በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንመላለስ!

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንመላለስ!

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንመላለስ!

“እኔ በበኩሌ፣ ንጹሕ አቋሜን ጠብቄ እመላለሳለሁ።”—መዝ. 26:11 NW

1, 2. ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በተመለከተ ምን ብሏል? ኢዮብ ምዕራፍ 31 ስለ እሱ ምን ይጠቁመናል?

በጥንት ጊዜ ሰዎች ነገሮችን ለመመዘን ባለአግዳሚ ሚዛን ይጠቀሙ ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ሚዛን መሃል ለመሃል ማንጠልጠያ ካለው አግዳሚ የሚሠራ ሲሆን በአግዳሚው ጫፍና ጫፍ ላይ ሳህን ይንጠለጠላል። የሚመዘነው ነገር በአንደኛው ሳህን ላይ ይደረግና በሌላኛው ሳህን ላይ ደግሞ መመዘኛ ይቀመጥ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች ትክክለኛ ሚዛንና መመዘኛ መጠቀም ይጠበቅባቸው ነበር።—ምሳሌ 11:1

2 ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ፣ ሰይጣን ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ጥቃት በሰነዘረበት ጊዜ “[ይሖዋ] በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኛል፤ አምላክ ንጹሕ አቋም እንዳለኝ ያውቃል” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 31:6 NW) ኢዮብ ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ፈተና ላይ እንዲወድቁ ሊያደርጓቸው የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎችን ጠቅሷል። ሆኖም በኢዮብ መጽሐፍ ምዕራፍ 31 ላይ ከሰፈረው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው ኢዮብ ፈተናውን በድል ተወጥቷል። የኢዮብ ግሩም ምሳሌነት እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግና እንደ መዝሙራዊው ዳዊት “እኔ በበኩሌ፣ ንጹሕ አቋሜን ጠብቄ እመላለሳለሁ” በማለት በእርግጠኝነት እንድንናገር ያነሳሳናል።—መዝ. 26:11 NW

3. በትላልቅም ሆነ በትናንሽ ጉዳዮች ለአምላክ ታማኝ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 ኢዮብ ከባድ ፈተና የደረሰበት ቢሆንም ለአምላክ ታማኝ ሆኗል። እንዲያውም አንዳንዶች ኢዮብ ይህ ሁሉ ከባድ ፈተና ደርሶበት ከንጹሕ አቋሙ ፍንክች አለማለቱ እንደ ጀግና እንደሚያስቆጥረው ይናገራሉ። እርግጥ ነው፣ ማናችንም ብንሆን ኢዮብ የደረሰበት ዓይነት ሥቃይ አልደረሰብንም። ይሁን እንጂ በንጹሕ አቋም እንደምንመላለስና የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት ከፈለግን በትላልቅም ሆነ በትናንሽ ጉዳዮች ለአምላክ ታማኝ መሆን አለብን።—ሉቃስ 16:10ን አንብብ

በሥነ ምግባር ረገድ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ አስፈላጊ ነው

4, 5. ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ይመላለስ የነበረው ኢዮብ ምን ከማድረግ ተቆጥቧል?

4 ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ ከፈለግን እኛም እንደ ኢዮብ ይሖዋ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መመሪያዎች በጥብቅ መከተል አለብን። ኢዮብ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። . . . ልቤ ሌላዋን ሴት ከጅሎ፣ በባልንጀራዬ ደጅ አድብቼ ከሆነ፣ ሚስቴ የሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤ ሌሎች ሰዎችም ይተኟት።”—ኢዮብ 31:1, 9, 10

5 ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ስለነበር ሴትን በፍትወት ዓይን ከመመልከት ተቆጥቧል። ኢዮብ ባለትዳር እንደመሆኑ መጠን ያላገቡ ሴቶችን አሽኮርምሞም ሆነ የሌላ ሰው ሚስትን በፍቅር ስሜት ቀርቦ አያውቅም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ የፆታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፤ በእርግጥም ይህ ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ የሚፈልጉ ሰዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ማሳሰቢያ ነው።—ማቴዎስ 5:27, 28ን አንብብ።

ፈጽሞ ተንኮለኞች አትሁኑ

6, 7. (ሀ) ከኢዮብ ሁኔታ መመልከት እንደምንችለው አምላክ ንጹሕ አቋማችንን ለመለካት ምንን ይጠቀማል? (ለ) ተንኮለኞች ወይም አታላዮች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?

6 ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ የምንፈልግ ከሆነ ተንኮለኞች መሆን አይኖርብንም። (ምሳሌ 3:31-33ን አንብብ። *) ኢዮብ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ከሚዋሹ ሰዎች ጋር ሄጄ ከሆነ፣ እግሬም ለማታለል ተጣድፎ እንደሆነ፣ [ይሖዋ] በትክክለኛ ሚዛን ይመዝነኛል፤ አምላክ ንጹሕ አቋም እንዳለኝ ያውቃል።” (ኢዮብ 31:5, 6 NW) ይሖዋ ሁሉንም ሰው “በትክክለኛ ሚዛን” ይመዝናል። ከኢዮብ ሁኔታ መመልከት እንደምንችለው አምላክ ንጹሕ አቋማችንን ለመለካት ፍጹም መመዘኛ የሆነውን ፍትሑን ይጠቀማል።

7 ተንኮለኞች ወይም አታላዮች ከሆንን ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እየተመላለስን ነው ማለት አይቻልም። ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች “አሳፋሪ የሆኑትን ስውር ነገሮች” ትተዋል፤ እንዲሁም ‘በተንኮል አይመላለሱም።’ (2 ቆሮ. 4:1, 2) ሆኖም ተንኮል የተሞላበት ነገር በመናገራችን ወይም በማድረጋችን ምክንያት አንድ የእምነት ባልንጀራችን ለእርዳታ ወደ አምላክ ቢጮህስ? እንዲህ ማድረጋችን የሚበጀን አይደለም! መዝሙራዊው “በተጨነቅሁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ተጣራሁ፤ እርሱም መለሰልኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሐሰተኛ ከንፈር፣ ከአታላይ ምላስም አድነኝ” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 120:1, 2) አምላክ በእርግጥ በንጹሕ አቋም እየተመላለስን እንደሆነ ለማወቅ ውስጣዊ ማንነታችንን ሊመለከት ማለትም ‘ልባችንንና ኵላሊታችንን ሊመረምር’ እንደሚችል ማስታወሳችን ተገቢ ነው።—መዝ. 7:8, 9

ከሌሎች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምሳሌ ሁኑ

8. ኢዮብ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ምን ዓይነት ሰው ነበር?

8 ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመመላለስ ፍትሐዊ፣ ትሑትና ለሌሎች አሳቢ እንደነበረው እንደ ኢዮብ መሆን አለብን። እንዲህ ብሏል፦ “ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ፣ ፍርድ አዛብቼ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ? እኔን በማሕፀን ውስጥ የፈጠረኝ እነርሱን የፈጠረ አይደለምን? በሆድ ውስጥ የሠራንስ እርሱ ራሱ አይደለምን?”—ኢዮብ 31:13-15

9. ኢዮብ ከአገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነት የትኞቹን ባሕርያት አንጸባርቋል? እኛስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 በኢዮብ ዘመን የሕግ ጉዳዮችን ለማስፈጸም የተወሳሰበ የአሠራር ሂደት መከተል አያስፈልግም ነበር። የፍርድ ጉዳዮች ሥርዓት ባለው መንገድ እልባት የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ ባሪያዎችም እንኳ ሳይቀሩ አቤቱታቸውን የሚያሰሙባቸው ሸንጎዎች ነበሩ። ኢዮብ ከአገልጋዮቹ ጋር ባለው ግንኙነት ፍትሕንና ምሕረትን ያንጸባርቅ ነበር። እኛም፣ በተለይ ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆነን የምናገለግል ወንድሞች በንጹሕ አቋም መመላለስ ከፈለግን እንደነዚህ ያሉትን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይገባናል።

ለጋስ ሁኑ እንጂ አትጎምጁ

10, 11. (ሀ) ኢዮብ ለጋስና ሰዎችን የሚረዳ ሰው እንደነበር እንዴት እናውቃለን? (ለ) ኢዮብ 31:16-25 ከጊዜ በኋላ የተጻፉትን የትኞቹን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ያስታውሰናል?

10 ኢዮብ ለጋስና ሌሎችን የሚረዳ ሰው ነበር እንጂ ራስ ወዳድና የመጎምጀት አባዜ የተጠናወተው ሰው አልነበረም። እንዲህ ብሏል፦ “የመበለቲቱን ዐይን አፍዝዤ ከሆነ፣ እንጀራዬን ከድኻ አደጉ ጋር ሳልካፈል፣ ለብቻዬ በልቼ ከሆነ፣ . . . በልብስ ዕጦት ሰው ሲጠፋ [አይቼ ከሆነ፣] . . . በአደባባይ ተሰሚነት አለኝ ብዬ፣ በድኻ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ ከሆነ፣ ትከሻዬ ከመጋጠሚያው ይነቀል፤ ክንዴም ከመታጠፊያው ይሰበር።” ኢዮብ ወርቅን “አንተ መታመኛዬ ነህ” ብሎ ቢሆን ኖሮ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል ሊባል አይችልም ነበር።—ኢዮብ 31:16-25

11 ኢዮብ በግጥም መልክ የተናገረው ይህ ሐሳብ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደሚከተለው በማለት የጻፈውን ሐሳብ ያስታውሰናል፦ “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ‘ወላጅ የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።” (ያዕ. 1:27) በተጨማሪም ኢየሱስ “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ ስላልሆነ ተጠንቀቁ፤ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እናስታውስ ይሆናል። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ስለ አንድ ባለጠጋ ሰው ምሳሌ ነገራቸው፤ የመጎምጀት አባዜ የተጠናወተው ይህ ሰው በሞተበት ወቅት ‘በአምላክ ዘንድ ሀብታም አልነበረም።’ (ሉቃስ 12:15-21) ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ የምንፈልግ ከሆነ እንደ ኃጢአት የሚታየው የመጎምጀት ወይም የመስገብገብ ባሕርይ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ ይኖርብናል። መጎምጀት የጣዖት አምልኮ ነው፤ ምክንያቱም ስግብግብ የሆነ ሰው የጎመጀለትን ነገር ከይሖዋ አስበልጦ ስለሚመለከተው ያ ነገር እንደ ጣዖት ይሆንበታል። (ቆላ. 3:5) ንጹሕ አቋምና ስግብግብነት አብረው የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም!

እውነተኛውን አምልኮ አጥብቃችሁ ያዙ

12, 13. ኢዮብ ከጣዖት አምልኮ በመራቅ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

12 በንጹሕ አቋም የሚመላለሱ ሰዎች ከእውነተኛው አምልኮ አይወጡም። ኢዮብ እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ እሱም ከእውነተኛው አምልኮ እንዳልወጣ ያሳያል፦ “የፀሓይን ድምቀት አይቼ፣ ወይም የጨረቃን አካሄድ ግርማ ተመልክቼ፣ ልቤ በስውር ተታልሎ፣ ስለ ክብራቸው አፌ እጄን ስሞ ከሆነ፣ ለልዑል እግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኔ ነውና፣ ይህም ደግሞ የሚያስቀጣኝ በደል በሆነ ነበር።”—ኢዮብ 31:26-28

13 ኢዮብ ግዑዝ ነገሮችን አላመለከም። ኢዮብ እንደ ጨረቃ ያሉ የሰማይ አካላትን ሲመለከት ልቡ ሸፍቶ ቢሆን ኖሮ እንዲሁም ‘በአፉ እጁን ስሞ’ በሌላ አባባል የጣዖት አምላኪዎች እንደሚያደርጉት እጁን ከሳመ በኋላ ወደ ሰማይ ዘርግቶ ቢሆን ኖሮ ይሖዋን የካደ ጣዖት አምላኪ ይሆን ነበር። (ዘዳ. 4:15, 19) እኛም ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ እንድንችል ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ መራቅ ይኖርብናል።—1 ዮሐንስ 5:21ን አንብብ።

አትበቀሉ፤ ግብዞችም አትሁኑ

14. ኢዮብ ክፉ ሰው አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

14 ኢዮብ ክፉም ሆነ ጨካኝ ሰው አልነበረም። ኢዮብ እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ በንጹሕ አቋም ከሚመላለስ ሰው የሚጠበቅ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር፤ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ፣ በደረሰበትም መከራ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፣ እኔ ግን በነፍሱ ላይ ክፉ እንዲመጣ በመራገም፣ አንደበቴን ለኀጢአት ከቶ አሳልፌ አልሰጠሁም።”—ኢዮብ 31:29, 30

15. የሚጠላን ሰው መከራ ሲደርስበት መደሰታችን ተገቢ የማይሆነው ለምንድን ነው?

15 ቅን የነበረው ኢዮብ በሚጠሉት ሰዎች ላይ መከራ ቢደርስ የሚደሰት ሰው አልነበረም። ከጊዜ በኋላ የተጻፈ አንድ ምሳሌ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “ጠላትህ ሲወድቅ ደስ አይበልህ፤ ሲሰናከልም ልብህ ሐሤት አያድርግ፤ አለዚያ እግዚአብሔር ይህን አይቶ ደስ አይለውም፤ ቍጣውንም ከእርሱ ይመልሳል።” (ምሳሌ 24:17, 18) ይሖዋ ልብን ማንበብ የሚችል እንደመሆኑ መጠን ሌላ ሰው መከራ ሲደርስበት በልባችን መደሰት አለመደሰታችንን ያውቃል፤ በመሆኑም በሰዎች መከራ መደሰታችን ይሖዋን እንደማያስደስተው የታወቀ ነው። (ምሳሌ 17:5) አምላክ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” በማለት ስለተናገረ እንዲህ ካደረግን እርምጃ ይወስድብናል።—ዘዳ. 32:35

16. ሀብታሞች ባንሆንም እንኳ እንግዳ ተቀባይ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

16 ኢዮብ እንግዳ ተቀባይ ነበር። (ኢዮብ 31:31, 32) እኛም ሀብታሞች ባንሆንም እንኳ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ማዳበር እንችላለን። (ሮም 12:13) “ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል” የሚለውን ጥቅስ በማስታወስ ያለችንን ትንሽ ነገር ከሌሎች ጋር መካፈል እንችላለን። (ምሳሌ 15:17) ንጹሕ አቋሙን ከሚጠብቅ የእምነት ባልንጀራችን ጋር ፍቅር በሰፈነበት ሁኔታ ያለችውን እንኳ ተካፍለን መመገባችን ደስታ እንደሚያስገኝልን ብሎም በመንፈሳዊ እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።

17. የሠራነውን ከባድ ኃጢአት ለመደበቅ መሞከር የሌለብን ለምንድን ነው?

17 ኢዮብ ግብዝ ሰው ስላልነበር በእንግድነት የሚቀበላቸው ሰዎች በመንፈሳዊ ታንጸው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ኢዮብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደ ጉባኤ ሰርገው እንደገቡትና “ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን [እንደሚክቡት]” ሰዎች አልነበረም። (ይሁዳ 3, 4, 16) ከዚህም በላይ ሌሎች እንዳይንቁት በመፍራት በደሉን ለመሰወር አልሞከረም ወይም ‘ኀጢአቱን አልሸሸገም።’ ኃጢአት ሠርቶ እንኳ ቢሆን በደሉን የሚናዘዝለት አምላክ እንዲመረምረው ፈቃደኛ ነበር። (ኢዮብ 31:33-37) እኛም ከባድ ኃጢአት ሠርተን ከሆነ የሌሎችን አክብሮት ላለማጣት ስንል ኃጢአታችንን ለመደበቅ መሞከር የለብንም። ታዲያ በንጹሕ አቋም ለመመላለስ ጥረት እያደረግን መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ስህተታችንን አምነን በመቀበል፣ ንስሐ በመግባት፣ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት በመጣጣርና አስፈላጊውን ማካካሻ በማድረግ ነው።—ምሳሌ 28:13፤ ያዕ. 5:13-15

ንጹሕ አቋሙን መጠበቁን ለማረጋገጥ በችሎት ፊት ቀረበ

18, 19. (ሀ) ኢዮብ ማንንም ሰው ፈጽሞ አልበዘበዘም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢዮብ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ ምን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር?

18 ኢዮብ ሐቀኛ የነበረ ከመሆኑም በላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም ነበር። በመሆኑም እንዲህ ብሎ መናገር ችሏል፦ “ዕርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ ከሆነ፣ ትልሞቿ ሁሉ በእንባ ርሰው እንደ ሆነ፣ ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፣ የባለመሬቶቿን ነፍስ አሳዝኜ ከሆነ፣ በስንዴ ፈንታ እሾህ፣ በገብስም ምትክ ዐረም ይብቀልብኝ።” (ኢዮብ 31:38-40) ኢዮብ የሌሎችን መሬት ነጥቆ አልወሰደም፤ ወይም ሠራተኞችን አልበዘበዘም። እኛም እንደ ኢዮብ በትላልቅም ሆነ በትናንሽ ጉዳዮች በንጹሕ አቋም መመላለስ ያስፈልገናል።

19 ኢዮብ በሦስት ጓደኞቹ አልፎ ተርፎም ወጣት በነበረው በኤሊሁ ፊት ሕይወቱን ስለመራበት መንገድ ተናግሯል። ኢዮብ ‘በፊርማው’ ሊያረጋግጠው የሚችለውን ሕይወቱን በተመለከተ ተቃውሞ ያለው ሰው ካለ ክስ እንዲመሠርት ግብዣ አቅርቧል። ኢዮብ በደለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከቀረበበት ቅጣቱ የሚያስከትልበትን ሥቃይ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። በመሆኑም ጉዳዩን ለመለኮታዊው ፍርድ ቤት አቅርቦ የሚሰጠውን ብይን ተጠባብቋል። በዚህ ሁኔታ “የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።”—ኢዮብ 31:35, 40

ንጹሕ አቋምህን መጠበቅ ትችላለህ

20, 21. (ሀ) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለስ የቻለው እንዴት ነው? (ለ) ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

20 ኢዮብ ለአምላክ ፍቅር ነበረው፤ ይሖዋም እሱን ይወደውና ይረዳው ነበር። ይህ ደግሞ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለስ እንዲችል ረድቶታል። ኢዮብ “ሕይወትን ሰጠኸኝ፤ በጎነትንም [“ፍቅራዊ ደግነትንም፣” NW] አሳየኸኝ፤ እንክብካቤህም መንፈሴን ጠበቀ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 10:12) በተጨማሪም ኢዮብ ለሌሎች ፍቅር ያሳይ ነበር፤ ምክንያቱም ለወዳጆቹ “ፍቅራዊ ደግነት” ወይም ጽኑ ፍቅር የማያሳይ ሰው ሁሉን ለሚችለው አምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ከሌላቸው ሰዎች እንደሚፈረጅ ተገንዝቦ ነበር። (ኢዮብ 6:14 NW) ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች አምላክንም ሆነ ሰዎችን ይወዳሉ።—ማቴ. 22:37-40

21 የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብና ቃሉ ስለ ይሖዋ በሚናገረው ነገር ላይ በማሰላሰል ለእሱ ያለንን ፍቅር ማዳበር እንችላለን። ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ይሖዋን ልናወድሰው ብሎም ስላደረገልን በጎ ነገር ልናመሰግነው እንችላለን። (ፊልጵ. 4:6, 7) ለይሖዋ መዘመር እንችላለን፤ እንዲሁም ከሕዝቡ ጋር አዘውትረን በመሰብሰብ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ዕብ. 10:23-25) ከዚህም በላይ በአገልግሎት በመካፈል አምላክ ስለሚያስገኘው ‘ማዳን’ የሚናገረውን ምሥራች ስናውጅ ለእሱ ያለን ፍቅር ይጨምራል። (መዝ. 96:1-3) ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ካደረግን “እኔ በበኩሌ ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል። . . . ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት እንደ ዘመረው መዝሙራዊ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ እንችላለን።—መዝ. 73:28 NW

22, 23. የይሖዋን ሉዓላዊነት የምንደግፍ እንደመሆናችን መጠን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችን በጥንት ዘመን የነበሩ ንጹሕ አቋማቸውን የጠበቁ ሰዎች ካከናወኑት ሥራ ጋር ሲነጻጸር ምን ይመስላል?

22 ባለፉት ዘመናት ይሖዋ የጽድቅ አቋማቸውን ለጠበቁ ሰዎች የተለያየ ተልእኮ ሰጥቷቸው ነበር። ኖኅ መርከብ የገነባ ሲሆን ‘የጽድቅ ሰባኪም’ ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) ኢያሱ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ አድርጓል፤ በዚህ ረገድ ሊሳካለት የቻለው ግን ‘የሕጉን መጽሐፍ ቀንም ሆነ ሌት’ በማንበቡና ያነበበውን ተግባራዊ በማድረጉ ነው። (ኢያሱ 1:7, 8) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይካፈሉ የነበረ ከመሆኑም በላይ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት ዘወትር ይሰበሰቡ ነበር።—ማቴ. 28:19, 20

23 እኛም ጽድቅን በመስበክ፣ ደቀ መዛሙርት በማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል እንዲሁም በጉባኤ፣ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በመሰብሰብ የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍና ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ እንችላለን። እንዲህ ያሉት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ደፋሮችና በመንፈሳዊ ጠንካሮች አልፎ ተርፎም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ረገድ ስኬታማ እንድንሆን ይረዱናል። በሰማይ የሚኖረው አባታችንና ልጁ ስለሚደግፉን የአምላክን ፈቃድ ማድረግም ሆነ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ አስቸጋሪ አይሆንብንም። (ዘዳ. 30:11-14፤ 1 ነገ. 8:57) በተጨማሪም በንጹሕ አቋም የሚመላለሱና ይሖዋን ሉዓላዊ ጌታቸው አድርገው የሚያከብሩ ‘በመላው የወንድማማች ማኅበር’ ውስጥ የታቀፉ ወንድሞቻችን ድጋፍ አይለየንም።—1 ጴጥ. 2:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ምሳሌ 3:32 (NW)፦ “ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፣ ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።”

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

የይሖዋን የሥነ ምግባር መመሪያዎች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

ከኢዮብ ባሕርያት በተለይ አንተን የሚማርክህ የትኛው ነው?

በ⁠ኢዮብ 31:29-37 ላይ እንደተገለጸው ኢዮብ ሕይወቱን የመራው እንዴት ነበር?

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል፤ እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን!

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መመላለስ እንችላለን!