በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብንና ንብረትን ሳይሆን ሰዎችን ውደድ

ገንዘብንና ንብረትን ሳይሆን ሰዎችን ውደድ

1ኛው ቁልፍ

ገንዘብንና ንብረትን ሳይሆን ሰዎችን ውደድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምራል? “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 6:10

ተፈታታኙ ሁኔታ ምንድን ነው? ማስታወቂያዎች ባለን ነገር ረክተን እንዳንኖር ተጽዕኖ ያደርጉብናል። የንግዱ ዓለም የሚፈልገው አዳዲስና በጥራትም ይሁን በመጠን የተሻሉ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚያስፈልገንን ገንዘብ ለማግኘት ያላንዳች እረፍት እንድንሠራ ነው። ገንዘብ አታላይ በመሆኑ በቀላሉ ሊያማልለን ይችላል። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ንብረት የሚወድ ሰው ፈጽሞ እንደማይረካ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። ንጉሥ ሰለሞን “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም” በማለት ጽፏል።—መክብብ 5:10

ምን ማድረግ ትችላለህ? ሰዎችን ከቁሳዊ ነገሮች አስበልጠህ በመውደድ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት አድርግ። ኢየሱስ ሰዎችን ይወድ ስለነበር ያለውን ነገር ሁሉ ሌላው ቀርቶ ሕይወቱን እንኳ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። (ዮሐንስ 15:13) ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ጊዜያችንን፣ ችሎታችንን፣ ጉልበታችንንና ሀብታችንን ለሌሎች የመስጠት ልማድ ካዳበርን ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉልናል። ኢየሱስ “ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል” ብሏል። (ሉቃስ 6:38) ገንዘብና ቁሳዊ ንብረት የሚያሳድዱ ሰዎች በራሳቸው ላይ ሥቃይና መከራ ያመጣሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) በሌላ በኩል ደግሞ አፍቃሪና ተወዳጅ የሆኑ ሰዎች እውነተኛ እርካታና ደስታ ያገኛሉ።

ታዲያ አኗኗርህን ቀለል ማድረግ ትችል ይሆን? እስቲ ይህን ጉዳይ ቆም ብለህ አስብበት። ካሉህ ንብረቶች አሊያም ልትገዛቸው ካሰብካቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን መቀነስ ትችል ይሆን? ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ትኩረት ለመስጠት የሚያስችልህን ጊዜና ጉልበት ታገኛለህ፤ በሌላ አባባል ሰዎችን መርዳት እንዲሁም ሁሉንም ነገር የሰጠህን አምላክ ማገልገል ትችላለህ።—ማቴዎስ 6:24፤ የሐዋርያት ሥራ 17:28

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል”