በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች—ሕይወታችሁን እንዴት ልትጠቀሙበት አስባችኋል?

እናንት ወጣቶች—ሕይወታችሁን እንዴት ልትጠቀሙበት አስባችኋል?

እናንት ወጣቶች—ሕይወታችሁን እንዴት ልትጠቀሙበት አስባችኋል?

“ቡጢዬን የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም።”—1 ቆሮ. 9:26

1, 2. እያደግህ ስትሄድ በሕይወትህ ስኬታማ እንድትሆን ምን ያስፈልግሃል?

አንድ መንገደኛ ወደማያውቀው አካባቢ ሲጓዝ ካርታና ኮምፓስ መያዙ ይጠቅመዋል። ካርታው ያለበትን ቦታ ለማወቅ የሚረዳው ከመሆኑም ሌላ የሚጓዝበትን ትክክለኛ መንገድ ለመምረጥ ያስችለዋል። ኮምፓሱ ደግሞ ትክክለኛውን አቅጣጫ ስቶ እንዳይወጣ ይረዳዋል። ይሁንና ይህ መንገደኛ መድረሻውን ካላወቀ ካርታውም ሆነ ኮምፓሱ እምብዛም አይጠቅሙትም። የት እንደሚሄድ በግልጽ ካላወቀ እንዲሁ ከመባዘን ውጭ የፈለገበት ቦታ ላይ መድረስ አይችልም።

2 አንተም እያደግህ ስትሄድ ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጥምሃል። በዚህ ወቅት ልትጠቀምበት የምትችል አስተማማኝ የሆነ ካርታና ኮምፓስ አለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛውን የሕይወት ጎዳና መምረጥ እንድትችል የሚረዳ ካርታ ነው። (ምሳሌ 3:5, 6) ሕሊናህ ደግሞ በሚገባ ከሠለጠነ ትክክለኛውን አቅጣጫ ስተህ እንዳትወጣ ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ እንደ ኮምፓስ ሊያገለግልህ ይችላል። (ሮም 2:15) ይሁንና በሕይወትህ ስኬታማ መሆን እንድትችል የት መሄድ እንደምትፈልግም ማወቅ ይኖርብሃል። በሌላ አባባል በግልጽ የተቀመጡ ግቦች ሊኖሩህ ይገባል።

3. በ1 ቆሮንቶስ 9:26 ላይ ጳውሎስ ግብ ማውጣት ምን ጥቅም እንዳለው ገልጿል?

3 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ግብ ማውጣትና እዚያ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም ጠቅለል አድርጎ ሲገልጸው እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኔ መድረሻውን እንደማያውቅ ሰው አልሮጥም፤ ቡጢዬን የምሰነዝረውም አየር ለመምታት አይደለም።” (1 ቆሮ. 9:26) በግልጽ የተቀመጡ ግቦች ካሉህ መድረሻህን ታውቃለህ። በመጪዎቹ ዓመታት አምልኮን፣ ሥራን፣ ትዳርን፣ ቤተሰብንና ሌሎች ወሳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ አንዳንድ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ታደርጋለህ። አንዳንድ ጊዜ ግራ የሚያጋቡ በርካታ አማራጮች እንዳሉህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው እውነትና መመሪያ ላይ ተመሥርተህ የምትከተለውን ጎዳና ቀደም ብለህ ከመረጥህ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመሄድ አትፈተንም።—2 ጢሞ. 4:4, 5

4, 5. (ሀ) ለራስህ ግብ ካላወጣህ ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? (ለ) በሕይወትህ ውስጥ የምትመርጠው ጎዳና አምላክን ለማስደሰት ያለህን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው?

4 ለራስህ ግብ ካላወጣህ እኩዮችህና አስተማሪዎችህ ለአንተ ጥሩ ነው ብለው ያሰቡትን አቅጣጫ እንድትከተል ተጽዕኖ ለማድረግ መሞከራቸው የማይቀር ነው። እርግጥ ነው፣ በግልጽ የተቀመጡ ግቦች ቢኖሩህም እንኳ አንዳንዶች የራሳቸውን አመለካከት ይሰነዝሩ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ፦ ‘እነሱ የጠቀሱልኝን ግቦች መከተሌ በወጣትነቴ ጊዜ ፈጣሪዬን እንዳስብ ይረዳኛል ወይስ ይህን እንዳላደርግ ትኩረቴን ይከፋፍልብኛል?’—መክብብ 12:1ን አንብብ።

5 በሕይወትህ ውስጥ የምትመርጠው ጎዳና አምላክን ለማስደሰት ያለህን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ያሉንን መልካም ስጦታዎች ሁሉ ያገኘነው ከይሖዋ በመሆኑ ነው። (ያዕ. 1:17) በእርግጥም ሁሉም ፍጥረታት ይሖዋን ለማመስገን የሚያነሳሷቸው ብዙ ምክንያቶች አሏቸው። (ራእይ 4:11) ግቦች በምታወጣበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር ያለህን ግንኙነት በአእምሮህ መያዝ ይኖርብሃል፤ ይህ ይሖዋ ላደረገልህ ነገሮች ምስጋናህን ለመግለጽ የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። ሊኖሩህ የሚገቡ አንዳንድ ግቦችንና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስቲ እንመልከት።

ምን ዓይነት ግቦች ማውጣት ትችላለህ?

6. የትኛውን መሠረታዊ ግብ ማውጣት ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ልታወጣ ከምትችላቸው ግቦች መካከል ዋነኛው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እውነት መሆኑን ራስህ ማረጋገጥ ነው። (ሮም 12:2፤ 2 ቆሮ. 13:5) እኩዮችህ በዝግመተ ለውጥ ወይም በተለያዩ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ያምኑ ይሆናል፤ ይህን የሚያደርጉት ሌሎች ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ማመን እንዳለባቸው ስለነገሯቸው ነው። አንተ ግን ከእምነትህ ጋር በተያያዘ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ መከተል የለብህም። ይሖዋ በሙሉ አእምሮህ እንድታገለግለው እንደሚፈልግ አስታውስ። (ማቴዎስ 22:36, 37ን አንብብ።) በሰማይ የሚገኘው አባታችን በማስረጃ የተደገፈ እምነት እንዲኖርህ ይፈልጋል።—ዕብ. 11:1

7, 8. (ሀ) የትኞቹን የአጭር ጊዜ ግቦች ማውጣትህ እምነትህን ለማጠናከር ይረዳሃል? (ለ) ያወጣሃቸው የአጭር ጊዜ ግቦች ላይ ስትደርስ ምን ጥቅሞች ታገኛለህ?

7 እምነትህን ለማጠናከር እንድትችል በአጭር ጊዜ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን አንዳንድ ግቦች ለምን አታወጣም? ልታወጣው የምትችለው አንዱ ግብ በየቀኑ መጸለይ ሊሆን ይችላል። በቀኑ ውሎህ ያጋጠሙህን በጸሎትህ ውስጥ ልታካትታቸው የምትፈልጋቸው ነገሮች በአእምሮህ መያዝህ ወይም በማስታወሻ ላይ ማስፈርህ፣ በጸሎትህ ላይ የምትፈልገውን ነገር ለይተህ መጥቀስ እንድትችል እንዲሁም ሁልጊዜ ተመሳሳይ ጸሎት ከማቅረብ እንድትቆጠብ ይረዳሃል። ያጋጠሙህን ተፈታታኝ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ያስደሰቱህንም ነገሮች በጸሎትህ ላይ መጥቀስህን አትዘንጋ። (ፊልጵ. 4:6) ልታወጣው የምትችለው ሌላው ግብ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ነው። በየዕለቱ አራት ገጽ ገደማ ብታነብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ መጨረስ እንደምትችል ታውቃለህ? * መዝሙር 1:1, 2 በይሖዋ ‘ሕግ ደስ የሚሰኝ ሰው’ ደስተኛ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል” ይላል።

8 በአጭር ጊዜ ውስጥ ልትደርስበት የምትችለው ሦስተኛው ግብ ደግሞ በእያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀት ነው። መጀመሪያ አካባቢ መልሱን ከጽሑፉ ላይ በቀጥታ ማንበብ አሊያም ጥቅሶችን አውጥተህ ማንበብ ትችል ይሆናል። እያደር ደግሞ በራስህ አባባል መልስ የመስጠት ግብ ልታወጣ ትችላለህ። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በሰጠህ ቁጥር ለይሖዋ መሥዋዕት ያቀረብህ ያህል ነው። (ዕብ. 13:15) ካወጣሃቸው ግቦች አንዳንዶቹ ላይ ስትደርስ በራስ የመተማመን ስሜትህ እንዲሁም ለይሖዋ ያለህ አድናቆት እየጨመረ ስለሚሄድ የረጅም ጊዜ ግቦችን ለማውጣት ዝግጁ ትሆናለህ።

9. የመንግሥቱ አስፋፊ ካልሆንህ የትኞቹን የረጅም ጊዜ ግቦች ልታወጣ ትችላለህ?

9 በረጅም ጊዜ ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ምን ዓይነት ግቦችን ማውጣት ትችላለህ? ምሥራቹን ለሰዎች መናገር ካልጀመርህ ልታወጣ ከምትችላቸው የረጅም ጊዜ ግቦች አንዱ የመንግሥቱ አስፋፊ መሆን ነው። ይህ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ግብ ሲሆን እዚህ ግብ ላይ መድረስ ከቻልህ አንድም ወር ቢሆን ሳታገለግል እንዲያልፍህ አትፍቀድ፤ አዘውታሪና ውጤታማ አስፋፊ ለመሆን ጥረት አድርግ። ከዚህም በተጨማሪ በአገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መጠቀም እንደምትችል መማር ያስፈልግሃል። እንዲህ ስታደርግ የስብከቱ ሥራ ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል። ከዚያም ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት የበለጠ ለመካፈል አልፎ ተርፎም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ያልተጠመቅህ አስፋፊ እንደመሆንህ መጠን ለጥምቀት የሚያስፈልግህን ብቃት ማሟላት እንዲሁም ራስህን ለይሖዋ አምላክ ወስነህ መጠመቅ ልታወጣው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ግብ ነው።

10, 11. የተጠመቁ ወጣቶች የትኞቹን የረጅም ጊዜ ግቦች ማውጣት ይችላሉ?

10 የተጠመቅህ የይሖዋ አገልጋይ ከሆንህ ደግሞ ልትደርስባቸው ከምትችላቸው የረጅም ጊዜ ግቦች መካከል አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል። ለምሳሌ፣ እምብዛም ያልተሠራባቸው ክልሎች ወዳሏቸው ጉባኤዎች አልፎ አልፎ እየሄድህ መስበክ ትችላለህ። እንዲሁም የወጣትነት ጉልበትህንና ጤንነትህን ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ ሆነህ ለማገልገል ልትጠቀምበት ትችላለህ። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት ደስተኛ የሆኑ አቅኚዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በወጣትነትህ ጊዜ ፈጣሪህን ለማሰብ የሚያስችል የሚክስ የአገልግሎት መስክ እንደሆነ ይመሠክራሉ። እነዚህ ከቤተሰቦችህ ጋር እያለህ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች ናቸው። እነዚህ ግቦች ላይ በመድረስህ ጉባኤህም ይጠቀማል።

11 ከጉባኤህ ወጣ ብለህ ለማገልገል የሚያስችሉህ ሌሎች የረጅም ጊዜ ግቦችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደህ ለማገልገል ግብ ልታወጣ ትችላለህ። የመንግሥት አዳራሾችን ወይም ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመገንባት ሥራ መካፈል ትችል ይሆናል። አልፎ ተርፎም በቤቴል ማገልገል፣ ልዩ አቅኚ መሆን ወይም በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት መካፈል ትችላለህ። እርግጥ ነው፣ ከላይ የተጠቀሱት የረጅም ጊዜ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ከማድረግህ በፊት ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባው አስፈላጊ ግብ መጠመቅ ነው። ካልተጠመቅህ እዚህ አስፈላጊ ግብ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግህ አስብበት።

ለመጠመቅ ያወጣኸው ግብ ላይ መድረስ

12. አንዳንዶች ለመጠመቅ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ምክንያቶች በቂ አይደሉም የምንለው ለምንድን ነው?

12 የጥምቀት ዓላማ ምን ይመስልሃል? አንዳንዶች ጥምቀት ኃጢአት እንዳይሠሩ ጥበቃ እንደሚሆናቸው ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ እኩዮቻቸው ስለተጠመቁ ብቻ መጠመቅ እንዳለባቸው ሊያስቡ ይችላሉ። አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸውን ለማስደሰት ሲሉ ለመጠመቅ ይፈልጉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥምቀት፣ ግዴታ ውስጥ ስለገባህ ብቻ ልብህ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ከማድረግ እንድትቆጠብ የሚያግድ ከአምላክ ጋር የሚደረግ ውል አይደለም፤ ወይም ደግሞ ሌሎች ስለገፋፉህ ብቻ መጠመቅ አይኖርብህም። መጠመቅ የሚገባህ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት በሚገባ ከተገነዘብህና ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁና ፈቃደኛ መሆንህን እርግጠኛ ከሆንህ ብቻ ነው።—መክ. 5:4, 5

13. ለመጠመቅ የሚያነሳሳህ ምክንያት ምን ሊሆን ይገባል?

13 ለመጠመቅ ሊያነሳሳህ የሚገባው አንዱ ምክንያት ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሰዎችን “እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚል ትእዛዝ ስለሰጣቸው ነው። ኢየሱስ ራሱም በመጠመቅ አርዓያ ትቶልናል። (ማቴዎስ 28:19, 20ን እና ማርቆስ 1:9ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ጥምቀት መዳን ለማግኘት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኖኅ እሱና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ የዳኑበትን መርከብ እንደሠራ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር እናንተን እያዳናችሁ ሲሆን ይህም ጥምቀት ነው፤ . . . የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት ነው።” (1 ጴጥ. 3:20, 21) መጠመቅ ሲባል ግን አደጋ ቢደርስብህ ሊረዳህ የሚችል የመድን ዋስትና መግዛት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምትጠመቀው ይሖዋን ስለምትወደውና በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ አእምሮህና ኃይልህ ልታገለግለው ስለምትፈልግ ነው።—ማር. 12:29, 30

14. አንዳንዶች ከመጠመቅ ወደኋላ የሚሉት ለምን ሊሆን ይችላል? ሆኖም ምን ማረጋገጫ ተሰጥቶሃል?

14 አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ ብወገድስ ብለው በመፍራት ከመጠመቅ ወደኋላ ይሉ ይሆናል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ እንዲህ ያለው ፍርሃት በራሱ መጥፎ ነገር ነው ማለት አይደለም። እንዲህ የሚሰማህ መሆኑ የይሖዋ ምሥክር መሆን ከባድ ኃላፊነት እንደሚያስከትል መገንዘብህን ያሳያል። ይሁንና ሌላስ ምክንያት ይኖርህ ይሆን? ምናልባትም አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች መከተል ሕይወትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመምራት እንደሚያስችልህ እርግጠኛ አልሆንህ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ችላ ማለት የሚያስከትላቸውን መዘዞች ማስታወስህ ውሳኔ ላይ እንድትደርስ ይረዳሃል። በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ያወጣቸውን መመሪያዎች መከተል ብትፈልግም ይህን ማድረግ መቻልህን ትጠራጠር ይሆናል። እውነቱን ለመናገር እንዲህ የሚሰማህ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ትሕትና እንዳለህ የሚያሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ፍጹም ያልሆነ ሰው ሁሉ ልቡ ተንኮለኛ ወይም አታላይ እንደሆነ ይናገራል። (ኤር. 17:9) ሆኖም በአምላክ ‘ቃል መሠረት ለመኖር’ ሁልጊዜ ጥረት የምታደርግ ከሆነ የአምላክን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሊሳካልህ ይችላል። (መዝሙር 119:9ን አንብብ።) ከመጠመቅ ወደኋላ እንድትል የሚያደርጉህ ምክንያቶች ምንም ይሁኑ ምን ለእነዚህ እንቅፋቶች መፍትሔ ማግኘት ያስፈልግሃል። *

15, 16. ለጥምቀት ዝግጁ መሆንህን እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

15 ይሁንና ለመጠመቅ ዝግጁ መሆንህን እንዴት ማወቅ ትችላለህ? አንዱ መንገድ ራስህን እንደሚከተለው በማለት መጠየቅ ነው፦ ‘መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለሰዎች ማብራራት እችላለሁ? ወላጆቼ በአገልግሎት ባይካፈሉም እንኳ እኔ እንዲህ አደርጋለሁ? በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት አደርጋለሁ? የእኩዮቼን ተጽዕኖ የተቋቋምኩባቸውን አንዳንድ አጋጣሚዎች መጥቀስ እችላለሁ? ወላጆቼና ጓደኞቼ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙም እንኳ እኔ ማገልገሌን እቀጥላለሁ? ከአምላክ ጋር ያለኝን ዝምድና ምን ያህል ከፍ አድርጌ እንደምመለከተው በጸሎት ለይሖዋ ነግሬዋለሁ? ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ እንደወሰንኩ በጸሎት ነግሬዋለሁ?’

16 ጥምቀት ሕይወትህን የሚለውጥ እርምጃ በመሆኑ አቅልለህ ልትመለከተው አይገባም። ይህን እርምጃ በቁም ነገር ለማጤን የሚያስችል ብስለት አለህ? ብስለት ሲባል ጥሩ ንግግር ከማቅረብ ወይም በስብሰባ ወቅት የሚያስደምሙ ሐሳቦችን ከመስጠት የበለጠ ነገርን ይጨምራል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተረድቶ በዚያ መሠረት ውሳኔ ማድረግን ይጠይቃል። (ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምትችል ከሆነ ከሁሉ የላቀ መብት ይኖርሃል፤ ይኸውም ይሖዋን በሙሉ ልብህ ለማገልገልና ራስህን የወሰንከው ከልብህ እንደሆነ በሚያሳይ መንገድ ሕይወትህን ለመምራት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፈትልሃል።

17. ከተጠመቅህ በኋላ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል?

17 እንደተጠመቅህ አምላክን በግለት ማገልገል ትፈልግ ይሆናል። ብዙም ሳይቆይ ግን እምነትህንና ጥንካሬህን የሚፈትኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 3:12) እነዚህን ፈተናዎች ብቻህን መወጣት እንዳለብህ አይሰማህ። የወላጆችህን ምክር እንዲሁም በጉባኤ የሚገኙ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን እርዳታ ጠይቅ። ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ያለህን ወዳጅነት አጠናክር። ይሖዋ እንደሚያስብልህና ሊያጋጥምህ የሚችለውን ማንኛውም ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስፈልግህን ጥንካሬ እንደሚሰጥህ ፈጽሞ አትዘንጋ።—1 ጴጥ. 5:6, 7

ግቦችህ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው?

18, 19. ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መመርመርህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?

18 ግቦችህ ላይ ለመድረስ ከልብህ ብትመኝም የምትፈልገውንና የግድ የሚያስፈልግህን ነገር ለማከናወን በቂ ጊዜ እንደሌለህ ይሰማሃል? ከሆነ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መመርመር አለብህ። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንድ የፕላስቲክ ባልዲ ውስጥ በርከት ያሉ ትልልቅ ድንጋዮች ጨምር። ከዚያም ባልዲውን በአሸዋ ሙላው። አሁን ባልዲው በድንጋይ እና በአሸዋ ተሞልቷል። ቀጥለህ ደግሞ ባልዲውን በመገልበጥ አሸዋውንና ድንጋዩን ለየብቻ አስቀምጠው። አሁን ከበፊቱ በተቃራኒ መጀመሪያ አሸዋውን ባልዲው ውስጥ ጨምረው፤ ከዚያም ድንጋዮቹን ክተት። ሁሉንም ድንጋዮች ለመጨመር ቦታ አነሰህ አይደል? ይህ የሆነው ባልዲው ውስጥ መጀመሪያ አሸዋውን በመጨመርህ ነው።

19 ከጊዜ አጠቃቀምህ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንደ መዝናኛ ላሉት ትናንሽ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠህ ትልልቅ ለሆኑት ነገሮች ይኸውም ለመንፈሳዊ ጉዳዮች በቂ ጊዜ አይኖርህም። በሌላ በኩል ግን “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ካደረግህ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮችም ሆነ በተወሰነ መጠን ለመዝናናት ጊዜ ይኖርሃል።—ፊልጵ. 1:10

20. ግቦችህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ ብትጨነቅ እንዲሁም ጥርጣሬ ቢያድርብህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

20 መጠመቅን ጨምሮ ሌሎች ግቦችህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ አልፎ አልፎ ትጨነቅ እንዲሁም ጥርጣሬ ያድርብህ ይሆናል። እንዲህ ሲሰማህ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል።” (መዝ. 55:22) አሁን፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑት ሁሉ ይበልጥ አስደሳችና አስፈላጊ በሆነው ሥራ ይኸውም በዓለም አቀፉ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ የመካፈል አጋጣሚ ተዘርግቶልሃል። (ሥራ 1:8) ይህ ሥራ ሲከናወን ዳር ቆመህ ለመመልከት ትመርጥ ይሆናል። አሊያም በሥራው መካፈል ትችላለህ። ያለህን ችሎታ በመጠቀም አምላክን ከማገልገልና መንግሥቱን ከመደገፍ ወደኋላ አትበል። “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን” በማገልገልህ ፈጽሞ አትቆጭም!—መክ. 12:1

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.14 በዚህ ረገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 34⁠ን ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ግብ ማውጣት ያለብህ ለምንድን ነው?

• ልትደርስባቸው የምትችላቸው አንዳንድ ግቦች የትኞቹ ናቸው?

• ለመጠመቅ ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ያስፈልግሃል?

• ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮች መመርመር ግቦችህ ላይ ለመድረስ የሚረዳህ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ግብ አለህ?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመጠመቅ ያወጣኸው ግብ ላይ መድረስ እንድትችል ምን ይረዳሃል?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?