በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ይኖርብኛል?

የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ይኖርብኛል?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ይኖርብኛል?

በቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች አልፎ ተርፎም በቀሳውስት መካከል በሚታየው ግብዝነትና መከፋፈል ምክንያት ተስፋ ቆርጠህ የአንድ ሃይማኖት አባል ላለመሆን እያመነታህ ነው? ከሆነ “ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀረብክ ቁጥር ከአምላክ ትርቃለህ” የሚለው የፈረንሳውያን አባባል የአንተንም ስሜት ይገልጽ ይሆናል።

ምናልባትም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ይኖርህ ይሆናል፤ እንዲሁም አንድ ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመያዝ መብቱን መንግሥታትም ሆኑ ግለሰቦች ማክበር እንዳለባቸው ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ‘አምላክ ተቀባይነት ባለው መንገድ እሱን ለማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች የግድ የአንድ ሃይማኖት ድርጅት አባል መሆን እንዳለባቸው ተናግሯል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

በአጭሩ መልሱ አዎን የሚል ነው። እንዲህ ብለን በእርግጠኝነት የምንናገረው ለምንድን ነው? ሁሉም ሃይማኖታዊ ድርጅቶችስ ተቀባይነት አላቸው?

እስቲ ኢየሱስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል ነበር? ኢየሱስ ወጣት እያለ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ በተደራጀ መልክ በሚቀርበው አምልኮ ላይ የመካፈል ልማድ ካላቸው አይሁዳዊ ቤተሰቦቹና ሌሎች ሰዎች ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር። (ሉቃስ 2:41-43) ትልቅ ከሆነም በኋላ አምላክን ለማምለክ ከሌሎች አይሁዳውያን ጋር በአካባቢው ባለ ምኩራብ ይገኝ ነበር። (ሉቃስ 4:14-16) ኢየሱስ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ለሆነች አንዲት ሴት “እኛ ግን . . . የምናውቀውን እናመልካለን” ብሏታል። (ዮሐንስ 4:22) ከዚህ ጥቅስ በግልጽ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ራሱን የአይሁድ ሃይማኖት አባል እንደሆነ አድርጎ ይቆጥር ነበር።

ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ አይሁዳውያን በብሔር ደረጃ እሱን ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው አምላክ የተበከለ አምልኳቸውን እንደማይቀበል ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:33 እስከ 24:2) ያም ቢሆን አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማምለክ የሚፈልጉ ሰዎች የአንድ ሃይማኖት ድርጅት አባል እንደሚሆኑ ጠቁሟል። ለተከታዮቹ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ አንድ ሰው ለእምነት ባልንጀሮቹ ፍቅር ማሳየት የሚችለው ከእነሱ ጋር ሲቀራረብና አብሯቸው ሲሰበሰብ ብቻ ነው። እንዲያውም ኢየሱስ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ሁለት መንገዶች ብቻ እንዳሉ በግልጽ ተናግሯል። ኢየሱስ “ትልቅና ሰፊ” በማለት የገለጸው አንደኛው መንገድ “ወደ ጥፋት” የሚወስድ ነው። ከዚህ በተቃራኒ “ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ መንገዱም ቀጭን ነው፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።”—ማቴዎስ 7:13, 14

ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ሁሉም ሃይማኖት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሃይማኖት ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሃይማኖትን ኀይል ይክዳሉ” በማለት ከጠቀሳቸው ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳንፈጥር ያስጠነቅቃል። በተጨማሪም “ከእነዚህም ሰዎች ራቅ” በማለት ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:5 የ1980 ትርጉም) በሌላ በኩል ግን ወደ ሕይወት የሚመራውን መንገድ ለይተን ማወቃችንና በዚያ መንገድ ከሚጓዙ ሰዎች ጋር መተባበራችን ይህ ነው የማይባል ጥቅም ያስገኝልናል። እንዲህ ማድረጋችን በአሁኑ ጊዜ ድጋፍና ማበረታቻ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል።—ዕብራውያን 10:24, 25

ታዲያ በጠባቡ መንገድ ላይ የሚገኘው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ መለየት የምትችለው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 እንድትመለከት እንጋብዝሃለን። የምትይዘውን ሃይማኖት ለመምረጥ ስትወስን ይህ መጽሐፍ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንድታደርግ ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።