በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጃችሁ ምን መልስ ይሰጣል?

ልጃችሁ ምን መልስ ይሰጣል?

ልጃችሁ ምን መልስ ይሰጣል?

ወላጆች፦ በጥር 15, 2010 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 16-20 ላይ በወጣው ርዕስ ላይ ከልጆቻችሁ ጋር የልምምድ ፕሮግራም እንድታደርጉ ሐሳብ አቅርበንላችሁ ነበር። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ ልጃችሁ በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች መቋቋም እንዲችል ለማዘጋጀት የሚረዷችሁ ሐሳቦች ቀርበዋል። የቤተሰብ አምልኮ በምታደርጉበት ምሽት ላይ ከልጃችሁ ጋር ልምምድ ማድረግ ትችሉ ይሆናል።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ብሔራዊ መዝሙር መዘመርን፣ ልደትን ማክበርንና ከበዓላት ጋር የተያያዙ የቤት ሥራዎችን መሥራትን ጨምሮ እነዚህን በመሳሰሉት ነገሮች ለምን እንደማይካፈሉ አብረዋቸው የሚማሩት ልጆች ብዙ ጊዜ ይጠይቋቸዋል። ልጃችሁ እንዲህ ያለ ጥያቄ ቢቀርብለት ምን መልስ ይሰጣል?

ክርስቲያን የሆኑ አንዳንድ ልጆች “አይ፣ እኔ እንዲህ አላደርግም። ሃይማኖቴ አይፈቅድም” የሚል መልስ ይሰጣሉ። እነዚህ ልጆች ጠንካራ አቋም መውሰዳቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። እንዲህ ብለው መመለሳቸው አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች ተጨማሪ ጥያቄዎች እንዳይጠይቋቸው ያደርግ ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ እምነታችንን በተመለከተ ‘ምክንያት እንድናቀርብ ለሚጠይቀን ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች’ እንድንሆን ይመክረናል። (1 ጴጥ. 3:15) ይህም “አይ፣ እኔ እንዲህ አላደርግም” የሚል መልስ ከመስጠት የበለጠ ነገር ማድረግን ይጨምራል። አንዳንዶች በምንሰጣቸው መልስ ባይስማሙም እንኳ እንዲህ ዓይነት አቋም የወሰድንበትን ምክንያት ለማወቅ ይፈልጉ ይሆናል።

በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ከታላቁ አስተማሪ ተማር እንደሚሉት ያሉ ጽሑፎችን በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን አብረዋቸው ለሚማሩ ልጆች ነግረዋቸዋል። እነዚህ ታሪኮች፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ልጆች አንዳንድ ነገሮችን የሚያደርጉበትን ወይም የማያደርጉበትን ምክንያት ለማስረዳት ያስችላሉ። አንዳንድ ተማሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ሲተረኩላቸው በትኩረት ይከታተላሉ፤ በዚህ መንገድ ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። ሌሎች ተማሪዎች ግን አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እስከ መጨረሻው ማዳመጥ ይሰለቻቸው ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ ተማሪዎቹ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መረዳት እንዲችሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሚንሂ የተባለችን የ11 ዓመት ልጅ አንዲት ጓደኛዋ ልደቷን ስታከብር እንድትገኝ ጋብዛት ነበር፤ ሚንሂ እንዲህ አለቻት፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ልደታችሁን አክብሩ አይልም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ መጥምቁ ዮሐንስ የሚባል ሰው የተገደለው የልደት በዓል ሲከበር ነው።” ይሁንና ሚንሂ፣ የሰጠችው መልስ ለጓደኛዋ ግልጽ እንዳልሆነላት ተሰምቷት ነበር።

አንዳንድ ጊዜ ልጃችሁ፣ በጽሑፎቻችን ውስጥ የሚገኙትን ሥዕሎች ወይም ታሪኮች አብረውት ለሚማሩት ልጆች ማሳየቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ይሁንና የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆች እንዳያሳዩ ቢከለክሉስ? ልጆቻችሁ ጽሑፎችን ሳይጠቀሙ ጥሩ አድርገው መመሥከር ይችሉ ይሆን? ልጆቻችሁ ስለ እምነታቸው ማስረዳት እንዲችሉ እንዴት ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ?

የልምምድ ፕሮግራም ይኑራችሁ

ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በቤት ውስጥ ልምምድ ማድረጋቸው ጠቃሚ ነው፤ በልምምዱ ወቅት ወላጆች፣ ከልጆቻቸው ጋር የሚማሩትን ተማሪዎች ወክለው ሊሠሩ ይችላሉ። ወላጆች፣ ልጆቻቸው እምነታቸውን ለማስረዳት ሲሞክሩ የሚያደርጉትን ጥረት ማድነቅ ይኖርባቸዋል፤ እንዲሁም ስለ እምነታቸው በተሻለ ሁኔታ ማስረዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሊገልጹላቸው ይገባል። ለምሳሌ በእነሱ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች የሚያውቋቸውን ቃላት እንዲጠቀሙ ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። ጆሹዋ የተባለ የዘጠኝ ዓመት ልጅ አብረውት የሚማሩት ልጆች እንደ “ሕሊና” እና “ታማኝነት” የመሳሰሉት ቃላት እንደማይገቧቸው ተናግሯል። ስለሆነም ከእነሱ ጋር ሲወያይ ቀለል ያሉ ቃላትን መጠቀም ነበረበት።—1 ቆሮ. 14:9

አንዳንድ ተማሪዎች ጥያቄ ጠይቀውም እንኳ የሚሰጣቸው መልስ ረዘም ያለ ከሆነ ሊሰለቻቸው ይችላል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወጣቶች፣ አብረዋቸው የሚማሩት ልጆች በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግና አሳማኝ ነጥቦችን በማቅረብ ልጆቹ ውይይቱ እንዳይሰለቻቸው ማድረግ ይችሉ ይሆናል። ሃንዩል የተባለች የአሥር ዓመት ልጅ “አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ስለ አንድ ነገር እኔ ማብራሪያ ከምሰጣቸው ይልቅ ብንወያይበት ደስ ይላቸዋል” ብላለች። ልጆቻችሁ ውይይት ለመጀመር ጥያቄዎችን ማንሳት ይችላሉ፤ ከዚያም አብረዋቸው የሚማሩት ልጆች የሚሰጧቸውን መልስ በትኩረት ያዳምጡ።

ከዚህ በታች በውይይት መልክ የቀረቡት ሐሳቦች፣ ክርስቲያን የሆኑ ልጆች አብረዋቸው ለሚማሩት ተማሪዎች ስለ እምነታቸው እንዴት ማስረዳት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። እነዚህን ሐሳቦች መሸምደድ አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ሁሉም ልጆች አንድ አይደሉም። በተጨማሪም ልጆቻችሁ ለሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያየ መልስ መስጠት ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር ሐሳቡ ሊገባውና በራሱ አባባል እንዴት እንደሚገልጸው ሊለማመድ ይገባል፤ ከዚያም ካጋጠመው ሁኔታ ወይም አብረውት የሚማሩት ልጆች ካነሱት ጥያቄ ጋር በሚስማማ መልኩ መልስ መስጠት ይችላል። ተማሪ የሆኑ ልጆች ካሏችሁ ከታች ባሉት ሐሳቦች በመጠቀም ከልጆቻችሁ ጋር ልምምድ ማድረግ ትችላላችሁ።

ልጆችን ማሠልጠን ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ክርስቲያን የሆኑ ወላጆች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ መቅረጽ እንዲሁም በእነዚህ ሥርዓቶች እንዲመሩ ልጆቻቸውን ማሳመን ይፈልጋሉ።—ዘዳ. 6:7፤ 2 ጢሞ. 3:14

በቀጣዩ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁ ላይ እዚህ ላይ የቀረቡትን ሐሳቦች ከልጆቻችሁ ጋር ተለማመዱ። ይህ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ለምን አትሞክሩትም? ዓላማችሁ ልጆቹ የሚሰጡትን መልስ ወይም እያንዳንዱን ቃል እንዲሸመድዱት ማድረግ እንዳልሆነ አስታውሱ። እንዲያውም አንድን ሁኔታ እንደ ምሳሌ በማንሳት ልጆቻችሁ ከዚያ ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ሊሰጡ የሚችሏቸውን የተለያዩ መልሶች ተለማመዱ፤ በዚህ ወቅት ልጆቻችሁ መልስ የሚሰጡበትን መንገድ ለማስተዋል ሞክሩ። በአንድ ነገር የሚያምኑት ለምን እንደሆነ ሲያስረዱ ምክንያታዊና ዘዴኞች እንዲሆኑ አሠልጥኗቸው። በዚህ መንገድ ልጆቻችሁ አብረዋቸው ለሚማሩት ልጆችም ሆነ ለጎረቤቶቻቸውና ለአስተማሪዎቻቸው ስለ እምነታቸው ማስረዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ቀስ በቀስ ልታዘጋጇቸው ትችላላችሁ።

[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልደትን ማክበር

ሚርያም፦ ዮኒ፣ ለልደቴ ትመጣለህ አይደል?

ዮናታን፦ ስለጋበዝሽኝ አመሰግናለሁ፤ እኔ ግን የልደት በዓል አላከብርም።

ሚርያም፦ እንዴ ለምን?

ዮናታን፦ የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮች የምናምነው በመጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሙሴ፣ ዳዊት ወይም ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ልደታቸውን እንዳከበሩ አይናገርም።

ሚርያም፦ ይገርማል። ታዲያ ወላጆችህ ጨርሶ ስጦታ አይሰጡህም ማለት ነው?

ዮናታን፦ አይ፣ ይሰጡኛል። ይህን ለማድረግ ግን የግድ የልደት ቀኔን አይጠብቁም። በማንኛውም ጊዜ ስጦታ ይሰጡኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ሰዎች በልደታቸው ቀን ስጦታ መቀበል የሚያስደስታቸው ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ ይናገራል። በልደታችን ቀን ስለ ራሳችን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ሕይወት የሰጠንን አምላክ ማመስገን እንዲሁም ስለ ሌሎች ማሰብና ለእነሱ ጥሩ ማድረግ የተሻለ አይመስልሽም?

ሚርያም፦ እኔ እንጃ፣ እንደዚህ እንኳ አስቤ አላውቅም። ግን እኮ እኔ የጠራሁህ ግብዣው ላይ እንድትገኝ ነው። ታዲያ ይሄ ምን ችግር አለው?

ዮናታን፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልደታቸውን እንዳከበሩ የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች ብቻ ሲሆኑ እነሱም ጣዖት አምላኪዎች ናቸው።

ሚርያም፦ ኧረ?

ዮናታን፦ አዎ፣ እንደውም ከፈለግሽ ታሪካቸውን ነገ እነግርሻለሁ።

ብሔራዊ መዝሙር

አቢጋኤል፦ እኔ የምልሽ ኬብሮን፣ ብሔራዊ መዝሙር የማትዘምሪው ለምንድን ነው?

ኬብሮን፦ የማልዘምርበትን ምክንያት እነግርሻለሁ። ከዚያ በፊት ግን እስቲ አንድ ነገር ልጠይቅሽ፦ አንቺ ራስሽ የምትዘምሪው ለምንድን ነው?

አቢጋኤል፦ አገሬን በጣም ስለምወድ ነዋ!

ኬብሮን፦ እኔም እዚህ አገር በመኖሬ ደስተኛ ነኝ። ሆኖም ምንጊዜም ቢሆን ነገሮችን አምላክ በሚያይበት መንገድ ለማየት እጥራለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ እንደማያዳላ ይናገራል። አምላክ፣ የየትኛውም አገር ዜጋ ቢሆኑ ሁሉንም ሰዎች ይወዳል። አንዱን አገር ከሌላው አስበልጦ ማየት በእሱ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። ብሔራዊ መዝሙር የማልዘምረው ለዚህ ነው።

አቢጋኤል፦ እኔ ግን ይሄ አክራሪነት ይመስለኛል!

ኬብሮን፦ የሚገርምሽ እንዲህ ዓይነት አቋም ያለኝ እኔ ብቻ አይደለሁም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት አቋም ስለነበራቸው ወጣቶች ይናገራል። እነዚህ ወጣቶች ለአንድ ፖለቲካዊ ምስል እንዲሰግዱ ታዘው ነበር፤ ይህን ባያደርጉ እንደሚገደሉ ቢነገራቸውም ለምስሉ አልሰገዱም።

አቢጋኤል፦ እውነት? ይሄን ሰምቼ አላውቅም።

ኬብሮን፦ ከፈለግሽ ታሪኩን በእረፍት ሰዓት እነግርሻለሁ።

ፖለቲካ

ሚካኤል፦ ቶሚ፣ ለመምረጥ ዕድሜህ ቢደርስ ማንን የምትመርጥ ይመስልሃል?

ቶማስ፦ ማንንም አልመርጥም።

ሚካኤል፦ እንዴ ለምን?

ቶማስ፦ የምፈልገውን አስቀድሜ ስለመረጥኩ ነው።

ሚካኤል፦ ኧረ፣ ዕድሜህ መች ደረሰና?

ቶማስ፦ ይሄኛው ምርጫ ዕድሜ አይገድበውም። እኔም ከሁሉ የተሻለውን መንግሥት መርጫለሁ።

ሚካኤል፦ ታዲያ የትኛውን መንግሥት ነው የመረጥከው?

ቶማስ፦ በኢየሱስ የሚመራውን መንግሥት ነው። ኢየሱስ ከሁሉ የተሻለ መሪ እንደሆነ ይሰማኛል። እንዲህ ያልኩት ለምን እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ?

ሚካኤል፦ አይ፣ እሱ እንኳ ይቅርብኝ።

ቶማስ፦ እሺ፣ ሌላ ጊዜ ማወቅ ከፈለግህ ግን ልነግርህ ፈቃደኛ ነኝ።

[ሥዕል]

“ዮኒ፣ ለልደቴ ትመጣለህ አይደል?”

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ብሔራዊ መዝሙር የማትዘምረው ለምንድን ነው?”