በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጸሎት—አምላክ ሰምቶ መልስ ይሰጣል?

ጸሎት—አምላክ ሰምቶ መልስ ይሰጣል?

ይህ ጥያቄ የብዙ ሰዎችን የማወቅ ጉጉት እንደሚቀሰቅስ እሙን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ቢሆን ጸሎትን በእርግጥ እንደሚሰማ ይጠቁማል። ያም ሆኖ ጸሎታችን መሰማት አለመሰማቱ በአመዛኙ የተመካው በእኛ ላይ ነው።

ኢየሱስ፣ እሱ በኖረበት ዘመን የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች የሚጸልዩት ለታይታ ስለነበር አውግዟቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች በጣም የሚያሳስባቸው ጸሎተኛ መስለው የመታየታቸው ጉዳይ ብቻ ነበር። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹ “ሙሉ ብድራታቸውን” እንደተቀበሉ በሌላ አባባል አጥብቀው ሲፈልጉት የነበረውን የሰዎችን ትኩረት እንዳገኙ ተናግሯል፤ የሚያሳዝነው ግን ወሳኙን ነገር ማለትም የአምላክን ጆሮ ማግኘት አልቻሉም። (ማቴዎስ 6:5) በዛሬው ጊዜም የብዙ ሰዎች ጸሎት፣ የራሳቸውን ፈቃድ እንጂ የአምላክን ፈቃድ አያንጸባርቅም። እስካሁን የተወያየንባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ችላ ስለሚሉ በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት አያገኙም።

የአንተስ ጸሎት እንዴት ነው? አምላክ ሰምቶ መልስ የሚሰጠው ዓይነት ጸሎት ነው? የጸሎትህ ተሰሚነት የተመካው በዘርህ፣ በጎሳህ ወይም በኑሮ ደረጃህ ላይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት” እንዳለው ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) አንተስ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነህ? አምላክን የምትፈራ ከሆነ እሱን ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ከመሆኑም በላይ እንዳታሳዝነው ትጠነቀቃለህ። የጽድቅ ሥራ የምትሠራ ከሆነ ደግሞ የራስህን ወይም የሌሎች ሰዎችን ፈቃድ ሳይሆን አምላክ ትክክል ነው የሚለውን ነገር ለማድረግ ትጥራለህ። በእርግጥ አምላክ ጸሎትህን እንዲሰማልህ ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚሰማው ዓይነት ጸሎት ማቅረብ የምትችልበትን መንገድ ይጠቁምሃል። *

እርግጥ ነው፣ ብዙ ሰዎች አምላክ በተአምር ጸሎታቸውን እንዲመልስላቸው ይፈልጋሉ። ይሁንና አምላክ በጥንት ጊዜም እንኳ ተአምር የፈጸመው አልፎ አልፎ ነበር። በጽሑፍ ከሰፈሩት ዘገባዎች እንደምንመለከተው አንዳንድ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ተአምራት መካከል በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ተአምር መፈጸሙ እንደቀረ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል። (1 ቆሮንቶስ 13:8-10) ታዲያ ይህ ማለት አምላክ በዛሬው ጊዜ ለጸሎት ምላሽ አይሰጥም ማለት ነው? በጭራሽ! አምላክ እንዴት ላሉ ጸሎቶች መልስ እንደሚሰጥ እንመልከት።

አምላክ ጥበብ ይሰጣል። የእውነተኛ ጥበብ ሁሉ ዋነኛ ምንጭ ይሖዋ ነው። ይሖዋ ጥበቡን በልግስና ለመስጠት ፈቃደኛ ነው፤ የእሱን መመሪያ ለሚሹና በዚያ መሠረት ለመኖር ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች ጥበቡን በነፃ ይሰጣቸዋል።—ያዕቆብ 1:5

አምላክ መንፈስ ቅዱስንና ይህ መንፈስ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በሙሉ ይሰጣል። መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል ነው። ከዚህ መንፈስ የበለጠ ኃይል የለም። መንፈስ ቅዱስ በፈተናዎች እንድንጸና ሊረዳን ይችላል። ስሜታችንን የሚረብሽ ነገር ሲያጋጥመን ሰላም በመስጠት ሊያረጋጋን ይችላል። ሌሎች ማራኪና ተወዳጅ ባሕርያትን እንድናፈራም ይረዳናል። (ገላትያ 5:22, 23) ኢየሱስ፣ አምላክ ይህን ስጦታ በልግስና እንደሚሰጣቸው ለተከታዮቹ አረጋግጦላቸዋል።—ሉቃስ 11:13

አምላክ አጥብቀው ለሚሹት እውቀትን ይሰጣል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27) በዓለም ዙሪያ እውነትን በቅንነት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ስለ አምላክ ማለትም ስለ ስሙ፣ ለምድርና ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ እንዲሁም ወደ እሱ መቅረብ ስለሚችሉበት መንገድ ማወቅ ይፈልጋሉ። (ያዕቆብ 4:8) የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ሲሆን ሰዎቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችም ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ መስጠት ያስደስታቸዋል።

አንተስ ይህን መጽሔት የወሰድከው ለጥያቄዎችህ መልስ ለማግኘት በማሰብ ይሆን? አምላክን እየፈለግከው ነው? ምናልባት አምላክ ይህ መጽሔት እንዲደርስህ በማድረግ ለጸሎትህ መልስ እየሰጠህ ሊሆን ይችላል።

^ አን.5 አምላክ የሚሰማው ዓይነት ጸሎት ማቅረብ የምትችልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።