በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች—በአምላክ ቃል ተመሩ

እናንት ወጣቶች—በአምላክ ቃል ተመሩ

እናንት ወጣቶች—በአምላክ ቃል ተመሩ

“ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት።”—ምሳሌ 4:5

1, 2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ከራሱ ጋር የሚያደርገውን ትግል በተሳካ ሁኔታ መወጣት እንዲችል የረዳው ምንድን ነው? (ለ) ጥበብና ማስተዋል ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

“ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።” ይህን ያለው ማን እንደሆነ ታውቃለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ ይሖዋን ቢወድም ትክክል የሆነውን ለማድረግ መታገል ያስፈለገው ጊዜ ነበር። ሐዋርያው ከራሱ ጋር ስለሚያደርገው ትግል ምን ተሰምቶት ነበር? “እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” በማለት ጽፏል። (ሮም 7:21-24) የጳውሎስን ስሜት መረዳት ትችላለህ? አንተስ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ትግል የሚሆንብህ ጊዜ አለ? ይህስ ልክ እንደ ጳውሎስ እንድታዝን ያደርግሃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ጳውሎስ ከራሱ ጋር ትግል ማድረግ ቢኖርበትም ትክክል የሆነውን በማድረግ ረገድ ተሳክቶለታል፤ አንተም ሊሳካልህ ይችላል።

2 ጳውሎስ ስኬታማ መሆን የቻለው ‘በጤናማ ቃላት’ ለመመራት ፈቃደኛ ስለነበር ነው። (2 ጢሞ. 1:13, 14) ይህም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመወጣትና ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዳውን ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት አስችሎታል። ይሖዋ አምላክ ጥበብና ማስተዋል እንድታገኝ አንተንም ሊረዳህ ይችላል። (ምሳሌ 4:5) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ምክር አስፍሮልናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከወላጆችህ ጋር ባለህ ግንኙነት፣ በገንዘብ አያያዝ ረገድ እንዲሁም ብቻህን በምትሆንበት ጊዜ እንዴት ሊረዱህ እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት።

በቤተሰብ ውስጥ በአምላክ ቃል መመራት

3, 4. የወላጆችህን መመሪያ መታዘዝ አስቸጋሪ የሚሆንብህ ለምን ሊሆን ይችላል? ወላጆች መመሪያ የሚያወጡት ለምንድን ነው?

3 ወላጆችህ የሚያወጧቸውን መመሪያዎች መታዘዝ አስቸጋሪ ይሆንብሃል? ይህ የሚሆነው ለምን ሊሆን ይችላል? አንዱ ምክንያት ወላጆችህ ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡህ የምትፈልግ መሆኑ ነው። እንዲህ ያለው አዝማሚያ የተለመደ ነው። ነፃነት መፈለግ ከእድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነገር ነው። ይሁንና ቤት እስካለህ ድረስ ወላጆችህን የመታዘዝ ግዴታ አለብህ።—ኤፌ. 6:1-3

4 ወላጆችህ መመሪያዎችንና ሕጎችን የሚያወጡት ለምን እንደሆነ መረዳትህ መታዘዝ ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ አንተም ብሌን * እንደተባለችው የ18 ዓመት ወጣት ይሰማህ ይሆናል፤ ብሌን ስለ ወላጆቿ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በእኔ ዕድሜ ያለፉ አይመስሉም። አመለካከቴን እንድገልጽ፣ የራሴን ምርጫ እንዳደርግ ወይም ትልቅ ሰው እንድሆን አይፈልጉም።” ልክ እንደ ብሌን አንተም ወላጆችህ ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆኑ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ወላጆችህ መመሪያዎችን የሚያወጡበት ዋነኛው ምክንያት የአንተ ደኅንነት ስለሚያሳስባቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያን ወላጆች አንተን የሚያሳድጉበትን መንገድ በተመለከተ ይሖዋ እንደሚጠይቃቸው ያውቃሉ።—1 ጢሞ. 5:8

5. ወላጆችህን መታዘዝ ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት ነው?

5 የወላጆችህን መመሪያ መታዘዝ ለባንክ ዕዳን ከመክፈል ጋር ይመሳሰላል፤ ዕዳህን በመክፈል ረገድ እምነት የሚጣልብህ በሆንክ መጠን ተጨማሪ ብድር ታገኛለህ። በተመሳሳይም ወላጆችህን የማክበርና የመታዘዝ ዕዳ አለብህ። (ምሳሌ 1:8ን አንብብ።) ወላጆችህን በታዘዝካቸው መጠን እነሱም ለአንተ የበለጠ ነፃነት ለመስጠት ይነሳሳሉ። (ሉቃስ 16:10) እርግጥ ነው፣ ዕዳህን በጊዜው ካልከፈልክ ባንኩ ለአንተ የሚሰጠውን ብድር ሊቀንስ አሊያም ከናካቴው ሊያቆም እንደሚችል ሁሉ በተደጋጋሚ ጊዜ የወላጆችህን ትእዛዝ የምትጥስ ከሆነም ወላጆችህ በአንተ ላይ ያላቸው እምነት ቢቀንስ ወይም እስከነጭራሹ ቢጠፋ ልትገረም አይገባም።

6. ወላጆች ልጆቻቸው ታዛዥ እንዲሆኑ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

6 ወላጆች፣ ያወጧቸውን መመሪያዎች ልጆቻቸው እንዲታዘዙ መርዳት የሚችሉበት አንዱ መንገድ እነሱ ራሳቸው ምሳሌ በመሆን ነው። ወላጆች ይሖዋ የሚጠብቅባቸውን በፈቃደኝነት ሲታዘዙ የአምላክ መመሪያዎች ምክንያታዊ መሆናቸውን ያሳያሉ። ይህም ወጣቶች፣ ወላጆቻቸው የሚያወጧቸውን መመሪያዎች መታዘዛቸው ተገቢ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል። (1 ዮሐ. 5:3) በተጨማሪም ይሖዋ አገልጋዮቹ በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ አመለካከታቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ የሰጠባቸው ጊዜያት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጽ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። (ዘፍ. 18:22-32፤ 1 ነገ. 22:19-22) ወላጆችስ አንዳንድ ጊዜ ልጆቻቸው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ አጋጣሚ መስጠት ይችሉ ይሆን?

7, 8. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ለ) ከሚሰጥህ ተግሣጽ ጥቅም ለማግኘት የትኞቹን ነጥቦች መገንዘብህ ሊረዳህ ይችላል?

7 ከዚህም በተጨማሪ ወጣቶች አንዳንድ ጊዜ ወላጆቻቸው የሚሰነዝሩባቸው ነቀፋ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸው ይሆናል። አንተም ካሌብ እንደተባለው ወጣት ተሰምቶህ ያውቅ ይሆናል፤ ካሌብ “እናቴ ፖሊስ ይመስል ሁልጊዜ በእኔ ላይ ስህተት ትፈላልጋለች” በማለት ተናግሯል።

8 ብዙውን ጊዜ እርማት ወይም ተግሣጽ ሲሰጠን ነቀፋ እንደተሰነዘረብን ይሰማናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ተገቢ የሆነ ተግሣጽም እንኳ ለመቀበል ከባድ እንደሆነ ይገልጻል። (ዕብ. 12:11) ወላጆችህ ከሚሰጡህ ተግሣጽ ጥቅም ለማግኘት ምን ሊረዳህ ይችላል? ወላጆችህ ተግሣጽ የሚሰጡህ ስለሚወዱህ እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 3:12) መጥፎ ባሕርያትን እንዳታዳብር ከዚህ ይልቅ መልካም ባሕርያት እንዲኖሩህ ሊረዱህ ይፈልጋሉ። ወላጆችህ ለአንተ እርማት አለመስጠት አንተን ከመጥላት ተለይቶ እንደማይታይ ይገነዘባሉ! (ምሳሌ 13:24ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ከስህተት መማር የእድገት አንዱ ክፍል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልግሃል። ስለዚህ እርማት ሲሰጥህ በውስጡ የሚገኘውን እንደ ውድ ማዕድን የሚቆጠር ጥበብ ለይተህ ለማውጣት ለምን ጥረት አታደርግም? “[ጥበብ] ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናት።”—ምሳሌ 3:13, 14

9. ወጣቶች ትክክል እንዳልሆነ የተሰማቸውን ነገር እያሰቡ ከመብሰልሰል ይልቅ ምን ማድረግ ይችላሉ?

9 ይሁንና ወላጆች ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። (ያዕ. 3:2) አንዳንድ ጊዜ ተግሣጽ ሲሰጡህ በግዴለሽነት ወይም እንዳመጣላቸው ሊናገሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 12:18) ለዚህ መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል? ወላጆችህ ውጥረት ውስጥ ሆነው አሊያም የአንተ መሳሳት የእነሱ ጥፋት እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። ትክክል እንዳልሆነ የተሰማህን ነገር እያሰብክ ከመብሰልሰል ይልቅ አንተን ለመርዳት የሚያደርጉትን ልባዊ ጥረት እንደምታደንቅ ለማሳየት ለምን አትሞክርም? የሚሰጥህን ተግሣጽ መቀበል መቻልህ ትልቅ ሰው ስትሆን ይጠቅምሃል።

10. ወላጆችህ የሚያወጧቸውን መመሪያዎችና የሚሰጡህን እርማት መቀበል እንዲሁም ከዚህ ጥቅም ማግኘት ቀላል እንዲሆንልህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

10 ወላጆችህ የሚያወጧቸውን መመሪያዎችና የሚሰጡህን እርማት መቀበል እንዲሁም ከዚህ ጥቅም ማግኘት ቀላል እንዲሆንልህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሐሳብህን የምትገልጽበትን መንገድ ማሻሻል ያስፈልግሃል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ ማዳመጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት” ይላል። (ያዕ. 1:19) ላደረግኸው ነገር ምክንያት ለመደርደር ከመጣደፍ ይልቅ ስሜትህን ተቆጣጥረህ ወላጆችህ የሚሉህን አዳምጥ። በተናገሩበት መንገድ ላይ ሳይሆን ሊያስተላልፉት በፈለጉት ነጥብ ላይ ትኩረት አድርግ። ከዚያም ጥፋትህን እመን፤ ጥፋትህን የምታምን ከሆነ ወላጆችህ የተናገሩት ነገር እንደገባህ ታሳያለህ። ይሁንና አንድን ነገር የተናገርክበትን ወይም ያደረግክበትን ምክንያት መግለጽ ብትፈልግስ? አብዛኛውን ጊዜ ወላጆችህ የሚጠብቁብህን ነገር እስክትፈጽም ድረስ ‘አንደበትህን መግታቱ’ የጥበብ እርምጃ ነው። (ምሳሌ 10:19) ወላጆችህ የተናገሩትን ነገር እንዳዳመጥካቸው ሲገነዘቡ የምትለውን ለመስማት ይበልጥ ፈቃደኛ ይሆናሉ። እንዲህ ያለው ብስለት የሚንጸባረቅበት አካሄድ በአምላክ ቃል እንደምትመራ ያረጋግጣል።

በገንዘብ አያያዝ ረገድ በአምላክ ቃል መመራት

11, 12. (ሀ) ከገንዘብ ጋር በተያያዘ የአምላክ ቃል ምን ምክር ይሰጠናል? እንዲህ የሚለውስ ለምንድን ነው? (ለ) ወላጆችህ ገንዘብን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ እንዴት ሊረዱህ ይችላሉ?

11 መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” ይናገራል። ይሁን እንጂ ይኸው ጥቅስ ጥበብ ከገንዘብ ይበልጥ ዋጋ እንዳለው ይገልጻል። (መክ. 7:12) የአምላክ ቃል ገንዘብን እንድናከብረው እንጂ እንዳንወደው ይመክረናል። የገንዘብ ፍቅር እንዳያድርብህ መጠንቀቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው? የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት፦ በምግብ ዝግጅት ለተካነ ሰው የሰላ ቢላ ጠቃሚ መሣሪያ ነው። ይኸው ቢላ ልምድ በሌለው ወይም ጥንቁቅ ባልሆነ ሰው እጅ ቢገባ ግን ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ገንዘብም አጠቃቀሙን ካወቅህበት ጠቃሚ መሣሪያ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ግን “ሀብታም ለመሆን ቆርጠው የተነሱ” ሰዎች ከጓደኞቻቸው፣ ከቤተሰባቸው አልፎ ተርፎም ከአምላክ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተበላሽቷል። በዚህ ምክንያት “ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።”—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።

12 ገንዘብን በአግባቡ የመጠቀም ልማድ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በጀት ማውጣት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም? ሰለሞን “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 1:5) አና የተባለች ወጣት፣ ከገንዘብ ጋር በተያያዘ መመሪያ ወይም ምክር እንዲሰጧት ወላጆቿን ጠይቃቸው ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ እንዴት አድርጌ በጀት ማውጣት እንደምችል ያስተማረኝ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡን ገቢ አብቃቅቶ ለመጠቀም የተደራጁ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አሳይቶኛል።” እናቷም ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን አስተምራታለች። “እናቴ፣ አንድን ዕቃ ከመግዛት በፊት የተለያዩ ቦታዎች ጠይቆ ዋጋውን ማወዳደር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አሳይታኛለች” ስትል አና ተናግራለች። አና ምን ጥቅም አግኝታለች? “አሁን የራሴን ገንዘብ በሚገባ መያዝ እችላለሁ። ገንዘብ እንዳላባክን ስለምጠነቀቅ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አልገባም፤ ይህ ደግሞ የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል” ብላለች።

13. በገንዘብ አጠቃቀም ረገድ ራስህን መግዛት የምትችለው እንዴት ነው?

13 ያየኸውን ሁሉ ካልገዛሁ የምትል ወይም ጓደኞችህን ለማስደመም ብለህ ገንዘብ የምትበትን ከሆነ ዕዳ ውስጥ መዘፈቅህ አይቀርም። እንዲህ ያለው ጎጂ ልማድ እንዳይጠናወትህ ምን ሊረዳህ ይችላል? በገንዘብ አጠቃቀም ረገድ ራስህን መግዛትን መማር ይኖርብሃል። በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኘው ኤሌና የምታደርገው እንደዚህ ነው። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ ቦታ ስንሄድ ምን እንደምናደርግ አስቀድሜ በማሰብ ምን ያህል እንደማወጣ እወስናለሁ። . . . በተጨማሪም ገበያ በምወጣበት ጊዜ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቃ ከሆኑት እንዲሁም የተለያየ ሱቅ ገብቼ ዋጋ ሳላወዳድር አንድን ነገር ገና እንዳየሁት ከመግዛት እንድቆጠብ ከሚያበረታቱኝ ጓደኞቼ ጋር መሄዱን ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”

14. “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ወጥመድ እንዳይሆንብህ መጠንቀቅ ያለብህ ለምንድን ነው?

14 ገንዘብ ማግኘትና ያገኙትን ገንዘብ በአግባቡ መያዝ በሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ ነው። ይሁንና ኢየሱስ፣ እውነተኛ ደስታ የሚያገኙት “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 5:3) በተጨማሪም “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” አንድ ሰው ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለውን ፍላጎት ሊያንቀው እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ማር. 4:19) እንግዲያው በአምላክ ቃል በመመራት ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበርህ ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ለብቻህ ስትሆን በአምላክ ቃል መመራት

15. ለአምላክ ያለህ ታማኝነት ይበልጥ የሚፈተነው መቼ ነው?

15 ለአምላክ ያለህ ታማኝነት ይበልጥ የሚፈተነው መቼ ይመስልሃል? ከሌሎች ጋር ስትሆን ነው ወይስ ብቻህን ስትሆን? በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ስትሆን መንፈሳዊ ጥቃትን ለመመከት ይበልጥ ዝግጁ እንደምትሆን የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜ ሊያጋጥሙህ የሚችሉትን መንፈሳዊ አደጋዎች በንቃት ትከታተላለህ። የሚያጋጥምህን ፈተና ለመቋቋም ያን ያህል ዝግጁ በማትሆንበትና ዘና በምትልበት ጊዜ ግን የሥነ ምግባር አቋምህን እንድታላላ ለሚሰነዘርብህ ጥቃት ይበልጥ ትጋለጣለህ።

16. ብቻህን በምትሆንበት ጊዜም ይሖዋን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው?

16 ብቻህን በምትሆንበት ጊዜም ይሖዋን መታዘዝ ያለብህ ለምንድን ነው? ብቻህን በምትሆንበት ወቅት የምታደርገው ነገር የይሖዋን ልብ ሊያሳዝነው አሊያም ደስ ሊያሰኘው እንደሚችል አስታውስ። (ዘፍ. 6:5, 6፤ ምሳሌ 27:11) ይሖዋ በምታደርገው ነገር ስሜቱ የሚነካው ‘ስለ አንተ ስለሚያስብ’ ነው። (1 ጴጥ. 5:7) እሱን እንድትሰማው የሚፈልገው ይህን ማድረግህ እንደሚጠቅምህ ስለሚያውቅ ነው። (ኢሳ. 48:17, 18) በጥንቷ እስራኤል የነበሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ምክሩን ችላ በማለታቸው እጅግ አዝኖ ነበር። (መዝ. 78:40, 41) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ መልአክ፣ ነቢዩ ዳንኤልን “እጅግ የተወደድህ” ብሎ መጥራቱ ይሖዋ ይህን ነቢይ በጣም ይወደው እንደነበር ያሳያል። (ዳን. 10:11) ይሖዋ ዳንኤልን እንዲወደው ያደረገው ምንድን ነው? ዳንኤል ከሌሎች ጋር ሲሆን ብቻ ሳይሆን ለብቻው በሚሆንበት ጊዜም ለአምላክ ታማኝ ነበር።—ዳንኤል 6:10ን አንብብ።

17. መዝናኛ በምትመርጥበት ጊዜ የትኞቹን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅ ትችላለህ?

17 ብቻህን በምትሆንበት ጊዜም ለአምላክ ታማኝ መሆን እንድትችል ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የማስተዋል ችሎታህን’ ማዳበር ይኖርብሃል፤ ከዚያም ይህን ችሎታህን “በማሠራት” ማሠልጠን ይኸውም ትክክል እንደሆነ የተማርከውን ነገር ማድረግ ያስፈልግሃል። (ዕብ. 5:14) ለምሳሌ ያህል፣ የምታዳምጠውን ሙዚቃ ወይም የምትመለከታቸውን ፊልሞች አሊያም የምትቃኛቸውን የኢንተርኔት ድረ ገጾች በምትመርጥበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅህ ትክክለኛ ምርጫ ለማድረግና ስህተት ከሆነው ነገር ለመራቅ ይረዳሃል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የማየው ነገር ከአንጀት የምራራ እንድሆን ይረዳኛል? ወይስ “በሌላው ሰው መከራ” እንድደሰት ተጽዕኖ ያደርግብኛል?’ (ምሳሌ 17:5) ‘“መልካሙን ውደዱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እንዳደርግ ይረዳኛል ወይስ “ክፋትን መጥላት” ከባድ እንዲሆንብኝ ያደርጋል?’ (አሞጽ 5:15) ብቻህን ስትሆን የምታደርገው ነገር፣ ከፍ አድርገህ የምትመለከታቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ያሳያል።—ሉቃስ 6:45

18. በድብቅ ኃጢአት እየፈጸምክ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለምንስ?

18 ስህተት እንደሆነ የምታውቀውን ነገር በድብቅ የምትፈጽም ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ። (ምሳሌ 28:13) ስህተት መሥራትህን በመቀጠል “የአምላክን ቅዱስ መንፈስ [ማሳዘን]” ምንኛ ጥበብ የጎደለው አካሄድ ነው! (ኤፌ. 4:30) የምትፈጽመውን ማንኛውንም ኃጢአት ለአምላክም ሆነ ለወላጆችህ የመናገር ኃላፊነት አለብህ፤ ጥፋትህን መናገርህ ለራስህም ቢሆን ይጠቅምሃል። በዚህ ረገድ “የጉባኤ ሽማግሌዎች” ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱልህ ይችላሉ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “[የጉባኤ ሽማግሌዎች] በይሖዋ ስም ዘይት ቀብተው [ስህተት ለሠራው ሰው] ይጸልዩለት። በእምነት የቀረበ ጸሎት የታመመውን ሰው ይፈውሰዋል፤ ይሖዋም ያስነሳዋል። በተጨማሪም ኃጢአት ሠርቶ ከሆነ ይቅር ይባልለታል።” (ያዕ. 5:14, 15) ስህተትህን መናገር ሊያሳፍርህና ቅጣት ሊያስከትልብህ እንደሚችል አይካድም። ያም ሆኖ እንደምንም ራስህን አደፋፍረህ እርዳታ ከጠየቅህ በራስህ ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከማምጣት ትድናለህ፤ እንዲሁም ሕሊናህ ንጹሕ ስለሚሆን እፎይታ ታገኛለህ።—መዝ. 32:1-5

የይሖዋን ልብ አስደስት

19, 20. ይሖዋ ምን እንድታገኝ ይፈልጋል? አንተስ ምን ማድረግ አለብህ?

19 ይሖዋ “ደስተኛ” አምላክ ሲሆን አንተም ደስተኛ እንድትሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 1:11) ስለ አንተ በጥልቅ ያስባል። ትክክለኛውን አካሄድ ለመከተል የምታደርገውን ጥረት ማንም ሰው ባያስተውለውም እንኳ ይሖዋ ጥረትህን ይመለከታል። ከይሖዋ ዓይኖች የተሰወረ ምንም ነገር የለም። ይሖዋ የሚመለከትህ ስህተት ለመፈለግ ብሎ ሳይሆን መልካም የሆነውን ለመፈጸም በምታደርገው ጥረት አንተን ለማገዝ ነው። “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ።”—2 ዜና 16:9

20 እንግዲያው የአምላክ ቃል እንዲመራህ ፍቀድ፤ እንዲሁም ምክሮቹን ተግባራዊ አድርግ። ይህን ካደረግህ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም እንዲሁም ከባድ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስፈልግህን ጥበብና ማስተዋል ታገኛለህ። ወላጆችህንና ይሖዋን የምታስደስት ከመሆኑም በላይ በሕይወትህ ውስጥ እውነተኛ ደስታ ታገኛለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

ወጣቶች፣ ወላጆቻቸው የሚያወጧቸውን መመሪያዎችና የሚሰጧቸውን እርማት መቀበል እንዲሁም ከዚህ ጥቅም ማግኘት ቀላል እንዲሆንላቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ብቻህን በምትሆንበት ጊዜም ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለብቻህ በምትሆንበት ጊዜም ለአምላክ ታማኝ ትሆናለህ?