በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሲሑን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?

መሲሑን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?

መሲሑን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሕዝቡ እሱ በተናገራቸው ነገሮች ተገርመው እንዲሁም በፈጸማቸው ተአምራት ተደንቀው ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙዎች ‘በእሱ ያመኑ’ ከመሆኑም በላይ ትንቢት የተነገረለት መሲሕ ወይም ክርስቶስ መሆኑን አምነው ተቀብለው ነበር። ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ ያመኑበትን ምክንያት ሲገልጹ “ክርስቶስስ በሚመጣበት ጊዜ ከዚህ ሰው የበለጠ ብዙ ምልክቶች ያደርጋል እንዴ?” ብለዋል።—ዮሐንስ 7:31

ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም እንኳ እሱን ካዩትና የተናገረውን ከሰሙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ አማኞች አልሆኑም። የሚያሳዝነው፣ መጀመሪያ ላይ በእሱ አምነው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ከጊዜ በኋላ እሱን መከተል አቁመዋል። አሳማኝ ማስረጃዎች ቢኖሩም ብዙ ሰዎች የኢየሱስን መሲሕነት ያልተቀበሉት ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረጉበትን ምክንያት እስቲ እንመርምር፤ አንተም ‘በዛሬው ጊዜ እኔም ተመሳሳይ ስህተት ልፈጽም እችል ይሆን?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

ተስፋ ያደረጉት ነገር አለመፈጸሙ

ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት ብዙ አይሁዳውያን የመሲሑን መምጣት እየተጠባበቁ ነበር። ኢየሱስ በሕፃንነቱ ወደ ቤተ መቅደስ በተወሰደበት ጊዜ ተስፋ በተደረገበት መሲሕ አማካኝነት የሚገኘውን “የኢየሩሳሌምን መዳን [የሚጠባበቁ]” ሰዎች አግኝተውት ነበር። (ሉቃስ 2:38) ከጊዜ በኋላም መጥምቁ ዮሐንስ ያከናወናቸውን ሥራዎች የተመለከቱ በርካታ ሰዎች “ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን?” ብለው አስበው ነበር። (ሉቃስ 3:15) ይሁንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዶች መሲሑ ምን እንዲያደርግላቸው ጠብቀው ነበር?

በዚያ ዘመን የነበሩ አብዛኞቹ አይሁዳውያን መሲሑ መጥቶ ከሮማውያን የጭቆና ቀንበር ነፃ እንደሚያወጣቸው፣ በኋላም ንጉሣዊ አገዛዝ በእስራኤል እንደሚመሠርት ያምኑ ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ተደማጭነት ያላቸው በርካታ መሪዎች ተነስተው የነበረ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ አገዛዝ ላይ እንዲያምፅ ይቀሰቅሱ ነበር። እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ነገር፣ ሕዝቡ መሲሑ ያከናውናል ብለው በሚጠብቁት ነገር ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስ እንዲህ ካሉ የሐሰት መሲሖች ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኢየሱስ ሕዝቡ እንዲያምፅ ከመቀስቀስ ይልቅ አድማጮቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱና ለባለሥልጣናት እንዲገዙ አስተምሯል። (ማቴዎስ 5:41-44) ሕዝቡ እሱን ለማንገሥ ያደረጉትን ጥረት አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ የእሱ መንግሥት ‘የዚህ ዓለም ክፍል እንዳልሆነ’ አስተምሯል። (ዮሐንስ 6:15፤ 18:36) ያም ሆኖ ሕዝቡ መሲሑን በተመለከተ ቀደም ሲል የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት በአስተሳሰባቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ተአምራዊ ማስረጃዎችን አይቷል እንዲሁም ሰምቷል። ሆኖም በወኅኒ ቤት ሳለ “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው ኢየሱስን እንዲጠይቁት ደቀ መዛሙርቱን ልኳቸው ነበር። (ማቴዎስ 11:3) ምናልባትም ዮሐንስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው አይሁዳውያን ተስፋ እንደሚያደርጉት በእርግጥ ኢየሱስ እስራኤልን ነፃ የሚያወጣው መሲሕ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሊሆን ይችላል።

የኢየሱስ ሐዋርያትም ኢየሱስ እንደሚገደልና በኋላም ትንሣኤ እንደሚያገኝ ሲሰሙ ለመቀበል ከብዷቸው ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ መሲሑ መከራ መቀበል ብሎም መሞት እንዳለበት ሲናገር ጴጥሮስ “ለብቻው ገለል አድርጎ ይገሥጸው ጀመር።” (ማርቆስ 8:31, 32) ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከሞተ መሲሕ ሆኖ የሚጫወተውን ሚና እንዴት ሊፈጽም እንደሚችል መረዳት አልቻለም ነበር።

በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የፋሲካ በዓል ትንሽ ቀደም ብሎ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ወቅት በደስታ የፈነደቀው ሕዝብ ንጉሣዊ አቀባበል አድርጎለት ነበር። (ዮሐንስ 12:12, 13) ይሁንና ሁኔታው በቅጽበት ተለወጠ! ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ተይዞ ተገደለ። ከሞተ በኋላም ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱ “እኛ ግን ይህ ሰው እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” በማለት በሐዘን ተናግረዋል። (ሉቃስ 24:21) ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠ ጊዜም እንኳ ደቀ መዛሙርቱ መሲሑ በእስራኤል ምድራዊ መንግሥት ያቋቁማል ከሚለው አመለካከታቸው ገና አልተላቀቁም ነበር። “ጌታ ሆይ፣ ለእስራኤል መንግሥትን መልሰህ የምታቋቁመው በዚህ ጊዜ ነው?” በማለት የጠየቁት ለዚህ ነበር። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የኢየሱስ አድማጮች መሲሑ ስለሚፈጽማቸው ነገሮች የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት በልባቸውና በአእምሯቸው ውስጥ ሥር ሰዶ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 1:6

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገና በተከታዮቹ ላይ መንፈስ ቅዱስን ካፈሰሰ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ፣ መሲሑ በሰማይ ሆኖ እንደሚገዛ በግልጽ መረዳት ችለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4, 32-36) ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ በድፍረት የሰበኩ ሲሆን ተአምራት በመፈጸም የአምላክ ድጋፍ እንዳላቸው አረጋግጠዋል። (የሐዋርያት ሥራ 3:1-9, 13-15) በዚህ የተነሳ በኢየሩሳሌም የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት አማኞች ሆኑ። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ አይሁዳውያን ባለ ሥልጣናትን አላስደሰታቸውም። እነዚህ ባለ ሥልጣናት ኢየሱስን እንደተቃወሙት ሁሉ ሐዋርያቱንና ደቀ መዛሙርቱን ተቃወሙ። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን አምርረው የተቃወሙት ለምን ነበር?

የሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞ

ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብና ተግባር በመንፈስ መሪነት የተጻፉ መጻሕፍት ከሚያስተምሩት ትምህርት በጣም ርቆ ነበር። በዚያ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ማለትም ሰዱቃውያን፣ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ሰብዓዊ ወጎችን በጽሑፍ ከሰፈረው የአምላክ ቃል አስበልጠው ይመለከቱ ነበር። ኢየሱስ በሰንበት ተአምራዊ ፈውስ በመፈጸሙ ምክንያት ሕጉን ጥሷል በማለት በተደጋጋሚ ጊዜ ከሰውት ነበር። ኢየሱስ ትምህርታቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆነ በድፍረት በመናገር ሥልጣናቸውን የተገዳደረ ከመሆኑም በላይ እነሱ እንደሚሉት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው አጋልጧል። ኢየሱስ የተወለደው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ባለው ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን በወቅቱ የሚሰጠውን መደበኛ ሃይማኖታዊ ትምህርትም አልተከታተለም። እነዚህ ኩሩ የሃይማኖት መሪዎች ኢየሱስን መሲሕ አድርገው መቀበል ቢከብዳቸው ምንም አያስደንቅም! እነዚህ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር የገጠሙት እንዲህ ያለው ፍጥጫ በጣም ስላናደዳቸው “እሱን እንዴት ሊያጠፉት እንደሚችሉ ተማከሩ።”—ማቴዎስ 12:1-8, 14፤ 15:1-9

ይሁንና የሃይማኖት መሪዎቹ የኢየሱስን ተአምራት የማድረግ ችሎታ በተመለከተ ምን ይሉ ነበር? ኢየሱስ ተአምራት መፈጸሙን አልካዱም። ሆኖም “ይህ ሰው በአጋንንት አለቃ በብዔልዜቡል ካልሆነ በስተቀር አጋንንትን ሊያስወጣ አይችልም” በማለት ኃይሉን ያገኘው ከሰይጣን እንደሆነ ተናግረዋል፤ በዚህ መንገድ ስሙን በማጥፋት ሰዎች በኢየሱስ እንዳያምኑ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።—ማቴዎስ 12:24

የሃይማኖት መሪዎቹ የኢየሱስን መሲሕነት ላለመቀበል ግትር የሆነ አቋም እንዲይዙ ያደረጋቸው ሌላም ምክንያት ነበር። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ካስነሳው በኋላ የተለያዩ ሃይማኖታዊ አንጃ መሪዎች አንድ ላይ ተሰብስበው እንዲህ በማለት ተመካከሩ፦ “ይህ ሰው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች እያደረገ ስለሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።” የሃይማኖት መሪዎቹ ሥልጣናችንን እናጣለን የሚል ስጋት ስላደረባቸው ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል አሴሩ።—ዮሐንስ 11:45-53፤ 12:9-11

ጭፍን ጥላቻና ስደት

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አስተሳሰብ ማኅበረሰቡ ኢየሱስን መሲሕ አድርጎ የሚቀበልን ሰው እንደጠላት እንዲመለከት አድርጓል። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ባላቸው ከፍ ያለ ቦታ ይኩራሩ ስለነበር “ከገዥዎች ወይም ከፈሪሳውያን መካከል በእሱ ያመነ አንድም የለም፤ አለ እንዴ?” ብለው በመናገር በኢየሱስ የሚያምንን ሰው ያጥላሉ ነበር። (ዮሐንስ 7:13, 48) እንደ ኒቆዲሞስና የአርማትያሱ ዮሴፍ ያሉ አንዳንድ የአይሁድ መሪዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር፤ ይሁን እንጂ ፍርሃት ስላደረባቸው በኢየሱስ ማመናቸውን በይፋ አልተናገሩም ነበር። (ዮሐንስ 3:1, 2፤ 12:42፤ 19:38, 39) የአይሁድ መሪዎች “ኢየሱስን ክርስቶስ ነው ብሎ የመሠከረ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲገለል” ደንግገው ነበር። (ዮሐንስ 9:22) በኢየሱስ መሲሕነት የሚያምን ሰው ይፌዝበትና ከማኅበረሰቡ ይገለል ነበር።

በኢየሱስ ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት ላይ ይደርስ የነበረው ተቃውሞ ተባብሶ ወደ ስደት ተለወጠ። ሐዋርያት በድፍረት በመስበካቸው ምክንያት ሳንሄድሪን በተባለው የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንግልት ይደርስባቸው ጀመር። (የሐዋርያት ሥራ 5:40) ተቃዋሚዎች በደቀ መዝሙሩ በእስጢፋኖስ ላይ አምላክን ተሳድቧል የሚል የሐሰት ክስ አቅርበው ነበር። በዚህም ምክንያት በሳንሄድሪን ተፈርዶበት በድንጋይ ተወግሮ ሞተ። ከዚያም “በኢየሩሳሌም በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከባድ ስደት ተነሳ፤ ከሐዋርያትም በስተቀር ሁሉም በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።” (የሐዋርያት ሥራ 6:8-14፤ ከሥራ 7:54 እስከ 8:1) ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው ሳኦል፣ “ሊቀ ካህናቱም ሆነ መላው የሽማግሌዎች ጉባኤ” በሚደግፉት ክርስቲያኖችን የማሳደድ ዘመቻ ተካፍሏል።—የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2፤ 22:4, 5

ከኢየሱስ ሞት በኋላ በነበሩት ዓመታት እንዲህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የክርስትና እምነት በከፍተኛ ፍጥነት ተስፋፍቶ ነበር። በወቅቱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አማኞች ቢሆኑም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፓለስቲና ምድር ከነበረው ሕዝብ ብዛት አንጻር የክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት ነበር። የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ብሎ በይፋ መናገር መገለልን አልፎ ተርፎም የዓመፅ ድርጊት ሰለባ መሆንን ያስከትል ነበር።

ኢየሱስን ያልተቀበሉ ሰዎች ከፈጸሙት ስህተት መማር

እስካሁን እንዳየነው የተሳሳተ አመለካከት፣ ኅብረተሰቡ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እና ስደት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ሰዎች በኢየሱስ እንዳያምኑ እንቅፋት ሆነውባቸዋል። በዛሬው ጊዜም ስለ ኢየሱስና እሱ ስላስተማራቸው ነገሮች የተሳሳተ አመለካከት መስፋፋቱ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች የአምላክ መንግሥት በልባቸው ውስጥ እንደሆነ ወይም መንግሥቱ ሰዎች በሚያደርጉት ጥረት እንደሚመጣ ተምረዋል። ሌሎች ደግሞ የሰው ልጆችን ችግሮች የሚፈታው ሳይንስ ወይም ቴክኖሎጂ እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል፤ ይህ ደግሞ በመሲሑ የማመን አስፈላጊነት እንዳይታያቸው አድርጓል። በዘመናችን የሚገኙ በርካታ ተቺዎች ከኢየሱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ስለተፈጸሙት ክስተቶች የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ትክክለኛ ታሪኮች እንዳልሆኑ ይናገራሉ፤ ይህ ሁኔታ ሰዎች የኢየሱስን መሲሕነት አምነው እንዳይቀበሉ አድርጓል።

እንዲህ ያሉት አመለካከቶችና ንድፈ ሐሳቦች ብዙዎች ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ ስለሚጫወተው ሚና ግራ እንዲጋቡ ወይም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው አድርገዋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ለመመርመር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው የበለጠ ማስረጃ ማግኘት ይችላሉ። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ መሲሑ ምን እንደሚያደርግ የሚተነብዩ በርካታ ትንቢቶችን የያዙ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትንና ኢየሱስ እነዚህን ትንቢቶች ለመፈጸም ምን እንዳደረገ የሚገልጹ አራት የመጽሐፍ ቅዱስ ወንጌሎችን ማግኘት እንችላለን። *

በእርግጥም እያንዳንዳችን በዚህ ጉዳይ ላይ በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ወይም ውሳኔ እንድናደርግ የሚያስችሉን በቂ ማስረጃዎች አሉ። ደግሞም ይህን ውሳኔ ማድረጋችን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ለምን? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት መሲሐዊ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ምድርን የሚያጠፏትን ሁሉ በማጥፋት ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ የሚያስችል የጽድቅ አገዛዝ ለማምጣት በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ ይናገራል። (ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15, 18፤ 21:3-5) አንተም ከአሁኑ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ለመማርና በእሱ ላይ ያለህን እምነት በተግባር ለማሳየት ጥረት የምታደርግ ከሆነ ይህን አስደናቂ ተስፋ ማግኘት ትችላለህ። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ሐሳብ በቁም ነገር ተመልከት፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.22 በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ገጽ 200 ላይ የሚገኘውን “ስለ መሲሑ የተነገሩ ትንቢቶች” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በኢየሱስ ዘመን ኖረህ ቢሆን ኖሮ መሲሕነቱን ትቀበል ነበር?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቀደም ሲል የነበረህ አመለካከት ስለ ኢየሱስ እውነቱን ከመማር እንዲያግድህ አትፍቀድ