በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሌባና የዓማፂ ቡድን ወታደር የነበረ አንድ ሰው በአኗኗሩ ላይ ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? የማርሻል አርት ሻምፒዮን የነበረች አንዲት ሴት በሕይወቷ ውስጥ ትከተለው የነበረውን ግብ የቀየረችው ለምንድን ነው? አንድ አባት በልጁ ላይ እምነት በማሳደሩ የተካሰው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ተሞክሮዎች በማንበብ መልሱን ማግኘት ትችላለህ።

“የቀድሞ ሕይወቴ የተበላሸ ቢሆንም አሁን ደስተኛ ነኝ።”—ጋሪ አምብሮስዮ

ዕድሜ፦ 47

የትውልድ አገር፦ ፊሊፒንስ

የኋላ ታሪክ፦ የዓማፂ ቡድን ወታደር

የቀድሞ ሕይወቴያደኩት ቪንታር በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። የምንኖርበት ሰፊ ሸለቋማ አካባቢ ለምለም በሆኑ ተራሮች የተከበበ ሲሆን ንጹሕ የሆኑ ወንዞች የሚያቋርጡትና ያልተበከለ አየር ያለበት ቦታ ነበር። አካባቢው የሚማርክ ቢሆንም ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። ሰዎች ከብቶቻችንን ይሰርቁ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቤታችንን ይዘርፉ ነበር።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጥ እጠጣና ሲጋራ አጨስ የነበረ ሲሆን እነዚህን መጥፎ ሱሶች ለማርካት ስል ገንዘብ እሰርቅ ነበር። ሌላው ቀርቶ የአያቴን ጌጣጌጦች እንኳ የሰረቅኩበት ጊዜ ነበር። ወታደሮች ኒው ፒፕልስ አርሚ (ኤን ፒ ኤ) የተባለው ዓማፂ ቡድን አባል እንደሆንኩ ስለሚሰማቸው ብዙ ጊዜ ክፉኛ ይደበድቡኝ ነበር። በዚህ ምክንያት የዓማፂ ቡድኑን ለመቀላቀል ወሰንኩ። ከዓማፂው ቡድን ወታደሮች ጋር ለአምስት ዓመት በተራራ ላይ ኖሬአለሁ። ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። ወታደሮች እንዳያገኙን ስንል ያለንበትን ቦታ በየጊዜው እንለዋውጥ ነበር። ከጊዜ በኋላ በተራራዎች ላይ እየተሽሎከለኩ መኖር ስለሰለቸኝ ኢሎኮስ ኖርቴ የሚባለውን ግዛት ለሚያስተዳድር ሰው እጄን ሰጠሁ። አስተዳዳሪው በጥሩ ሁኔታ የተቀበለኝ ከመሆኑም ሌላ ደህና ሥራ እንዳገኝ ረዳኝ። ያም ሆኖ የቀድሞ አመሌን እርግፍ አድርጌ ስላልተውኩ ቤቶችን እዘርፍና ሰዎችን አስፈራራ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በምሠራበት ቦታ ሎይዳ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ይህች የይሖዋ ምሥክር ከሆቨንስዮ ጋር አስተዋወቀችኝና ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ይሁንና ከቀድሞ አኗኗሬ መላቀቅ አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነበር። ሆቨንስዮ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስጠናኝ ከመምጣቱ በፊት ሲጋራ አጨስ የነበረ ሲሆን ሕገ ወጥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መካፈሌንም አላቆምኩም ነበር። በአንድ ወቅት ሕገ ወጥ የሆነ ድርጊት ስፈጽም በፖሊስ ተይዤ ለ11 ወራት እስር ቤት ታስሬያለሁ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ እንዲረዳኝ በጸሎት ተማጸንኩ። በተጨማሪም ይቅር እንዲለኝ እንዲሁም መመሪያና ብርታት ለማግኘት የሚያስችለኝን ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት።

እስር ቤት እያለሁ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ የጠየቀኝ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስም አምጥቶልኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሱን ሳነብ ይሖዋ መሐሪ፣ አፍቃሪና ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ እንደሆነ ተረዳሁ። ቀደም ሲል ይሖዋ ምሕረት አሳይቶኝ እንዲሁም ስለ እሱ የመማር አጋጣሚ ሰጥቶኝ እንደነበር ተገነዘብኩ። መጥፎ ልማዶቼን ለማሸነፍ የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ይሖዋን ለመንኩት። ምሳሌ 27:11 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዳደርግ ረድቶኛል። ይህንን ጥቅስ ሳነብ ይሖዋ በቀጥታ ያነጋገረኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው፤ ለሚንቁኝ ሁሉ መልስ መስጠት እችል ዘንድ።”

ከእስር ቤት ከተለቀቅኩ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን የቀጠልኩ ሲሆን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን በሥራ ላይ ማዋል ጀመርኩ። በመጨረሻም በይሖዋ እርዳታ መጥፎ ልማዶቼን እርግፍ አድርጌ መተው ቻልኩ። ከዚያም ሕይወቴን ለይሖዋ አምላክ ወስኜ ተጠመቅሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ የቀድሞ ሕይወቴ የተበላሸ ቢሆንም አሁን ደስተኛ ነኝ። ቀደም ሲል የመጥፎ ልማዶች ባሪያ ነበርኩ፤ አሁን ግን አዲስ ሰው ሆኛለሁ። (ቆላስይስ 3:9, 10) በአሁኑ ጊዜ፣ ንጹሕ ከሆነው የይሖዋ ሕዝብ ጋር መቀላቀል መቻሌን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ የመርዳት መብት ማግኘቴን እንደ ክብር እቆጥረዋለሁ።

‘ብራዚልን ወክዬ መወዳደር እፈልግ ነበር።’—ጁሊያና አፓራሴዳ ሳንታና ኢስኩዲዬሮ

ዕድሜ፦ 31

የትውልድ አገር፦ ብራዚል

የኋላ ታሪክ፦ የማርሻል አርት ኤክስፐርት

የቀድሞ ሕይወቴ፦ ያደግኩት ሎንድሪና በምትባል ከተማ ውስጥ ነበር። በዚህች ከተማ ውስጥ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ድሆች ቢሆኑም አካባቢው ንጹሕና ሰላማዊ ነበር። የአሥር ዓመት ልጅ እያለሁ ታላቅ ወንድሜ ከእሱ ጋር ቴኳንዶ የሚባለውን የማርሻል አርት ትምህርት እንድማር አበረታታኝ፤ ቴኳንዶ የሚለው ቃል “የእጅና የእግር ጥበብ” የሚል ትርጉም አለው። አባቴ ይህን አዲስ ስፖርት መማሬ አላስደሰተውም ነበር፤ ይሁንና ብዙም ሳይቆይ መቃወሙን አቆመ።

ከባድ ልምምድ አደርግ ስለነበር በፓራና ግዛት ውስጥ በተካሄዱ በርካታ የቴኳንዶ ውድድሮች ላይ ተካፍዬ ማሸነፍ ችያለሁ። ከጊዜ በኋላ በብራዚል በተዘጋጁ አገር አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ ማሸነፍ የቻልኩ ሲሆን በ1993 የብራዚል ቴኳንዶ ሻምፒዮን ለመሆን በቃሁ። በዓለም አቀፍ ውድድሮችም ላይ የመካፈል ፍላጎት ነበረኝ። ይሁንና ቤተሰቦቼ ድሆች ስለነበሩ ወደ ውጭ አገር ሄጄ ለመወዳደር የሚያስፈልገኝን ወጪ ለመሸፈን አቅም አልነበራቸውም።

ቴኳንዶ በኦሎምፒክ ውድድሮች ውስጥ ይካተታል የሚል ተስፋ ነበረኝ፤ ደግሞም ከጊዜ በኋላ ተካትቷል። ብራዚልን ወክዬ በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ የመካፈል ፍላጎት ስለነበረኝ ከባድ ልምምዶችን አደርግ የነበረ ከመሆኑም በላይ በፈረንሳይ፣ በቬትናም፣ በደቡብ ኮሪያና በጃፓን እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ በተደረጉ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ስፖንሰር አግኝቼ ነበር። የሚቀጥለው ግቤ በፓን አሜሪካን ጨዋታዎች ላይ መካፈል ነበር፤ በጣም ጥሩ ውጤት ስላስመዘገብኩ በ2003 በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሳንቶ ዶሚንጎ ውስጥ በሚካሄደው የፓን አሜሪካን ጨዋታዎች ላይ ለመካፈል ከተመረጡት ሦስት ተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ለመሆን በቃሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? በ2001 እኔና የወንድ ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርን። መጀመሪያ አካባቢ ለጥናቱ ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም። በምናጠናበት ወቅት በጣም ከመሰላቸቴ የተነሳ በትምህርቱ ላይ ማተኮር ያቅተኝ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ ያስቸግረኝ ነበር። ያም ሆኖ በምማረው ነገር ልቤ ይነካ ጀመር፤ ይህንን በግልጽ መረዳት የቻልኩት በቀጣዩ ትልቅ ውድድር ወቅት ነበር።

በፓን አሜሪካን ጨዋታዎች ላይ እንድካፈል ተመርጬ ስለነበር የቴኳንዶ አሠልጣኞች በማጣሪያ ውድድር ላይ እንድካፈል አደረጉኝ። የእኔ ተራ ደርሶ የመፋለሚያው ምንጣፍ ላይ ከወጣሁ በኋላ ግትር ብዬ ቆምኩ፤ የመፋለም ፍላጎቴ ጠፍቶ ነበር። እዚያው እንደቆምኩ፣ አንድ ክርስቲያን በስፖርታዊ ውድድር ላይ ቢሆንም እንኳ ከሌሎች ጋር መደባደብ እንደሌለበት ትዝ እያለኝ መጣ! “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ አስታወስኩ። (ማቴዎስ 19:19) ምንም ሳላመነታ ፊቴን አዙሬ ከመድረኩ ወረድኩ። ሕዝቡ ማመን አቅቶት በግርምት ይመለከተኝ ነበር።

ቤት ከደረስኩ በኋላ በሕይወቴ ውስጥ ምን ዓይነት ግብ መከተል እንዳለብኝ ቁጭ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። አምላክ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ የሚያብራራውን በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር አንስቼ ማገላበጥ ጀመርኩ። በብሮሹሩ ውስጥ መዝሙር 11:5 ተጠቅሶ አየሁ፤ ጥቅሱ ይሖዋን በሚመለከት “ዐመፃን የሚወዱትን ግን፣ ነፍሱ ትጠላቸዋለች” ይላል። መዝሙራዊው የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እውነት መሆናቸውን ተቀብዬ ቴኳንዶ ለማቆም ወሰንኩ።

የቴኳንዶ አሠልጣኞቼ ባደረኩት ውሳኔ አልተደሰቱም። አሠልጣኞቹ፣ በአገሪቱ ውስጥ እኔን የሚያክል ተወዳዳሪ እንደሌለና በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ ምንም ያህል እንዳልቀረኝ በመናገር ሐሳቤን እንድለውጥ ሊያግባቡኝ ሞከሩ። እኔ ግን ባደረኩት ውሳኔ ጸናሁ።

በዚህ ጊዜ እኔና የወንድ ጓደኛዬ ትዳር መሥርተን ነበር። ባለቤቴ ቀደም ብሎ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል ጀምሮ ነበር። ሁልጊዜ አገልግሎት ውሎ ወደ ቤት የሚመለሰው በጣም ተደስቶ ሲሆን ከሰዎች ጋር ስላደረገው ውይይትም አንድ በአንድ ይነግረኝ ነበር። በዚህ የአገልግሎት መብት ለመካፈል በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርብኝ አውቅ ነበር። ቀድሞ የነበርኩበትን ሃይማኖት ለቅቄ ወጣሁ፤ ከጊዜ በኋላም ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን የሚያስችለኝን ብቃት አሟላሁ።

ያገኘሁት ጥቅም፦ እኔና ባለቤቴ በትዳራችን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት ማድረጋችን ደስታና አንድነት አስገኝቶልናል። ባለቤቴ ጉባኤያችንን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት እሱን መደገፍ መቻሌ ያስደስተኛል። በስፖርቱ መስክ ብዙ ጥረት ባደርግ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘትና ዝነኛ መሆን እችል ነበር። ይሁንና ኢፍትሐዊ የሆነው ይህ ዓለም ሊሰጠኝ የሚችለው ነገር፣ ይሖዋ አምላክን ከማገልገል መብት ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር እንደማይችል ይሰማኛል።

“አባቴ ፈጽሞ በእኔ ተስፋ ቆርጦ አያውቅም።”—ኢንጎ ዚመርመን

ዕድሜ፦ 44

የትውልድ አገር፦ ጀርመን

የኋላ ታሪክ፦ የጭፈራ ቤት ጸጥታ አስከባሪ

የቀድሞ ሕይወቴ፦ የተወለድኩት የድንጋይ ከሰል በሚመረትባት ጌልዘንኪርከን በምትባል ከተማ ውስጥ ሲሆን ቤተሰባችን በሃይማኖት የተከፋፈለ ነበር። አባቴ የይሖዋ ምሥክር ነበር። እናቴ፣ እኔንና ታላቅ ወንድሜን እንዲሁም ሁለት እህቶቼን በእሱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ኮትኩቶ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ትቃወም ነበር። አባቴ የከባድ መኪና ሹፌር ሲሆን በቀን አሥር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ሰዓት በሥራው ላይ ያሳልፋል። ብዙውን ጊዜ ሥራ የሚጀምረው ከሌሊቱ ስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው። ያም ሆኖ ለእኛ መንፈሳዊ ሥልጠና ከመስጠት ቦዝኖ አያውቅም። እኔ ግን የሚያደርገውን ጥረት በቁም ነገር አይቼው አላውቅም ነበር።

የ15 ዓመት ልጅ እያለሁ ከአባቴ ጋር የምገኝባቸው ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ስለሰለቹኝ ወደ ስብሰባዎች መሄድ አቆምኩ። ከዓመት በኋላ በአንድ የቦክስ ክበብ ውስጥ አባል ሆንኩ። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ አባቴ በእኔ ባሕርይ ምክንያት ሊያብድ ምንም አልቀረውም ነበር። በ18 ዓመቴ ከቤት ወጣሁ።

ስፖርት በጣም እወድ ስለነበር በሳምንት ስድስት ጊዜ ያህል ልምምድ አደርግ ነበር፤ በመጀመሪያ ቦክስ ከዚያም ክብደት ማንሳት እለማመድ ነበር። ቅዳሜና እሁድ እኔና ጓደኞቼ አዘውትረን ወደ ጭፈራ ቤቶች እንሄድ ነበር። በአንድ ወቅት በጭፈራ ቤት ውስጥ አስፈሪ ከሚመስል ሰው ጋር ተደባደብኩ፤ ሆኖም በቀላሉ አሸነፍኩት። የጭፈራ ቤቱ ባለቤት ሁኔታውን አይቶ ስለነበር ወዲያውኑ በጸጥታ አስከባሪነት ሊቀጥረኝ እንደሚፈልግ ገለጸልኝ። ክፍያው ጥሩ ስለነበር ሥራውን ተቀበልኩ።

ቅዳሜና እሁድ በጭፈራ ቤቱ በር ላይ ቆሜ ማን መግባት እንዳለበትና እንደሌለበት እወስናለሁ። ወደ ጭፈራ ቤቱ እስከ 1,000 የሚደርሱ ሰዎች ይገቡ ስለነበር ፋታ አልነበረኝም። መደባደብ የተለመደ ነገር ነበር። ሰዎች በጦር መሣሪያና በተሰበረ ጠርሙስ የሚያስፈራሩኝ ጊዜ ነበር። እንዳይገቡ የከለከልኳቸው ወይም ከጭፈራ ቤቱ ያስወጣኋቸው አንዳንድ ሰዎች ውጭ ጠብቀው ሊበቀሉኝ ይሞክራሉ። በዚያ ጊዜ የ20 ዓመት ወጣት የነበርኩ ሲሆን በማንም የማልበገር ሰው እንደሆንኩ አድርጌ አስብ ነበር። ይሁንና መረን የለቀቀ ሰው ማለትም ጠበኛ፣ ትዕቢተኛ፣ እልኸኛና እብሪተኛ ሆኜ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው? አባቴ ፈጽሞ በእኔ ተስፋ ቆርጦ አያውቅም። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት * ቤት ድረስ እንዲመጣልኝ ዝግጅት አድርጎ ነበር። መጽሔቶቹ ክፍሌ ውስጥ እየተከመሩ መጡ፤ ሆኖም አንዱንም አንብቤ አላውቅም። አንድ ቀን ከእነዚህ መጽሔቶች መካከል አንዳንዶቹን ለማየት ወሰንኩ። አሁን ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት እንዴት እንደሚጠፋ የሚናገሩ አንዳንድ ርዕሶችን ማንበቤ እህቴን ጠርቼ እንዳነጋግራት አነሳሳኝ። እህቴና ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ግብዣ አቀረቡልኝ፤ እኔም ለማጥናት ተስማማሁ።

በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት በሕይወቴ ላይ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። ዛሬ የማደርገው፣ የምናገረው ወይም የምወስነው ማንኛውም ነገር በነገው ሕይወቴ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ከተሞክሮ መማር ችያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በኢሳይያስ 1:18 ላይ የሚገኘው ግብዣ በጣም አበረታቶኛል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “‘ኑና እንዋቀስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል።’” ይህ ጥቅስ ጥናት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የማልረባ ወይም ወደ ይሖዋ መመለስ የማልችል ሰው እንደሆንኩ አድርጌ እንዳላስብ ረድቶኛል።

ብርቱ ጥረት ማደረግ ቢጠይቅብኝም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አደረኩ። ይህን ለማድረግ አደገኛ ከሆኑ አካባቢዎችና ከመጥፎ ጓደኞች መራቅ አስፈልጎኛል። በመሆኑም ለጓደኞቼ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናሁ መሆኑን እነግራቸው እንዲሁም የተማርኩትን ነገር አካፍላቸው ጀመር። ጓደኞቼ ከእኔ ከመሸሻቸውም በላይ ቄሱ እያሉ ይጠሩኝ ጀመር። በእህቴ እርዳታ ከበፊቱ የተሻለ ተስማሚ ሥራ አገኘሁ።

ምንም እንኳ እህቴና ባለቤቷ የሚሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሽ 30 ኪሎ ሜትር ያህል የሚርቅ ቢሆንም በዚያ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በምኖርበት ቤት አቅራቢያ የመንግሥት አዳራሽ የነበረ ቢሆንም ከልጅነቴ ጀምሮ ከሚያውቁኝ ሰዎች ጋር መገናኘት አሳፍሮኝ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በምኖርበት አካባቢ ከቤት ወደ ቤት ሄዶ መስበክ አስፈርቶኝ ነበር። በቅርቡ ከጭፈራ ቤት ካስወጣሁት ወይም አደገኛ ዕፅ ከሰጠሁት ሰው ጋር ብገናኝ ምን ላደርግ ነው? የሚል ፍርሃት ነበረብኝ። ይሁን እንጂ ስፖርት በተማርኩበት ወቅት በጣም አስቸጋሪ የሆኑት ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ተገንዝቤ ነበር። አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለኝን ብቃት ካሟላሁ በኋላ በተቻለኝ መጠን ራሴን በስብከቱ ሥራ አስጠመድኩ።

በተጨማሪም ላሸንፈው የሚገባኝ ሌላም ችግር ነበረብኝ፤ ይኸውም ማንበብ ወይም ማጥናት የማልወድ መሆኔ ነው። ነገር ግን ጠንካራ እምነት እንዲኖረኝ ከፈለግሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘውን እውነት በትጋት ለማጥናት ራሴን መገሠጽ እንዳለብኝ ተገንዝቤ ነበር። መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል፤ ይህ ሁኔታ ክብደት ከማንሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል።

ያገኘሁት ጥቅም፦ ካገኘኋቸው ጥቅሞች አንዱ እስከ አሁን ድረስ በሕይወት መቆየቴ ነው! እርግጥ አሁንም ቢሆን ባሉብኝ ድክመቶች እንዳልሸነፍ መጠንቀቅ አለብኝ። በአሁኑ ወቅት ግሩም ክርስቲያናዊ ባሕርይ ካላት ባለቤቴ ጋር አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እያጣጣምኩ ነው። ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ሙሉ እምነት ልጥልባቸው የምችል እውነተኛ ጓደኞች ማግኘት ችያለሁ። አባቴ  በፊት በሞት ያንቀላፋ ቢሆንም ከመሞቱ በፊት ልጁ ወደ እውነት ሲመለስ የመመልከት አጋጣሚ አግኝቶ ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.34 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ።