በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

መላዋን ምድር የሚለውጥ መንግሥት

መላዋን ምድር የሚለውጥ መንግሥት

ይህ የትኛው መንግሥት እንደሆነ መገመት ትችላለህ?— * ኢየሱስ እንድንጸልይለት ያስተማረን መንግሥት ነው። ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን አምላክን እንድንለምነው አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:9, 10) የኢየሱስ ተከታዮች ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ ሲጸልዩ ቆይተዋል። አንተስ ስለዚህ መንግሥት ጸልየህ ታውቃለህ?—

መንግሥት ምን እንደሆነ መረዳት እንድትችል ንጉሥ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልግሃል። ንጉሥ አንድን አካባቢ የሚያስተዳድር ሰው ነው። የሚያስተዳድረው ቦታ ደግሞ ግዛት ይባላል። የአምላክ መንግሥት የሚገዛው መላዋን ምድር ነው። የአምላክ መንግሥት ሲመጣ በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው ይህ መንግሥት የሚያመጣውን በረከት ያገኛል።

የአምላክ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 9:6 ላይ የዚህን መንግሥት ንጉሥ በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ . . . አለቅነትም [“የልዑል አገዛዝም፣” NW] በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ . . . የሰላም ልዑል ይባላል።”

ልዑል ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— አዎን፣ ልዑል የንጉሥ ልጅ ነው። ታዲያ የሁሉ የበላይ የሆነው ሰማያዊ ንጉሥ ማን ነው?—ይሖዋ ብለህ ከመለስክ ትክክል ነህ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “በምድር ሁሉ ላይ ጌታና ሁሉን ቻይ አምላክ” እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 83:18 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ “የአምላክ ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። እንዲህ ተብሎ የተጠራበት አንዱ ምክንያት ለኢየሱስ ሕይወት የሰጠው ይሖዋ ስለሆነ ነው። በእርግጥም ይሖዋ የኢየሱስ አባት ነው።—ሉቃስ 1:34, 35፤ ዮሐንስ 1:34, 49፤ 3:17፤ 11:27፤ 20:31፤ የሐዋርያት ሥራ 9:20

ኢየሱስ እንድንጸልይለት ያስተማረው የአምላክ መንግሥት ለየት ያለ መስተዳድር ነው። ይህ መስተዳድር “የልዑል አገዛዝ” የተባለው ይሖዋ ልጁን ኢየሱስን የዚህ መንግሥት ገዥ ወይም ንጉሥ ስላደረገው ነው። ይሁንና ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው በአባቱ መንግሥት እንዲገዙ የተመረጡ ሌሎች ሰዎችም እንዳሉ ታውቃለህ?— እስቲ ስለ እነዚህ ሰዎች እንመልከት።

ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለታማኝ ሐዋርያቱ በሰማይ ወዳለው የአባቱ “ቤት” እንደሚሄድ ነግሯቸው ነበር። ኢየሱስ “የምሄደው ለእናንተ ቦታ ለማዘጋጀት ነው” ካለ በኋላ “እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ . . . እወስዳችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:1-3) ሐዋርያቱና የተመረጡት ሌሎች ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ምን እንደሚያደርጉ ታውቃለህ?— እነዚህ ሰዎች “ከእሱ ጋር ነገሥታት ሆነው . . . ይገዛሉ።” መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙት ምን ያህል እንደሆኑም ይነግረናል። ቁጥራቸው 144,000 ነው።—ራእይ 14:1, 3፤ 20:6

የሰላሙ ልዑልና የተመረጡት 144,000 ሰዎች በሚገዙበት ጊዜ በምድር ላይ ምን እንደሚከናወን መገመት ትችላለህ?— እጅግ አስደናቂ የሆነ ነገር ይከናወናል! ጦርነት አይኖርም። እንስሳት እርስ በርሳቸውም ሆነ ከእኛ ጋር በሰላም ይኖራሉ። የሚታመም ወይም የሚሞት ሰው አይኖርም። ማየት የተሳናቸው ሰዎች ያያሉ፣ መስማት የማይችሉ ሰዎች ጆሮ ይከፈታል እንዲሁም አንካሳው መሮጥና እንደ ሚዳቋ መዝለል ይችላል። ምድር ለሁሉም ሰው የሚበቃና ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ትሰጣለች። እንዲሁም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ባስተማራቸው መሠረት ሁሉም ሰዎች እርስ በርስ ይዋደዳሉ። (ዮሐንስ 13:34, 35) እስቲ በኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ የሚገኙትን እዚህ ላይ የቀረቡ ጥቅሶች እናውጣና በዚያ ወቅት ስለሚከናወኑት አስደናቂ ነገሮች እናንብብ።—ኢሳይያስ 2:4፤ 11:6-11፤ 25:8፤ 33:24፤ 35:5, 6፤ 65:21-24

ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ሰዎችን ካስተማረበት ጊዜ አንስቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለዚህ መንግሥት ተምረዋል። ያገኙት እውቀትም ሕይወታቸውን ለውጦታል። በቅርቡ ይህ መንግሥት የሚመጣ ሲሆን አሁን በምድር ላይ ያሉትን ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ በማስወገድ መግዛት ይጀምራል፤ በዚያ ወቅት ይሖዋንና እሱ ገዥ አድርጎ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያገለግሉ ሁሉ ሰላም፣ ፍጹም የሆነ ጤንነትና ደስታ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 17:3

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከልጆች ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ የተደረገው ቆም ብለህ ጥያቄውን ለልጆቹ እንድታቀርብላቸው ለማስታወስ ተብሎ ነው።