎች ሁሉ ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ውስጥ የጠቀሰው ሦስተኛው ልመናም ትኩረታችንን ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ እንድናደርግ ይረዳናል፤ በሌላ አባባል በራሳችን ፈቃድ ላይ ሳይሆን በአምላክ ፈቃድ ላይ እንድናተኩር ያደርገናል። ለፍጥረታት በሙሉ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኘው ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው። ፍጹም ሰው የነበረው ኢየሱስም እንኳ ለአባቱ “የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” ብሎ የጸለየው ለዚህ ነው።—ሉቃስ 22:42

“የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን።”

ኢየሱስ ይህን ልመና ማስተማሩ ስለ ግል ጉዳዮቻችን ጭምር መጸለይ እንደምንችል ያሳያል። ለዕለት ኑሯችን ስለሚያስፈልጉን ነገሮች ብንጸልይ ምንም ስህተት የለውም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጋችን “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው” ይሖዋ እንደሆነ ያስታውሰናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:25) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን መስጠት የሚያስደስተው አፍቃሪ አባት እንደሆነ ይገልጻል። እንደ አንድ ጥሩ ወላጅ ሁሉ ይሖዋም ልጆቹ የማይጠቅማቸውን ነገር ቢጠይቁ አይሰጣቸውም።

በደላችንን ይቅር በለን።”

በእርግጥ አምላክን እንደበደልከው ታምናለህ? ይቅርታውስ ያስፈልግሃል? በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የኃጢአት ምንነት ስለጠፋባቸው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ ነገር እንደሆነ አይገነዘቡም። መጽሐፍ ቅዱስ ግን አስከፊ ለሆኑት ችግሮቻችን ሁሉ ምንጩ ኃጢአት እንደሆነ ያስተምራል፤ ምክንያቱም ኃጢአት ለሰዎች ሞት ዋነኛ መንስኤ ነው። ኃጢአተኞች ሆነን የተወለድን እንደመሆናችን መጠን ዘወትር ኃጢአት ስለምንሠራ ወደፊት ዘላቂ ደኅንነት የማግኘት ተስፋችን የተመካው በአምላክ ይቅርታ ላይ ነው። (ሮም 3:23፤ 5:12፤ 6:23) መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ቸርና ይቅር ባይ ነህ” በማለት ስለ ይሖዋ መናገሩ ትልቅ እፎይታ ይሰጠናል።—መዝሙር 86:5

“ከክፉው አድነን።”

የአምላክን ጥበቃ ማግኘትህ ምን ያህል አጣዳፊና አንገብጋቢ እንደሆነ ተገንዝበሃል? ብዙ ሰዎች “ክፉው” ማለትም ሰይጣን እስከነጭራሹ መኖሩንም ማመን አይፈልጉም። ሆኖም ኢየሱስ ሰይጣን እውን አካል እንደሆነ ያስተማረ ሲሆን እንዲያውም ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 16:11) ሰይጣን በቁጥጥሩ ሥር ያለውን ይህን ዓለም አበላሽቶታል፤ በመሆኑም ከአባትህ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዳትመሠርት ለማድረግ የአንተንም አቋም ማጉደፍ ይፈልጋል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ይሁን እንጂ ይሖዋ ከሰይጣን እጅግ የበለጠ ኃይል ያለው ከመሆኑም በላይ ለሚወዱት ሰዎች ጥበቃ ማድረግም ያስደስተዋል።

ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ የገለጻቸውን ዋና ዋና ነጥቦች በአጭሩ ተመልክተናል፤ ሆኖም ይህ ርዕስ ልንጸልይባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በሙሉ አይሸፍንም። አንደኛ ዮሐንስ 5:14 “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” በማለት ስለ አምላክ እንደሚናገር አስታውስ። ስለዚህ ችግሮችህ በጸሎትህ ውስጥ ሊካተቱ የማይገባቸው አነስተኛ ጉዳዮች እንደሆኑ አድርገህ ልታስብ አይገባም።—1 ጴጥሮስ 5:7

ይሁንና ስለምንጸልይበት ጊዜና ቦታስ ምን ማለት ይቻላል? የምንጸልይበት ጊዜና ቦታ ልዩነት ያመጣል?