በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ

“አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው።”—ማቴ. 9:37

1. የጥድፊያ ስሜትን እንዴት ትገልጸዋለህ?

በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ቀጠሮ አለህ እንበል። ሰዓት ቢረፍድብህ ምን ታደርጋለህ? የተሳፈርክበትን ታክሲ ሹፌር “በጣም ቸኩያለሁ፤ ትንሽ ፈጠን ማለት ትችላለህ?” ትለው ይሆናል። ወይም ደግሞ ዛሬውኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ አንድ ሰነድ ቢኖር ምን ታደርጋለህ? ሰነዱ ላይ “አስቸኳይ!” ብለህ ትጽፍበታለህ። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ማለቅ ያለበት ሥራ ቢኖርህና ጊዜው ቢሄድብህ በጣም እንደምትጨነቅ ወይም እንደምትረበሽ የታወቀ ነው። ሰውነትህ አድሬናሊን የተባለውን ሆርሞን ስለሚያመነጭ በተቻለህ መጠን በፍጥነት ለመሥራትና አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ትጥራለህ። የጥድፊያ ስሜት የሚባለው ይህ ነው!

2. በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሁሉ ይበልጥ አጣዳፊ የሆነው ሥራ የትኛው ነው?

2 በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበክና ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ከማድረግ የበለጠ አጣዳፊ ሥራ የለም። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን በመጥቀስ ይህ ሥራ “አስቀድሞ” ይኸውም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት መሠራት እንዳለበት ጽፏል። (ማር. 13:10) ይህ መሆኑም ተገቢ ነው። ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው” ብሏል። አዝመራ ወቅቱ ከማለፉ በፊት መሰብሰብ አለበት።—ማቴ. 9:37

3. ብዙዎች አጣዳፊ በሆነው የስብከቱ ሥራ ለመካፈል ሲሉ ምን አድርገዋል?

3 የስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ስለሆነ አቅማችን በፈቀደ መጠን ጊዜያችንን፣ ኃይላችንንና ትኩረታችንን በዚህ ሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ እያደረጉ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። አንዳንዶች አቅኚዎች ወይም ሚስዮናውያን አሊያም ቤቴላውያን ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ አኗኗራቸውን ቀለል አድርገዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው በሥራ የተጠመደ ነው። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ ብዙ መሥዋዕቶችን ከፍለው ይሆናል፤ እንዲሁም በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ያም ሆኖ ይሖዋ በእጅጉ ባርኳቸዋል። እኛም በዚህ እንደሰታለን። (ሉቃስ 18:28-30ን አንብብ።) ሌሎች ደግሞ የሙሉ ጊዜ አዋጅ ነጋሪዎች መሆን ባይችሉም በዚህ ሕይወት አድን ሥራ የቻሉትን ያህል ጊዜ ለማሳለፍ ይጥራሉ፤ ይህ ሥራ ልጆቻችን እንዲድኑ መርዳትንም ይጨምራል።—ዘዳ. 6:6, 7

4. አንዳንዶች የጥድፊያ ስሜታቸውን እንዲያጡ የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?

4 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ብዙውን ጊዜ ሰዎች የጥድፊያ ስሜት የሚታይባቸው አንድ ነገር የጊዜ ገደብ ወይም የሚያበቃበት ጊዜ ሲኖረው ነው። የምንኖረው በመጨረሻው ጊዜ ውስጥ ሲሆን ይህን የሚያረጋግጡ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊና ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ። (ማቴ. 24:3, 33፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) ያም ቢሆን መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚያውቅ ማንም ሰው የለም። ኢየሱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ምን እንደሆነ በገለጸበት ወቅት “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 24:36) በመሆኑም አንዳንዶች በተለይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በጥድፊያ ስሜት ሲያገለግሉ የቆዩ ከሆኑ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይህን ስሜት ይዘው መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። (ምሳሌ 13:12) አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማሃል? ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ እንድናከናውነው ለሚፈልጉት ሥራ የጥድፊያ ስሜት እንዲኖረንና ይህን ስሜት ይዘን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?

ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስን ተመልከቱ

5. ኢየሱስ ከአገልግሎቱ ጋር በተያያዘ የጥድፊያ ስሜት ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

5 ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት የጥድፊያ ስሜት ካሳዩት ሰዎች ሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ይህን እንዲያደርግ ካነሳሱት ምክንያቶች አንዱ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሊያከናውነው የሚገባ በጣም ብዙ ሥራ የነበረው መሆኑ ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ባከናወነው ነገር ኢየሱስን ማንም ሊወዳደረው አይችልም። የአባቱን ስምና ዓላማ አሳውቋል፣ የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል፣ የሃይማኖት መሪዎችን ግብዝነትና የሐሰት ትምህርቶችን አጋልጧል እንዲሁም የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ጸንቷል። ኢየሱስ በሄደበት ቦታ ሁሉ ራሱን ሳይቆጥብ ሰዎችን አስተምሯል፣ ረድቷል እንዲሁም ከበሽታቸው ፈውሷል። (ማቴ. 9:35) ማንም ሰው ቢሆን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ያከናወነውን ያህል አከናውኖ አያውቅም። ኢየሱስ በዚህ ሥራ ላይ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ አድርጓል።—ዮሐ. 18:37

6. የኢየሱስ ሕይወት በምን ላይ ያተኮረ ነበር?

6 ኢየሱስ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በአገልግሎቱ በትጋት እንዲካፈል ያነሳሳው ምንድን ነው? በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራውን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንዳለው ከዳንኤል ትንቢት መረዳት ይችል ነበር። (ዳን. 9:27) በትንቢቱ መሠረት ‘በሱባዔው እኩሌታ’ ላይ ወይም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱ ያበቃል። ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 12:23) ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ ቢያውቅም ይህ ሕይወቱን እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም፤ ተግቶ እንዲሠራ ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ይህ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም አጋጣሚ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸምና ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት ተጠቅሞበታል። ይህ ፍቅር ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እንዲሁም እነሱን አሠልጥኖ በስብከቱ ሥራ ላይ እንዲካፈሉ ለመላክ አነሳስቶታል። ይህን ያደረገው እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ እንዲያውም ከእሱ የበለጠ ሥራ እንዲያከናውኑ ስለሚፈልግ ነው።—ዮሐንስ 14:12ን አንብብ።

7, 8. ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ሲያጸዳ ደቀ መዛሙርቱ ምን ተሰማቸው? ኢየሱስ ይህን ያደረገውስ ለምን ነበር?

7 በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸመ አንድ ክንውን ምን ያህል ቅንዓት እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። ሁኔታው የተፈጸመው አገልግሎቱን በጀመረበት አካባቢ ይኸውም በ30 ዓ.ም. በዋለው የፋሲካ በዓል ወቅት ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ “ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን” ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ? ደቀ መዛሙርቱስ የወሰደውን እርምጃ ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው?—ዮሐንስ 2:13-17ን አንብብ።

8 ኢየሱስ በዚህ ወቅት ያደረገውና የተናገረው ነገር ደቀ መዛሙርቱ፣ በዳዊት መዝሙሮች ውስጥ የሚገኘውን “የቤትህ ቅናት በላችኝ” የሚለውን ትንቢት እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። (መዝ. 69:9) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ትንቢት ያስታወሱት ለምን ነበር? ምክንያቱም ኢየሱስ ያከናወነው ነገር ለአደጋ የሚያጋልጠው በመሆኑ ነው። በቤተ መቅደሱ በሚካሄደው ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት ንግድ ላይ የቤተ መቅደሱ ባለሥልጣናት ይኸውም የካህናቱ፣ የጸሐፍቱና የሌሎች ሰዎች እጅ ነበረበት። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ምግባረ ብልሹነት የሚንጸባረቅበትን ይህን ሥራቸውን በማጋለጡና በማስተጓጎሉ በወቅቱ ከነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ጠላትነት ፈጥሯል። በእርግጥም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ‘ለአምላክ ቤት’ ወይም ለእውነተኛው አምልኮ ‘ቅንዓት’ እንዳለው የሚናገረውን ጥቅስ ማስታወሳቸው ትክክል ነበር። ይሁንና ቅንዓት ምንድን ነው? ከጥድፊያ ስሜት ይለያል?

የጥድፊያ ስሜት ከቅንዓት የሚለየው እንዴት ነው?

9. ቅንዓት እንዴት ሊገለጽ ይችላል?

9 አንድ መዝገበ ቃላት “ቅንዓት” የሚለውን ቃል “አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጉጉትና ጽኑ ፍላጎት ማሳደር” በማለት ፈትቶታል፤ እንዲሁም ኃይለኛ ስሜትና ግለት ከሚሉት ቃላት ጋር ተቀራራቢ ትርጉም እንዳለው ይገልጻል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን እንዲህ ዓይነት ስሜት እንደነበረው ጥርጥር የለውም። የ1980 ትርጉም ከላይ ያለውን ጥቅስ “ለቤትህ ያለኝ መንፈሳዊ ቅንኣት በውስጤ እንደ እሳት ይነድዳል” በማለት አስቀምጦታል። “ቅንዓት” የሚለው ቃል በአንዳንድ የምሥራቃውያን አገሮች ቋንቋ የሚገለጸው በሁለት ቃላት ነው፤ የእነዚህ ቃላት ቀጥተኛ ትርጉም “የጋለ ልብ” የሚል ሐሳብ የሚያስተላልፍ ሲሆን ይህም ልብ በእሳት እየነደደ እንዳለ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌያዊ አባባል ነው። በእርግጥም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳቸው አያስገርምም። ይሁንና ኢየሱስ ልቡ በእሳት እየነደደ ያለ ያህል እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳው ወይም የገፋፋው ምንድን ነው?

10. ‘ቅንዓት’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በምን መንገድ ነው?

10 በዳዊት መዝሙር ላይ የሚገኘው ‘ቅንዓት’ የሚለው ቃል ከአንድ የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች የሚገኘው ይህ ቃል ጠለቅ ያለ ትርጉም አለው። (ዘፀአት 20:5⁠ን፤ ዘፀአት 34:14ን እና ኢያሱ 24:19ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይህን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ነው። . . . አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት የትዳር ጓደኛቸው የእነሱ ብቻ እንዲሆን የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ሁሉ አምላክም የእሱ የሆኑት እሱን ብቻ እንዲያመልኩት የመጠየቅ መብት አለው፤ ይህን መብቱን ሌላ እንዲጋራው አይፈቅድም።” በመሆኑም ቅንዓት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ ለአንድ ነገር ኃይለኛ ስሜትና ግለት ከማሳየት የበለጠ ነገርን ለማመልከት ነው፤ ለምሳሌ በርካታ የስፖርት ደጋፊዎች ለሚወዱት ስፖርት ከሚኖራቸው ስሜት የተለየ ነው። ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ ዳዊት ቅንዓትን የገለጸው በአዎንታዊ ጎኑ ነው፤ ይኸውም ተቀናቃኝን ወይም ነቀፌታን በዝምታ አለማየትን፣ ጥሩ ስም እንዳይጎድፍ ለመከላከል አሊያም የጎደፈውን ስም ለማስተካከል የሚያነሳሳ ኃይለኛ ስሜትን ለማመልከት ነው።

11. ኢየሱስ በትጋት እንዲሠራ ያነሳሳው ምንድን ነው?

11 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያደረገውን ነገር ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ማያያዛቸው ትክክል ነበር። ኢየሱስ በትጋት ይሠራ የነበረው ሥራውን ለማከናወን ያለው ጊዜ የተወሰነ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአባቱ ስምና ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ስለነበረው ጭምር ነው። በአምላክ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋና ስድብ ሲመለከት በቅንዓት ተነሳስቶ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ኢየሱስ፣ ተራው ሕዝብ በሃይማኖት መሪዎች ሲጨቆንና ሲበዘበዝ በተመለከተበት ወቅት ቅንዓት ስላደረበት ሰዎቹ እረፍት እንዲያገኙ የሚያስችል እርምጃ ወስዷል፤ እንዲሁም ጨቋኝ የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎች ጠንከር ባሉ ቃላት አውግዟቸዋል።—ማቴ. 9:36፤ 23:2, 4, 27, 28, 33

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ

12, 13. በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች (ሀ) ከአምላክ ስም (ለ) ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ ምን አድርገዋል?

12 በዛሬው ጊዜም አምላክን እናመልካለን የሚሉ ሰዎች አመለካከትና ድርጊት በኢየሱስ ዘመን ከነበረው ጋር ይመሳሰላል፤ እንዲያውም ይብሳል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረው ጸሎት መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ስለ አምላክ ስም እንደነበር አስታውስ፤ “ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:9) በዛሬው ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች በተለይም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁና ስሙን እንዲቀድሱት ወይም እንዲያከብሩት ሲያስተምሩ አይተን እናውቃለን? ከዚህ በተቃራኒ እንደ ሥላሴ፣ ገሃነመ እሳትና የሰው ነፍስ አትሞትም እንደሚሉ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን በማስተማር አምላክን ሚስጥራዊ፣ ለመረዳት የሚከብድ፣ ጨካኝ አልፎ ተርፎም በሰዎች ሥቃይ የሚደሰት እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። በተጨማሪም አሳፋሪ የሆነው ምግባራቸውና ግብዝነታቸው በአምላክ ላይ ስድብ እንዲከመር አድርጓል። (ሮም 2:21-24ን አንብብ።) ከዚህም በላይ የአምላክ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ ሌላው ቀርቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ እንኳ አውጥተውታል። ይህ ድርጊታቸው ሰዎች ወደ አምላክ እንዳይቀርቡና ከእሱ ጋር የግል ዝምድና እንዳይመሠርቱ እንቅፋት ሆኗል።—ያዕ. 4:7, 8

13 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት እንዲጸልዩም አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:10) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ይህን ጸሎት አዘውትረው የሚደግሙት ቢሆንም ሰዎች ፖለቲካዊና ሌሎች ሰብዓዊ ተቋማትን እንዲደግፉ ያበረታታሉ። በተጨማሪም ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰብኩና ምሥክርነት ለመስጠት የሚጥሩ ሰዎችን ያንቋሽሻሉ። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች እንደሆኑ ከሚናገሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአምላክ መንግሥት ማመን ይቅርና ስለዚህ መንግሥት ሲናገሩ እንኳ አይሰሙም።

14. የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የአምላክን ቃል አለሳልሰው የሚያቀርቡት እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐ. 17:17) ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደግሞ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ምግብ የሚያዘጋጅ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚሾም ጠቁሟል። (ማቴ. 24:45) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የአምላክ ቃል መጋቢዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፤ ሆኖም ጌታ በአደራ የሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት ተወጥተዋል? በጭራሽ! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ተረት ወይም አፈ ታሪክ እንደሆነ የመናገር አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ቀሳውስቱ ለመንጎቻቸው መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ መጽናኛና እውቀት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ሰብዓዊ ፍልስፍናን በማስተማር የአማኞቻቸውን ጆሮ ይኮረኩራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የሚፈልጉትን ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያዎች ለማስተማር ሲሉ የአምላክን መሥፈርቶች አለሳልሰው ያቀርባሉ።—2 ጢሞ. 4:3, 4

15. ቀሳውስት በአምላክ ስም የሚያደርጓቸውን ነገሮች ስትመለከት ምን ይሰማሃል?

15 ይህ ሁሉ የሚደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው አምላክ ስም በመሆኑ በርካታ ቅን ሰዎች ግራ ተጋብተዋል ወይም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጨርሶ እምነት አጥተዋል። እንዲሁም በሰይጣንና ክፉ በሆነው ሥርዓቱ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ነጋ ጠባ ስትሰማና ስትመለከት ምን ይሰማሃል? የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን በአምላክ ስም ላይ የሚከመረውን ስድብና ነቀፋ ስትሰማ ይህን ለማስተካከል ልብህ አይገፋፋህም? ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሲታለሉና መጠቀሚያ ሲደረጉ ስትመለከት እነዚህን የተጨቆኑ ሰዎች ለማጽናናት አትነሳሳም? ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ሲመለከት በጣም ያዘነ ከመሆኑም በላይ ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማቴ. 9:36፤ ማር. 6:34) እኛም እንደ ኢየሱስ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲኖረን የሚገፋፉን ብዙ ምክንያቶች አሉን።

16, 17. (ሀ) በአገልግሎት በትጋት እንድንካፈል ሊያነሳሳን የሚገባው ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

16 በአገልግሎታችን ቀናተኞች ስንሆን ሐዋርያው ጳውሎስ በ⁠1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4 ላይ የተናገረው ሐሳብ ጥልቅ ትርጉም ይኖረዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) አገልግሎታችንን በትጋት የምናከናውነው በመጨረሻው ጊዜ ውስጥ እንዳለን ስለምናውቅ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስለምንገነዘብም ነው። አምላክ፣ ሰዎች እውነትን አግኝተው እሱን እንዲያመልኩትና እንዲያገለግሉት በዚህም በረከት እንዲያጭዱ ይፈልጋል። አገልግሎታችንን በትጋት እንድናከናውን በዋነኝነት የሚያነሳሳን የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ማወቃችን ሳይሆን የአምላክን ስም ለማክበርና ሰዎች ፈቃዱን እንዲያውቁ ለመርዳት ያለን ፍላጎት ነው። እንዲሁም ለእውነተኛው አምልኮ ያለን ቅንዓት ነው።—1 ጢሞ. 4:16

17 የይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ያለውን ዓላማ በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ተባርከናል። በተጨማሪም ሰዎች ደስታና ለወደፊቱ ጊዜ የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖራቸው መርዳት እንችላለን። የሰይጣን ሥርዓት ሲጠፋ ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ልናስተምራቸው እንችላለን። (2 ተሰ. 1:7-9) የይሖዋ ቀን የዘገየ በመምሰሉ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ጊዜ በመኖሩ መደሰት ይኖርብናል። (ሚክ. 7:7፤ ዕን. 2:3) እንዲህ ያለ ቅንዓት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በአገልግሎቱ በትጋት እንዲካፈል ያነሳሳው ምንድን ነው?

• “ቅንዓት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?

• በዛሬው ጊዜ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲኖረን የሚያነሳሳን ምን ዓይነት ሁኔታ አለ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ትኩረት ያረፈው የአባቱን ፈቃድ በመፈጸምና ለሰዎች ፍቅር በማሳየት ላይ ነበር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲኖረን የሚገፋፉን ብዙ ምክንያቶች አሉን